By, Esleman Abay
ሙሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ በቅፅሉ ‘ሄሜቲ’ የሚመሩት የፖሊስ ኃይል ለሲቪሉ መንግስት መሆን አለበት የሚለውን ህጋዊ መርህ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አስታውቀዋል። የወታደራዊ ክንፉ ሊቀመንበር አብደል ፋታህ አል ቡርሃን እና በቃል አቀባዩ መሐመድ አል-ፋቂ መካከል በተፈጠረ ውዝግብ የተነሳም በሉዓላዊ ምክር ቤቱ ሊደረግ የነበረ ስብሰባ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆይ አስገድዷል፤ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ።
ከዚህ በተጨማሪም የወታደራዊ ክፍሉ ቃል አቀባይ ሙሐመድ አል-ፋኪ ከምክር ቤቱ እንዲወገድ ሔሜቲ ስለመጠየቃቸው የወጡ ዘገባዎች ነበሩ። ሄሜቲ ሐሙስ ዕለት በሰጡት ምላሽም በሉዓላዊ ምክር ቤት የሚገኝ ማንኛውም ሲቪል አባል እንዲሰናበት አልጠየቅሁም ብለዋል።
በሱዳን አሁን ያለው ቀውስ በሉዓላዊ ወታደራዊ ክንፉ የተፈጠረ አይደለም ያሉት ሔሜቲ ገዥው የሲቪል አመራር ጥምረት የጠየቀውን እና የፖሊስ ተጠሪነት በሲቪሉ መንግስት ስር እንዲሆን የቀረበውን ጥሪ አልቀበልም ብለዋል። ፖሊስና የደህንነት ተቋሙን ለተመራጩ መንግሥት ብቻ ነው የምናስረክበው ሲሉ ገልፀዋል።
የሱዳንን ሽግግር በሚመራው ሕገ-መንግስታዊ ሰነድ መሰረት ፖሊስ በሲቪል ካቢኔው ስር መሆኑን አስፍሯል። በዚሁ ሰነድ አንቀጽ 36 “ፖሊስ ለሲቪሉ መንግስት ተገዥ ነው” ይላል።
በጥቅምት 8 (ዕለተ አርብ)
የሐምዶክ መንግሥት የሄሜቲን አቋም አልቀበልም ሲል አስጠነቀቀ፤
የሱዳን ሽግግር መንግስት በሄሜቲ የተሰጠው መግለጫ ሕገ-መንግስታዊ ሰነዱን በግልፅ መጣስ ነው በማለት ምላሽ ሰጥቷል። ምላሹን የሰጡት የሱዳን ካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ካሊድ ኡመር የሱፍ ሁለቱም የፀጥታ ተቋማት በሲቪል በሚመራው መንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የሄሜቲ እምቢተኛ መግለጫዎች በመስከረም 21 የተደረገውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ይህን ተከትሎም ይኸው ወታደራዊ ክንፍ በምሥራቃዊ ሱዳን ወደቦችን እና ወሳኝ አውራ መንገዶችን ፀጥታ ለማስጠበቅ ፈቃደኛ አለመሆኑ በሲቪልና ወታደራዊ ክፍሉ መካከል እየተባባሰ ከመጣው የውጥረት አውድ የመነጨ መሆኑ በስፋት ተዘግቧል።
የሱዳኔ ካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ካሊድ ኡመር የሱሲፍ የሔሜቲ መግለጫ ለሕገ -መንግስታዊ ሰነዱ ቀጥተኛ ስጋት መሆኑን ጠቁመው ይህን ስጋትም “በከባድና ጥብቅ በሆነ መንገድ” እንደሚፈቱት ቃል ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በሲቪል እና በወታደራዊ ወገኖች መካከል አስማሚ ሀሳብ ለማቅረብ ሞክረዋል ያለው መግለጫው አሁን ያለው ቀውስ የሽግግር ሰነዱን ያገናዘበ የኃይል ሚዛንን የማስተካከያ፣ ለዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር መሠረት ሊሆነን ይገባል ሲሉ ነው ምኒስትሩ አርብ ለነፃነትና ለውጥ ኃይሎች መሪ የፃፉት።
የሱዳን ወታደራዊ ልዑካን ድብቅ ጉብኝት በእስራኤል | ዕለተ ቅዳሜ ጥቅምት 9
የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ ባለሥልጣናት አወዛጋቢውን የፈጥኖ ደራሽ ሃይል Rapid support Force-RSF ምክትል አዛዥን ያካተተ ጉብኝት በእስራኤል ስለማድረጋቸው ሱዳን ትሪቡን አረጋግጧል። የሱዳን ዲፕሎማቲክ ምንጮች የአገሪቱ ወታደራዊና የደህንነት ልዑካን በሳምንቱ ወደ እስራኤል በድብቅ ጉብኝት ማድረጋቸውንም ነው የገለፁት።
ጉብኝቱን ያደረገው ልዑካን ቡድን በ RSF ምክትል አዛዥ ሌ/ጄኔራል አብደል-ራሂም ሃምዳን የተመራ ሲሆን የእስራኤል ጉብኝት ከተጠናቀቀ በኋላ ስሟ ወዳልተገለፀች አረባዊ ሀገራት መካከል ወደ አንዷ ማምራቱን አል-ሻርቅ ጋዜጣ በዕለተ ቅዳሜ ህትመቱ አስነብቧል። ልዑካኑ በሁለት ቀናት ጉብኝቱ ከእስራኤል ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ኢያል ሁላታ ጋር መገናኘቱን የዘገው ደግሞ አል-አረቢያ ቲቪ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ መንግሥት ውስጥ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ቅዳሜ ዕለት ለ “ሱዳን ትሪቡን” እንደገለፁት ገዢው ካቢኔ ስለ ጉብኝቱ ምንም አልተነገረውም።
ወታደራዊ ልዑኩ ከሲቪሉ መንግስት በሚጋጭባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እስራኤል እጇ እንደሌለበት ስምምነት ስለመኖሩም የሐምዶክ መንግስት ማወቅ አለመቻሉንም ነው ሱዳን ትሪቡን የዘገበው።
በሱዳን የሽግግር አመራሩ ሀላፊነቱን በምርጫ የሚያስረክበው በቀጣዩ ወር ነው።
by, Esleman Abay የዓባይ ልጅ