ኢትዮጵያና እና ሩሲያ በመልክዓ ምድር የተራራቀ ክፍለ ዓለም ላይ ቢገኙም በአሁኑ ጎልማሳ ትውልድ ከማይረሳው የሶሻሊዝም ዘመን ብዙ መቶ ዓመታት በፊት ሁለቱ ሀገራት በመረጃ፣ በባህል፣ በታሪክ፣ በማኅበራዊ ሕይወት፣ በፖለቲካና በዲፕሎማሲ፣ በአርበኝነት፣ በመንፈሳዊ የእምነት አስተሳሰብ በደም የተሣሠረ ቤተሰባዊነት እና ጠንካራ መሠረት ያለው የወዳጅነት ግንኙነት አላቸው።
ኢትዮጵያና ሩሲያን በርካታ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ። ብዙ ቋንቋ የሚናገሩ፣ የተለያዩ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ፣ እምነትና ፖለቲካን በአንድነት ሲያራምዱ የቆዩ ሕዝቦች ሀገራት ናቸው። ከሶቪየት ኅብረት በኋላ አሁን የሩሲያ ፌደሬሽን የምትባለው ሀገር 147 ሚሊዮን አካባቢ የሕዝብ ቁጥር ያላት፣ 160 የሚደርሱ ጎሣዎች በአንድነት የሚኖሩባት፣ እስከ 100 የሚደርሱ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ በፕሬዚዳንታዊ ሕገ መንግሥት የምትመራ በዓለም ትልቅ ግዛት፣ ከፍ ያለ ኢኮኖሚ፣ የላቀ የሳይንስ ዕውቀት፣ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ያላት፣ ተገዳዳሪ የፖለቲካ አቋም የምታራምድ ሉዓላዊ ሀገር ናት። አብዛኛው ሕዝብ አንድ ሀገራዊ ቋንቋን ሩሲኛን ሲናገር ብዙ የጎሣ ቋንቋዎች ዕውቅና አላቸው። ሩሲያ የሚለው ስም የሚወክለው የሩሲያውያን ሀገር (Land of the Russian) ሲሆን ከሩሲያ ጎሣ ሥያሜ ተነሥቶ አሁን የፌደሬሽኑ መጠሪያ የሆነ ሥያሜ ነው። በአካባቢው በርካታ የቅድመ ታሪክ ቅርሶች እንዳሉ ቢታወቅም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ1500 ዓመት በፊት በአሁኑ የሩሲያ ምዕራባዊ ግዛትና በፖላንድ አካባቢ የስላቭ ተወላጆች መሥፈርና መኖር እንደጀመሩ ይነገራል። በ500 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የኖረው ተጓዥና ጸሐፊ ሔሮዱቶስ በአሁኑ ሩሲያ በትላልቅ የእንጨት ቤቶች የሚኖሩ ሕዝቦች ነበሩ በማለት ስለ ሩሲያ ህልውና አጭር መግለጫ ትቷል። ጥንታዊ ዜጎቿ በአርብቶ አደርነት እና ባልተዋቀረ ማኅበራዊ አደረጃጀት የሚኖሩ ስለነበሩ እና የርስ በርስ ግጭት ባለማቋረጡ ምክንያት ቋሚ የሆነ የመንግሥትና የማኅበራዊ መዋቅር በጊዜው ለመመሥረት አልቻሉም።
በሩሲያውያን ትውፊት መሠረት ከ862 ዓ.ም በኋላ የሩስኪ (ሩሲያ) መንግሥት በቪኪንግ አማካኝነት ተመሠረተ። በሃያ ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአካባቢው ደቡባዊ ግዛት እያቆጠቆጡ ከነበሩ እንደ ኬይቭ ካሉ ግዛቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር በ882 ዓ.ም ትልቅ ኃይል ያለው ግዛት፣ ጥቃቅን አካባቢዎችን የጠቀለለ፣ ርስ በርስ የተባበረ ሀገር ኬይቫን-ሩስኪ በማለት መሠረቱ። በቀጣዩ ክፍለ ዘመን በአንፃሩ ከተዳከመው የባዛንታይን ግዛት ጋር ሰፊ የንግድ፣ የባህልና የማኅበራዊ ሕይወት ግንኙነት በማድረግ፣ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነትን በይፋ በመቀበል ኦርቶዶክስን ዋና መለያቸው እና ይፋዊ የመንግሥት ሃይማኖት አድርገው የተቀበሉትም የኬይቭ ነዋሪዎችና ልዑሉ ቭላድሚር ቀዳማዊ ነበሩ። ይህ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ክስተት የሕዝቡን አንድነት በማጠንከር የጋራ ሕልውናውን በማስተሳሰር በነዋሪዎቹ ማኅበራዊ ሕግጋት፣ ቋንቋ እና ባህል፣ ሥነ ጽሑፍና ግብረ ሕንፃ ጥበብን በማሳደግ ለአዲስ የማኅበራዊ አመለካከትና ዘይቤ በር ከፍቷል። በ13ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በውስጥ ልዩነት እና የርስ በርስ ግጭት በተከፈተው ቀዳዳ እና መዳከም በሞንጎሎች ለወረራ ተዳርገው ከፍተኛ የመለያየትና የብዙ ሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ ጦርነት ቢገጥማቸውም መልሰው አንድነታቸውን በማጠንከርና ማእከላዊ አስተዳደርን መሥርተው መንግሥታቸውን አጽንተዋል። ከዚህ ሁኔታ ለማገገም እና የአሁኗን ታላቅ ሩሲያ ለመመሥረት ከሁለት መቶ ዓመት በላይ ፈጅቷል። ይሁን እንጅ ሩሲያውያን ተባብረው ሀገራቸውን ለማሳደግና ከባዛንታይን መዳከም ጋር ተያይዞ ከጥንታዊቷ ሮምና ዳግማዊት ሮም ከተባለችው ቁስጥንጥንያ ቀጥሎ ሦስተኛዋ ሮም ለማድረግ ማለማቸውን አላቆሙም። (ኒኮላይ ሚካኤሎቪች፣ የሩሲያ ታሪክ) ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት መጀመርም በጥቂቱም ቢሆን ከዚሁ ዕቅድ ጋር የተያያዘ ነበር። 1-የኢትዮጵያ-ወ-ሩሲያ ግንኙነት በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን-ኢየሩሳሌም በሩሲያ ታላቅ ሀገር ለመመሥረት የሚያስችል ሕልም ወደ ተግባር ለመለወጥ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው እንቅስቃሴ እና በኋላ ዛር (በቄሣር/አጼ/ዣን እንደ ማለት ነው) ንጉሥ ኢቫን አራተኛ (እአአ ከ1533-1547) የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል። ንጉሡ አዳዲስ ሥርዓቶችን በመመሥረት፣ ሕግ በማውጣት፣ የነበረውን ሕብረ ብሔራዊነትና ብዝኅ እምነት ያማከለ ራስ አገዝ የክፍለ ሀገር አስተዳደሮችን በመመሥረት፣ ማእከላዊ መንግሥቱን በማጠናከር ትልቋን ሩሲያ መመሥረት ችሏል። ይህ አደረጃጀትም በየዘመኑ ማኅበረሰብ ወለድ የሆኑ አመጾች፣ ግጭቶችና ፉክክሮች፤ እንደ ርሀብ፣ ድርቅና በሽታ ያሉ የተፈጥሮ ችግሮች፤ ድንበር ዘለል ጦርነቶች እና ወረራዎች ለማይለዩአት ሩሲያ ችግሮችን ተቋቁማ እንደ ሀገር ለመቀጠል ድምር አቅም ሁኗት ቆይቷል። የአንድ መንግሥት ሕልውና በጽኑ መሠረት ላይ የሚቆመው በታማኝ አስተሳሰብ የተገነባ፣ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚየደርግ አገዛዝ ሲኖረው፣ በግዛቱ ውስጥ በየጊዜው የሚደርሱበትን የልዩነትና የመከፋፈል አስተሳሰቦች ውል ባለውና በተመረጠ ዘዴ ሲፈታ፤ የጠላትን ወረራ መክቶ ማቆም ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ አንድነቱን እና ጥንካሬውን በማይናወጥ መሠረት ላይ በማቆም፣ በውስጡ ለሚኖሩ ሕዝቦች የተረጋጋ የኑሮ ዋስትና ሲሰጥ፣ ጽኑ መከታና ሩቅ ዘመን ተሻጋሪ መመሪያ ካለው ሲሆን እንዲህ ያለ መንግሥት ቢወድቅ የሚነሣ፣ ቢደክም የሚበረታ፣ በጦር የማይፈታ ለመሆኑ የሩሲያውያን ታሪክ ጥሩ ምሳሌ ነው።
በዘመኑ ከነበረው ጠንካራ እንቅስቃሴ አንፃር የሩሲያ ኦርቶዶክስ መነኰሳትና ተሳላሚዎች ከሀገራቸው ውጭ በሰሜናዊ ሜዲትራንያን በአቶስ ተራሮችና በኢየሩሳሌም መንፈሳዊ ጉዞዎችን በማድረግ በዚያም ይዞታቸውን ያጠናክሩ ነበር። ይህ ደግሞ በተመሳሳይ ዓላማ ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ በኢየሩሳሌም ከነበሩ የኢትዮጵያ መነኰሳት ጋር እንዲገናኙ እድል ፈጥሮላቸዋል። በዚህ ዘመን አንድ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ ማዕረጉ አርኬሜንዴሬት የሆነ ግሬቴኒዎስ የተባለ መነኰስ በጻፈው ሪፖርት “የኢትዮጵያውን ንጉሥ አጼ ይስሐቅ ለኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ገዳም ስጦታ ልከዋል፣ መነኰሳቱም በዴር ሱልጣን ገዳማቸው በጎለጎታ ቤተ መቅደስ በቀኝ በኩል የሚገኝ ሲሆን ንጉሣቸው አጼ ይስሐቅ ያሠራላቸው የራሳቸው ቤተ ክርስቲያን አላቸው። በኢየሩሳሌም ባሉ አርመኖች፣ ግሪኮችና በሌሎች ክርስቲያኖች የሚደርሰውን መከራ ሁሉ አብረው ይቀበላሉ” በማለት የጻፈው ሰነድ የፈረንሳይኛ ቅጅ ዛሬም በሩሲያ አርኬዎሊጅ ሙዚየም ይገኛል።
እአአ በ1558 አካባቢ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘ ሌላ የሩሲያ መነኰስም እንዲሁ ብዙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ መነኰሳት በጌታሴማኒ የቅድስት ድንግል ማርያም መቃብርና ጌታችን በጸለየበት ቦታ መካነ ጸሎት ሠርተው እንዳገኛቸው፣ በትንሣኤ ሌሊትም የእውነተኛ ብርሃን መውረድ “ርደተ ብርሃን” ሥርዓት እነሱ ባሉበት ከግሪኩ የኢየሩሳሌም ፓትርያርክ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ካህን ተከትሎ ከዚያ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ሁነው ሥርዓተ ዑደት እንዳደረጉ ዘግቧል። ይኽ መነኰስ በሰጠው መረጃ መሠረትም ኢትዮጵያውያን በጎለጎታ ዴር ሡልጣን ገዳማቸው አራት የሚያምሩ ከበሮዎች ይዘው ማኅሌት ሲያደርሱ፣ ሲያሸበሽቡና ሲዘምሩ ማደራቸውን ጭምር ለሩሲያ ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቹ ተናግሯል። እንግዲህ በዚህ ዘመን የሩሲያ ኦርቶዶክስ አማኞች፣ ቤተ ክርስቲያን እና መንግሥት ስለ ኢትዮጵያ መጠነኛ መረጃ እንዲያገኙ ረድቷቸዋል። (ቺዝላው ጀስማን፤ እኤአ 1958)
2-የኢትዮጵያ-ወ-ሩሲያ ግንኙነት በ17ኛው መ/ክ/ዘ- ፒተርስበርግ/ሞስኮ
ታላቁ ጴጥሮስ (እአአ 1672-1725) በሩሲያ የማይረሳ ባለውለታ ነው። ሩሲያን ከጎረቤት ሀገሮች እኩል የሰለጠነች፣ በኢኮኖሚ ያደገች፣ ከባልቲክ ባህር እስከ ሰላማዊ (ፓስፊክ) ውቅያኖስ የሰፋ ግዛት ያላት በዓለም ትልቋ ሀገር እንድትሆን ያደረገ መሪ ነው። በየትኛውም ዓለም ያሉ ሕዝቦች የሀገራቸውን ድንበር አስፍቶ፣ ጠላት ረትቶ፣ ከጎረቤት ተስማምቶ፣ ወዳጅ መሥርቶ፣ ለሕዝብ መከታ፣ ለሀገር ዋልታ የሆነን መሪ እንደሚያከብሩ ሁሉ ንጉሥ ጴጥሮስ ጉልበተኛ ቢሆንም በሩሲያ ሕዝቦች ዘንድ የተከበረ ንጉሥ ሆነ። በተለይ ከሩሲያ አብዮት በፊት የተጻፉ በርካታ የታሪክ ክታቦች ለዚህ ንጉሥ ትልቅ ክብርን ይሰጣሉ። የነገሥታትን የታሪክ አምባ አፍራሹ አብዮታዊ ትውልድ ከመጣ በኋላ ደግሞ በንጉሡ ዘመን የነበረውን እልቂት፣ ትግልና በርካታ ውጣ ውረድ በመጉላቱ ታሪኩ በአሁኑ ትውልድ አወዛጋቢ እንዲሆን አድርጎታል። ታላቁ ጴጥሮስ እአአ በ1703 አዲስ ከተማ ፒተርስበርግ በማለት መሥርቷል። እአአ በ1720 ሰፊና ትልቅ ሀገር ለመሥራት ባደረገው ተጋድሎ የሩሲያ ንጉሥ (አጼ) ለመሆንና ሀገሪቱም የሩሲያ ኤምፓየር ለመባል በቃች። የመንበረ ፓትርያርኩንም ሥልጣን ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍ በማድረግ አስተዳደሩ ዘመናዊ እንዲሆን አድርጓል። የግዛቱ መስፋት ከፈጠረለት የሀብት ክምችት እና የተፈጥሮ ሀብት በረከት በላይ የመዋቅሩ አደረጃጀት፣ የሰው ኃይሉን አሰላለፍ በማጠንከሩ ያለጥርጥር ዋስትና ያለው ከመላው አውሮፓ ጋር አቻ የሆነ መንግሥት ለማደራጀት ችሏል።
ከዚህ ዘመን በፊት ሩሲያን ከኢትዮጵያ ጋር ሊያገናኛት የሚችል የመንግሥት ለመንግሥት ሁኔታ ለመኖሩ እስከ አሁን ብዙ መረጃዎች ባይገኙም በርከት ያሉ የማኅበራዊ፣ የሥነ ጥበብና እና በተለይም በሃይማኖቱ በኩል ለጥናት በር የሚከፍቱ ርእሰ ጉዳዮች አሉ። እንደ 15/16ኛው ክፍለ ዘመን ሁሉ አሁን ስለኢትዮጰያ ከኢየሩሳሌም መረጃ መገኘቱ አላቋረጠም። እነዚህ መረጃዎች ደግሞ በወቅቱ ከፍተኛ መስፋፋት ላይ የነበረችውን ቱርክን ለመቋቋም አማራጭ እየፈለጉ ለነበሩ አውሮፓውያን ጠቃሚ ስለነበሩ በትኩረት ይከታተሏቸው ነበር። እንደምሳሌ የሚወሰደው ደግሞ ታላቁ ጴጥሮስ በዘመኑ ከኢትዮጵያ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ለማድረግ መሞከሩ ነው። ታላቁ ጴጥሮስ ከኢየሩሳሌም ከሚገኘው መረጃ በመነሣት ሩቅ ሀገር ካለ የኢትዮጵያ ክርስቲያን መንግሥት ጋር ዘላቂ ግንኙነት መመሥረት ሃይማኖትን ለማጽናት፣ ሀገሩን ለማረጋጋት ጠቃሚ መሆኑን አምኖበት ነበር። ይልቁንም በቀድሞው የአክሱም ዘመን ሩሲያ ገና ጠንካራ መንግሥት ሳትሆን ኢትዮጵያ ከባዛንታይን (ቁስጥንጥንያ) ንጉሥ ጁስቲኒያን ጋር የነበራትን ግንኙነት በርሱ ዘመን ከሩሲያ ጋር እንድትመሠርት ከፍተኛ ጉጉት ነበረው።
ይኽ በእንዲህ እንዳለ አንድ ተአምር ለታላቁ ጴጥሮስ ንጉሠ ሩሲያ ተፈጠረለት። በቱርኮች ተማርኮ ወደ አውሮፓ የተወሰደው ኢትዮጵያዊ አብርሃም ሐኒባል ከንጉሡ ቤተ መንግሥት ሰተት ብሎ በልጅነት ማዕረግ ገባ። ሐኒባል የሚለው ሥያሜ በግእዙ ሕንበል (ብርኩማ፣ ድራብ)፣ ወይም ሕንባል ኮርቻ ድልዳል፣ ከሚለው (ነባር ቃል) የተወሰደ ሊሆን ይችላል። አብርሃም ሐኒባልን ወደ አውሮፓ የወሰዱት ቱርኮች ኢብርሒም ይሉት ነበር፣ እርሱ በትውልዱ የአንድ ኢትዮጵያዊ መስፍን ልጅ ሲሆን የሩሲያ ንጉሥ ታላቁ ጴጥሮስ እንደ ልጅ አደርጎ አሳደገው። በትምህርት እና በእድሜ እየጐለበተ ሲሄድ በውትድርና አገልግሎት በመሰማራትም እስከ ጀኔራል ማዕረግ ደርሷል። አብርሃም ለኢትዮጵያና ለሩሲያ ግንኙነት መመሥረት የተሟላ መረጃ የሰጠ ቢሆንም ግንኙነት ከመመሥረት ባሻገር ጀነራሉ በንጉሡ ቤት እጅግ የተወደደ እና በሂደት የቤተ መንግሥት ባለሟል ለመሆን በመብቃቱ ከንጉሣውያን ቤተሰብ ተጋብቶ በሩሲያ እና በዓለም ሥነ ጽሑፍ ሥልጣኔ ታሪክ ከፍተኛ ቦታ ለሚሰጠው ስመ ጥር ደራሲ አሌክሳንደር ፑሽኪን አያት ለመሆን በቃ። በዚህ ክፍለ ዘመን የነበረው ግንኙነት ለሩሲያውያን ስለኢትዮጵያ የተሟላ መረጃን የሰጠ፣ በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በደም የተሣሠረ ቤተሰባዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው ደማቅ ዱካ የተወ ማኅተም ያለው የታሪክ ምእራፍ ሆኗል።
3-የኢትዮጵያ-ወ-ሩሲያ ግንኙነት በ18/19ኛው መ/ክ/ዘ- አሌክሳንደር ፑሽኪን
አሌክሳንደር ፑሽኪን Alexander Sergeyevich Pushkin (እአአ ከ1799-1837) ደራሲ፣ ገጣሚ፣ የቲያትር ሥነ ጽሑፍ አዘጋጅ፣ ሲሆን በሩሲያ ዘመናዊ ድርሰት መሥራች ተደርጎ ይቆጠራል። ፑሽኪን በሩሲያ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ የሥነ ጽሑፍ፣ ቴያትር፣ ሥነ ግጥምና የቋንቋ ታሪክ ውስጥ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከተ ባለዝና ነው። አንዳንድ ጊዜ ፑሽኪን ካለው የአንድ ወገን ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ አንፃር በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥም ሲጠቀስ ይታያል። ፑሽኪን የተወለደው ከ120 ዓመት እአአ በግንቦት 29 ቀን 1711 ነበር። (ከሁለት ዓመት በፊት የፑሽኪን 120ኛ ዓመት በድምቀት እንደሚከበር አንዳንድ ዜናዎች ተሠራጭተው የነበረ መሆኑን ልብ ይሏል)።
ፑሽኪን በአባቱ በኩል የጥንታዊት ሩሲያ መሳፍንት ዘር ሲሆን በእናቱ ወገን ደግሞ ከላይ እንደተጠቀሰው ቅድመ አያቱ ከኢትዮጵያ የሆነው አብርሃም ሐኒባል ነው። አሌክሳንደር ፑሽኪን ብዙ ግጥሞችን፣ የቲያትር ጽሑፎችን፣ የዜማ ድርሰቶችን፣ ረጃጅምና አጫጭር ድርሰቶችን ሠርቶ አልፏል። ግጥሞቹ ታሪክን፣ ባህልን፣ የማኅበረሰብ አኗኗርን፣ ፍቅርን፣ ወቅታዊ ጉዳዮችን … በሰፊው የዳሰሱ ናቸው። በጽሑፎቹ ውስጥ ካለው የቋንቋ ውበት እና የፈጠራ ችሎታ የተነሣ ለሩሲያ ቋንቋ መዳበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይነገራል። በአንዳንድ ድርሰቶቹም ስለ አያቱ እንደ ልጅ ስላሳደገው ንጉሥ ታላቁ ጴጥሮስ፣ ስለ ሀገሩ እና ስለ አያቱ ሀገር ኢትዮጵያ አነሣሥቷል። ሩሲያውያን ስለ ፑሽኪን በከፍተኛ ኩራት ይጽፋሉ፣ ያዜማሉ፣ ይሥላሉ፣ በርካታ መርሐ ግብሮችን በስሙ ያዘጋጃሉ።
በታላላቅ ተቋሞቻቸው ባሉ ሙዚየሞችና የሥነ ጥበብ ማእከላት ባለፉት ሠላሣ ዓመታት ብቻ ከ200 በላይ ዐውደ ርእዮችን አዘጋጅተዋል። በፑሽኪን የሥጋ ልጆች አማካኝነት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የፑሽኪን ፋውንዴሽን ስለፑሽኪን ማስታወሻ የሆኑ በርካታ ሥራዎችን ይሠራል። (http://www.pouchkine.org)። በእኛም ሀገር ወጉ ደርሶን በስሙ ሐውልት አቁመን፣ አደባባይ ሰይመን፣ የባህል ማዕከል ፑሽኪን በማለት ጠርተን የቆየን ቢሆንም ዛሬ ላይ አደባባዩ ፈርሶ፣ ሐውልቱም ተነሥቶ ዝክሩም ተዘንግቶ ይገኛል። ለዚህኛው ጽሑፍ ፑሽኪን ለኢትዮጵያና ለሩሲያ ግንኙነት በስምና በግብር የተሳሰረ ትልቅ ቤተሰባዊ ድልድይ መሆኑን እያወሳን በማለፍ ወደፊት እርሱን ብቻ የተመለከተ ጽሑፍ አቀርባለሁ።
4-የኢትዮጵያ-ወ-ሩሲያ ግንኙነት በ19ኛው መ/ክ/ዘ- አጼ ቴዎድሮስ- ሴባስቶፖል
በሩሲያ ታሪክ ከፍ ብለው ከሚታወቁ የውትድርና ታሪኮች ውስጥ ዛር ኒኮላስ ቀዳማዊ (እአአ ከ1825-1855) እጅግ ዘመናዊ የማይባል ግን ቁጥሩ አንድ ሚሊዮን ሠራዊት በማደራጀት ከሀገሩ አልፎ ለአውሮፓም ኩራት ለመሆን የበቃ መሪ ነበር። በዚህም ምክንያት ሩሲያ በመጀመሪያ ናፖሊዎንን፣ በኋላ በክሬሚያ ጦርነት ኦቶማን ቱርክን፣ እና ኦቶማንን ለማገዝ ያበሩ እንግሊዝንና አጋሮቿን በሴባስቶፖል ከተማ/መንደር ክፉኛ አሸነፈቻቸው። ይህ ሁኔታ ከአብርሃም ሐኒባል እና የልጅ ልጁ አሌክሳንደር ፑሽኪን ቀጥሎ የተፈጠረውን ኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት ያስታውሰናል። ወደ ኢትዮጵያ ባልታወቀ ምክንያት ገብተው በአጼ ቴዎድሮስ እስር ከነበሩ አውሮፓውያን መካከል የሩሲያ ተወላጅ ወይም ዜጋ የሆነ ወይም ስለሩሲያ የሚያውቅ ሰው እንዳለ ታወቀ። ንጉሠ ነገሥቱ ግርማዊ አጼ ቴዎድሮስም አቅርበው በአውሮፓ ስላለው ሁኔታ ጠይቀውታል። በወቅቱ በሩሲያ ታላላቅ ድሎችን የተቀዳጀው ንጉሥ ኒኮላስ ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር ትዩዩ ነበር። በመሆኑም ለአጼ ቴዎድሮስ የትልቁ መድፋቸው ሥያሜ ሴባስቶፖል፣ ትልቁ ሕልማቸው ኃያልና ገናና ሀገር የመፍጠር ዕቅድ፣ ዘመናዊና የሰለጠነ ሀገርን አረጋግቶ ማኖር የሚችል የጦር ኃይል የማደራጀት፣ በራስ አገዝ ኢንዱስትሪ ላይ የቆመ የኢንዱስትሪ መንደር የመገንባት ዕቅድ አንዱ ምንጭና ምሳሌ ሩሲያ መሆኗን መገመት አይከብድም።
የቼክ ተወላጅ የሆነው ቼዝላው ጀስማን (The Russian in Ethiopia; 1958) በሚል ርዕስ ከታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ትንተና ጋር እንደጸፈው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በሩሲያ በኩል ስለ ኢትዮጵያ ከነበረው ፍላጎት አንፃር ለመጀመሪያ ጊዜ በምሥራቅ ኦርቶዶክሳዊት ሀገር የግእዝ ጥናት የተጀመረው በሩሲያ ነው። እአአ በ1829 አካባቢ ግእዝ በአንድ ታዋቂ የቋንቋ ምሁር በሩሲያ ካርኮቭ ዩኒቨርሲቲ መሰጠት የጀመረ ሲሆን መምህሩ ከአምስት ዓመት በኋላ የበርካታ ግእዝ ብራና መጻሕፍት መግለጫ በሩሲያ አሳትመዋል። ብዙም ሳይርቅ በዚሁ ክፍለ ዘመን በተመሳሳይም በኢትዮጵያ በኩል ስለ ሩሲያ ለማወቅ እና ግንኙነት ለመመሥረት እጅግ ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ነበሩ። ግርማዊነታቸው በተለይ ታላቅ የኦርቶዶክስ ሀገር ክሬሚያ በተባለው ግዛት ሴባስቶፖል በተባለ ከተማ አካባቢ ከቱርክ ጋር ተዋግታ የማሸነፏን ዜና የሰሙት ገና በትኩሱ ነበር። በዚህ ጦርነት ከቱርክ ጋር ለመወገን ወደቦታው የሄዱት እንግሊዝና ፈረንሳይም በተመሳሳይ በሩሲያ የመደምሰሳቸው ዜና በአጥጋቢ መልኩ ከግርማዊ አጼ ቴዎድሮስ ዘንድ መድረሱ የሚታወቀው አጼ ቴዎድሮስ በጊዜው ከእንግሊዝ ጋር በኋላ ከቱርክ ጋር በተከታታይ ለገጠማቸውና ላሰቡት ጦርነት የፕሮፖጋንዳ ማስፈራሪያ እንዲሆን ታላቁን መድፋቸውን “ሴባስቶፖል” ብለው የሰየሙት በሰሙት የድል መረጃ መሠረት ነበር። በመሆኑም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሩሲያ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመመሥረት ፍላጎት የተወጠነው በአጼ ቴዎድሮስ ነበር። ከአውሮፓውያን እስረኞችም ጋር በተያያዘ እና በአጠቃላይ ስለነበረው ሁኔታ ከሩሲያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ቦጎሖስ እአአ በየካቲት ወር 1867 ደብዳቤ መጻፉ በሩሲያ ተዘግቧል። ይኽም ቀጥሎ ለነገሡት ለአጼ ዮሐንስ አንድ መሠረት ያስቀመጠ የዲፕሎማሲ ደረጃ ነበር።
5-የኢትዮጵያ-ወ-ሩሲያ ግንኙነት በ18/19ኛው መ/ክ/ዘ- አጼ ዮሐንስ አራተኛ
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ አራተኛ ለኢትዮጵያና ሩሲያ ግንኙነት ያላቸው ፍላጎት ጨምሯል፣ ስለሩሲያ ከአጼ ቴዎድሮስ ዘንድ የነበረው መረጃ በቀላሉ ወደ አጼ ዮሐንስ አራተኛ ተሻግሮ ወደ አንድ ተምሳሌታዊና ተጨባጭ ግንኙነት እንዲያመራ እገዛ አድርጓል። በሩሲያ በኩል አሽኖቭ የተባለ ተጓዥ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ተልእኮ በመያዝ ወደ ቀይ ባህር መጥቶ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። አሽኖቭ ከነበሩት ዕቅዶች ውስጥ አንዱና ዋናው በኢትዮጵያ እና በሩሲያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ግንኙነት መመሥረት ነበር። በመጀመሪያ ለግርማዊ አጼ ዮሐንስ ግብጽ የነበረ አንድ መልእክተኛ ወይም ሰላያቸው ሩሲያ በቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ ለመሥፈር ስለነበራት ፍላጎት መረጃ ሰጥቷል። በመቀጠል በአሁኗ ጅቡቲ የቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ ከነበረው የሩሲያ የጦር ኃይል ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያደረጉ ቀሳውስት ብዙ መረጃዎችን አግኝተዋል። የሩሲያ ጦር በቀይ ባሕር – ጅቡቲ መገኘት ለአጼ ዮሐንስ ብቻ ሳይሆን ለምኒልክ ንጉሠ ሸዋ (በኋላ ንጉሠ ነገሥት)፣ ለራስ አሉላ፣ ለራስ መኰንን መስፍነ ሐረር፣ እና ለሌሎችም መኳንንትና መሳፍንት መተዋወቅ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።
ንጉሠ ነገሥቱ አጼ ዮሐንስ በሰሙት መረጃ ስለተደሰቱ ከራስ አሉላ ጋር ተማክረው በከፍተኛ ወንድማዊ ስሜት ለሩሲያው ንጉሥ ዛር አሌክሳንደር ዳግማዊ (እአአ ከ1855-81) በቀጥታ ይፋዊ ደብዳቤ ልከው ነበር። በተላከው ደብዳቤ የተደሰቱት ንጉሡና የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሀገሪቱ መጠናከር፣ ለኦርቶዶክስ እምነት መስፋፋት አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል። በመልሱም የሩሲያ ኦርቶዶክስ 900ኛ ዓመት ክብረ በዓል ንጉሠ ነገሥቱ እንዲገኙ በይፋ ጋብዘው ነበር። አጼ ዮሐንስ ለግብዣ መልስ ይሆን ዘንድ እአአ በየካቲት ወር 1888 በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት አበምኔት አባ ዮሐንስ የተመራ፣ አባ ግሬጎርዮስ እና ሊቀ ዲያቆን ሚካኤልን ያካተተ ልዑክ ሩሲያን እንዲጎበኙና በዓሉን እንዲሳተፉ አድርገዋል።
የአጼ ዮሐንስ ዘመንም እያደገ ለመጣው ግንኙነት የራሱን የዲፕሎማሲ አሻራና ወቅታዊ ድርሻ አበርክቶ አለፈ።
6-የኢትዮጵያ-ወ-ሩሲያ ግንኙነት በ19/20ኛው መ/ክ/ዘ- ዳግማዊ አጼ ምኒልክ
ወደ ሩሲያ ከተላኩ የንጉሠ ነገሥት አጼ ምኒልክ ደብዳቤዎች ውስጥ አንዱ በዓለም የሥነ ጽሑፉና የሰው ልጅ የጽሑፍ ማስታወሻዎች (Memory of the World registration of Human Documentary/Literary Heritage) በቅርስነት ተመዝግቧል። “ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ይድረስ ኀበ ልዑል ወክቡር ፫ኛ እስክንድር ንጉሠ ነገሥት ዘሀገረ መስኮፍ” ይኽ ንጉሠ ነገሥት አጼ ምኒልክ ለንጉሥ እስክንድር ሦስተኛ የላኩት ደብዳቤ መግቢያ ነው። ንጉሠ ነገሥቱ ከኒኮላስ ዳግማዊና ከአሌክሳንደር ሣልሳዊ ጋር ከደብዳቤ በላይ ወደ ቆንሲላ ምሥረታ፣ የልዑካን ልውውጥ እና ግንኙነት ያደገ ውጤታማ እና በሥጦታዎች፣ በጋብቻ፣ በአርበኝነት የተመሰከረ የላቀ ግንኙነት ለማድረግ ችለዋል። በአጼ ምኒልክ ጊዜ ዘመን የተፈጠረው ትስስር አሁን ላለው ዘመናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሠረት የጣለ ግንኙነት ሲሆን ታሪኩን አንደኛ ከዐድዋ ጦርነት በፊት፣ ሁለተኛ በዐድዋ ጦርነት/ከዐድዋ ጦርነት በኋላ በማለት በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን።
6፡1 ከዐድዋ ጦርነት በፊት (ቅድመ ዐድዋ)
ሩሲያን ከአውሮፓ የሥልጣኔና የአስተሳሰብ ደረጃ ካደረሰው መሪ ከታላቁ ጴጥሮስ ቀጥሎ በሩሲያ የተመሰገነ መሪ የነበረው የአሌክሳንደር ልጅ ዛር ኒኮላስ ዳግማዊ በነገሠበት ዘመን (እአአ 1894-1917) ንጉሠ ነገሥት አጼ ምኒልክ ወደ ሩሲያ በርከት ያሉ ልዑካንን ከደብዳቤ ጋር ልከዋል። ከጠላት ወረራ በፊት እአአ በ1895 በፊታውራሪ ዳምጠው (የራስ ደስታ አባት) የተመራ ልዑክ ሩሲያ ደርሶ ተልዕኮውንም በአግባቡ ፈጽሟል። ተልእኮው በአንድ በኩል የራሱ የሆነ ይዘት እና ዓላማ ያለው ቢሆንም በሌላ በኩል ግን ጉዞው የተካሔደው ከውጫሌ ውል በኋላ ስለሆነ ኢትዮጵያ የውጫሌን ውል በሐሳብም በተግባርም እንዳልተቀበለችው፣ ነፃና ሉዓላዊ ሀገር በመኾኗ ከውጭ ሀገራት ጋር ያለ ጣሊያን ሞግዚትነት ግንኙነት ማድረግ እንድምትችል በተግባር ያሳየ የጀግናን የተግባር ቋንቋ ያዘለ መልእክት ነበር። በዚሁ ትዩዩ ደግሞ ሩሲያ ጣሊያን የፈለገቸውን የሞግዚነት ሥልጣን የማትቀበል መሆኑን ያሳየችበት ገና ከጠዋቱ ለኢትዮጵያ ያላትን አጋርነት ያረጋገጠችበት ወሳኝ ምልከት ነበር።
“አጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት፡ 1983 ዓ.ም” በሚለው መጽሐፋቸው ክቡር አቶ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ (20፡ ገጽ 107) ሩሲያ በሃይማኖት ኦርቶዶክስ መሆኗ፣ በአፍሪካ የቅኝ ግዛት የሌላት እና ከምዕራብ አውሮፓ አስተሳሰብ የተለየ መርሕ ማራመዷ በአጼ ምኒልክ እና በመሳፍንቱ ምክር ቤት ትልቅ ዋጋ ተሰጥቶታል ይላሉ። በተግባር ግን ለግንኙነቱ መጀመር እና ማደግ አቺኖቭ ኒኮላይ ኢቫኖቪች፣ ማስኮቭ ባሲሊ የተባሉ የጦር መኰንኖች፣ ካውንት ሊዎንቲቪ ኒኮላይ ስቲቫኖቪች የተባለ የሩሲያ ንጉሥ ከፍተኛ አማካሪ መኰንን እና አባ ኤፍሬም የተባለ መነኩሴ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በተለይም ሊዎንቲቭ Nikolay Stepanovich Leontiev (እአአ 1862-1910) ከወታደርነቱ በተጨማሪ በጣም ንቁ፣ ተግባቢ፣ ሃይማኖተኛ፣ ከንጉሡ ጋር በቅንነት የሚነጋገር ሐቀኛ፣ ሰፊ ዓለም አቀፍ ዕውቀት ያለው የመልክዓ ምድር አሳሽና በአፍሪካ ልዩ ተልእኮ ተሰጥቶት የሚንቀሳቀስ ስለነበር ግንኙነቱን ለመጀመር ሁነኛ ሰው ሆነ። ከዐድዋ ጦርነት በፊት የመጀመሪያውን የሩሲያ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ ይዞ የመጣ ታሪካዊ መሪ ሲሆን በንጉሡ ፊት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ታማኝ ዲፕሎማት ተደርጎ ተቆጠረ። ንጉሡም ከኢጣሊያ ጋር ያለውን ሁኔታ በሚገባ ነገሩት፤ ስለዚህ ከጦርነቱ በፊት አስፈላጊውን ድጋፍ ከሩሲያ ለማግኝት ወደሩሲያ መሔድ ግድ መሆኑ ስለታመነበር ኢትዮጵያን ወክሎ ወደ ሩሲያ የሚጓዝ ልዑክ ምርጫ ተካሔደ።
በመጀመሪያ ልዑኩን እንዲመሩ ሊቀ መኳስ አባተ ቢመረጡም ሊቀ መኳስ አባተ ለዐድዋ ጦርነት ሠራዊት እያሰለጠኑ ስለነበር በምትካቸው ፊትአውራሪ ዳምጠው ከተማ የቡድኑ መሪ ሁነው ተሰየሙ። በአባልነትም ቀኛዝማች ገነሜ፣ መ/ር ገብረ እግዚአብሔር (ካህን)፣ ልጅ በላቸው፣ አቶ ዮሴፍ (የልዑኩ አስተርጓሚ)፣ ልጂ ረዲ (የሊዎንቲቭ የግል አስተርጓሚ) ሁነው ተመረጡ። ራስ መኰንን ከልዑኩ ውስጥ አስተርጓሚው አቶ ዮሴፍ ከጣሊያን ብር እየተቀበሉ ወሬ/መረጃ ስለሚሰጡ በዚህ ከፍተኛ ልዑክ ውስጥ መካተታቸውን አልፈለጉም። ይሁን እንጅ በንጉሠ ነገሥቱና በእቴጌ ጣይቱ ውሳኔ ጣሊያንም ቢሆን “ከፍሎ ይናደድ” ብለው ነው መሰል አካተቱት። ከጉዞው በፊትም ስለ ሀገር ጥቅም ሰፊ የምክር ዝግጅት ተደርጎ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ አንድ ወንጌለ ወርቅ፣ በሐበሻ አንጥረኛ የተሠራ የወርቅ ዘውድ፣ መስቀል፣ እቴጌ ጣይቱም ለንግሥት አሌክሳንድራ የሚሆን የሐር ጥሩር፣ የወርቅ መሶበ ወርቅ፣ የእግር ክታብ፣ የወርቅ አልቦ፣ ጠልሰም፣ የወርቅ ድሪ፣ የወርቅ ወልባ ተዘጋጀ። ጉዞውም በሊዎንቲቭ መንገድ መሪነት ተወጠነ። (ተክለፃድቅ፡ 105)
የግርማዊ ጃንሆይ ዳግማዊ ምኒልክ ልዑክ ሩሲያ ሲገባ በንጉሡ፣ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በፒተርስበርግ ሜትሮፖሊታን፣ እና በልዩ ልዩ መሳፍንት እጅግ ከፍተኛ አቀባበል ተደረገለት። የልዑኩ የጉዞ ዘገባ እና አጠቃላይ ገጽታ ሰነድ አጭር መሆኑ በተለይ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ በአጥጋቢ ሁኔታ አለመጻፋቸውን ክቡር አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ይወቅሳሉ። የሆነው ሁኖ የጉዞው ውጤት አጥጋቢና የተሳካ ነበር። ሩሲያ ለኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ፣ የትምህርት ዕድል እና የሕክምና እርዳታ፣ ከበጎ ፈቃደኞች ጋር ለመስጠት ተስማማች። 30 ሺህ ጠብመንጃ፣ 5 ሚሊዮን ጥይት/ቀልሀ፣ 5ሺህ ሻሞላ/ሳንጃ፣ እና ጥቂት መድፎች፣ በካውንት ሊዎንቲቭ የሚመሩ እና ከኢትዮጵያውያን ጎን ጎን የሚዋጉ የሰለጠኑ በጎ ፈቃደኛ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ልዑኩ ሲመለስ የመጀመሪያው ይፋዊ የውጭ ሀገር የነፃ ትምህርት እድል ለሁለት ኢትዮጵያውያን ተሰጠ። የዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑት ኢትዮጵያውያን መካከል ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ይገኙበታል። በኢትዮጵያ የሩሲያ ጉብኝትና በተገኘው ውጤት እጅግ የተበሳጨው ጣሊያን ባይሳካለትም ሀገር ውስጥ ባሉት ተከፋይ ባንዶቹና በውጭ ወዳጆቹ አማካኝነት ጥላቻ አዘል የሃይማኖት ዲስኩር ጀምሮ ነበር።
ለዚህ ግንኙነት በሩሲያም በኢትዮጵያም የመጀመሪያውን ተልእኮ የፈጸመው ካውንት ሊዎንቲቭ ኒኮላይ ስቲቫኖቪች በሩሲያ ከተሰጠው “ካውንት” የተሰኘ ማዕረጉ በተጨማሪ የደጃዝማችነትና ፊትአውራሪነት ማዕረግ ከንጉሠ ነገሥቱ አገኘ። ከርሱ በመቀጠልም በርካታ የሩሲያ የጦር መኰንኖች ተመሳሳይ ገድሎችን ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ ፈጽመዋል። የሁሉም ውለታና ተሳትፎ የተወሳው ከዐድዋ ጦርነት በኋላ ቢሆንም ከዐድዋ ጦርነት በፊት ቁምነገር የሠሩ የሩሲያውያን ባለሙያዎች፣ የጦር መኰንኖች ተሳትፎ በአግባቡ ባለመጠናቱ በወቅቱ የነበራቸው ተሳትፎና አስተዋጽኦ እስካሁን በሚገባ ሳይታወቅ ቀርቷል።
6.2. የኢትዮጵያና የሩሲያ ትብብር በዐድዋ እና ከዐድዋ ጦርነት በኋላ
በካውንት ሊዎንቲ አነሣሽነት ኢትዮጵያን ለመርዳት ወደ አዲስ አበባ የመጡት በጎ ፈቃደኛ ወታደሮች እንደደረሱ በሁለት ወር ውስጥ ወደ አድዋ ዘምተው ከኢትዮጵያ አርበኞች ጋር ሆነው ተዋግተዋል። ይኽ ክስተት እአአ በ1527 በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜ ከፖርቱጋል ከመጡት የክርስቶፎር ደጋማ ወታሮች ቀጥሎ ሁለተኛው የውጭ እርዳታ ያገኘንበት ታሪክ ነበር። የፖርቱጋሉ ድጋፍ መሪ ክርስቶፎር ደጋማ የሞተበትን በሰሜን ጎንደር ማክሰኝት አካባቢ ያለ ቦታ በስሙ ተሰይሞለት አሁንም “ደጎማ” እየተባለ ይጠራል። በመጀመሪያው የጣሊያን ወረራ ወቅት ሩሲያውያን በአካል መጥተው መደገፋቸው ይቅርና በሩቁ ግንኙነት በማድረጋቸው በጠላት ሰፈር ከፍተኛ የሆነ መደናገጥን መፍጠሩ ከጦርነቱ በፊት የተገኝ የዲፕሎማሲ የበላይነት እና የፕሮፖጋንዳ ድል ነበር። ለዚህ ትልቅ ዕውቅና መስጠትና ማስታወሻ ማቆምም ተገቢ ነው፡፡
ሩሲያውያን በጎ ፈቃደኛ ወታደሮች ጥቂትም ቢሆኑም በዐድዋ ጦርነት የበኩላቸውን ድጋፍ አድርገዋል። ከዐድዋ ጦርነት በኋላ በፖለቲካ፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በብዙ መስኮች የሁለቱ ሀገሮች ትብብር ተጠናክሮ ከመቀጠሉ ባሻገር የጦርነቱ ውጤት በፈጠረው ተጽዕኖ ሩሲያም እንደሌሎቹ የአውሮፓ ሀገሮች በአፍሪካ ያላትን ፖሊሲ እንድትፈትሽ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላታል። ከፖለቲካው ባሻገር በሃይማኖት ጉዳዮች የነበረው ትብብር ሳይቀድምም ሳይዘገይም በእኩል ማደጉን አላቋረጠም፣ ሩሲያ የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ያላት ይዞታ እንዲጠነክር ድጋፏን ሰጥታለች፣ አቡነ ማቴዎስ እአአ በ1902 ኢትዮጵያን ወክለው ሩሲያን ጎብኝተዋል። በሩሲያ መንግሥት ጠንካራ ድጋፍና በጀኔራሎቹ ጥረትም በኢየሩሳሌም የኦቶማን ቱርክ ገዥ የዴር ሱልጣን የኢትዮጵያ ይዞታ እአአ በ1906 እንዲከበር የበኩላቸውን አድርገዋል።
ከዐድዋ ጦርነት በኋላ በጊዜው ይደርሳል ተብሎ የተጠበቀው የሕክምና ቡድን ጦርነቱ ከተፈጸመ ጥቂት ወራት በኋላ አዲስ አበባ ደርሷል። የሩሲያ ቀይ መስቀል ማኅበር አባላት በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት በጀኔራል ኒኮላ ሳቭዶቭ የተመራ 61 የሚደርሱ አባላት ያሉት የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን በነሐሴ ወር አዲስ አበባ ደርሷል። በጊዜው የሩሲያ መንግሥት 150 ሺህ ሩብል ለቡድኑ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በአዲስ አበባ እና በሐረር ከተሞች አገልግሎት ሰጥቷል። ለሥራው የሚያስፈልገው የሕክምና አደረጃጀት ባይኖርም አገልግሎቱ በድንኳን ውስጥ ሁነው በየቀኑ በትንሹ እስከ 150 ሕሙማንን እና የጦር ጉዳተኞችን በማከም አገልግሎት ይሰጥ ነበር።
በሂደትም የመጀመሪያው ዘመናዊ ሆስፒታል መሠረት ለመሆን በቅቷል። የሩሲያ ሐኪሞክ በሚሠሩበት ወቅት ራስ መኰንን እና እቴጌ ጣይቱ ይጎበኟቸው እንደነበር ሲገለጽ ንጉሠ ነገሥቱ አጼ ምኒልክ አበክረው ከመመላለስ በተጨማሪ ሐኪሞቹ የቀዶ ጥገና ሥራ በሚሠሩበት ጊዜ በትኩረት ይከታተሉ እንደነበር ከመነገሩ በተጨማሪ የመጀመሪያው የሕክምና ቡድን ወደ ሀገሩ ሲመለስ ሌሎች ሐኪሞች እንዲተኩ ባቀረቡት ጥያቄ ለሁለተኛ ዙር ሐኪሞች ሲመጡ በሀገራችን የመጀመሪያው ዘመናዊ ሕክምና መስጫ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በመባል ተመሠረተ። በቀጣይም በ1945 ዓ.ም አሁንም ሁለተኛው ሆስፒታል ባልቻ በሚል ሥያሜ ሊቋቋም ለምሥረታው ምክንያት የሆነው የዐድዋ ድል ሃምሳኛ ዓመት አከባባር ሲሆን በዓሉ በአዲስ አበባ የሩሲያ ባህል ማዕከል ሲከበር አብሮ የታሰቡት የሩሲያ ቀይ መስቀል አባላትም ነበሩ። የሆስፒታሉ የመሠረት ድንጋይ በዚሁ ቀን ተቀምጦ በሁለት ዓመት ውስጥ ሥራው ተጠናቆ በ1947 ዓ/ም አገልግሎት ጀመረ።
በሩሲያውያን እና በኢትዮጵያውያን መካከል እየጎለበተ የመጣው የማኅበራዊ፣ የፖለቲካ፣ የውትድርና እና መሰል ትብብር በራሱ በቋሚነት የሚቀጥልበት በኤምባሲ ደረጃ ያደገ የመጀመሪያው የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተወጠነው በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት እአአ በየካቲት ወር 1898 ነው። ተያይዞ የሚነገረው የመጀመሪያው ዘመናዊ የማዕድን ፍለጋ፣ የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት፣ የመጀመሪያው የክቡር ዘበኛ ውትድርና ሥልጠና፣ የጤና ተቋም፣ የመሳሰሉት የሆኑት በዚሁ ወቅት ነበር። ከመጀመሪያዎቹ በደጃዝማች/ፊታውራሪ ካውንት ሊዎንቲቭ የተመሩ በጎ ፈቃደኛ ወታደሮች Shedevr፣ Babichev፣ Agapov፣ Adzeiv፣ Petrov እና መሰሎቻቸው ሁሉ በኋላም በሊዎንቲቭ እና ሌሎች ወዳጆች አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቸው አልተቋረጠም። ቀጥሎ ከመጡት በጎ ፈቃደኞች ውስጠ በተለይ ጀኔራል ባቢችፍ እስከ ፊታውራሪነት ማዕረግ የደረሰ ባለሟል ነበር። ፊታውራሪ ባቢችፍ ከፍተኛ የጦር መኰንን እና አማካሪ የሩሲያው ካዛን ድራጎን 25ኛ ሬጅመንት መሪ እአአ በ1897/98 ወደ ኢትዮጵያ በቋሚነት ለመኖር የመጣ በጎ ፈቃደኛ ነበር። በኢትዮጵያ ከነበረው ቆይታና ኢትዮጵያውያን ከሰጡት ክብር የተነሣ ባቢችፍ ለአንዲት የንጉሣዊ ቤተሰብ ቆንጆ ኢትዮጵያዊት ባል መሆን ችሏል። እህቱ ደግሞ እንዲሁ የተከበረ የኢትዮጵያ ልዑል ሚስት ሆነች። ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚባለው ፊታውራሪ ባቢችፍ እንደ አብርሃም ሐኒባል ሩሲያን እና ኢትዮጵያን በቤተሰባዊ የትውልድ ግንድ ያስተሣሠረ ሁለተኛው ስመ ጥር ባለታሪክ ሆነ። ጀኔራል አብርሃም ሐኒባል በሩሲያ ፊታውራሪ ባቢችፍ በኢትዮጵያ ይሏል እንዲህ ነው። በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡትን አውሮፕላኖች እና ወደፊት በቀጣይነት እንዲመጡ የታቀዱትን የጦር ጀቶችን ለማብረር እንዲችሉ በ1922 ዓ/ም በጅግጅጋ የአውሮፕላን በረራ ት/ ቤት የመጀመሪያውን የበረራ ሥልጠና ወስደው ካጠናቀቁት ሰባት ኢትዮጵያውያን ውስጥ አስፋው አሊ እና የፊታውራሪ ባቢችፍ ልጅ ሚሽካ ባቢችፍ በጥቅምት ወር 1923 ዓ/ም ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ የሥልጠና ማስረጃ ተቀብለዋል። ይኽን ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተሰጠ ሥልጠና የፊታውራሪ ባቢችፍ ወንድ ልጅ ሚሽካ ባቢችፍ በሙሉ የኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ዜግነት አስፋው አሊ ከተባለ ወንድሙ ጋር ሁነው በመሰልጠን የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን አብራሪዎች ተብለዋል። ሚሽካ ባቢችፍ በመቀጠል የጦር አውሮፕላን አብራሪነትም በፈረንሳይ ሀገር ተምረው በተለያዩ የጦር ዐውዶች ለሀገራቸው ከፍተኛ የአርበኝነት ግዳጅ የፈጸሙ ጀግና የበረራ ሻለቃ ነበሩ። በሁለተኛው የጠላት ወረራ ጊዜ ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ጋር ተሰደው በርካታ የዲፕሎማሲ ሥራዎችንም ሠርተዋል፤ የክብር ኒሻኖችንም ተሸልመዋል። የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽንን በማቋቋምና በመምራት፣ በበረራ አሰልጣኝነት፣ በኋላም በዲፕሎማትነት ሀገራቸውን አገልግለዋል። የፊታውራሪ ባቢችፍ ልጅ ሻለቃ ሚሽካ እንደ ጀኔራል አብርሃም ሐኒባል የልጅ ልጅ አሌክሳንደር ፑሽኪን በኢትዮጵያ በልዩ የሙያ ዘርፍ ዝነኛ ሆኑ። የፊታውራሪ ባቢችፍ የልጅ ልጅ የሆኑት ወ/ሮ ናዲያ ባቢችፍ ዝነኛው አባታቸው ሻለቃ ሚሽካ ባቢችፍ በ1958 ዓ/ም ዓርፈው በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በአርበኞች መቃብር በክብር ባረፉበት ቦታ በየጊዜው ዝክራቸውን የደርጋሉ፤ ያረፉበትን መካን አሳይተውኛል። በግርማዊ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የነበረው የኢትዮጵያ ሩሲያ ግንኙነት በወፍ በረር ተነገረ እንጅ በጥልቀት መጠናት ያለበት ለአሁኑ ግንኙነት ቋሚ መሠረት ያስቀመጠ ሰፊ ታሪክ ነው።
7-የኢትዮጵያ-ወ-ሩሲያ በ20ኛው መ/ክ/ዘ- በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ
ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ በኋላ በልጅ ኢያሱ አምስተኛ ዘመን ይህ ነው የሚባል ግንኙነት አልነበረም። በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት በሩሲያ በተፈጠረው የሶሻሊስት አብዮት ምክንያት ግንኙነቱ ተቋረጠ ወይም ቀዘቀዘ። እአአ በ1919 ግንኙነቱን አጠንክሮ ለመቀጠል የቀረበውን ዕቅድም ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ አልተቀበሉትም ነበር። ይሁን እንጅ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በሩሲያ የተደረገው አብዮት ምክንያት ተቋርጦ/ቀዝቅዞ የነበረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት እና ትሥሥር የበለጠ እንዲያድግ እንደሚፈልጉ በግልጽ አሳዩ። አጼ ኃይለ ሥላሴ በኢትዮጵያ ካሉ የሩሲያ ተወላጆች እና የዲፕሎማሲ ተወካዮች ጋር ግንኙነታቸውን አጥብቀው ተጓዙ። ይህ ግንኙነት በሂደት ጠቃሚ ውጤት ማስገኘት ችሏል። በርግጥ በወቅቱ የነበረው ግንኙነት ሩሲያ በሚል ሥያሜ ሳይሆን የተባበረች የሶቪየት ሶሻሊስት ሪፐብሊክ (Union of Soviet Socialist Republics/ USSR) በሚል ነበር። ይህ ሥያሜ በሩሲያ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት፣ የባህል፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ አደረጃጀት አስተሳሰብ እና ሕይወት ዘውግ ውስጥ ሥር ነቀል አብዮታዊ ለውጥ ያመጣ ቢሆንም በኢትዮጵያ ያለውን እውነት በመቀበል ግንኙነቱ ቀጥሎ ነበር።
ኢጣሊያ በድጋሜ ኢትዮጵያን በመውረር ጦርነት ውስጥ በገባችበት ወቅት የኢጣሊያው ንጉሥ ቪክቶር ኢማኑኤል ሣልሳዊ ራሱን የጣሊያን እና የኢትዮጵያ ንጉሥ አድርጎ አወጀ። ይህ አዋጅ በሀገር ውስጥ ኢትዮጵያውያንን በማስቆጣቱ በርካታ አርበኞች፣ አቡነ ጴጥሮስን እና አቡነ ሚካኤልን ሳይቀር ማስቆጣቱ እና ለውጊያ መዳረጉ ይታወቃል። በውጭ ኢትዮጵያ አቤቱታዋን በተባበሩት መንግሥታት ስታሰማ ከጎኗ ከቆሙ ሀገራት መካከል ከፍተኛ ተሰሚነት ያላት ሩሲያ (የሶቪየት ኅብረት) አንዷ ነች። ይኽ መሠረታዊ የሆነ በኢጣሊያ ላይ በቀጥታ የተደረገ የሩሲያ ተቃውሞ ሩሲያ ለኢትዮጵያ በዐድዋ ካደረገችው ድጋፍ የማይተናነስ በኢትዮጵያ ታሪክ ሁል ጊዜ ሲታወስ የሚኖር አጋርነት ነበር። እዚህ ላይ ሊሠመርበት የሚገባው ሩሲያ በፋሽስት ጣሊያን ላይ ያደረገቸው ተቃውሞ ከራስዎ ጥቅምና የውጭ ሀገር ፖሊሲ ብቻ የመነጨ ሳይሆን ሩሲያ ለኢትዮጵያ ካላት ቁርጠኛ አጋርነት ጋር የተያያዘ ለመሆኑ አንዳንድ የሩሲያ ምሁራን ጸፈዋል፡፡
አጼ ኃይለ ሥላሴ በመሠረቱት ግንኙነት መነሻነት በርካታ ትብብሮች እና ድጋፎች ቀጠሉ። ጃንሆይ ሩሲያ ከናዚ ጀርመን ጋር ባደረገችው ጦርነት ለሩሲያ የቀይ ለባሽ ሠራዊት የበኩላቸውን የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ። በሩሲያ በኩል (ሶቪየት ኅብረት) በኢንዱስትሪ፣ በእርሻ፣ በኃይል ማመንጫ ልማቶች እንዲሁም በትምህርት እና በባህል የምታደርገውን ድጋፍ መስጠት ጀመረች። የባህር ዳር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ፣ መልካ-ዋከና ኃይል ማመንጫ፣ የአሰብ ወደብ የነዳጅ ማጣሪያ እና የመሳሰሉት የዚሁ ትብብሩ ውጤቶች ነበሩ። በመንግሥት ደረጃ ጃንሆይ እአአ በ1959 ሩሲያን ሲጎበኙ፤ በግርማቸው ተክለሐዋርያት የተመራ የዲፕሎማቲክ ቡድንም ወደ ሩሲያን ተጉዟል። በርካታ የሩሲያ ከፍተኛ የኦርቶዶክስ አባቶች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። በባህል መስክ በኢትዮጵያ አሌክሳንደር ፑሽኪን መታሰቢያና የሩሲያ የባህል ማዕከል ሲቋቋም በተለያዩ ጊዜያት የሩሲያ የባህል ቡድን እና የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በየሀገራቱ በተከታታይ በመጓዝ የየሀገሮቻቸውን ባህል በመድረክ እና በዐውደ ርእይም አቅርበዋል። በትምህርት ከዳግማዊ ምኒልክ ጀምሮ የተወጠነው ግንኙነት የሩሲያ መምህራን ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣት በተጨማሪ ከሃያ ሽህ በላይ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውን የነፃ ትምህርት እድል እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗል። በትምህርት እድሉ በተለይ በ1960ዎቹ ወደ ሩሲያ የሄዱት ወጣቶች የሶሻሊዝምን ጽንሰ ሐሳብ እና ርዕዮተ ዓለም በማጥናት በሀገራቸው አብዮታዊ ለውጥ ወይም ነውጥ ለማምጣት የሚያስችል ትግል ለመጀመር አንዱ መሠረት ነበር።
በአጠቃላይ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሶቪየት ኅብረት ምንም እንኳ በአንዳንድ ጉዳዮች በውሳኔዋ የመጽናት ችግር ቢኖርባትም ለኢትዮጵያ ያጋደለ የፖለቲካ አቋም ታራምድ የነበረች ለመሆኑ አምባሳደር ዘውዴ ረታ “በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የኤርትራ ጉዳይ (እአአ ከ1941-1963 ዓ/ም)” በሚለው መጽሐፋቸው በመጠኑ ጠቁመዋል። በተለይ ታላቋ ሀገር እና የብዙ ሕዝብ መኖሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር የባሕር በር ያስፈልጋታል የሚለውን የሩሲያን (የሶቪየት ኅብረትን) ጽኑ አቋም በማድነቅ ገልጸዋል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር አክሊሉ ኃብተወልድም በመጠኑ ጠቀስ አድርገውታል። የሶቪየት ኅብረት በኢትዮጵያ ከደጋፊነት በማለፍ በውስጥ የፖለቲካና የማኅበራዊ ሕይወት ለውጥ ውስጥ ቀስ በቀስ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንድታደርግ በር የከፈተውና ራሳቸው በላኳቸው የነፃ ትምህርት እድል ተጠቃሚ ወጣቶች የለውጥ አራማጅነት ከዙፋናቸው የወረዱት የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ነው። የሶሻሊዝም አብዮት በኢትዮጵያ የፈጠረው ታሪካዊ ክስተትም በራሱ በክፍለ ዘመኑ መጀመሪያ በሩሲያ አብዮት ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር ተመሳሳለ። በዓይነቱና በይዘቱ ከመመሳሰሉ ጋር ዓላማውን በመከተሉ በታሪክ ከፍተኛ ለሚባለው የሩሲያ (ሶቪየት ኅብረት) እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ጉልህ መሠረት ሆነ።