ጥቅምት 2019 BBC
ትናንት ጥቅምት 11፣ 2012 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በሩሲያ አፍሪካ የጋራ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ወደ ሩስያ ሶቺ አቅንተዋል። በሩስያ ሶቺ ከተማ በሚካሄደው በዚህ ጉባዔ ላይ ከ35 የአፍሪካ አገራት መሪዎች በላይ ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ በቆይታቸውም የሩስያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ጨምሮ ከአፍሪካ አገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ ለማወቅ ተችሏል።
ሶቪየት ሕብረት ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በፊት በአፍሪካ የተለያዩ አገራት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተሰማርታ የነበረች ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን በአፍሪካ ውስጥ በምጣኔ ኃብትና በፖለቲካ ያላት ተጽዕኖ እየቀነሰ መጥቷል።
• “ኢትዮጵያ የኢህአዴግ አባት እንጂ፤ ኢህአዴግ የኢትዮጵያ አባት አይደለም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ
ሩሲያ ከአፍሪካ ይልቅ ከአውሮጳና ከኢሲያ ጋር የተሻለ የንግድ ግንኙነት አላት። እኤአ ከ2017 ወዲህም አፍሪካ ጠንካራ የንግድ ግንኙነት ያላት ከሕንድ፣ ቻይናና አሜሪካ እንጂ ከሩሲያ ጋር አይደለም።
ለአፍሪካ ሩሲያ ከምታደርገው ሰብዓዊ እርዳታም በላቀ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ጃፓንና አውሮጳ ሕብረት ያደርጋሉ።
“ሩሲያ በአንድ ወቅት የሶቪየት ሕብረት በአፍሪካ ላይ የነበራትን ተጽዕኖ ይኖራታል ማለት ከባድ ነው” የሚሉት ባለሙያዎች “የሩሲያ ተጽዕኖ ውስን ከሆኑ የአፍሪካ አገራት ጋር በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ብቻ በሚኖር ትብብር ይመሰረታል” ይላሉ።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር የሩሲያ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።
ለመሆኑ ሩሲያ ከአፍሪካ የምትፈልገው ምንድን ነው?
የሩሲያ ፍላጎት
ሞስኮ በአፍሪካ ያላትን ሥፍራ ለማስፋት እንዲሁም ግንኙነቷን ማጠናከር እንደምትፈልግ ከሶቪየት ሕብረት ወቅት ጀምሮ የታወቀ ነው።
ፑቲን ከዚህ ጉባዔ ቀደም ብሎ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ እንዳስታወቁት ” የሩሲያ አፍሪካ ግንኙነት እያደገ ነው” በማለት ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን፣ የመከላከያና ደህንነት ርዳታዎችን፣ የምጣኔ ኃብት ድጋፍ፣ ሕክምና፣ ሰብዓዊ ርዳታ እንዲሁም የሙያ ትምህርት ስልጠና ላይ ድጋፍ ለማድረግ እንደተዘጋጁ ዘርዝረዋል።
• የዋግ ኽምራ አርሶ አደሮች ለከፋ ችግር ተጋልጠናል እያሉ ነው
ሩሲያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ፖለቲካዊ ግንኙነት ከ12 አፍሪካ መሪዎች ጋር እኤአ ከ2015 ጀምሮ የጀመረች ሲሆን ከእነዚህ መካከል ስድስቶቹ በ2018 የተቀላቀሉ ናቸው።
ባለፈው ዓመት የቀድሞው የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጆን ቦልተን አሜሪካ ለአፍሪካ አዲስ አጋርነት ስልት እንዳዘጋጀች ጠቅሰው የዚህ ስልት ከፊሉ የቻይናና ሩሲያን ተጽዕኖ መቀነስ ያለመ ነው ብለው ነበር።
ነገር ግን በቅርቡ በዋሺንግተን ፖስት ላይ የወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው ሩሲያ “በደህንነት ጉዳዮች ላይ ግንኙነቶችን ማጠናከርና ስምምነቶች ላይ መድረስ” በከፍተኛ ሁኔታ ትፈልጋለች።
ወታደራዊ ግንኙነት
ሩሲያ ለአፍሪካ ዋነኛ የመከላከያ አጋር ስትሆን የጦር መሳሪያም አቅራቢ ናት። ነገር ግን የመከላከያ ገበያዋ ዋነኛ መዳረሻ አፍሪካ ሳትሆን ኢሲያ ነው።
እንደ ስቶክሆልም ዓለም ዓቀፍ የሰላም ጥናት ተቋም ከሆነ ከ2014 እስከ 2018 በአፍሪካ ግብፅን ሳይጨምር ከሩሲያ 17 በመቶ መሳሪያ ገዝተዋል።
ከዚህ 17 በመቶው ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የምትይዘው አልጄሪያ ስትሆን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ድርሻቸው በጣም ያነሰ ነው።
• አዲስ አበባ ውስጥ ሲካሄዱ የነበሩ ስብሰባዎች በወጣቶች መስተጓጎላቸው ተነገሯል
ለሩሲያ የመሳሪያ ዋና ገበያ ኢሲያ ስትሆን ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ድርሻ በጣም አናሳ ነው። ይህ ቢሆንም ግን ሩሲያ ከ2014 ጀምሮ ከ19 የአፍሪካ አገራት ጋር ወታደራዊ ስምምነት ከፈፀመች ወዲህ እያደገ ነው።
እኤአ በ2017/ 18 ሩሲያ ከአንጎላ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር የመሳሪያ አቅርቦት ስምምነት ፈርማለች። ይህ የተዋጊ ጀቶችን፣ የጦርና የመጓጓዣ ሂሊኮፕተሮችን፣ ፀረ ታንክ ሚሳዔል እና ለተዋጊ አውሮፕላኖች የሚሆን ሞተሮችን ማቅረብን ያጠቃልላል።
የግል ጠባቂ ቡድኖች
የሩሲያ ወታደራዊና ደህንነት ስምምነት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ላይ ያተኮረ ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንዴ የግል ጠባቂ ቡድኖችን እስከማቅረብ የደረሰ ስምምነት ያላቸው የአፍሪካ አገራት አሉ።
ለምሳሌ ሩሲያ በማዕከላዊ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈውን መንግሥት ከአማጺያን ጥቃት ለመከላከል ተሰማርታለች።
ነገር ግን በዚያ ያለው የሩሲያ ወታደራዊ ኃይል ለመንግሥት እና ወሳኝ ለሆኑ የኢኮኖሚ ሀብቶች ጥበቃ ያደርጋል።
የሩሲያ የግል ጠባቂ ወታደራዊ ኃይል፣ ከክሬምሊን ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው የግል ጠባቂ ኃይል፣ ዋግነር፣ በሱዳንና በሊቢያ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካ አገራት ጥበቃ እንደሚያደርግ ይታወቃል።
የሩሲያ ባለሥልጣናት ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ከማለት ተቆጥበዋል።
የምጣኔ ኃብት ፍላጎቶች
ሩሲያ በአፍሪካ በግልጽ የምጣኔ ኃብት ፍላጎቶች አሏት። እንደ ማንጋኒዝ፣ ቦክሳይት እና ክሮሚየም ያሉና ለኢንዱስትሪ ወሳኝ ግብዓት የሆኑ ማዕድኖችን ትፈልጋለች። የሩሲያ የመንግሥት ኩባንያዎች በጊኒ ቦክሳይት ማዕድን የሚያወጡ ሲሆን በአንጎላ ደግሞ ዳይመንድ ለማውጣት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ከሞዛምቢክ ጋርም እንዲሁ ጋዝ በማውጣት ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል።
• “አሁን ያለው ሁኔታ ከቀጠለ ነገ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንደሚገባ ግልጽ ነው” አቦይ ስብሃት
ትልቁ የሩሲያ ኢነርጂ ኩባንያ በካሜሮን፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ፕሮጀክቶች ያሉት ሲሆን በኮንጎ ደግሞ ስምምነት ላይ ለመድረስ እየሰራ እንደሆን ለማወቅ ተችሏል።
ሩሲያ ለበርካታ የአፍሪካ አገራት የኒውክለር ኃይል ቴክኖሎጂን የምታቀርብ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በሚቀጥለው ዓመት በግብፅ በ25 ቢሊየን ዶላር ብድር የሚገነባው የመጀመሪያው የኒውክለር ኃይል ይገኝበታል።