ተፈጥሮ ስታስነጥስ እኛን ያስለናል! ሥርዓተ ምህዳሩ ሲዛነፍ ሁሉ ይከስማል…

ጀማል ሙሐመድ አሊ


አካባቢ የሚባለው ከአካላችን ውጪ ያለው መጥፎም ሆነ ጥሩ ተፅዕኖ ሊያሳድርብን የሚችል ማንኛውም ነገር/እንቅስቃሴ/ ከባቢያዊ ሁኔታ ሲሆን…ህይወት ያላቸው ፍጡራን ከሌሎች ህይወት ካላቸው ፍጡራን (biotic factors) እና ህይወት ከሌላቸው የፍጥረት አካሎች (abiotic factors) ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ደግሞ ስርዓተ ምህዳር(ecosystem)ይሰኛል…
.
ተፈጥሮአዊ ትስስሮሹና የአንዱ መኖር ለሌላው ህልውና የሚያበረክተው ተዋፅኦ የስርዓተ-ምህዳር ግልጋሎት/ፋይዳዎች [ecosystem services] ይባላሉ።
.
በአከባቢያችን ውስጥ ያሉ ከሊቅ እስከደቂቅ ፍጥረታቶች የስርዓተ-ምህዳር ጥቅሞች እንዲኖሩ ወይንም እንዲመረቱ በማድረጉ ሂደቶች ውስጥ ይሳተፋሉ።ከእነዚህ ፍጥረታቶች ውስጥ የተወሰኑቱ በሰዎች ላይ ጉዳት ሊያመጡ ቢችሉም ከአደጋቸው ጋር ከመኖራቸው የሚገኘው ስነምህዳራዊ ፋይዳቸው ይበልጣል ።
.
እያንዳንዱ ቅንጣት ፍጥረታት በአካባቢያቸው ላይ ለውጦች በማምጣቱ ረገድ የላቀ ድርሻ አላቸው።ሁሉም ፍጡራን ባለማቋረጥ እርስ በርሳቸው የሚገናኙ የተሣሠሩና የሚገነዛዘቡ ናቸው፡፡ አንዱ ፍጥረት የራሱን ህልውና ለማስቀጠል ለሌላው ህያውነት ይተጋል።

ማሳያዎች:-
.
በገጠራማው የሀገራችን ክፍል ጭልፊት የዶሮ ጫጩቶችን እየሞጨለፈ ገበሬዎችን ሊያስቸግር ይችላል፤ በሌላ መልኩ ግን የጭልፊት መኖር በርካታ አይጦችን ከሰብል ማሳዎች ለቅሞ በመብላት አርሶ አደሮችን ይጠቅማል።
.
የሰው ልጅ የሌሊት ወፎችን በሽታ ሊያመጡብን ይችላሉ ብሎ ቢያጠፋቸው፣ በምትኩ ለኢንሴክቶች ማጥፊያ የሚሆን ኬሚካል በቢልዮን ዶላር ሊያስወጣው ይችላል፤ ምክንያቱም ኢንሴክቶችን በማደን ቁጥራቸውን የሚመጥኑት አብዛኛውን ጊዜ የለሊት ወፎች ናቸውና።
.
ትላልቆቹ እንጨት ሰርሳሪ ጢንዚዛዎች የቤቶቻችንን ግድግዳዎች በመቦርቦር ቀዳዳዎችን ይፈጥራሉ/የእጨቱንም እድሜ ያሳጥሩታል። ነገር ግን እነዚህ ጥንዚዛዎች የዕፅዋት ህልውናያስቀጥላሉ። የወንዴውን (የአበባ ዘር) ወደ ሴቴ በማሰራጨት የሰብል ምርትን ውጤታማ ማድረግግ የሚችሉበት ሥርዓተ ምህዳራዊ ፋይዳ አላቸው።
.
ነፍሳቶች በአለማችን ካሉት እንስሳቶች ዉስጥ በቁጥር እጅግ በጣም ብዙ ሲሆኑ ለሰው ልጆችም በበርካታ መንገዶች ጠቃሚ ናቸው። ንቦች በአብዛኛው እጅግ በጣም በተሳካ ሁኔታ የወንዴን አበባ ዘር ወደ ሴቴ የሚያሰራጩ ሲሆን።
.
ንቦች ይናደፋሉና እናጥፋቸው ብንል፣ እፅዋቶች የመራባት ሂደታቸው ስለሚስተጓጎል፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምድረ በዳነት ሊከሰት ይችላል፤ አሊያም የሰው ልጅ በምትኩ የማራባት ተግባሩን ራሱ ማከናወን አለበት፤ ይህ ደግሞ የማይቻል ነው፡፡
.
የጉንዳን መንጋ ንክሻ በፍጹም አስደሳች አይደለም ጉንዳኖች አንዳንዴ ከንብ ቀፎ ማርና ሰም ቢዘርፉም ማሳዎችን አቆራርጠው በሚያልፉበት ጊዜ ፀረ-ሰብል ተባዮችን የመቀነስ ዘመቻን ያከናውናሉ።ሰብል አጥቂ ተባዮችን በመቆጣጠር የራሳቸውን ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።
.
ሁሉም ሸረሪቶች በሚባል ደረጃ ነፍሳቶችን ይመገባሉ።ከሚመገቧቸው ነፍሳቶች ውስጥ የተወሰኑ የሰብል ተባዮች ይገኙበታል። የሰብል ተባዮች ብዛት ሊቀንስ የሚችለው እነርሱን በሚመገቡ እንስሳቶች ምክንያት ብቻ ሳይሆን ፓራሳይቶች (ጥገኛ ረቂቅ ተህዋሲያን)ተብለው በሚጠሩት ሲጠቁም ጭምር ነው ።
.
ፓራሳይቶች ትናንሽ ነፍሳቶች ሲሆኑ እንቁላሎቻቸውን በሌሎች ነፍሳት ዝርያዎች እጭ ዉስጥ በመጣል እነዚያን ዝርያዎች ከውስጥ ይገድሏቸዋል ። ፓራሳይቶች በማንኛውም የግብርና ሥርዓት ውስጥ በብዛት የመገኘት እድላችው ሰፊ ቢሆንም፤ ነገር ግን ስለ እነሱ ስነ-ህይወት የሚታወቀው ትንሽ ነው ።
.
በደኖች ውስጥ ያሉ ብዙ የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች ለበርካታ ወፎች እና ነፍሳቶች መጠለያ ናቸው። የተወሰኑ በዛፎች ቅርንጫፎች ላይ የሚበቅሉ እፀዋቶችም አሉ። እርጥበትና ጥላ ያለበት የደን መሬት ወለል ላይም የተለያዩ ዕፅዋትና እንስሳት ሊገኙ ይችላሉ። ተመራማሪዎች የትሮፒካል ደኖች መውደም በአከባቢና አለም ደረጃ ለብዙ ዕፅዋት እና እንስሳት ዝርያዎች መመናመን ዋና ስጋት እንደሆነ አመልክተዋል።
.
ዛፎች በግብርና የመሬት ገጽታዎች ላይ ብዙ መልካም ተፅዕኖዎች አላቸው።በስሮቻቸው የአፈር መሸርሸርን ይከላከላሉ። የተወሰኑ የዛፍ ዝርያዎች በስሮቻቸው ውስጥ ካሉ ባክቴሪያዎች ጋር ህብረት በመፍጠር አልሚ ነገሮችን [ማለትም ናይትሮጂን] ከአየር በመውሰድ እና የአፈር ለምነት በመጨመር ምርታማነትን ያሳድጋሉ።
.
በነዚህ ግንኑነቶች ውስጥ የሚደረጉ ተፈጥሮአዊ ክዋኔዎች መዛነፍ አለያም የያንዳዱ ፍጡር ግንኙነትና ትስስር በሆነ ምክኒያት መቋረጥ አጠቃላይ በስርዓተ ምህዳሩ ላይ ጎጂ ውጤት ያስከትላል። ምህኛቱም ከፍጥረት ዓለም ውስጥ አንድን እንስሳ፣ እፅ ወይም ሌላ ፍጡር በአካባቢው ላይ ስኬታማ እንዳይሆን ሊያደርገው ስለሚችል ነው።
.
በአካባቢያዊ ስርዓተ ምህዳር ውስጥ በፍጥረታት መካከል በሚኖር ግንኙነት፣ አንዱ ሌላኛውን ሙሉ ለሙሉ ጨቁኖ ሳያጠፋ ሚዛኑን ጠብቆ ለትውልዶች የሚኖር ከሆነ፣ ጤናማ ሊባል ይችላል፤ ነገር ግን አልፎ አልፎ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ልጅ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ውጤቱ ለሰው ልጅ ዕውቀት ምን ሊሆን እንደሚችል የማይታወቅ ድርጊት ሊፈፀም ይችላል፤ በዚህ ጊዜ አጠቃላይ ስርዓተ ምህዳሩ ሊረበሽና ሊጎዳ ይችላል።
.
ህልውናችን ለከሌላው ፍጥረት ተነጥሎ የቆመ አይደለም ከግዑዝ ወ ህያዋን ፍጥረታት ጋር የተሣሠርን ነን፡፡ፍጥረታትን ሁሉ መንከባከብና መጠበቅ ያለብን ለእርሱ ብለን ሳይሆን ለራሳችን ስንል ነው፡፡ እርሱ ለእኛ የግድ ያስፈልጋልና፡፡ እንኳንስ ሌላውን የሰው ዘር፣ ዕጽዋትና እንስሳትን፣ ነፍሳትና ተሐዋስያንን ሳይቀር መጠበቅና መንከባከብ ከህልውና ጋር የተቆራኘ ግዳጅ ነው፡፡
.
የዓለመ ዘራው ህልውና የቆመው አንዱ ላንዱ ደጀን፣ሌላው ለሌላው ህልውና መሠረታዊ አስፈልጎት ሆኖ አብሮ በመኗኗር ላይ ነውና… ሁላችንም ተደጋፊዎች፣ደጋፊዎችና ተደጋጋፊዎች ሆነን ነው ህልውናችን የተመሠረተው፡፡
.
“የሥነ ምኅዳር(ecology)ና ሥርዓተ ምኅዳር (ecosystem) ጉዳይም አትኩሮቱ ቅንጣቶች በውሕደት ተደጋግፈው የሚኖሩበትን ዓለም መስተጋብሩንና መስተሣሥሩን ስለማስጠበቅ መስተማሪያ ነው፡፡”
.
እያንዳንዱ ፍጡር ለስርዓተ ምህዳሩ እያበረከተ ያለውን ተግባር በምጣኔ ሀብት ስሌት ልንተምነው ከሚቻለን በላይ ነው…ሥነምህዳራዊ ግንዛቤያች ሲዳብር ለህልውናችን መሠረት ስለሆኑ አካባቢያዊ ጉዳዮችና ሥነፍጥረታዊ እውነቶችን ተረድተን ክብር ልንሰጠው ልንንከባከበው የሚቻለን። በተጨማሪም በፍጥረት ውስጥ አንዱ ለሌላው አስፈላጊ መሆኑንና ተከባብሮ የመኗኗርንም ብልሀት እንማርበታለን፡፡ የአነዳችን መኖር ለሌላው ሕልውና አስፈላጊ ነው። የማሕበራዊ ትስስሮሸና መስተጋብር ተፈጥሯዊ ስሌት/ቀመርም የሚያስገነዝብ ይሄንኑ ሀቂቃ ነው።

እናማን እምለው…
ይህን ተፈጥሯዊ እውቀት ያልተደገፈ ለውጠኛ ቅስቃሴና በዚህ አምሳል ያልተቀመረ ፖለቲካዊ ስሌትና ስልት ታዲያ እንደምን ተፈጥሯዊ ውጤት ሊያስገኝ ይቻለዋል…?

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories