በስብዕና ጡብ ኢትዮጵያን እንገንባ

       የዓባይ፡ልጅ ✍️ እስሌማን ዓባይ

“ስህተቱ ከኮከቦቻችን ሳይሆን ከኛ ከራሳችን ናቸው” ይላል ሼክስፒር፤ የምንገኝበት ተጨባጭ አባባሉን እውነትነት ይበልጥ ያደርገዋል። ዙሪያችንን ከሞሉ ወሬዎች መጥላትን የሚገልፁ ቃላት አብላጫውን ተቆጣጥረዋል፤ ምክንያቱ አንድም እኩይ ነገሮች ከመብዛታቸው ወይም ደግሞ መጥላትን በሚያስወድድ ቡቃያ መሀል በመቆማችን ሊሆን ይችላል። ይሁንና መጥላት በተቆጣጠረው እሳቤያችን ውስጥም ሆነን የተወደደ ነገር ይመጣ ዘንድ መመኘታችን እንዳለ መሆኑን ስንታዘብ ..ምን ነካን…ያስብላል። ከዬት ሊመጣልን?

ማህበረሰባችን ሀገርን በተላበሰ ስብእና እስካልተገነባ ድረስ የምንፈራውም ሆነ የምንጠላው ነገር በየትኛውም ግንብ ሊከለልልን አይችልም። እንደ ሀገር ሁሌም የምንታመንለት የጋራ ጉዳይ ለምን አጣን? የትኛውም አስቸጋሪ አውድ የማይበግረው በአንድ ስሜት የሚያራምደን ጉዳይ እንዴት ጠፋብን? የዚህን ጥያቄ እንዲሁም ምላሽ ከጥንታዊት ቻይና እውነተኛ ታሪክ ውስጥ ተገንብቶ የሚገኝ ነው ብየ ላስብ..፤ ለመላው አለም በትልቅ አስተምህሮነቱ ሲወሳ በርካታ መቶ ዓመታት የተሻገረውን አንድ የቻይና ታሪክ ላውሳላችሁ።

የጥንቶቹ ቻይናውያን ወረሪን ለመመከትና ሰላማዊ ህይወት እንዲኖራቸው በማሰብ ታላቁን የቻይና ግንብ እውን ያደርጉ ዘንድ ምክንያት ሆኗቸዋል ይላል የታሪኩ ጅማሮ። ታላቁን የቻይና ግንብም በብዙ ሀብት ገነቡ። ከቁመቱ ከፍታ የተነሳ ምንም አይነት ጠላት ሊወጣው አይችልም በማለትም እምነት አሳደሩ..። 21,000 ኪ.ሜ. ርዝመት፣ 30 ጫማ ስፋትና 50 ጫማ ከፍታ …. ታላቁ የቻይና ግንብ በርግጥም የማይበገር ኃያል ነበር። ነገር ግን…
ግንቡ እውን በሆነ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ነበር እንደወትሮው ሁሉ በጠላት ይወረሩና ጥቃት ያስተናግዱ የጀመረው። ሶስት ጊዜም የጠላት ወረራ ሲከታተልባት ግንቡ አልታደጋትም…። ያንን ያክል ግዙፍ ግንብ አልፎ ጠላት መሻገር የቻለው እንዴት ይሆን? የጥንቷ ቻይና ትልቅ አገራዊና አሳሳቢ አጀንዳ ሆነ።

በያንዳንዱ ወረራ ግዙፉ የጠላት እግረኛ ሀይል ታላቁን ግንብ መደርመስም ሆነ መንጠላጠል አላስፈለገውም…፡፡ እንዲሁ ሰተት ብሎ ነበር በበሮቹ እያደረገ የሚገባው፡፡ እንዴት ለሚለው ነገሩ ቀላል ነበር..። ለግንቡ ጥበቃዎች ጉቦ ይሰጣሉ፡፤ ከዚያ ነገሩ ሁሉ ያበቃለታል። የሃያሉ ግንብ ሁሉም በሮች ለጠላት ተከፈቱ… እነዚያ ጠባቂዎች ሀገራቸውንና ብሄራዊ ስብእናቸውን በሰባራ ሳንቲም ይሸጡ ስለነበር…። የሀገራቸውን ክብር ጠላት በገንዘብ ሸተው… በተቆለፉ በሮች በኩልም በቀላሉ በመግባት ሀገሪቱን ለወረራ ዳረገ።
ቻይናውያን ጠላትን ለማስቆም ግንቡን እንጂ በግንቡ ወሳኝ በሮች ላይ የቆሙ ጠባቂ/ወታደሮችን ዘንግተዋቸው ነበር፤ የግንቡን ጠባቂ ቻይናዊያን ስብእና መገንባቱ ተረስቷል።
“የመልካም ሰው ጥሩ ቃል ደረጃው እንደ ማሰሪያው ነው” ይባላል።

በአሁኑ ጊዜ ጥቂት ሰዎች ብቻ የኃላፊነት ስሜት አላቸው። አብዛኛችን ጊዜና ትዕግስት የለንም። ሁላችንም ስኬትን በአቋራጭ እንከጅላለን። ብዙ ሀብት በመንጠቆ ወይም በዝርፊያ ለማግኘት መጣር።

ታላቁ ግንብ የሀገሪቱን ዘላቂ የብርታትና የመንፈስ ጥንካሬ ምልክትነቱ ጥርጥር ባይኖረውም ነገር ግን ቻይናውያን ኋላ ላይ የተማሩት ቢኖር ወራሪን ለመገደብ ከረጂሙ ግንብ በበለጠ ጠንካራ ስብእና የተላበሰ ማህበረሰብ ነው የሚለውን ነበር። በዚህም የሰውን ባህሪ መገንባት ላይ ማተኮር ።

አንድ የትውፊታዊ ታሪክ ምሁር፡- “የአንድን ሀገር ስልጣኔ ማፈራረስ ከፈልግክ መንገዶች ሶስት ናቸው” ይላል። እነሱም

  1. ቤተሰብን ማፍረስ
  2. የትምህርት ስርአቱን ማፍረስ
  3. መልካም ምሳሌና የአርኣያ ሰዎችን ስብእና ማጠልሸት
    ቤተሰብን ለማፍረስ እናት ሚናዋን እንዳትወጣ አድርጋት፡፡ “የቤት እመቤት” በመባሏ እንድታፍር አድርጋት፡፡
    የትምህርት ስርኣቱን ለማፍረስ አስተማሪው ላይ አነጣጥር፡፡ ህብረተሰቡ ጋር ያለውን ቦታ አሳጣው፡፡ ተማሪዎቹ ይንቁት ዘንድ ደረጃውን አውርደው፡፡
    አርአያዎችን ለማፍረስ ምሁራን/መምህራን ላይ አነጣጥር፡፡ እነሱን አንቋሻቸው፡፡ ዋጋ አሳጣቸው፡፡ ማንነታቸውን ሰዎች እንዲጠራጠሩ አድርግ፡፡ ያኔ ሰዎች አይሰሟቸውም፡፡ አርአያም አያደርጓቸውም፡፡ ታዲያ፣ አስተዋይ እናት ከጠፋች፤ ከልቡ የሚያስተምር መምህር ከጠፋ እና አርአያ ሰዎች ዋጋ ሲያጡ፤ ማነው ትውልዱን በመልካም ስነ-ምግባር የሚያንፀው?
    በዚህ ሁኔታ ውስጥ መጥላታችንም ሆነ መውደዳችን ትክክል ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
    ጉዳያችን ሀገር ሆኖ እያለ ስብእናችን ግን ከሀይማኖት፣ ከዘር፣ ከግል ጥቅም፣ ከገንዘብ እና “ትክክለኛ” የሆነውን ነገር ለመምረጥ ተፈላጊውን ስብእና አጥተናል። ጥፋተኛ አንድ ቡድን ወይም ግለሰብ አይደለም። እያንዳንዳችን ራሳችንን ብንፈትሽ ህሊናችን የሚነግረን አካል ላይ ነው የሚገኘው፤ እሱም በሁላችን ውስጥ የሚገኝ ነው። እያንዳንዱ ዜጋ ተገቢውን ስብእና ከተላበሰ ሀገር በፍጥነት መለወጧ አይቀርም። ለዚህ አንዱ ዘዴ የትምህርት ስርአት ነው ይባላል። የተሻሉ ዜጎችን ማፍራት የሚያስችሉ መልካም እሴቶች ለማስተማር ብዙ ሀገራት የ character education ትምህርትን የሚያካትቱት ለዚሁ ነው።

“Intelligence plus character – that is the goal of true education.” – Martin Luther King

ጠንካራና የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ለሀገራዊ ስብእና ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ማህበረሰብ ሊኖር ይገባል። ትምህርትም ክህሎትን ከማስጨበጥ ባለፈ ስብእናን ይቀርፅ ዘንድ ተገቢውን ፖሊሲ ይሻል።

በቀደምት የኢትዮጵያም ሆነ የሌሎች ስልጣኔ ወርቃማ ዘመናት ላይ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚሰራባቸው ውስጥ የዜጎች ስብእና እንደነበር ድርሳናት ያወሳሉ።

እናም ጣት ችግሩ የሁላችን ለሁላችን ከሁላችን መሆኑን መጀመሪያ አምነን ተቀብለን ወደመፍትሄው እናምራ።
“ስህተቱ ከኮከቦቻችን ሳይሆን ከኛ ከራሳችን ናቸው”

Esleman abay

charactereducation #BuildEthiopiaTogether

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories