በፖሊስ ለወንጀል ማጣራት ተፈልጎ በቁጥጥር ሥር መዋል detention መያዝ arrest እና መታሠር imprisonment

Isl

HS Hailu, የህግ ባለሙያ

-ምንም እንኳን ሦስቱም የነጻነት፣ የአካል ደኅንነት እና የመንቀሳቀስ መብቶችን የሚገድቡ በመሆናቸው ተመሳሳይነት ቢኖራቸውም በዓላማቸው፣ በይዘታቸው እና በአፈጻጸም ሥነ-ሥርዓታቸው ጭምር የተለያዩ ናቸው።

-በሀገራችን ግን እነዚህን የሕግ ፅንሰ ሀሳቦች ከስያሜአቸው ጀምሮ ልዩነታቸውን ሳይጠነቅቁ የፖሊስ-ግለሰቦች ነጻነት-ነክ መስተጋብሮችን በመሉ እንደ እሥራት የሚጠባይበት ሁኔታ ስላለ ሊታረም ይገባዋል እያልን (መንደርደሪያ መሆኑ ነው?) እንጀምር፡:

  1. በፖሊስ ለወንጀል ማጣሪያ ጥያቄ ተፈልጎ በቁጥጥር ሥር መዋል (detention): ማለት ፖሊስ አንድን ሰው ወንጀል ፈጽሟል፣ በመፈጸም ላይ ነው ወይም ሊፈጽም ይችላል በሚል ምክንያታዊ ጥርጣሬ (reasonable/particularized suspicion) ለአጭር ጊዜ አስፈላጊ ከሆነ ተመጣጣኝ ኃይልን ተጠቅሞ የመንቀሳቀስ ነጻነቱን ገድቦ በተወሰነ ስፍራ በቁጥጥሩ ሥር በማቆየት ሰውዮው ማንነቱን እንዲገልጽና ቀጥሎም ለተጠረጠረባቸው ወንጀል-ነክ ጥያቄዎች “ከፈቀደ” ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠይቅበት ሥነ-ሥርዓት ነው።
    በመሆኑም በዚህ ጥርጣሬ አንድን ሰው በቁጥጥር ሥር ለማዋል የፍ/ቤት ትእዛዝ አያስፈልግም፣ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላም ፖሊስ ወደ ፍ/ቤት አያቀርበውም:: በወንጀል መዝገብም ላይ ስሙ አይመዘገብም:: ይሁንና ፎቶ ግራፍ እና የጣት አሻራም ሊነሣ ይችላል። ይህም የሚሳየው መርማሪ ፖሊስ አንድን ሰው ወንጀል ፈጽሟል ብሎ ሳያምንበት ነገር ግን በምክንያታዊ ጥርጣሬ ብቻ በቁጥጥር ሥር ሊያውልና ጥያቄዎችን ሊጠይቅ እንደሚችል ነው። ሰውየውን ለጥያቄ መፈለጉ ወደ መያዝ ደረጃ እስካላደገ ድረስ ሰውየው ዋስ አምጣ ወይም የዋስትና ሰነድ ላይ ፈርም ሳይባል እንዲሁ ይለቀቃል። እንግዲህ ሰውየው ለምን ያህል ጊዜ በዚህ ሁኔታ በቁጥጥር እንደሚቆይ በወንጀል ሥነ ሕግና በሀገራት አሠራር ግልጽ የጊዜ ገደብ ባይኖርም ሁሉንም የሚያስማማው ግን ሰውየው ካልተያዘ በቀር በምክንያታዊ የጊዜ ገደብ ውስጥ ሊለቀቅ ይገባዋል የሚለው ነው።
  • ፖሊስ ይህን የማጣራት ሥራ ሲሠራ በቁጥጥሩ ሥር ያለው ሰው የጦር መሣሪያ ወይም ሌላ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ዕቃ (ቢላ..) በአካሉ ይዟል ወይም በአጠገቡ አስቀምጧል ብሎ በምክንያት በጠረጠረ ጊዜ ሁሉ በሰውየው ሰውነት፣ ቦርሳ ወይም ተሽከርካሪ ላይ ቀለል ያለ ፍተሻ (“frisk/pat search”) ሊያደርግ ይችላል። የዚህ ፍተሻ ዓላማም ፖሊስ ራሱን ወይም በአቅራቢያው ያለውን ሰው ከጥቃት ለመከላከል ነው። በዚህ ፍተሻ ፖሊስ ሰውየው ከጦር መሣሪያ ወይም ጉዳት ሊያደርስ ከሚችል ዕቃ በተጨማሪ የኮንትራባንድ ዕቃ ይዞ ቢያገኘው ለዚህ ወንጀል ሰውየውን ሊይዘው፣ ደንበኛ ፍተሻም ያለ ፍ/ቤት ትእዛዝ ሊያደርግበት ይችላል።
  1. መያዝ (Arrest)፡- ፖሊስ አንድን ሰው ተለይቶ የታወቀን ወንጀል (specific crime) ፈጽሟል በሚል #ምክንያታዊ_እምነት (reasonable/objective belief) በዋናነት በፍ/ቤት ትእዛዝ ወይም በልዩ ሁኔታ ደግሞ ያለ ፍ/ቤት ትእዛዝ ነጻነቱን ገድቦ ወደ ፖሊስ ጣቢያ/ማረፊያ ቤት በመውሰድ የሰውየውን ስም በወንጀል መዝገብ ላይ በመመዝገብ፡ ለተያዘው ሰው የምን ወንጀል እንደፈጸመ ታምኖ እንደተያዘ በመንገር እና ያሉትን መብቶች (ያለ መናገር መብት እንዳለው፣ ራሱን ያለመወንጀል መብት እንዳለው፣ ያለበትን ሁኔታና ቦታ ለቤተሰብ…ማሳወቅ እንደሚችል፣ የጤና ጉዳይ ካለው በሐኪም ሊታይ እንደሚችል፣ የሕግ ጠበቃ በራሱ ምርጫ ወይም ዐቅም ከሌለውና ሕጋዊ መሥፈርትን ካሟላ በመንግሥት እንደሚመደብለት፣ ወደ ፍ/ቤት እንደሚቀርብ፣ ቋንቋውን ካልቻለ አስተርጓሚ እንደሚመደብለት…) የሚያስረዳ ሠነድ በመስጠትና በማስረዳት ከሰውየው የተከሳሽነት ቃል የሚቀበልበት ሥነ-ሥርዓት ነው።

የተያዘው ሰው ዝም የማለት መብት ቢኖረውም ሙሉ ስሙን፣ አድራሻውን፣ የተወለደበትን ጊዜ ሳይዋሽ ለመርማሪ ፖሊስ የመግለጽ ግዴታ አለበት። ሰውየው ማንነቱን አልገልጽም ቢል ወይም ሐሰተኛ ማስረጃ ቢሰጥ በወንጀል ይጠየቅበታል። (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 811)- [The right to remain silent is not a right to remain anonymous.]

በዚህ ሁኔታ በፍ/ቤት ትእዛዝም ሆነ ያለ ፍ/ቤት ትእዛዝ የተያዘ ሰው በወንጀል መዝገብ ላይ ስሙ ይመዘገባል፣ የጣት አሻራም ይነሣል:: የያዘው የፖሊስ መ/ቤትም ሰውየውን ከተያዘ በተወሰኑ ሰዓታት ውስጥ (በኛ ሀገር በ48 ሰዓታት ውስጥ) ወደ ፍ/ቤት በማቅረብ በምን ወንጀል ጠርጥሮ እንደያዘው ዳኛውን በሚያሳምን መልኩ ሊያስረዳ ይገባዋል::

እንግዲህ መርማሪ ፖሊስ አንድን ሰው ሲይዝ ሰውየው ወንጀሉን ስለመፈጸሙ እና ጥፋተኛም እንደሆነ አምኗል ማለት ነው። ይሁንና የተያዘው ሰው በፍ/ቤት በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ እንደሆነ (ንጹሕ እንዳልሆነ) ከሳሽ እስካላስረዳበት ድረስ ንጹሕ ሆኖ የመገመት መብት ስላለው ንጽሕናውን የማስረዳት ግዴታ የለበትም። ከዚህ ጋር በተያያዘም የመርማሪ ፖሊስ የመያዣ መለኪያ እና የዐ/ሕግ የክስ ማቅረቢያ መለኪያ በሕግ ደረጃ ተመሳሳይ ስላልሆኑ ፖሊስ ወንጀል ፈጽሟል በሚል እምነት በያዘው ሰው ላይ ዐ/ሕግ ክስ ላያቀርብ ይችላል ::

የተያዘ ሰው በዋስ፣ በፍ/ቤት ነጻ የማሰናበት ብይን ወይም ተከላክሎ በፍርድ ትእዛዝ፣ የተያዘበት ሁኔታ ሕገ ወጥ ከሆነም የአካል ነጻነትን በማስከበር የፍ/ብሔር ውሳኔ ወዘተ. ሊለቀቅ ይችላል።

  1. እሥራት (Imprisonment)፡- በወንጀል የተከሰሰን ሰው ፍ/ቤት ማስረጃን በመስማት በተከሰሰት ወንጀል ጥፋተኛ (ወንጀለኛ) ነው ብሎ በመፍረድ ለጥፋቱ ቅጣትም ለተወሰነ ጊዜ ነጻነቱን የሚገድብ ቅጣት ጥሎ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ በመወሰኑ ምክንያት የሚፈጸም ተግባር ነው። (በዚህ አግባብ) የታሠረ ሰው ንጹሕ ሆኖ የመገመት መብት የለውም:: በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ የታሠረ ሰው የእሥራቱን 1/3ኛ ከመፈጸመ በኋላ በይቅርታ (አቤቱታ ለፍትሕ ሚ/ር (ለክልል ፍትሕ ቢሮ) በማቅረብ..)፣ የእሥራቱን 2/3ኛ ከፈጸመ በኋላ ደግሞ በአመክሮ (አቤቱታ ለፈረደበት ፍ/ቤት በማቅረብ)፣ የእሥራት ጊዜውን በማጠናቀቅ ወዘተ. ከእሥራቱ በሕግ በተቀመጠው አግባብ ከእሥራቱ ሊለቀቅ ይችላል።

By, HS Hailu

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories