ቪላ – ሶማሊያ ~ የአዲሱ መሪ መሪዎች

     ▪️የዓባይ፡ልጅ 

የሶማሊያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ውጤት በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የሀይል አሰላለፍን የሚለውጥ ነው በማለት የፃፈው የህወሃት ደጋፊው ተንታኝ ማርቲን ፕላው ነው። ማርቲን ፕላው “ፋርማጆ ከአብይ አህመድ እና ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበራቸው። ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ ደግሞ በመጋቢት ወር ከህወሃት ጋር የተስማሙት አለ” በማለት በደምሳሳው የፃፈ ሲሆን “ሰውዬው ከህወሃት ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነት አላቸው።” ሲልም ነው ያሰፈረው።
ተንታኙ አክሎም “ህወሃት ኤርትራ ላይ ላሴረው የጥቃት እቅድ በሶማሊያ የመሪ ለውጥ መደረጉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።” በማለት ገልፆ ሴራውንም በትግራይ ክልል የሚገኙ ሶስት ዲፕሎማቶች ‘ስማችኝ አይጠቀስ’ በማለት ነግረውኛል” ብሏል።
የዛሬ ሁለት ወር ገደማ የአሜሪካ መከላከያ የበላይ ሹም በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ የሰጡት መግለጫ ዋሽንግተን ለቀጣናው የተለየ ትኩረት መስጠት እንዳለባትና አፋጣኝ ተግባር መጀመር ግድ እንደሚላት ገልፀዋል። በዚህም “በአፍሪካ ቀንድ ዋነኛ ስጋት ቻይና፣ ሩሲያ፣ አልሼባብ፣ አሀዳዊ መሪዎች ናቸው።” በማለት ዘርዝረዋል። ለዚህ የአሜሪካ ስጋት ዋሽንግተን “ወደ ቀጣናው ዶላር፣ የተወሰነ ወታደራዊ ሃይል፣ የትብብር አማራጮች በአስቸኳይ ተፈፃሚ ሆነው ስጋቱ እንዲወገድ መደረግ አለበት።” ነበር ያሉት።
ይህን ተከትሎም በቪላ-ሶማሊያ ዋሽንግተን ስጋቴ ያለችው መሪ በሌላ አጋር ይሆነኛል በምትለው ሰው እንዲተካ እጇን ያስገባችበት ምርጫ በሞቃዲሾ ተካሂዷል።

▪️
“ከማይታወቅ ምሁርነት ወደ ሀገር ፕሬዝደንትነት” በሚል አርእስት ነበር ከአስር አመት በፊት የሶማሊያ ፕሬዝደንት አሸናፊ የሆኑት ሰው በብሪታኒያው አለማቀፍ የወሬ ተቋም የገለፃቸው። የዲፕሎማቲክ ምንጮች የሰጡኝ መረጃ በማለት በ 2012ቱ የሶማሊያ ምርጫ አሸናፊ የሆኑት “ሀሰን ሼህ ማህሙድ ስማቸው ሲጠራ የተሰማው እንኳ ምርጫው ሊጠናቀቅ 48 ሰአታት እንደቀሩት ነበር” ብሏል BBC በወቅቱ ዘገባው።

ዳግም ፕሬዝደንት በሆኑበት የዘንድሮው ምርጫ ግን ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ የሚለው ስም ከአስር አመት በፊት ከነበረው በተለዬ ታዋቂ ነው። እንዴት ይህ ሊሆን ቻለ? የሚል ጥያቄም ተጠባቂ ነው።
ለሀሰን ሼክ ላለፈው ዘመነ ስልጣናቸው መጨረሻ በነበረው 2017 እኤአ ላይ “foreign state influence & somalia’s presdential election” በሚል አርዕስት ይፋ የሆነ ሰፊ ዳሰሳ የተደረገበት ጥናት ነበር። ጥናቱ ወደ ኋላ አምስት አመታት መለስ ብሎ ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ ለማሸነፍ የረዳቸው ምን እንደሆነ ያስቀምጣል። ይኸውም ፖለቲካዊ ልምዳቸው አሊያም ህዝባዊ ድጋፍ አግኝተው አይደለም ይላል፤ ይልቁንም ብዙ ዶላር ከሳቸው ጋር ስለነበረ ነው ሲል ነው ያሰፈረው። ዶላር ከፍሎ የምርጫ ድምፅ መሸመት በተለይም በሶማሊያ የካርኒቫል ያህል የአደባባይ ባህል ከሆነ ሰነባብቷል። ሀሰን ሼክ ከዚህ የተለዩ አይደሉም፤ ሊሆኑም አይችሉም።
…..
በሚገርም መመሳሰል ለኢትዮጵያ ዜጎች ነው የምንታገለው የሚሉ(የህወሃት ደጋፊ ከተለያየ ብሄር የሆኑ) አንቂዎች በስሜትም ሆነ በተልእኮ ያንፀባረቁት ሀሳብ ከአንድ ፋብሪካ የተመረተ ሊባል የሚችል አይነት ነው። ኢትዮጵያ ከሶማሊያ የተስማማችውን ወደብ የመጠቀም ድርሻዋን ልትነጠቅ ነው በማለት የደስታ ቃላት የደረደሩት በምንም ስሌት ለኢትዮጵያ ሊሆን አይችልም። ይልቁንም አሜሪካ ያወገዘችውን አውግዘው ያደነቀችውን አድንቀዋል። ዩቱበሮች ፖለቲከኞች ሙያዊ ተንታኞች እንዲሁም በአሶሼትድ ፕሬስ AP እና ሌሎች አለማቀፍ ሚዲያዎች ላይ የሚሰሩ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኞች ይህንኑ ሲፈፅሙ ተስተውለዋል። ይህም የሚፈነጥቀው አንዳች ተጨባጭ ግን አይጠፋውም።
……
ፋርማጆ መሸነፋቸውን አምነው ተቀብለው አሸናፊያቸውን (ያውም ራሳቸውን በመተቸት የሚታወቀውን) አዲስ መሪ እንኳን ደስ አለህ ነው ያሉት። ልብ በሉ የምእራባዊያን ብዙሃን መገናኛዎች “አምባገነን” እያሉ ደጋግመው ስም ሲሰጧቸው የነበሩት ሰው ናቸው ይህን የምርጫ ውጤት ተቀብለው መልካም ምኞት የገለፁት። ታዲያ ምእራባዊያን ስለ ዲሞክራሲ የሚነዙት ዲስኩርም ሆነ የመንግስታት ዴሞክራሲያዊነት ደረጃ አሰጣጣቸው ውሸት አይደለም ለማለት ምን ማስረጃ ያቀርቡ ይሆን? ( በጉልበታቸው ካልሆነ በስተቀር)። የፋርማጆን የምርጫ ሂደት እና ውጤት አቀባበለሰ በበጎነተለ እውቅና ያልሰጡት በአፍሪካ ስለሆነ ነው ሊባል ይችላል። የምእራባዊያን ሚዲያዎች በተለመደው ክህደታዊ ተቋምነታቸው ቀጥለዋል ማለት ነው። ነገሩ ሁሉ የሆነው ፋርማጆ ፈቅደው ሳይሆን ሲጨንቃቸው ነው የሚል ነጭ አምላኪ ካለ ደግሞ “ፋርማጆ ተጨንቀውም ከሆነ በምእራባዊያን ጣልቃ ገብነት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው” ተብሎ ይነገረዋል። እዚጋ አምባገነኑ ባይደን ወይስ የአፍሪካ ሀገራት..?
…..
ኢትዮጵያ ላይ አሜሪካ ለህወሃት መሳሪያ አስታጥቃ ወደ አራት ኪሎ ስትመራው ያልተቆጨ ኢትዮጵያዊ ከሶማሊያ ጥቅም የሚያስገኙ የሆኑ ትብብሮችን ጣልቃ ገብነት ነው በማለት በአማርኛ ለሞቃዲሾ ጥብቅና ከመቆም በላይ የቁም ሞት ሊኖር አይችልም።
ይሁንና ጭፈራውን ቆም አርጎ ወደ ቀልቡ ሲመለስ ግን አዲሱ ፕሬዝደንት ጋር አዳዲስ ነገር ግን አሉታዊ እውነታዎች ጋር በሂደት ይገናኛል።
የተወሰኑ ነጥቦችን እንመልከት፦
▪️ሀሰን ሼክ ሸሪፍ ባለፈው ዘመነ ስልጣናቸው ከሰሯቸው ቁልፍ ስራዎቻቸው መካከል የአይሮፕላን ጣቢያ ግንባታው ዋነኛ ተጠቃሽ ነው። የገንዘብ ወጪውም የሸፈነችው ቱርክ ስትሆን ፕሬዝደንት ኤርዶጋን የድጋፍ ፊርማውን ያሰፈሩ ናቸው።
▪️በሶማሊያ ታሪክ ከእስራኤል መሪ ጋር ተገናኝተው በመምከር ቀዳሚው ይሆኑ ዘንድ ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ 2016 ላይ ቤንያሚን ናታንያሁ ጋር ስለሁለትዮሽ ጉዳዮች ሊገናኙ ችለዋል።
▪️ኳታር ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ በ2012 እንዲያሸንፍ በማድረግ እንዲሁም አቋሟን በመለወጥ በ1017ቱ ምርጫ የመሪነት ድሉ ለሌላኛው ሶማሊያዊ ይሆን ዘንድ የገንዘብ እና ሌሎች አቅርቦቶችን ያዋለች አገር ነች። የሶማሊያ ምርጫ ውስጥ የኳታር ጣልቃ ገብነት ታሪክ ጥቅሜን ያሳጣኛል ስትል ያሳሰባት ዋሽንግተን ተደጋጋሚ መግለጫዎች ስታወጣም ነበር። ከሁለት አመት በፊትም የአመረሪካን የፖሊሲ አቋም በማመላከት ከ1985 እኤአ ጀምሮ የሚታወቀው the National ሰኔ 2020 ላይ “somalia must save itself from qatar” ሲል ማስነበቡን መጥቀስም ይቻላል።
▪️በዘንድሮው የሶማሊያ ምርጫ ላይ አቅሟ እምብዛም የሆነባት ኳታር በኤምሬትስ ጨዋታ ተሸንፋለች። ኤምሬትስ ከሀሰን ሼህ ሞሀሙድ ጋር ከአመታት በፊት ጀምሮ ቅርብ ግንኙነት ነበራት። በዘንድሮው የሶማሊያ ምርጫ ላይ ያደረገችው እንቅስቃሴ የአቡዳሃቢ አጋር የሆነው ሰው እንዲያሸንፍ ሆኗል።
▪️ሀሰን ሞሀሙድ ከህወሃት ጋር ቅርርብ የነበረው ነው። ህወሃት 40ኛውን የምስረታ በአል ባከበረበት ወቅት ተገኝተው ነበር። በወቅቱ እነ አልበሺር በመቀሌው በአል ሲታደሙ ሀሰን ሞሀሙድ አዲስ አበባ በነበረው ስነስርአት ላይ ከቀድሞው ጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ አቀባበልና ቆይታ አድርገዋል።
▪️ሀሰን ሞሀሙድ ቻይና ልማትን በመደገፍ ወደር የሌላት ሀገር ናት ማለታቸውም ይታወሳል። ቻይና በሶማሊያ ኤምባሲዋን መልሳ በከፈተችበት ወቅት የዛሬ ሰባት አመት ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ እንዳሉት ቻይና የሶማሊያ ሁለገብ አጋር የነበረችው ከጥንት ጀምሮ መሆኑን ገልፀዋል። “ቻይና የአፍሪካዊ ሀገራትን የምትፈልገው ማእድናትን ለመውሰድ ብቻ ነው ይባላል” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “ቻይና ሀገራቱ ውስጥ ጣልቃ አትገባም። መሪዎች አውቀውት ካልሆነ የምታደርገው የለም” ሲሉ መልሰዋል።
▪️ሶማሊያ የቻይናውን ቤልት ኤንድ ሮድ በፋርማጆ ፊርማ የተቀላቀለችው የዛሬ ሁለት አመት ነው።…..

እንዲህ በውስብስብ ጂኦፖለቲካዊ ጥልፍልፍ ስር የሚገኘው የሞቃዲሾው ቤተ መንግስት ቪላ ሶማሊያ አዲስ መሪ መቀየሩ እንጂ አዲሱን መሪ ማን ይዘውራቸዋል? የሚለው ጥያቄ ግን በደፈናው የምንመልሰው አይሆንም። ህወሃታዊው የተቃርኖ ዳንኪራ የሚመነጨው ይህን ባለማገናዘብ ነው ለማለት ከደርዘን በላይ ማሳያዎች መደርደር ይቻላል….

(አፅሁፌ ቀንጭቤ ያደርስኳችሁ ነው፤ ሙሉውን ቀጣይ የማጋራችሁ ይሆናል) ሰላም

እስሌማን ዓባይ ▪️ #የዓባይልጅ

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

1 thought on “ቪላ – ሶማሊያ ~ የአዲሱ መሪ መሪዎች”

  1. Esleman Abay :- you are one of our best journalist in our generation, I used to follow your regular post and I’m so happy when I see your point of view .i’m all always very excited to see your next post’s.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories