ሰምና ወርቅ
(የምርምር መጽሔት)
Menu
የብላታ መርስዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስ አጭር የሕይወት ታሪክ

አምኃ መርስዔ ኀዘን
ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ መጋቢት 17 ቀን 1891 ዓ.ም. ሸዋ ጅሩ ውስጥ እምቧጮ መግደላዊት በተባለ ስፍራ ተወለዱ። አባታቸው አለቃ ወልደ ቂርቆስ አልታመን ይባላሉ። እሳቸውም በደብረ ሊባኖስና በእንጦጦ ማርያም የቤተልሔምን መዝገበ ድጓ ሲያስተምሩ የነበሩና በዜማ መምህርነት የታወቁ ናቸው። እናታቸው ወይዘሮ የሸዋ ወርቅ ምናጣ ይባላሉ። የአባታቸው አጎት አለቃ ገብረ ክርስቶስ የብሉይና የሐዲስ ሊቅና የቅኔ መምህር የነበሩ (በንጉሥ ኃይለ መለኮት፣ በአጼ ዮሐንስና በአጼ ምኒልክ ቤተ መንግሥት እጅግ የተከበሩ) ሰው ነበሩ።
መርስዔ ኀዘን በአራት ዓመት ዕድሜያቸው እምቧጮ ላይ ከንባብ አስተማሪው ከደብተራ እንደ ብልሃቱ ፊደል መቊጠር ጀመሩ። በ1896 ዓ.ም. ወደ እንጦጦ መጥተው ከአባታቸው ዘንድ ንባብ ተማሩና በሰባት ዓመታቸው ዳዊት ደገሙ። ቀጥሎም የዜማ ትምህርት ጀምረው ጾመ ድጓና ድጓን ተማሩ። በ1901 ዓ. ም. በጥር ወር ለቅኔ ትምህርት ወደ ጅሩ ሄደው ጅሑር ላይ ሲያስተምሩ ከነበሩት ከአለቃ ወልደ ማርያም ቅኔ መቊጠር ጀመሩ። ከሦስት ወር በኋላም ወደ ደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ ተላልፈው ከአለቃ ወልደ አብ ቅኔ ተማሩ። በ1902 ዓ. ም. በጥር ወር ወደ እንጦጦ ተመልሰው ከታላቁ የቅኔ መምህር ከአለቃ ዐወቀ ተማሩና ቅኔ ተቀኙ። በ1904 ዓ. ም. ወደ አዲስ አበባ ወርደው ከግራ ጌታ ገብረ መድኅን የቅኔ አገባብ ተማሩ።
ከዚያም በኋላ የሥራ መያዝ ፍላጎት ስላደረባቸው በ1906 ዓ. ም. በወምበሩ ቀኛዝማች ናቄ ዘንድ የጸሐፊነት ሥራ ያዙ። አንድ ዓመት ከአራት ወር በጸሐፊነት ከአገለገሉ በኋላ በአባታቸው ወዳጅ በአቶ ሕለተ ወርቅ እሸቴ (በኋላ ከንቲባ የተባሉት) ምክር የጸሐፊነቱን ሥራ ትተው በ1907 ዓ. ም. በነሐሴ ወር ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመለሱ። ከዚህ በኋላ የመጻሕፍተ ሐዲሳትን ትርጓሜ ከራጉኤሉ ከመምህር ወልደ ጊዮርጊስ ተማሩ። በ1910 ዓ. ም. ወደ ሐረር ወርደው በአደሬ ጢቆ ሥላሴ ከአለቃ ገብረ ክርስቶስ ወልደ ዮሐንስ የዮሐንስ አፈ ወርቅን ትርጓሜ ተማሩ። በለጣቂውም ዓመት ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ከቀድሞ አስተማሪያቸው ከመምህር ወልደ ጊዮርጊስ ሐዲሳቱን በመከለስ ትምህርታቸውን ቀጠሉ።
በ1912 ዓ. ም. ስለ ጽሕፈት ሥራ በደመወዝ ተቀጥረው በስመ ጥሩው ሊቅ በአለቃ ገብረ መድኅን ውስጥ የመንግሥት ሥራ ጀመሩ። ሥራውም የአረጋዊ መንፈሳዊን ትርጓሜ ልዩ ሙያ ካላቸው ሊቅ ከመምህር ደስታ ተምረው የትርጓሜውን ረቂቅ ማውጣትና፤ በባለሙያው ሊቅ አረጋግጠው ንባቡን ከነትርጒሙ ለኅትመት ማዘጋጀት ነበር። ይህ ‘አረጋዊ መንፈሳዊ’ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን በ1920 ዓ.ም. ድሬዳዋ ላይ ያሳተሙት ነው። መርስዔ ኀዘን ከዚህም በቀር ሌሎችን የትርጓሜ ሥራዎች አዘጋጅተው አቅርበዋል። በተለይም ከአለቃ ኃይለ ሥላሴ ጋር ሆነው የሠሩት የሲራክና የደቂቀ ነቢያት ትርጓሜ እዚህ ላይ ይጠቀሳል። ፊተኛው በልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ ፈቃድ በ1917 ዓ.ም. ከመጽሐፈ ሰሎሞን ጋር የታተመው ሲሆን ኋለኛው ግን የመታተም ዕድል አልደረሰውም።
በዚህ ዓይነት ሥራ ሳሉ የውጭ አገር ቋንቋን ለመማር ስለተመኙ በ1913 ዓ. ም. ከዳግማዊ ምኒልክ ተማሪ ቤት ገብተው ከነሙሴ በዳዊ እንግሊዝኛ መማር ጀመሩ። ከሦስት ወር በኋላም የትርጓሜ ሥራቸውን ብቻ እንዲከታተሉ የሚያደርግ አንድ ምክንያት ስላጋጠማቸው የቋንቋ ትምህርታቸውን አቋረጡ። ምከንያቱን መርስዔ ኀዘን “ትዝታዬ ስለራሴ የማስታውሰው” በሚል ርዕስ በ2005 ዓ. ም. ላይ ታትሞ በወጣው የግለ ታሪክ መጽሐፋቸው ላይ በሚከተለው ገልጸውታል።
“የቋንቋ ትምህርት መጀመሬንም እንዳይሰሙብኝ ለማድረግ ተጣጣርሁ። ዳሩ ግን ተደብቆ የሚቀር ነገር ስለሌለ ወሬውን ሰምተው ጠሩኝና እያዘኑ ክፉኛ ገሠጹኝ። ዳግመኛ ወደዚያ ስፍራ እንዳትመለስ ብለውም አስጠነቀቁኝ። እንግዲህ የተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት እስከ ተከፈተ ድረስ የቋንቋ ትምህርቴን አቋርጬ ተቀመጥሁ። ጌታ አለቃ ገብረ መድኅን ይህን ማድረጋቸው በእርሳቸው አስተያየት እኔን ለመጥቀም እንጂ ለክፋት እንዳላደረጉት ሕሊናዬ ስላወቀ አላዘንሁባቸውም።”
ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን ብርሃንና ሰላም ብለው የሰየሙት አንድ አዲስ ጋዜጣ ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም. በማተሚያ ቤቱ ዲሬክተር በአቶ ገብረ ክርስቶስ ተክለ ሃይማኖት መሪነት ሲመሠረት መርስዔ ኀዘን ወደ ጋዜጠኛነት ተዛውረው በዋና ጸሐፊነት ይሠሩ ጀመር። ከአራት ወር በኋላም ሚያዝያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም. የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርቆ ሲከፈት የግዕዝና የአማርኛ አስተማሪ ሆነው ወደ ትምህርት ቤቱ ተዛወሩ። በዚህ ጊዜ ያሰናዱት “ትምሕርተ ሕፃናት” የተባለች መጽሐፍ ግንቦት 1 ቀን 1917 ዓ. ም. ታትማ ወጣችና የግብረ ገብ ትምህርት ማስተማሪያ ሆነች። እሳቸውም በዚህ ጊዜ እንግሊዝኛ ለመማር በትጋት ይጣጣሩ ጀመር።
ከአንድ ዓመት በኋላ ጽፈው ያቀረቡዋት “በአዲስ ሥርዓት የተሰናዳ የአማርኛ ሰዋስው” በማጥኛ ደብተር እየተገለበጠ ወዲያው የተማሪዎች መማሪያ ሆኖ በአገልግሎት ላይ ዋለ። ይህ ሰዋስው ከጠላት ወረራ በኋላ በ1935 ዓ.ም. ታትሞ የወጣው ነው። ለግማሽ ምዕት ዓመታት ያህል ለኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች መደበኛ የሰዋስው ማስተማሪያ ሆኖ አገልግሏል። እንዲሁ ደግሞ የትምህርት ቤቱ ሹም ሐኪም ወርቅነህ በአማርኛ አስተርጕመውት የነበረውን “የዓለም ጅዖግራፊ” እንደገና ሲያርሙትና ለኅትመት ሲያዘጋጁት ሳሉ መርስዔ ኀዘን የሥራ አለቃቸውንና ልባዊ ወዳጃቸውን ለመርዳት በቅንነት አገለገሉ። ይህ ጅዖግራፊ በ1920 ዓ.ም. ታትሞ የወጣው ነው። የመጽሐፉ ባለቤት ሐኪም ወርቅነህም በመጽሐፋቸው መቅድም ላይ በጻፉት ቃል፤
“ይህንም ለማረም ምሁር የሆነ ወዳጄ አቶ መርስዔ ኀዘን በትዕግሥትና በልበ ፈቃድ ከእኔ ጋር በማረም ረዳኝ፤ ቀጥሎ መጽሐፉ ሲታተም ግድፈቱን እያረመ አሳተመልኝ፤ ይህን የመሰለ እርዳታ ባላገኝ ኖሮ ይህ የጅዖግራፊ ትርጒም ወደ ፍጻሜ ባልደረሰም ነበር”
ሲሉ ምስጋና ሰጥተዋቸዋል። አቶ መርስዔ ኀዘን በ1922 ዓ.ም. ወደ ጅጅጋ ከተማ ተዛውረው ከዚያ ለቆመው ለልዑል ራስ መኰንን ትምህርት ቤት ዋና ሹም በመሆን አምስት ዓመት አገልግለዋል። በዚሁም ጊዜ በተጨማሪ ከተሰጣቸው ሥራዎች ውስጥ በወሰን ክልል ሥራ ላይ ከወሰን ተከላካዮች ጋር የተፈጸመ አገልግሎት ይገኝበታል። በ1924 ዓ.ም. በታኅሣሥ ወር የተጀመረው የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ሱማሌላንድ የወሰን ክልል ኮሚሽን ሥራውን እስካበቃበት እስከ 1927 ዓ.ም. የካቲት ድረስ በዋና ጸሐፊነት ሦስት ዓመት ከሁለት ወር አገልግለዋል። የክልሉ ሥራ ከደርኬንጌኞ አንስቶ እስከ ጃሌሎ ድረስ የተዘረጋው ርዝመቱ ከሰባት ኪሎ ሜትር በላይ በሆነው የወሰን መስመር ላይ ሲሆን ሐበር አወልንና ገደቡርሲን ኢሳን በመርገጥ የተሠራ ነበር።
በመጨረሻም ኢጣልያኖች በውጋዴን ውስጥ ወልወል ላይ ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም. ረቡዕ አደጋ በጣሉ ጊዜ አቶ መርስዔ ኀዘን በስፍራው ላይ ተገኝተው ከወሰን ተከላካዮቹ ጋር ሆነው አደጋውን ተከላክለዋል። በ1927 ዓ.ም. ሰኔ 10 ቀን የትልቁ ወህኒ ቤት ዲሬክተር ሆነው ተሾሙ። ከአንድ ዓመት በኋላ በተከተለውም በጠላት ወረራ ዘመን በጅሩና በዓድአ በሌላም ስፍራ እየተዘዋወሩ ሕይወታቸውን አትርፈዋል።
ከጠላት ወረራ በኋላ የመንግሥት ሥራ አገልግሎት፤
የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ 1933 – 36 ዓ.ም.
የጋዜጣና ማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዲሬክተር 1936 ዓ.ም.
የታሪክና የቤተ መንግሥት ዜና ማሰናጃ ጽሕፈት ቤት ዲሬክተር 1936 – 46 ዓ.ም.
የብላታ ማዕርግ ሚያዝያ 1936 ዓ.ም.
የፍርድ ሚኒስቴር ም/ሚኒስትር 1941 – 50 ዓ.ም.
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ዓቃቤ ጉባዔ 1950 – 54 ዓ.ም.
የሕግ መወሰኛ ም/ቤት አባልና የሕግ ኮሚቴ ሊቀ መንበር 1950 – 63 ዓ.ም.
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ም/ፕሬዜዳንት 1954፣ 56፣ 60 – 61 ዓ.ም.
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተጠባባቂ ፕሬዜዳንት 1960 ዓ.ም.
የታሪካዊ ቅርሶች አስተዳደር አማካሪ 1963 – 66 ዓ.ም.
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በመደበኛ ሥራቸው ላይ ደርበው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሹም ሆነው ለ14 ዓመታት፤ የሕዝብ ጤና ሚኒስቴር ተጠባባቂ ሹም ሆነው ለአንድ ዓመት ሠርተዋል። እንዲሁም በአያሌ ቦርዶች በአባልነትና በሊቀ መንበርነት አገልግለዋል። ከነኚህም ዋኖቹ የሚከተሉት ናቸው፤
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ቦርድ ሊቀ መንበር፣ 1946-54 ዓ.ም.
የትምህርትና የሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ቦርድ አባል፣ 1940 – 54 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ቦርድ አባልና ምክትል ሊቀ መንበር፣ 1942 – 66 ዓ.ም.
የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ. ወ. ክ. ማ) ቦርድ አባልና ምክትል ፕሬዜዳንት 1941 – 1966 ዓ.ም.።
በልዩ ትእዛዝ የፈጸሟቸው አገልግሎቶች፤
ብላታ መርስዔ ኀዘን ከመደበኛ ሥራቸው ደርበው አያሌ ልዩ ልዩ ሥራዎችን እየታዘዙ ሠርተዋል። ከነኚህም ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
የኢትዮጵያና የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ድርድር
ኅዳር 1 ቀን 1940 ዓ.ም. ብላታ መርስዔ ኀዘን ኢትዮጵያ የራሷን ፓትረያርክ እንድትሾም በኢትዮጵያና በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያናት መካከል በሚደረገው ድርድር ተካፋይ እንዲሆኑ ተመረጡ። ብላታ መርስዔ ኀዘን እስከ ድርድሩ ፍጻሜና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትረያርክ፣ የአቡነ ባስልዮስ ሢመት እስኪፈጸም ድረስ ተሳታፊ ሆነው አገልግለዋል። ዝርዝር ታሪኩንም «ሢመተ ሊቀ ጳጳሳት ኢትዮጵያዊ» እና «የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትረያርክ» በሚል ርእስ ባዘጋጇቸው መጻሕፍት ጽፈውታል።
የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ማረም ኮሚቴ
የካቲት 27 ቀን 1939 ዓ.ም. የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ማረም ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሆኑ። ለዚህ ሥራ ተመርጠውና ታዝዘው በልዩ ልዩ ጊዜ የሥራ ተባባሪ የሆኑት ሊቃውንት ብዙ ነበሩ። ነገር ግን እስከ ሥራው መጨረሻ ድረስ ምንም ሳይለዩ ሥራውን በመቀጠል ላይ የነበሩት፤ በብሉይ ኪዳን ክፍል ሚስተር ግራሃምና ብላታ መርስዔ ኀዘን፤ በሐዲስ ኪዳን ክፍል ቄስ ማቲውና አለቃ አርአያ ሥላሴ ወሮታ ነበሩ። የተሻሻለው የአማርኛ ሐዲስ ኪዳን በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በ1947 ዓ.ም. ፤ ጠቅላላው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን) ሐምሌ 16 ቀን 1952 ዓ.ም. በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ታትሞ ወጥቷል።
የፍትሐ ነገሥት ኮሚሲዮን
መጋቢት 17 ቀን 1946 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ የፍትሐ ነገሥት ኮሚሲዮን (የኮዲፊኬሽን ኮሚሲዮን) ሲቋቋም የኮሚሲዮኑ ሊቀ መንበር የፍርድ ምክትል ሚኒስትሩ ብላታ መርስዔ ኀዘን ነበሩ። የኮሚሲዮኑ አባላት ሦስት የታወቁ የአውሮጳ የሕግ ፕሮፌሰሮችና የበሰለ የባህልና የሕግ ዕውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ነበሩ። የኮሚሲዮኑ ዓላማ በፍትሐ ነገሥትና በኢትዮጵያ የነበሩትን ልማዶችና ባህሎችን መሠረት በማድረግ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር፣ የንግድና የባሕር ሕጎችን ማዘጋጀት ነበር። የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በ1949 ዓ.ም. ፣ የፍትሐ ብሔር ሕግ በ1952 ዓ.ም. የንግድና የባሕር ሕጎች በ1953 ዓ.ም. በፓርላማ ጸድቀው ንጉሠ ነገሥቱም አጽድቀዋቸው ሕግ ሆነው ወጥተዋል። እነኚህ ሕጎች እስካሁን በመሠረቱ አልተቀየሩም፤ ከአንዳንድ ማሻሻያዎች በስተቀር አሁንም ድረስ በኢትዮጵያም በኤርትራም እየተሠራባቸው ናቸው።
መጽሐፈ ቅዳሴ
በ1918 ዓ.ም. “14ቱ መጽሐፈ ቅዳሴ” ታትሞ ወጥቶ ነበር። በ1942 ዓ.ም. የወጣውን መጽሐፈ ቅዳሴ ያዘጋጁት ብላታ መርስዔ ኀዘን ናቸው። በ1942 ዓ.ም. ተሻሽሎ የታተመው መጽሐፈ ቅዳሴ ውስጥ ሊጦን፣ መስተብቊዕና ዘይነግሥ ተጨምረውበታል።
የፍትሐ ነገሥት ንባብና ትርጓሜ ሥራ
በ1960 ዓ.ም. የፍትሐ ነገሥት ንባብና ትርጓሜ የሚሠራ ኮሚቴ ተቋቋመ። የኮሚቴው ሰብሳቢ ብላታ መርስዔ ኀዘን ሲሆኑ፤ አባላቱ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ (በኋላ አቡነ መልከ ጼዴቅ)፣ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ መልአከ ሰላም ሳሙኤልና መልአከ ብርሃን አድማሱ ነበሩ። ሥራው አንድ ዓመት ተኲል ወስዶ በ1962 ዓ.ም. ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ታትሞ ወጥቷል።
የአማርኛ መርሐ ልሳን
ሰኔ 20 ቀን 1964 ዓ.ም. የአማርኛ መርሐ ልሳን (አካዳሚ) ሲቋቋም ብላታ መርስዔ ኀዘን አባል ሆነው ተመረጡ። የመርሐ ልሳኑ ዓላማ የመንግሥቱን ቋንቋ አማርኛን ማዳበርና የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ እንዲስፋፋ ማበረታታት ነበር። ጡረታ እስከወጡበት ዘመን ድረስ በመርሐ ልሳኑ አባልነት አገልግለዋል።የመርሐ ልሳኑ አባል የነበሩት ዶክተር በላቸው አሥራት ስለ ብላታ መርስዔ ኀዘን ትዝታቸውን በሚከተለው ገልጸውታል
“ክቡር ብላታ በኮሚሽኑ ዘንድ የተከበሩ ሊቅ ነበሩ። በተለመደው ጠባያቸው ንግግራቸው የተቆጠበ፤ ሲያስፈልግ አስተያያት የሚሰጡ፤ በተረፈ ግን “ንግግራችሁን አደንቃለሁ” በማለት ሌሎቻችንን የሚያበረታቱ ነበሩ።”
በ1964 ዓ.ም. ብላታ መርስዔ ኀዘን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሽልማት ተሸላሚ ሆኑ። ብላታ መርስዔ ኀዘን በ1966 ዓ.ም. ጡረታ ወጡ። ከጠላት ወረራ በፊት 16 ዓመት ከ4 ወር ከጠላት ወረራ በኋላ 32 ዓመት ከ10 ወር በድምሩ 49 ዓመት ከ2 ወር በቅንነትና በታማኝነት ሀገራቸውንና መንግሥታቸውን አገልግለዋል።
ጥቅምት 19 ቀን 1971 ዓ.ም. ብላታ መርስዔ ኀዘን የቀኑን ሥራቸውን ጨርሰው ወደ መኝታቸው ሄዱ። ከዚያም በተኙበት በ79 ዓመታቸው ካለ ምንም ጻዕር ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ሥርዓተ ቀብራቸው ጥቅምት 21 ቀን 1971 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አቦ መካነ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ተፈጸመ።
በብላታ መርስዔ ኀዘን የተደረሱ
- “ትምሕርተ ሕፃናት” አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን ማተሚያ ቤት፣ ግንቦት 1 ቀን 1917 ዓ. ም. /ገጽ 36/
- “የአማርኛ ሰዋስው” የመጀመሪያው ረቂቅ በ1919 ዓ. ም. ተጻፈ ዳግመኛ በ1934 ዓ. ም. እንደገና ተጻፈ። አዲስ አበባ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ 1935 ዓ.ም. /ገጽ 232/ ከዚህ በኋላ ተደጋግሞ ታትሟል አራተኛ ጊዜ። አዲስ አበባ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ 1948 ዓ. ም.
- “የአማርኛ ሰዋስው መክፈቻ” አዲስ አበባ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ 1936 ዓ. ም. /በድጋሚ ታትሟል/ አዲስ አበባ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ 1945 ዓ. ም.
- “አማርኛ ሰዋስው 1ኛ ክፍል” የአማርኛ ሰዋስው ለጀማሪዎች መጀመሪያ እርምጃ ስም፣ ተውላጠ ስም፣ ቅጽል፣ መስተዋድድ አዲስ አበባ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ 1941 ዓ. ም. /ገጽ 40/ ከዚህ በኋላ በድጋሚ ተመላልሶ ታትሟል። 11ኛ እትም አዲስ አበባ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ 1958 ዓ. ም.
- “አማርኛ ሰዋስው 2ኛ ክፍል” የአማርኛ ሰዋስው ሁለተኛ ክፍል ግሥ፣ ተውሳከ ግሥ፣ መስተጻምር፣ ቃለ አጋኖ፣ አገባብ አዲስ አበባ፣ በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ 1942 ዓ. ም. /ገጽ 40/ ከዚህ በኋላ ተደጋግሞ ታትሟል። 3ኛ እትም አዲስ አበባ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ 1958 ዓ. ም.
- “የቤተ ክርስቲያን ጸሎት” በስደት አገር በነበረች በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ሲደረግ እንደ ነበረው ሥርዓት ንባቡና ሥርዓቱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋራ እንዲስማማ የፊተኛውን ጽሑፍ እንደገና አርመውና አሰናድተው ጽፈው ያቀረቡት፣ ሲታተም እየጠበቁ ያሳተሙ አሳቸው ሲሆኑ ስማቸው መጽሐፉ ላይ አልተጠቀሰም። አዲስ አበባ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ 1936 ዓ. ም. /ገጽ 142/
- “የቤተ ክርስቲያን ዜና” የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዜና መጀመሪያ ቊጥር በመንፈሳዊ ጉባኤ ዋና ጽሕፈት ቤት ተጠባባቂት ታተመ። አዲስ አበባ፣ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ 1938 ዓ. ም. /ገጽ 47/
- “የትእምርተ መንግሥት ታሪክ” አዲስ አበባ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ 1936 ዓ. ም
- “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጐንደርን የመጐብኘታቸው ታሪክ” በታሪክና ዜና ማሰናጃ መ/ቤት ታተመ አዲስ አበባ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ 1939 ዓ. ም. የመጽሐፉ ደራሲ መርስዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስ ሲሆኑ ስማቸው የተጻፈው በመቅድሙ ላይ ነው።
- “ዐውደ መዋዕል 1939 ዓ. ም.” ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ 1939 ዓ. ም. /ገጽ 52/ በአልማናክ ዓይነት በየዓመቱ እንዲገባ ታስቦ የነበረና በጅምር የቀረ የብላታ መርስዔ ኀዘን ሥራ ነው።
- “የኢትዮጵያ መዝገበ ዕለታት” አዲስ አበባ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ 1939 ዓ. ም. /ገጽ 224/ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የጽሕፈት ሚኒስቴር፣ የጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት በብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ የታሪክና የቤተ መንግሥት ዜና ማሰናጃ ጽ/ቤት ዋና ዲሬክተርና በአቶ ዐምደ ሚካኤል ደሳለኝ የተዘጋጀ።
- “የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዕረፍት መታሰቢያ።” ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ንጉሠ ሸዋ የዕረፍታቸው መቶኛ ዓመት ከታሪክና የቤተ መንግሥት ዜና ማሰናጃ ጽ/ቤት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ 1940 ዓ. ም. /ገጽ 21/ መጽሐፉን የጻፉት ብላታ መርስዔ ኀዘን ናቸው።
- “መጽሐፈ ቅዳሴ በግዕዝና በአማርኛ” ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ 1940 ዓ. ም. /ገጽ 220/ መጽሐፉን ያሳተሙት እቴጌ መነን ሲሆኑ ያሰናዱትና የጻፉት እየጠበቁም ያሳተሙት ብላታ መርስዔ ኀዘን ናቸው። ስማቸው የሚገኘው በመቅድሙ ላይ ነው
- “ሢመተ ሊቀ ጳጳሳት ኢትዮጵያዊ” አዲስ አበባ 1938 ዓ. ም. ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት። /ገጽ 36/ ስማቸው በመጽሐፉ ውስጥ ይገኛል እንጂ በአርእስቱ ላይ አልተገለጸም።
- “ጥበብን መፈለግ ቅን ጥበብ በቅን አማርኛ 1ኛ መጽሐፍ”፣ አየር ነፋስና ዝናም ሐርበርት ማኬይ ከጻፈው ላይ ተተረጐመ አዲስ አበባ 1947 ዓ. ም. አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት። /ገጽ 46/ ስማቸው በመጽሐፉ ላይ አልተገለጸም።
- “ጥበብን መፈለግ ቅን ጥበብ በቅን አማርኛ 2ኛ መጽሐፍ”፣ መስተዋቶችና ጧፎች ሐርበርት ማኬይ ከጻፈው ላይ ተተረጐመ አዲስ አበባ 1947 ዓ. ም. አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት። /ገጽ 51/ ስማቸው በመጽሐፉ ላይ አልተገለጸም።
- “ጥበብን መፈለግ ቅን ጥበብ በቅን አማርኛ 3ኛ መጽሐፍ”፣ ድምጾች ፀሐይና ጨረቃ ሐርበርት ማኬይ ከጻፈው ላይ ተተረጐመ አዲስ አበባ 1947 ዓ. ም. አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት። /ገጽ 56/ ስማቸው በመጽሐፉ ላይ አልተገለጸም።
- “ሔሮዶቱስ 1ኛ መጽሐፍ” የጥንት ታሪክ ሔሮዶቱስ እንደጻፈው። ትርጒም አዲስ አበባ 1948 ዓ. ም. አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት። /ገጽ 157/ ሁለተኛ እትም፣ አዲስ አበባ 1951 ዓ. ም. አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት።
- “ሔሮዶቱስ 2ኛ መጽሐፍ” የጥንት ታሪክ ሔሮዶቱስ እንደጻፈው። ትርጒም አዲስ አበባ 1949 ዓ. ም. አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት። /ገጽ 122/
- “ሔሮዶቱስ 3ኛ መጽሐፍ” የጥንት ታሪክ ሔሮዶቱስ እንደጻፈው። ትርጒም አዲስ አበባ 1949 ዓ. ም. አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት። /ገጽ 122/ ሁለተኛ እትም፣ አዲስ አበባ 1951 ዓ. ም. አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት።
- “ሔሮዶቱስ 4ኛ መጽሐፍ” የጥንት ታሪክ ሔሮዶቱስ እንደጻፈው። ትርጒም አዲስ አበባ 1952 ዓ. ም. አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት። /ገጽ 108
- “የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ” የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ 1956ዓ. ም. /ገጽ 151/ ስማቸው በመጽሐፉ ላይ ተገልጾአል።
- ቅዳሴ በእንግሊዝኛ ትርጒም
“THE LITURGY OF THE ETHIOPIAN CHURCH”
Translated by the Rev. MARCOS DAOUD
Revised by H. E. Blatta MARSIE HAZEN
- “ፍሬ ከናፍር” ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ 1944ዓ. ም. /ገጽ 532/
የአርትዖት ሥራ፤
1- ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ፤ ከጻሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ፤ 1959 ዓ ም ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ፤ አዲስ አበባ፣ ገጽ 365። በጠላት ወረራ ጊዜ ጠፍቶ የነበረውን የታሪኩን ጽሑፍ ከየቦታው ሰብስበው ያዘጋጁት፣ መቅድሙንም የጻፉት ብላታ መርስዔ ኀዘን ናቸው። ከአራቱ አሳታሚዎች አንዱም ናቸው። የገንዘብ አስተዋጽዖ ያደረጉ ሌሎች አሳታሚዎች ሊቀ ሊቃውንት ኃይለ መስቀል ገብረ መድኅን፣ ደጃዝማች ከበደ ተሰማና ከንቲባ (በኋላ ደጃዝማች) ዘውዴ ገብረ ሕይወት ናቸው።
2- ዜናሁ ለራስ መኮንን ዘጸሐፎ ግራ ጌታ ኃይለ ጊዮርጊስ ዘሐረር ፤ 1965 ዓ ም፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት። ገጽ 152። የግራ ጌታ ኃይለ ጊዮርጊስ የአጻጻፍ ዘዴ የካህናትን ድርሰት የተከተለ ስለነበረ በምዕራፍ፣ በርእስና በአናቅጽ የከፋፈሉት፣ መቅድሙንም የጻፉት ብላታ መርስዔ ኀዘን ናቸው። መጽሐፉ የተጻፈው በግዕዝ ነው። ብላታ መርስዔ ኀዘን መጽሐፉን ያሳተሙት በራሳቸው ወጪ ነው።
3- የደጃዝማች ገርማሜ አጭር የህይወት ታሪክ፤ ዓመተ ምሕረቱ አልተገለጸም። ገጽ 60። ብላታ መርስዔ ኀዘን ታሪኩን ከቀኝዝማች ኃይሌ ዘለቀ ሰምተው በራሳቸው እጅ በቁም ጽሕፈት የጻፉት ። መቅድሙንም የጻፉት ብላታ መርስዔ ኀዘን ናቸው። አልታተመም ግን ተባዝቶ ለቤተሰቡ ተከፋፍሏል፤ ኢትዮጵያ አንዳንድ ቤተ መጻሕፍት ውስጥም ይገኛል።
(አምኃ መርስዔ ኀዘን)