በእሥራኤል ላይ ማዕቀብ መጣል “ቀይ መሥመራችን ነው” ናታንያሁ

Esleman Abay የዓባይ ልጅ

..በእስራኤል ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተባለለት፤ ዋሽንግተን በእስራኤል ላይ አደርገዋለሁ ያለችው የማዕቀብ ዕቅድ በአንድምታው ብዙ የሚያስብል ነው …

ዩናይትድ ስቴትስ በእስራኤል ላይ ማዕቀብ ለመጣል እንቅስቃሴ ስለመጀመሯ ያስታወቀችበት ያልተለመደ አቋሟ የአለም አቀፍ ብዙሐን መገናኛዎችን ትኩረት የሳበ ሆኗል።

የፕሬዝደንት ባይደን መግለጫን ዋቢ በማድረግ ጋርዲያን ጋዜጣ ባስነበበው ፅሁፉ “የእስራኤል ሰፋሪ ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች የሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ ኢ-“ሰብአዊ ድርጊቶች፣ የጭካኔ ግድያዎችንና ከቀያቸው የማፈናቀል ድርጊታቸው እስራኤል ላይ ማዕቀብ ለመጣል መንስኤ ናቸው።”
በተለይም በእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ስራ የሚንቀሳቀሰው እና ‘አክራሪ’ መሆኑ የተገለፀው “ኔትዛ የሁዳ” የሚባለው እዝ የጭፍጨፋ ድርጊት መፈፀሙ ነው በዋነኛነት የተጠቀሰው። ምንም እንኳን መሰል ማዕቀቦች በተገቢው መንገድ ከተተገበሩ የኔትዛ የሁዳ ብርጌድ በፍልስጤማውያኑ ላይ ለሚደርሰው ሰቆቃ ልጓም ያበጅለታል ቢባልም፤ የዋሽንግተን አስተዳደር ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ግምባር ቀደም አጋሬ በሚላት እስራኤል ላይ ይህን ለመጀመሪያ ጊዜ ተፈፃሚ የሚሆን የተባለውን ማዕቀብ ትተገብረዋል ብለው ለማመን የተቸገሩ የጉዳዩ ታዛቢዎች የበረከቱ ሆነዋል።

ከአሜሪካ የተገለፀውን የማዕቀብ ዕቅድ በተመለከተ የእስራኤል ባለስልጣናት ለዋሽንግተን ማስጠንቀቂያ መሰል የቁጣ ምላሾች መስጠታቸው የተዘገበ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤንጃሚን ኔታንያሁ በሰጡት ምላሽ “የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት አካል በሆነ ኃይል ላይ ማዕቀብ ለመጣል የሚደረግን ማንኛውም ጥረት ባለኝ ነገር ሁሉ እፋለመዋለሁ” ብቡዋል።

“በፍልስጤማዊያን ላይ ከባድ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል በመፈፀም በተከሰሰው የእስራኤል ጦር ኔትዛ የሁዳ ሻለቃ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ከነጩ ቤተ መንግስት ሹማምንት ማረጋገጡን ኤክሲዮስ የዜና አውታር በዕለተ ቅዳሜ ዘገባው ይፋ ደረገ ሲሆን ሃሬትዝ የተሰኘው የእስራኤል ጋዜጣም በተከታዩ ዕለት ዩናይትድ ስቴትስ በዚሁ ሻለቃ እንዲሁም በሌሎች የእስራኤል የፖሊስ እና ወታደራዊ ክፍሎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እያሰበች ነው ብሏል።

ይሁን እንጅ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የእስራኤል ጦር አካል የሆነን አንድ ክፍል ኢላማው ያደረገ ማዕቀብ ለመጣል የመጀመሪያ የሆነውን እርምጃ ልወስድ ነው የሚለው መግለጫ ጋር የሀገሪቱ ኮንግረስ ጦርነት እያደረገ ለሚገኘው የእስራኤል መንግስት አዲስ የ 26 ቢሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ ለመስጠት በድምፀ ውሳኔ የማሳለፉም መረጃ መሰማቱ ነገሩን ግራ አጋቢ አድርጎታል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ደረጃ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሰሞንኛ አቋም ቀደም ሲል ከሚያስተጋባውና ለቤንጃሚን ኔታንያሁ ገደብ የለሽ ድጋፍ እንሰጣለን፤ ለእስራኤል በሚደረግ ድጋፍ ረገድም ዋሽንግተን ቁጥር አንድ ናት ከሚለው መግለጫቸው አንፃር “ዛሬ ምን ተገኘ?” በሚል ለሚሰነዘሩ መጠይቆች የተለያዩ ትንተናዎች ይሰነዘራሉ። በተለይም የማዕቀቡ መግለጫ ከተደመጠበት ጊዜ አንፃር ከመጋረጃው ጀርባ ያለው እውነተኛ ሰበብ ብዝም የተደበቀ አይደለም እየተባለ ሲሆን፤ ፕሬዝደንት ባይደን የማዕቀቡን እንቅስቃሴ የፈረሙት በሚቺጋን ከሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ሰልፍ ጋር የጊዜ መገጣጠም የታየበት ነው ይባላል።

ሚቺጋን በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛው አረብ-አሜሪካዊ ህዝብ የሚኖርበት ሲሆን፣ በፕሬዝደንታዊ ቅስቀሳው ተፎካካሪ የሆኑት ትራምፕ አሁን ላይ የግንባር ቀደምነቱን ስፍራ እየያዙ መሆናቸው ነው በስፋት የሚገለፀው።
በዚሁ ግዛት ባይደን ከአራት አመት በፊት ትራምፕን ሶስት በመቶ በሆነ ጠባብ ልዩነት ማሸነፋቸውን የሚያወሱት ዘገባዎቹ፤ ከኦክቶበር 7 ወዲህ ግን ባይደን ከዚሁ ከሚቺጋን የአረብ-አሜሪካዊ ማህበረሰብ በኩል የከፋ ትችት እና ውግዘት እያስተናገዱ ነው የሚገኙት። በቅርብ ጊዜያት በተደረጉ የፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዘመቻዎች ላይ በውል የተገለፀ እውነት ቢኖር ባለፉት 26 ዓመታት ውስጥ አብዛኛው አረብ-አሜሪካዊ የዲሞክራቲክ ፓርቲን ያለመምረጥ አዝማሚያ ማሳየቱ ነው እየተባለ ይገኛል።

በእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት ውስጥ ፕሬዝደንት ባይደን ከሰሞኑ ያስደመጡት የማዕቀብ መግለጫ ሞራላዊ ዋልታ ረገጥነት ያጠላበት ነው የሚሉት የመበራከታቸውን ያህል፤ የአባባሉን ተገቢነት ለመረዳትም የቅርብ ጊዜ ተከታታይ ክስተቶች በርግጥም ጥቆማ የሚሰጡ ናቸው።
እ.ኤ.አ ጥር 26፣ አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እስራኤል የደቡብ አፍሪካ መንግስት በቀረበው የዘር ማጥፋት ድርጊት ክስን አሜሪካ በይፋ ስትቃወምና ስትከላከል መታየቷ አይዘነጋም። ሌላው በወርሃ ታኅሳሥ፣ የአሜሪካው ቴሌቪዥን ሲ.ኤን.ኤን ባቀረበው ዘገባው “የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲ.አይ.ኤ እስራኤል በጋዛ የምትጠቀማቸው የጦር መሣሪያዎች በሲቪል ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ያውቅ ነበር” የሚለው ነው። በዚህ ነጥብ ላይ በዴይሊ ስታር ትንተና ያቀረቡት ራሚሳ ሮብ “የደቡብ አፍሪካ ጠበቆችም የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈፀሙን ለማረጋገጥ የተጠቀሱት መሳሪያዎችን አንድ ባንድ እንደማስረጃ ሲጠቁሙ ተደምጠው ነበር። ይሁንና ይህን ወንጀል የተከላከለው የጆ ባይደን  አስተዳደር የወንጀሉ ተባባሪ የመሆናቸው ማሳያ ነው፤ አለም በአሳዛኝነቱ እና በአሳፋሪነቱ በይፋ ከታዘበው በኋላ ጭምር ፕሬዝደንት ባይደን ለእስራኤል ጦር ተጨማሪ ጭፍን ድጋፍ ማድረጉን ቀጠለ።”  ብለዋል።
  በተጨማሪም እስራኤል በተመድ ለፍልስጤም ርዳታ ለማቅረብ በተቋቋመው ድርጅት የሚሰሩ 12 ሰዎችን  ከጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት ጋር ግንኙነት አላቸው የሚል ውንጀላ ባቀረበበት እና ለተቋሙ ዋነኛ በጀት አቅራቢ የሆነችው አሜሪካም ለዚሁ ተቋም የምትሰጠውን ድጋፍ ማቋረጧን ስታሳውቅ በአጋጣሚ ይህ ውሳኔ በተላለፈበት ወቅት የረድኤት ድርጅቱ የገንዘብ እገዳ ውሳኔው በጋዛ የተከሰተው ረሃብ ከሞት አፋፍ ያደረሳቸውን 800,000 የሚደርሱ ነዋሪዎች ለህልፈት ያጋልጣል በማለት አሳስቦ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ባይደን ያስተላለፉት የእገዳ ውሳኔ እውቅ ከሆኑ ዲሞክራቶች ለአብነትም እንደ በርኒ ሳንደርደር እና የአሌክሳንድሪያው ሴናተር ኦካሲዮ-ኮርትዝ ሳይቀር የተቃወሙት ነበር።

ይህን በመሰለው የባይደን እና የናታንያሁ ቅንጅት ውስጥ ዋሽንግተን እስራኤል ላይ ማዕቀብ የምትጥል ከሆነ ስራ ላይ ይውላል የተባለው የሊሂ ህግ እንደሚሆን ተጠቁሟል። እ.ኤ.አ. በ 1997 የፀደቀው “ሊሂ” የተሰኘው ህግ ገቢራዊ የሚሆነው አሜሪካ ለውጭ አገራት ከምትሰጠው ወታደራዊ ድጋፍ ውስጥ በወንጀል የተከሰሰውን የተለየ ክፍል እንዲሁም በዚህ ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ መሪዎችን ብሎም ለቡድኑ የገንዘብም ሆነ ማንኛውም ድጋፍ የሚያደርግ የየትኛውም ሀገር መንግስት ወይም ግለሰብና ተቋማት ላይ እቀባ ለመጣል የሚያገለግል ነው።
   የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ባለፈው አርብ በሰጡት መግለጫ “እስራኤል የ “ሊሂ” ህግን ተላልፋለች” ማለታቸውን ተከትሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሀገራቸው “ለእርምጃው ቁርጠኝነቱ አላት” ያሉ ሲሆን፤ ማዕቀቡ “ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በፈጽሙ የፖሊስ ወይም የደህንነት ክፍሎች ላይ ወታደራዊ እርዳታ መስጠትን ይከለክላል።” ሲሉ ተደምጠዋል።

በእስራኤል ጦር ውስጥ የ”ክፊር ብርጌድ” አካል እንደሆነ የተገለፀው “ኔትዛህ ይሁዳ” ሻለቃ በ1999 የተቋቋመ መሆኑን የሚያወሳው ጋርዲያን ጋዜጣ በእስራኤል ጽንፈኛ ከሚባሉ አካባቢዎች የመጡትን ጨምሮ ከአክራሪ ሃይማኖተኞች እና ከሀገሪቱ ሃይማኖታዊ ማህበረሰቦች በተውጣጡ ምልምሎች የተዋቀረ መሆኑን ይገልፃል።
Esleman, [Apr 23, 2024 at 11:59 PM]
በፕሬዝደንት ባይደን የእስራኤል ማዕቀብ መግለጫ ላይ ከአለም ዙሪያ ከተሰጡ አሉታዊ አስተያየቶች መካከል አብላጫዎቹ እንዳስቀመጡት፤ አሜሪካ የእስራኤልን ኢ ሰብአዊ ድርጊት ለማስቆም እውነተኛ ፍላጎቱ ካላት የማዕቀቡ ከለላ በአጠቃላይ በእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ላይ በምታደርገው ድጋፍ ላይ ማዕቀብ ብትጥል የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ በመጥቀስ፤ በተቃራኒው ተጨማሪ 26 ቢሊዮን ዶላር ለማቅረብ ከጫፍ መድረሷን ይተቻሉ። በሌላ በኩል አለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም የአሜሪካ መንግስት እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ ስታደርስ ከሚገኘው ጥቃት እንድትከለክል የሚጠይቁ ሰብአዊ ተማጋች ድርጅቶች እንደሚገልፁት አሜሪካ በአጋሮ በእስራኤል ላይ የምትጥለው ማዕቀብ እንደ ኢራቅ  በመሳሰሉ ሀገራት ላይ የጣለቻቸውን አይነት ይሆናል ብለው እንደማይጠብቁ ነው የሚናገሩት።

ናዳ ኤሊያ በዌስተርን ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የዘር እና የባህል ጥናቶች ምሁር የሆኑት ናዳ ኤሊያ በሰጡት አስተያየት፣ “አሜሪካ በእስራኤል ላይ ያቀደችውን ማዕቀብ ብትተገብረው እስራኤል በአሜሪካ ዓመታዊ የ 3.8 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ የተገዛውን መሳሪያ እንዴት እንደምትጠቀምበት  ተጠያቂነትን የማምጣት ፋይዳ ይኖረዋል።” ይላሉ። ምሁሯ አክለውም “አሜሪካ ለእስራኤል ከምትሰጠው ከዚህ አመታዊ ርዳታ ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነው በተለዬ ለጦር መሣሪያ ግዢ የተመደበ ከመሆኑ አንፃር ከእስራኤል ጦር በአንዱ ክፍል ላይ የሚደረግ ማዕቀብ ለትልቁ የአሜሪካ ሃላፊነት አንዱ እርምጃ ሊሆን የሚችል ነው።” ባይ ናቸው።

በተመሳሳይ ነጥብ ላይ አስተያየት የሰጡት ካሊድ ኤልጊንዲ በመካከለኛው ምስራቅ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ባልደረባ ሲሆኑ፣ በተቋሙ ውስጥ የፍልስጤም እና እስራኤል ጉዳዮችን የሚመሩ ናቸው። ካሊድ እንደሚሉት ” አሜሪካ በእስራኤል ላይ ስለምትጥላቸው ማዕቀቦች ስንናገር፣ ራሷ እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ ለበርካታ አስርት አመታት ያነበረቻቸውን ኢ ሰብአዊ ወንጀሎች እንድታቆም ከተደረገች ከአሜሪካ አጋርነቷ አንፃር ህገ ወጥ ክልከላዎችን መከልከል በራሱ እንደ ማዕቀብ የሚቆጠር ነው” ሲሉ ነው የሚያስረዱት።

“ዩናይትድ ስቴትስ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ያላትን ድምጽን በድምፅ የመሻር ስልጣኗን የእስራኤልን ወታደሮች ወንጀል ለመከላከል ትጠቀምበታለች” የሚሉት ደግሞ ካሊድ ኤልጊንዲ በመካከለኛው ምስራቅ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ባልደረባ እና፣ በተቋሙ የእስራኤል-ፍልስጤም ጉዳዮች መሪ የሆኑት ካሊድ ኤልጊንዲ፣ “ዋሽንግተን በተመድ ጉባኤዎች ላይ ስልጣኗል ለእስራኤል ወንጀል ጥብቅና በመቆም ከመጠቀም ከተቆጠበችም ማዕቀብ እንደጣለች ይቆጠራል፤ ለቀጣይ መልካም ርምጃዎችም መደላድል ይፈጥራል” በማለት አሜሪካ ከትንሹ ወደ ዋናው ሃላፊነቷ እንድትሸጋገር በተስፋ የሚናገሩት።

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories