
እስሌማን ዓባይ – የዓባይ፡ልጅ
ሀገር አማን መፅሔት ላይ ካቀረብኩት መጣጥፍ የቀነጨብኩት፤ ሙሉውን በዚህ የቴሌግራም ሊንክ ማግኘት ይችላሉ https://t.me/hageraman/397
ከአልሸባብ ሶስት የግድያ ሙከዎች ተርፈው አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝደንት ድጋሚ የቪላ ሶማሊያ መሪ ሲሆኑ ቀዳሚ አጀንዳቸው ሽብርተኝነትን መዋጋት የሚል ነበር። ከቀናት በፊት the Economist የተባለው የኒዮ ሊበራሊዝም አቀንቃኝ መፅሔት ፅሁፋቸውን አስነብቦላቸዋል። ሽብርተኝነት ከእስልምና ጋር አይገናኝም ሲሉ በይፋ የገለፀው መጣጥፋቸው ለአለም ተነበባቢነት በበቃበት ሳምንት ነው አልሸባብ የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ መንደሮችን ያጠቃው። በዚህ ዙሪያ እውነቱን እስክናረጋገጥ ድረስ ስለአሁናዊው ጥቃት መነሾ በተለያዩ አካላት የሚሰነዘሩ መላምቶችን በትላንት እውነቶች እያሟሸን እንቆያለን። ይህም ለሶማሊያ “ፍዬል ከመድረሷ” የሚያስብላት ታሪኳን በምልሰት እንዳስሳለን።
▪️ህወሃታዊ ታሪኳ
የሶማሊያ መንግስት በኢትዮጵያ ወረራ ሊያደርግ ሲዘጋጅ ያደረገው በፀረ ኢትዮጵያ አቋም ነፍጥ ያነሱ ድርጅቶችን ነበር የወረራው አካል ያደረጋቸው፡፡ ትግራይን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ መንግስት ለመመስረት ኢትዮጵያን ሲወጋ የነበረውን የሕወሓት መሪ መለስ ዜናዊ፤ እንዲሁም ከኦሮሚያና ሲዳማ የተነሱ ታጣቂዎች ምሽጋቸው ሞቃዲሾ ነበረች። እነዚህ ሰዎች በተለያዩ ሀገሮች የሚዘዋወሩት በሶማሊያ ፓስፖርት የነበረ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፤ (ሻ/ፍቅረስላሴ ወግደረስ፤ እኛና አብዮቱ)።
ደርግ ገና ስልጣን ከመያዙ ድንበሬ አዋሽ ወንዝ ነው ብሎ እስከ “ድሬዳዋ ኤይር ፖርት” የደረሰውን የሶማሌ ጦር እየተዋጋ ወደ ነበረበት እንድያፈገፍግ ሲያደርግ መለስ ዜናዊ እና የህወሃት ባለስልጣናት ዚያድ ባሬ በሰጣቸው የሶማሌ ፓስፖርት እና “ጊዚያዊ ዜግነት ” ኢትዮጵያን ለሚወጋው የሱማሌ ጦር ድጋፋቸውን መስጠት ብቻም ሳይሆን የስለላ ድጋፍም ያገኙ እንደነበር ይታወቃል።
▪️የህወሃት የተውሶ ጡንቻ
ሌላው ደግሞ አሜሪካ መራሹ የምዕራባዊያን “ፀረ ሽብር” የተባለ አለም አቀፍ የዘመቻ ተውኔት ነው። መሪር(ትራጄዲ) ዘውግ በነበረው “ፀረሽብር” ባሉት ትያትር ከዋነኞቹ ገፀ ባህርያት መካከል ሆና የገነነው የመለስ ዜናዊ ህወሃታዊ መንግስት ነበር፡፡ አቶ የሶማሊያ መንግስት አልባነትና የምዕራባዊያኑ የፀረ ሽብር ዘመቻ ትያትር ፍቅርን ተጠቅመው ለፖለቲካዊና በዶላር ዘረፋ ኪሳቸውን ለማሳበጥ ተጠቀሙበት፡፡ ህወሃትም በተውሶ ጡንቻው አበጠ፤ በዚህም ሀገር አንድነትን የሚያቀነቅኑ አስተሳሰቦችን ከማድቀቅ ውጪ ሳይፈይድ አመታትን አሳልፎ አልፏል።
አሜሪካ ለፀረ ሽብር አጋርነት ለመለስ ዜናዊ አገዛዝ በአመት እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ድረስ ትከፍል ነበር። ገንዘቡ በዋነኛነት በፀረ ሽብር ዘመቻ ለሚሰማሩ ወታደሮች የሚከፈል ቢሆንም ህወሃት ግን ሌሎች መንግስታት ከሚያደርጉት በተለየ ነበር የተጠቀመበት። ለወታደሮች የሚመጣውን ዶላር ተቀብሎ ከግማሽ ያነሰውን ነበር የሚከፍለው። ቀሪው ገንዘብ ወደ መንግስት ካዘና የሚቀመጥ ሳይሆን የህወሃት የዶላር ማሸሽ Currency Laundering ሰለባ ነበር የሆነው። የሚገርመው ደግሞ ህወሃት የራሱ ብሄር ወታደሮችን በሌላው ላይ የበላይ በማድረግ የነሱን የዶላር ሙሉ ክፍያ በውጭ ሀገራት በተከፈቱ አካውንቶች በዶላር ምንዛሪ እንዲያስቀምጡ ማድረጉ ነበር።
ከዚህ ባለፈ ለአቶ መለስ የሶማሊያ ቀውስና የአልሸባብ ሽብር ራሳቸውን በዓለም አቀፉ ፖለቲካዊ መድረክ ራሳቸውን እንዲያስቀምጡ የተጠቀሙበት የበር፡፡ የቀጣናው የአሜሪካ ቁልፍ አጋር እየተባለላቸው በቡድን 7፣ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረምና በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ተንታኝና ተሟጋች ሆነው ብቅ አሉ፡፡ ምእራባዊ ሚዲያዎችም አብዝተው ይዘምሩላቸው ጀመር፡፡ (ታዲያ ይህን ሁሉ ተውኔት የታዘብነው ከምርጫ 97 ህወሃታዊ የአዲስ አበባ እልቂት ማግስት መሆኑን ልብ ይሏል)።
ወደ አልሸባብ ሰሞንኛ ጥቃት ተመልሰን የክስተቱን ፖለሂካዊ መነሾ መጠየቅም አስፈላጊ ነው። የቀድሞው የቪላ ሶማሊያ ደህንነት ዋና ዳይሬክተር ዋና መነሻ ያደረጉት በአዲሱ የሶማሊያ መንግስት ሰርጎ የገባውን ህዋሃታዊ ነቀዝ ነው። ሐሰን ሼክ ማህሙድ ነቀዙን ማፅዳት አለባቸው ሲሉም መክረዋል።
ስለ ሰሞነኛው የአልሸባብ ድርጊት ከተለያዩ አካላት የተሰነዘሩ መላምቶችን በቀደሙት ዘመናት በተከሰቱ እውነታዎች መስኮት ለመመልከት እንሞክር። “አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ” የተሰኘው የፕሮፌሰር መስፍን የ2004 እትም መፃሐፋቸው ከገፅ 112 ጀምሮ ከሰፈሩ ታሪኮች ተከታዩን መራረጥኩላችሁ..።
የሶማልያ ታሪክ የማያስደንቅም የሚያሳዝንም ነው፤ በመሠረቱ ሶማልያ ሳይጸነስ የተወለደ አገር ነው) ሶማሊላንድ እኤአ በሰኔ 26 ቀን 195ዐ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ወጥቶ ራሱን ሲችል፤ በደቡብ በኩል የኢጣልያ ቅኝ ግዛት የነበረው ሶማልያም ለአሥር ዓመታት ያህል በኢጣልያ ስር የተባበሩት መንግሥታት የሞግዚት አስተዳደር ሆኖ ቆይቶ ራሱን የመቻል ዕድልን ኢኤአ በሐምሌ 195ዐ ዓም፤ ምንም የመመካከርና የመፈታተን ሙከራ ሳይደረግ ወዲያውኑ ሶማሊላንድና ሶማልያ የውኅደት ስምምነት ተፈራረሙና ሶማልያ የሚባል አገር በአጉል ቀዶ ጥገና ተፈጠረ፤ በእንግሊዝ አስተዳደርና በእንግሊዝ የባህል ተጽእኖ ስር የቆየሁ ሶማሊላንድ፣ በኢጣልያ አገዛዝና በኢጣልያ የባህል ተጽእኖ ስር ከቆየው ሶማልያ ጋር አንድ ላይ ሆነው : ሰማልያ በኋላ ደማዋ በጎሣ ስሜት ተቀዳዶ በመኖርና ባለመኖር መሀከል የሚያቃስት ነገር ሆኖአል፤ ያሳዝናል፣ አጀማመሩ ግን ከብዙ የአፍሪካ አገሮች የተሻለ የሕዝብ ሥልጣን የታየበት ነበር፣ ይህ ያስደንቃል፤
ሶማሊያ ጥሩ አብጦ የመፈንዳት ምሳሌ ነው፣ በአውሮፓ ጀርመን ሌላ አብጦ የመፈንዳት ምሳሌ ነበር፤ የእንግሊዝ ቅኚ ግዛት የነበረው የማሌላንድና የኢጣልያ ሶማሌላንድ ከላይ እንደተገለጸው አዲስ አገር ፈጠሩ፤ ገና መዳህ እንደ ጀመረ እኤአ በ 1963 ከኬንያ የድንበር ጠብ ጀመረ፤ በ1956 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በቱግ ውጫሌ በኩል ለመውረር ሞከረ! በጄኔራል አማን የተመራው የኢትዮጵያ ጦር የሶማልያን ጦር አባርሮ በአሜሪካ ተጽእኖ መሆን በሶማልያ ድንበር ላይ ቆሞአል። ይህ ጦርነት የሁለቱ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች የመጀመሪያው የእብጠት መግለጫ ነበር። አንድ በ1956 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የጦር ኃይል በምኑም በምኑም ከሶማልያ ጋር የማይወዳደር አገርን የሚያኮራ ነበረ፤ ነገር ግን በጦርነት ሳይንስ የሠለጠኑ ሰዎች ነበሩ ለማለት አያስደፍርም ምክንያቴን ልግለጽ፣ ሶማልያ ኢትዮጵያን የወረረው በቱግ ውጫሌ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ነበር፤ የጦርነትን ዓላማና ስልት የሚያጠና ሰው ሶማልያ በቱግ ውጫሌ በኩል ወደኢትዮጵያ የገባችው ለምንድን ነው? ብሎ በመጠየቅ መጀመር አለበት፣ ለዚህ ጥያቄ መልሱ ግልጽ ነው፤ የጂጂጋ፣ የሐረርና የድሬ ዳዋ ከተሞች በዚህ መስመር ናቸው፤ በተጨማሪም የባቡር ሀዲዱን ለመቆጣጠር ይህ አቅጣጫ አመቺ ነው ግን ሶማልያ በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ይህንን ለማድረግ በፍጹም አትችልም ነበር፤ ታዲያ ለምን ደፈረች? ብሎ መመርመርና ማሰብን የሚፈልገው በትክክለኛ አስተሳሰብ ሲታይ ጦርነት ጭፍን የጥፋት ተልእኮ ብቻ አይደለም፤ መሆንም የለበትም። ጦርነት የፖሊቲካ እንዲኖረው ያስፈልጋል፤ እንግዲህ ስል በተግ ወሌ በኩል ያደረገው ወረራ ፊት ለመያዝ ካልሆነ የፖሊቲካ ዓላማው ምን ነበረ? ትንሽ ምርምር አድርጌ እንደደረስሁበት…።
በዚያን ጊዜ በሰሜን ሶማልያ (የብሪታንያ ሶማሊላንድ) ወጣት መኮንኖች ዓምፀው የመገንጠል ንቅናቄ ጀምረው ነበረ። በዚህ ምክንያት አንድ ብልህ መሪ በቱግ-ውጫሌ በኩል በኢትዮጵያ ላይ የማያዋጣ ጦርነት ከፍቶ በማፈግፈግ የኢትዮጵያ ጦር ተከታትሎ የሰሜኑን የሶማልያ ክፍል እንዲቀጣለት አቅዶ ከሆነስ? የደቡቡ ሶማልያ መሪ ዓላማው ይህ ከነበረ ተሳክቶለታል። ኢትዮጵያ ባለዓየር ኃይል ሆነችና ሀርጌሳን በአውሮጵላን ደበደበች። ስለዚህም ሶማሊያ በጡንቻ ተሸንፎ የፖሊቲካ ዓላማን አሳክቶ ሊሆን ይችላል። እንግዲህ ይህ የመጀመሪያው ሶማልያ ጋና በመዳህ ላይ እያለ የከፈተው ጦርነት ነበር።
…የዚያድ ባሬ አገዛዝ በሀገሬው ህዝብ እየተጠላ በሄደ መጠን ጭካኔውና ማናለብኝነቱ እየከፋ ሄደ። በተቃውሞው ጥንካሬ የተነሣ የጦር ኃይሉንና የፖሊስ ሠራዊቱን እንዲያጠናክርና በዘመናዊ መሣሪያዎች እንዲያስታጥቅ ግድ ሆነበት ለዚህም ዓላማ በቂ መሣሪያ ለማግኘት ሶማልያን ለጨረታ አቀረበ፤ ሶማልያ በደቡብ በኩል ወደቀይ ባሕር መግቢያውንና የህንድ ውቅያኖስን የመርከቦች ጉዞ ለመቆጣጠር አቀማመጡ የተመቸ ነው። ሶማልያን በፖሊቲካ ሽርክና ለማጠናከር እአአ በ1974 የአረብ ማኅበር አባል ሆነ፤ በተጨማሪ ሶማልያ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ረጅም የባሕር ጠረፍ ሌላው የአቀማመጥ ጥቅም ነው፤ ሶማልያ ለጨረታ ያቀረበው እነዚህን ጥቅሞች ነበር፤ ጊዜውም የአሜሪካና የሶቭየት ኅብረት በከፋ ውድድር ተወጥረው የነበረበትና አሜሪካ በኢትዮጵያ (ኤርትራን ጨምሮ) ላይ ሙሉ ተጽእኖ ያሳደረበት ነበር። ስለዚህም በኢትዮጵያ ውስጥ በፖሊቲካና በጦር መሣሪያ ጫና ተጠናክሮ የደረጀውን አሜሪካ ለመቋቋም ሶቭየት ኅብረት ሶማልያን በጣም በማስታጠቅ በጦር ኃይል ከአካባቢው የበለጠ አገር አደረገው።
በስዒረ-መንግሥት 1969እኤአ ስልጣን የጨበጠው ጄኔራል ዚያድ ባሬ ከጀርመን ናዚዎች ባገኙት የተውሶ ምኞት ሶማሌዎች የሚኖሩበት መሬት ሁሉ የሶማሊያ ነው ብሎ አወጀ። በዚህም መሰረት ከጂቡቲ ቢያንስ ግማሹን፣ ከኬኒያ የሰሜኑን ክፍል እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦጋዴንን ወደ ሶማሊያ ግዛት ለማስገባት የአገር መመሪያ አደረጉት።
የውስጥ ችግሩን በአፈና ከአስተካከለ በኌላ ጡንቻውን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ። ይህም ሶማልያ በራሷ ለሁለተኛ ጊዜ ወረራ መጀመሩ ሲሆን፤ ደርግ በኢትዮጵያ መጠላት የጀመረበት ጊዜ ነበር። እንዲሁም ደርግ በሰሜን የሻቢያና የወያኔ ዓመጸኞች የተጠናከረ ጦርነት ከፍተው ነበር። በምዕራብ በኩል ደግሞ ኢዴኅ (የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ወይም ኢዲዩ) የሚባለው የደርግ ተቃዋሚ ድርጅት ጦርነት ጀምሮ ነበር፤ እንግዲህ በሶማልያ በኩል የተከፈተው አራተኛ የጦር ግንባር ነበር።
በዚህም የተነሣ የሶማልያ ጦር በአሥር ቀኖች ውስጥ በ1977 ዓ.ም ጂጂጋን ለመቆጠር በታ ከኢጣልያ ወሪራ በኋላ ኢትዮጵያ ውርደትን የተከናነበችበት ጊዜ ነበር፤ በአንዲት ትንሽ አገር ተደፍራ ሰፊ የሆነ መሬት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በሶማልያ ቁጥጥር ስር የሆነበት..።
…የሶማልያ እብጠት ለሶቭየት ኅብረትም የማይመችበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል፤ በዚህም ምክንያት የሶቭየት ኅብረት ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ኢትዮጵያ ገባ። ይህ ሁነት በጣም አስደናቂ ነበረ፤ የሶቭየት ኅብረት የበላይነት ነገሠ፤ መንግሥት የሚመስል የተባበሩት መንግሥታት የፖሊቲካ ጥረትም ሆነ የሰላም ኃይል የሶማልያን ሁኔታ ሊለውጠው አልቻለም። ዓለም ሰልችቶት ሶማልያ የእርስበርስ ጦርነት ሕዝቡ ሲያልቅና ንብረት ሁሉ ሲወድም ተመልካች ሆነ፤ በአፍሪካ ኅብረት በኩል የተደረገው ጥረት እንዲሁ ቀረ። የሶቬት መንግስት ብዙ እንጥፋቶች ያሳለፈበትን ወዳጅነት አቋርጦና አሜሪካን ያስጨነቀውን በኤደን የባሕር ሰላጤና በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የሶቭየት ኅብረት የነበረውን የበላይነት ትቶ ኢትዮጵያን ለመርዳት ቆረጠ። በምን ምክንያት እንደሆነ ብዙ ሰዎችን ያወዛገበ ጉዳይ ነበር፤ እኔ በኢትዮጵያ ረጂም ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት ተአምሮች አንዱ ነው ብዬ አምናለሁ። የሶቭየት ኅብረት ሶማልያን ትቶ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የሶማልያን የወረራ ዓላማ ለማክሸፍ ቆርጦ ነበር፤ ስለዚህም ከባድ የጦር መሣሪያዎችን ከሶቭየት ኅብረት፣ ከኩባ እና ከየመን ወታደሮችን በአውሮጵላን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማስመጣት የኢትዮጵያ ጦር አንሰራርቶ የሶማልያን ጦር ተጋፍጦ እንዲበታትነው አደረገ።
በሶማልያ ላይ የደረሰው ሽንፈት ከባድ ኪሳራንና ውርደትን በማስከተሉ እብጠቱ ተነፈሰ። የዚያድ ባሬም አገዛዝ ቁልቁለቱን ወርዶ ወደቀ።
የቀድሞው የአንግሊዝ ሶማሌላንድ የቀድሞ ስሙን ይዞ እኤአ በ 1991 ተገነጠለ፣ አንድ ሌላ ክፍል ደግሞ ፑንትላንድ የሚል ስም ይዞ እአአ በ1998 ተገነጠለ ከፊሉ የቀድሞው የኢጣልያ ሶማሊያ በጣም በከፋ እና በሚያሳዝን ሁኔታ በጎሣ መሪዎች ተበታትና ለሀያ ዓመታት ያህል አገር የሚባል ነገር ሳይኖር እስካሁን ቀጠለ፤ የሶማልያ እብጠት ፈጽሞ ፈነዳ! ዓለምን በሙሉ ያስቸገረ ሆነ፣ ኢኤአ በ1992 አሚሪካ ወታደሮችን ልኮ ሥርዓት ለመፍጠር ሞክሮ ተዋረደና በንዴት ብዙ ሶማሊዎችን ጨፍጭፎ በአንድ ዓመት ውስጥ ወጣ፤ የተባበሩት መንግሥታት የላከው ጦር እንዲሁ ሳይሳካለት አአአ በ1995 ከሶማልያ ወጣ። ከዚያ በኋላ ሶማልያ ብቻውን ይተራመሳል፡፡
አዲሱ የቪላ ሶማሊያ መሪ የሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ሶማሊያ እውነት ደግሞ ቀን ገልጦት የምንመለከተው ይሆናል።