በሠላም ስም ጭፍጨፋ: የአሜሪካ ወረራ በኢራቅ

    የዓባይ፡ልጅ

የአሜሪካ እና እንግሊዝ ርዕሣነ-መንግስታት ኢራቅን የመውረር ዕቅድ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ማብቂያ ጀምሮ የተለሙት መሆኑን በቅርብ ይፋ የሆኑ ሰነዶች ማሳየት ጀምረዋል። ወረራውን በተግባር የለወጡት ጆርጅ ዊሊያም ቡሽ እና ቶኒ ብሌር የፈረንጆቹ 2003 – ኢራቅ ላይ መዓት ለማውረድ እጅጉን የቋመጡበት አመት ነበር።

“ፕሬዝደንት ሳዳም ሁሴን ለኢራቃዊያን ክፉ መሪ ናቸው። በእብሪት ጎረቤት ሀገራትን ይወራል” ወዘተ.. ሲሉ ወነጀሉ፤ “ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ታጥቋል። ለሀገራችን ስጋት ናቸው። ሳይቀድመን እንቅደመው። እንማርከው። ኢራቃውያንን ነፃ እናውጣቸው”..ትርክት ማምረት ቀጥለዋል፤ ሰበብ አብዝተዋል…።

▪️የአንግሎ-አሜሪካ የደም ጥማት..
ይህን የወረራ ጉሰማ በመስጋትና በመቃወም ብዙ ሰላማዊ ሰልፎች ተደርገው ነበር። በተለይ በጣልያን ሮም ከተማ 3 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች ጦርነት እንዳይኖር የተቃወሙበት ሰልፍ በተለዬ የሚታወስ ነው።
ምዕራባዊያን የሚድያ ተቋማት ጦርነቱ እንዲጀመር የዜጎቻቸውን እና የአለምን ህዝብ አእምሮ በማሳመን Brainwashing ዘመቻቸውን ቀጠሉበት። ከአሜሪካዊያን በተሰበሰበ የአስተያየት ናሙና 64 በመቶ አሜሪካውያን “ኢራቅ” ላይ መታደራዊ ርምጃን ደገፉ” በማለትም ቆርጠው ቀጠሉ።

በመጨረሻም የአሜሪካ ኮንግረስ ጦርነቱን(ወረራውን) አፀደቀ። ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ “ሳዳም ሁሴንን እና ወንድ ልጆቹ በሃያ- አራት ሠዓታት ዉስጥ ኢራቅን ለቃችሁ ውጡ” የሰጡት ሶስት ቀናት እንደተጠናቀቁ በ 2003 መጋቢት 22 እኤአ ኢራቅ ላይ ጦርነት አወጁ። ከዛም…
የጥንታዊ ሥልጣኔ መገኛ፣ በነዳጅ፣ በተማረ ሰው ሀይል የላቀች የተባለላትን ኢራቅ በሂደት የጥፋት ሰበብና ተምሳሌት ትሆን ዘንድ ተገደደች።
የአሜሪካ ወረራ ዘ-ኢራቅ ከ 189 ሺህ በላይ የንፁሃንን ቀጥፏል፣ ከ 4 ሺህ በላይ የአሜሪካ ወታደሮች ሞተዋል፣ ከ 32 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ክፉኛ ቆስለዋል፣ ከ 3 ሚልዮን በላይ ኢራቃውያን ተፈናቀሉ፣ በታሪክም ብዙ ጋዜጠኞች የተገደሉበት ማለትም 154 ዘጋቢዎች የሞቱበት ጦርነት ሆኖም ተመዘገበ።

▪️ ከጦርነቱ በኋላ…

ኢራቅን እንውረር ሲሉ የነበሩት የያኔው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ስለ ሳዳም ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ መስራት የተናገሩት ውሸታቸዉን እንደነበረ ለማመን ተገደዋል። ስህተቴን አምናለሁ። ተቀብያለሁም አሉ። ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌርም ሥልጣናቸዉን በግድ እስከ መልቀቅ የሚጠይቅ መርማሪ ኮሚቴ ፊት ጥፋታቸዉን መናዘዝ ነበረባቸዉ።
በኢራቁ ጦርነት ዘማች የነበረው አሜሪካዊ ማይክ ፕሪስነር ቡሽን ካልደበደብኩ ሲል ውሸታምነቱንና በርካቶችን ለሞት መዳረጉን በአደባባይ በመጮህ ሲሳደብ ተመለከትነው።

ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ፣ የጆርጅ ደብሊዩ ቡሽ ወንድም ጄብ ቡሽ፣ የሲአይኤው ተንታኝ ጆን ኒክሰን፣ ፕሬዝደንት ትራምፕ… ሌሎችም ሌሎችም የቡሽን ውሳኔና የኢራቁን ወረራ ትልቅ ስህተት ሲሉ ከአመታት በኋላ ሲያወግዙና ሲፀፀቱ ተደመጡ። ይሁንና ዉሸታምነትንም ሆነ ጥፋተኝነትን ማመን ለኢራቅም ሆነ ለኢራቃዊያን የፈየደው ነገር የለም። ፀፀቱ ሁሉም ካለፈ፤ የልባቸውም ከሰመረላቸው በኋላ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጠባቸው እነዚያ ውሸታም መሪዎች በፍትህ ሲዳኙ አለመታየታቸውም ጭምር ዓለማችን ለተጠናወታት ፍርደ ገምድልነት ሕያው ምስክር ነበር…።

▪️ የአሜሪካ ወረራ የወለደው ሌላ ጭፍጨፋ…

ምዕራባዊያኑ ሳዳምን ከስልጣን አንስተው፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ያውም በዒደል አረፋ ዕለተ-በዓል ገድለውና ሃገሪቷን ካወደሙ በኋላ በምትኩ ISIS የተባለ ጨካኝ አሸባሪ ቡድን እንዲፈጠር ሁኔታዎችን አመቻቹ። ወረራው የኢራቅ ሰራዊትን በተነ፤ ስርአት አልበኝነት ነገሰ፤ ይህን ለማስተካከል ብሌርም ሆኑ ቡሽ ግድ አልነበራቸውም። በኢራቅ በርካታ ታጣቂ ቡድኖች መንግስት መንግስት መጫወት ጀመሩ። አንጃዎቹ እርስ በርስ እየተጠፋፉ አንዳንድ ጊዜም ጥምረት እየፈጠሩ ISIS ወይም ISIL የሚባለውን ደም መጣጭ ቡድንን ወለዱ። ቡድኑ ከወረራ የተረፈችውን ኢራቅ አፈራርሶ፤ ሶሪያን የደም ምድር ለማድረግ መስፋፋቱን ቀጠለ። የገዳይ ቡድኑ አባላት ከሁሉም ሀገራት በድብቅ ይመለመሉ ቀጠለ። በአይሲስ የሚሞቱ ዜጎችም የአለም ሀገራት ዜጎችን ሆነ። የኛ የኢትዮጵያ ወንድሞቻችን በዚሁ አሸባሪ በግፍ ታረዱ።
የዚህ ሁሉ መነሾ ነው በማለት፤ አንግሎ-አሜሪካ ኢራቅን መውረራቸው ስህተት ነው ያሉት ፕሬዝደንት አባማ-እሳቸውም ከጓዶቻቸው የተለዩ አልሆኑም። በሶሪያ የአሳድን መንግስት ለመጣል ሲሉ ISIL ሲሉ የጠሩትን አሸባሪ የኦባማ መንግስት መደገፍ ቀጠለ። አይሲስን ስለመደገፋቸው የተጠየቁት ፕሬዝደንት ኦባማ “We are supplying weapons to ISIL Moderate Soldiers to oust the Assad regime” ሲሉ አሸባሪውን moderate በምትል የስም ቅጥያ ማቆላመጥ ድጋፋቸውን አመኑ። ቀጣዩ መሪ ትራምፕ በተመሳሳይ ቡሽን ያወገዘ ቢሆንም፤ በዬሃገራቱ የሚሳይል ጥቃቱን ቀጥሎበት mother bomb የተሰኘውን ግዙፍ ገሃነማዊ መሳሪያ መፈተሻነት የመረጠው መካከለኛው ምስራቅን ነበር።

የዋሽንግተን አመራሮች ከዚህ ሁሉ ጥፋትና ውድመት ለመማር በቂ የሆኑ አስርት አመታት ቢቆጠሩም በተቃራኒው በስህተት ላይ ስህተትን መረጡና ወደ አፍጋኒስታን ዘልቀው በቆዩባቸው 20 አመታት ሚሊዮኖችን ሙት ቁስለኛና ስደተኛ አድርገዋል። ትሪሊዮን ዶላሮችን አፍስሰዋል።

በየመን ሊቢያና ሶሪያም በተመሳሳይ። ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ በታሊባን ኃይሎች ተገፍታና ተዋርዳ ከአፍጋኒስታን ብትወጣም ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም እንደሚባለው ዋሽንግተን ዛሬ ላይም ሩሲያ ቻይናና ከመሳሰሉ ተገዳዳሪዎቿ ጋር ጠብ ያለሽ በዳቦ ማለቷን አላቆመችም።
አሜሪካ እጇን ባስገባችባቸው ሀገራትና ባካሔደቻቸው ዘመቻዎች ሁሉ አገራቱ ሰላምና መረጋጋት ሲያገኙ አይታይም።
ምእራባዊያን ከጎልያዳዊ ታሪካቸው አሁንም ሲሻሻሉ አልተመለከትንም፤ የተለወጠ ነገር ቢኖር አዳዲስ ሃያላን ተቀናጅተው የአሜሪካ እና አውሮፓን እብሪት ወደ ፍፃሜው ማስጠጋታቸው ነው።

 #የዓባይልጅ Esleman Abay

iraq #iraq_invasion #USWarCrimes

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories