ሰኔ፣ ግብጽ፣ ዓባይና ኢትዮጵያ

የጥንት ግብጻውያን የዘመን መቁጠሪያ፣ ፀሐይን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ‹ዖን› የተባለችውን የፀሐይ አምላክ ያመልኩ ስለነበር ነው፡፡ የዚህች አምላክ ቤተ መቅደስ በሄልዮፖሊስ ይገኝ የነበረ መቅደስ ነው፡፡

በሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

በመጽሐፈ ፊሳልጎስ የሄልዮፖሊስ ቤተ መቅደስና የካህናቱ ሁኔታ ተገልጧል፡፡ ዖን ማለት ፀሐይ ማለት ነው፡፡ በአቡሻህር ሊቃውንት የሚታወቀውና ‹ጥንተ ዖን› (ቅድመ ፀሐይ፣ ቅድመ ብርሃን) የሚለው ቀመር ከዚሁ የተገኘ ነው፡፡

ግብጻውያን አዲሱን ዓመታቸው የሚጀምሩት በመስከረም ነበር፡፡ ስሙንም ‹አኬት› ይሉታል ‹የዓባይ ውኃ የመድረሻ ወር› ማለት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ክረምት የሚጀምረው በሰኔ ወር ነው፡፡ ለግብጽ ደግሞ ሰኔ ዝቅተኛው የዓባይ ውኃ የሚደርስበት ነው፡፡

ዓባይ የመጀመሪያውን አፈር ጭኖ ግብጽ የሚያደርሰው ለሦስት ወራት ተጉዞ በመስከረም ነው፡፡ በዚያ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥቁር አፈር ተሸክሞ ስለሚደርስ፣ ስሙን ‹ኦውር› ይሉታል፡፡ ጥቁር ማለት ነው፡፡

ከመስከረም እስከ ኅዳር በዓባይ ተጭኖ የመጣው የኢትዮጵያ አፈር፣ በዓባይ ዳርና ዳር የሚጠራቀምበት ጊዜ ነው፡፡ የግብጽ ገበሬዎች ዋናው ሥራቸው እርሱን ወደ ዳር እየወሰዱ መከመር ነው፡፡

ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ ዋናው የሰብል ወቅታቸው ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደኅና ክረምት መኖሩን ግብጻውያን የሚያውቁት የዓባይ ወንዝ በአፈር ተሞልቶ እየተገማሸረ እስክንድርያ ከደረሰ ነው፡፡ ወደ ሰሜን ግብጽ ደርሶ ዓባይ በወፍ እግር መልክ (ዴልታ) ግራና ቀኝ አፈሩን ሲደፋው የግብጻውያን ደስታ ያን ጊዜ ይጀምራል፡፡

ግብጻውያን ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያን ሁኔታ መከታተል የሚጀምሩት ከሰኔ ወር አንሥቶ ነው፡፡ የበልጉ ዝናብ ምልክቱን የሚሰጣቸው በሰኔ ስለሆነ፡፡ ከሰኔ በፊት ያለውን ወቅት ‹ሻሙ – ውኃ የሚንጠፋጠፍበት ወቅት› ይሉታል፡፡

በሰኔ ወር የኢትዮጵያ የአየር ሁኔታ መልካም ከሆነ የግብጻውያን መስከረም የተሳካ ይሆናል፡፡ በሰኔ ወር የኢትዮጵያ አየር ከተዛባ የግብጻውያን መስከረም ፈታኝ ይሆናል፡፡

ይሄንን ሁኔታ ግብጻውያን ከዛሬ 5000 ዓመታት በፊት ጀምረው በየሄሮግላፊክሶቻቸው መዝግበውታል፡፡

ግብጽን በዝናብ የሚመግበው የግብጽ ‹አምላክ› በአፈ ታሪክ ‹ሃፒ› ይባል ነበር፡፡ የሚኖረው በተራሮች ነው (ምናልባትም ኢትዮጵያ ማለታቸው ይሆናል)፡፡ ሃፒ ከተቆጣ ዝናብ አይኖርም፡፡ ሃፒ ከተደሰተ ደግሞ ከሰኔ እስከ መስከረም አፈር የሞላው ውኃ ይወርዳል፡፡

የዓባይ ግድብ እየተጠናከረ ከመጣበት ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ሰኔ ለኢትዮጵያውያን የመከራ ወቅት ሆኗል፡፡

ሰኔ ወር ላይ ሀገራችን አስከፊ ግድያዎችን፣ ጭፍጨፋዎችንና መከራዎችን አሳልፋለች፡፡ በሰኔ ወር ታቅደው የከሸፉት የሽብርና የሳይበር ጥቃቶች ደግሞ የትየለሌ ናቸው፡፡

የግድቡን ሂደት ለማስተጓጎል ተሞክሮ የነበረውንና ኢንሳና ሌሎች የጸጥታ ተቋማት ተባብረው ያከሸፉትን የቢልዮኖች የሳይበር ጥቃት ማስታወሱ ጠቃሚ ነው፡፡

ለምን ሰኔ?

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ሰኔ ለግብጽ መንግሥትና ፖለቲከኞች የራስ ምታት ወር ሆኗል፡፡ በሀገራችን ‹በመስከረም የሚቆስል እግር፣ በሰኔ ዝንብ ይወረዋል› ይባላል፡፡

ኢትዮጵያ ሁለት ታሪክ ቀያሪ ተግባራትን በሰኔ ወር ታከናውናለች፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ በበጋ ስንዴ ኢትዮጵያ ያገኘችው ውጤት በዓለም የናኘው በሰኔ ወር መሆኑ ሦስተኛ ራስ ምታት ሆኗል፡፡

የመጀመሪያው አረንጓዴ ዐሻራ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የግድቡ ሙሌት፡፡ አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ ለዘመናት ያጣችውን ሀብት የመጠበቂያና ለትውልድ የምትገነባውን የሕዳሴ ግድብ እድሜ ማራዘሚያ ነው፡፡

ግብጽ ለዘመናት ከኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ ብቻ አይደለም ያገኘችው፡፡ ዓባይ ይዞት የማይሄደው ነገር አልነበረም፡፡ ዕጽዋቱንና እንስሳቱን እየጫነ ይወስዳል፡፡ ታላላቅ ግንዶችን ጭኖ ይሄዳል፡፡ ‹ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል› የተባለውም ለዚህ ነው፡፡

ግብጻውያን ለጽሕፈት የተጠቀሙበት ፓፒረስ ከደንገል ዛፍ የተገኘ ነው፡፡ የደንገል ዛፍ መነሻው ደግሞ የጣና ሐይቅ ነው፡፡ የዓባይ ውኃ የደንገልን ዛፍ ፍሬ ተሸክሞ ወስዶ በግብጽ ሰሜን በዴልታው ግራና ቀኝ ዘርቶታል፡፡

ዓባይ ከመሬት ወለል ተነሥቶ የገባበትን ሸለቆ ለሚመለከት፣ በዘመናት ውስጥ ታጥቦ የሄደውን የኢትዮጵያ አፈር መገመት ይችላል፡፡

ከእንጦጦ ተራራ ጀምሮ በሚገኘው የዓባይ ቆሬ ውስጥ ያለው አፈር ሲጠረግ ነው የኖረው፡፡ በየዓመቱ ከ4 ቢልዮን ቶን በላይ ለም አፈር ይዞ ዓባይ ወደ ሱዳንና ግብጽ ይጓዛል፡፡

ይሄንን እንግዲህ ዓለም ከተፈጠረበት ዘመን ጀምሮ ባሉት ዓመታት ማባዛት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች የሚዘንበው ዝናብና በየጊዜው እየተመናመነ የሄደው የደን ሀብት አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡

ዓባይ መፍሰስ ተፈጥሮው ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሀብት ይዞ መሄድ ግን አልነበረበትም፡፡ የፈሰሰው በተፈጥሮው፣ ሀብት ይዞ የሄደው ግን በስንፍናችን ነው፡፡

የግብጽ ገበሬዎች የኢትዮጵያን አፈር ከዓባይ ግራና ቀኝ እያወጡ ነው በስንዴ ምርታቸው ታዋቂ ለመሆን የበቁት፡፡ አረንጓዴ ዐሻራ ሲጀመር ይህ የሺ ዘመናት ታሪክ ነው የተቀየረው፡፡

በየዓመቱ ቢልዮን ችግኞች መተከላቸው ለግብጽ ፖለቲከኞች ሰኔን በመልካም እንዳያዩት አድርጓቸዋል፡፡ የአረንጓዴ ዐሻራ መስፋፋት በአንድ በኩል የተመናመነውን የኢትዮጵያን የተራራ ደን ይመልሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ግብጽ እየታጠበ የሚወርደውን አፈር እየቀነሰው መሄዱ የማይቀር ነው፡፡ የደን ሽፋኑ ወዲያው ተጽዕኖ ባይኖረውም እንኳን ‹ኢትዮጵያ የአፈር ሀብቷን ለመጠበቅ ቢልዮን ዛፎችን ተከለች› የሚለው ዜና ግን ለግብጽ ፖለቲከኞች የሚመች አይደለም፡፡

ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዳይ የአፈር ሀብትን ከመጠበቅ ባለፈም የሕዳሴ ግድብ እድሜ እንዲራዘም የሚያደርግ ነው፡፡ የግድቦቻችን አንዱ ፈተና በደለል መሞላት ነው፡፡ የቆቃ ግድብ የገጠመው አንዱ ፈተና በደለል መሞላቱ ነበር፡፡ የሐይቁ ጥልቀት ከ10 ሜትር ወደ 1 ሜትር መቀነሱን ባለሞያዎቹ ገልጠዋል፡፡ በዚህ የተነሣ ከሦስቱ ተርባይኖች አንዱ ሥራ እስከ ማቆም ደርሷል፡፡ የሚያመነጨው ኃይልም ከ42 ሜጋ ዋት ወደ 10 ሜጋ ዋት ቀንሶ ነበር፡፡

የቆቃ ግድብ የሚመጣበትን ደለል ለማስወገድ የተጠቀመው ዘዴ ደለልን ከሐይቁ ማስወገድ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ለሃያ ዓመታት ያህል በመቋረጡ ከፍተኛ ኪሣራ ውስጥ ገብቷል፡፡ አረንጓዴ ዐሻራ ባህል እየሆነ ካልመጣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዕጣ ፈንታም ይሄ ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው የግብጽ ፖለቲከኞች አረንጓዴ ዐሻራን በፖለቲካ ጉሮሯቸው ላይ የቆመ አምስት ቁጥር አድርገው የቆጠሩት፡፡

የግብጽ የማኅበራዊ ሚዲያ አቀንቃኞች መነሻቸውን ከሜዲትራንያን ደሴቶች ባደረጉ ዘመቻዎች አረንጓዴ ዐሻራን የሚቃወሙ ቅስቀሳዎችን የጀመሩት በግንቦት ወር አጋማሽ ነው፡፡ በሰኔ ወር ግን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መምጣታቸውን የሳይበር ደኅንነት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የኢትዮጵያን የሳይበር ደኅንነት የሚያስከብሩ ተቋማት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ‹ቀይ ዐሻራ› የሚለውና አረንጓዴ ዐሻራን ለመቃወም የተጀመረው ዘመቻ የተፈጠረውም የሚመራውም በሜዲትራንያን ከምትገኝ አንዲት ደሴት ነው፡፡ የሚያስተጋቡትም የግብጽ የማኅበራዊ ሚዲያ አካላት ናቸው፡፡

በርግጥ ሰሞኑን የግብጽ የማኅበራዊ ሚዲያ መሪዎች ካይሮ ላይ ባደረጉት ስብሰባ ይሄና ሌሎችም ፀረ ኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎቻቸው የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳላመጡ ገምግመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች የክረምት ዝናብ የሚያገኙት ከሰኔ ወር ጀምሮ ነው፡፡ ‹ሰኔ ግም አለ› ይባላል፡፡ ተራሮች ልምላሜ የሚጀምሩበት ወቅት በመሆኑ የወሩ ስም ‹ሠነየ – አማረ› ሊባል ችሏል፡፡

ሰኔ ማለትም ያማረ፣ የለመለመ ማለት ነው፡፡ ከሰኔ ወር ጀምሮ የኢትዮጵያ ዝናብ በመካከልና በሰሜን ተራሮች ላይ መዝነብ ሲጀምር ከሐምሌ ወር ጀምሮ ደግሞ ታችኛው የዓባይ ክፍል ማለትም በምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በተለይ በቤኒሻንጉል ጉምዝ የሚገኘው ታኅታዩ የወንዙ ክፍል በውኃ መጥለቅለቅ ይጀምራል፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይ ግድብ የሙሌት ዝግጅቷን የምትጀምረው በሰኔ ወር ነው ብለው የግብጽ ፖለቲከኞች ያምናሉ፡፡ ስለዚህም ፖለቲካዊ ጭንቀት ውስጥ ይወድቃሉ፡፡

ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ የግብጽ ሚዲያዎችና ግብጻውያን የሰኔ ወር የኢትዮጵያን የሕዳሴ ሙሊቶች መከታተል የሚጀምሩበት ወር ነው፡፡ የግብጽ የመማሪያ መጻሕፍት ዓባይ የሚመነጨው ከደቡብ ግብጽ ነው ሲሉ ነው የኖሩት፡፡

ግብጽ የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን ከሰሜኑ ንፈቀ ክበብ እንጂ ከደቡቡ ንፍቀ ክበብ ጋር አጠናክራ አታውቅም፡፡ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገሮች በዓባይ ውኃ ላይ ተጽዕኖ ያመጣሉ ብላ አስባ አታውቅም፡፡

ግብጽ ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር ለዲፕሎማሲ ግንኙነት መሯሯጥ የጀመረችው ከሕዳሴ ግድብ በኋላ ነው፡፡ በ2009 ዓም ካይሮ ላይ ተደርጎ በነበረው የሕዝብ ውይይት ‹የአፍሪካ ሀገሮች በዓባይ ላይ ይሄንን ያህል ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ከሆነ እስከ ዛሬ ድረስ የተጠናከረ ዲፕሎማሲ ለምን አልመሠረትንም› ሲሉ የግብጽ ታላላቆች ጠይቀው ነበር፡፡

ሰኔ የግብጽ ፖለቲካ የመበጥበጫ ወር ነው፡፡ የግብጽ የደኅንነት ሰዎች ከኢትዮጵያ ባንዳዎች ጋር በመሆን በከፍተኛ ሁኔታ ሀገሪቱን ለማመስ የሚነሡት በሰኔ ወር ነው፡፡ የእሥራኤሉ መስፍን ሳምሶን ‹በጥጃዬ ባላረሳችሁ፣ የዕንቆቅልሼን ትርጓሜ ባላወቃችሁ› እንዳለው፣ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን እንዲያጠቁ የመረጃና የሎጂስቲክስ ድጋፍ የሚሰጧቸው፣ በመዋቅርም ከመዋቅርም ውጭ ያሉት የውስጥ ባንዳዎቹ ናቸው፡፡ የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎች ተደምረው በተለይም ከሰኔ ወር ጀምረው ጆሮ ጭው የሚያደርጉ ሤራዎችን ያውጠነጥናሉ፡፡

የከሸፈው ይከሽፋል፤ ያመለጠው ደግሞ የሕዝቡን ልብ ይሰብራል፡፡

ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓም (በመስቀል አደባባይ)፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓም (በባሕርዳር ከተማና በአዲስ አበባ)፣ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓም የሐጫሉ ግድያና በብዙ ከተሞች የተፈጠረው ግድያና የንብረት ውድመት)፣ ሰኔ 2013 (የሕወሐት ዳግም ወረራ)፣ ሰኔ 11 2014 ዓም (በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ እና ቄለም የተከሠተው ጭፍጨፋ)፡፡ እነዚህ ሁሉ ‹ሰኔና ሰኞ› ገጥመው የተፈጠሩ አይደሉም፡፡

ዓባይ፣ ግብጽና ሰኔ የሚገጥሙበት ወቅት ሆኖ እንጂ፡፡ ከሰሞኑም በዚሁ በሰኔ ወር በእስልምናም በኦርቶዶክስም ቤቶች ጫና የሚፈጥሩ ነገሮች እየታዩ ነው፡፡

ከሱዳን በኩል በድንበር በኩል በዚሁ በሰኔ ወር የተፈጠረው ነገርም ተጨማሪ ጫና ለመፍጠር የተፈለገ ነበር፡፡

የግብጽ ሚዲያ የሕዳሴውን ግድብ ዜና ትተው በኢትዮጵያ ውስጥ ስለደረሰው እልቂት፣ ግድያ፣ ጭፍጨፋ ማውራት ያበዛሉ፡፡ ከሰሞኑ በወለጋ የደረሱትን እልቂቶችና በሱዳን ድንበር የተከሠተውን ነገር፣ የግብጽ ሚዲያዎች እንዴት ተሯሩጠው እንደዘገቡት ማስታወስ ጥሩ ነው፡፡

በአንድ በኩል ኢትዮጵያን በማዳከም ወደፊት እንዳትቀጥል ለማድረግ፤ በሌላ በኩል የግብጽን ሕዝብ በሌላ አጀንዳ ለመያዝ ይጠቀሙበታል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ አዝማቾቻቸውና ዘማቾቻቸው በኩልም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር ይጀምራሉ፡፡ በተደጋጋሚ ባለፉት ሁለት ዓመታት የጸጥታው ምክር ቤት የሕዳሴው ግድብ በተመለከተ በሰኔ ወር እንዲጠራ ተደርጓል፡፡

ነገሩ ሁሉ ያማል፤ ያቆስላል፤ ልብ ያደማል፤ ግን መፍትሔው ከስሜታችን በላይ ከማሰብ የሚገኝ ነው፡፡ ሰው ችግሩን ከዐቅሙ በላይ አግዝፎ ካየው ከመፍትሔ ይልቅ ራሱን ወደ ማጥፋት ያዘነብላል፡፡ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ብዙ ጊዜ ችግራቸውን ከመፍትሔ በላይ አድርገው የሚያስቡ ናቸው፡፡ ማኅበረሰብም ይህ ራስን የማጥፋት የሥነ ልቡና ቀውስ ሊገጥመው ይችላል፡፡
የጸጥታ አካላትን ይበልጥ ማጠናከርና አብረናቸው መቆም አለብን፡፡

ድካማቸውን እያገዝን፣ ፈተናቸው እየተረዳን፤ አብረናቸው መጓዝ አለብን፡፡ በየአካባቢው ሕዝብ ተደራጅቶ ሀገሩንና አካባቢውን ከጸጥታ ኃይሎች ጋር እንዲጠብቅ ማድረግ ይገባናል፡፡ በሕዝብ ውስጥ አጥፊ ሰዎች አሉ እንጂ፣ አጥፊ ሕዝብ የለም፡፡

ሕዝብ የግለሰቦችንና የቡድኖችን ዕዳ እንዲሸከም ማድረግ የለብንም፡፡ ይህ ጠላትን እንጂ ሕዝብን አይጠቅምምና፡፡

ጥርሳችንን ነክሰን የሕዳሴው ግድብ ግንባታ አጠናቅቀን፣ ተፈላጊውን ሙሌት ጨርሰን፣ አረንጓዴ ዐሻራን ባህል አድርገን፣ በብሔራዊ ምክክሩ አማካኝነት ልዩነቶቻችንን አጥብበን፣ ከብሔራዊ ምክክሩ በኋላ የሀገሪቱን ሕጎች ፈትሸን፣ አሻሽለን፤ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷን የጠበቀች ጠንካራ ኢትዮጵያን በጋራ እስካልገነባን ድረስ መፈተናችን አይቀሬ ነው፡፡

በተለይም ከሰኔ እስከ ነሐሴ ያሉት ሦስት ወራት ወሳኝ ጊዜያት ናቸው፡፡

አናጺ ሚስማሩን በመዶሻው የሚመታው ከመዶሻው በላይ ሚስማሩን ጠልቶት ወይም ከሚስማሩ በላይ መዶሻውን ወድዶት አይደለም፡፡ ለእርሱ ዋናው ጉዳይ ጥቅሙ ነው፡፡ መዶሻው ከድንጋይ የተሻለ መምቻ ሆኖ ስላገኘው ብቻ ይጠቀምበታል፡፡ የተሻለ መምቻ ካገኘ መዶሻውን ይወረውረዋል፡፡ የተሻለ ማጣበቂያ ካገኘም ሚስማሩንም ይወረውረዋል፡፡ መዶሻውም አገልግሎቱን ከጨረሰ፣ በእሳት ቀልጦ ለሌላ ነገር እንዲውል እርሱን ለአንጥረኛ ይሰጠዋል፡፡ እርሱ መዶሻ በነበረ ጊዜ ሌላውን ሲቀጠቅጥ እንደነበረው ሁሉ፣ እርሱም በተራው በሌላ መዶሻ ይቀጠቀጣል፡፡

ጠላት አንዳችንን የሌላችን መምቻና መግደያ፣ አንዳችንን የሌላችን ማጥፊያና ማስለቀሻ ሲያደርግ ከሟቹ ይልቅ መግደያውን፣ ከአልቃሹ ይልቅ ማስለቀሻውን የበለጠ ወድዶትና አክብሮት አይደለም፡፡ ለጠላት የተመቸ መሣሪያ ሆኖ አግኝቶት ነው፡፡ ነገ በተራው ሌላ የተሻለ መሣሪያ ሲያገኝ እርሱንም አልቃሽና ሟች ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህ ሁነኛው መፍትሔ ሁላችንም ለሁላችንም ዘብ መቆም ነው፡፡

ጠላቶቻችን ምንም ያህል ግዙፍና አስቸጋሪ ቢሆኑም፣ የመፍትሔውን መንገድ ካወቅነው፣ ቀድመናቸው መሮጥ እንችላለን፡፡

‹መንገድ የምታውቅ አይጥ ከፈረስ በላይ ትሮጣለች› እንደሚባለው፡፡

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories