ቱርክ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የትኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ አለች

ቱርክ የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ተሳታፊዎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የትኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገለፀች።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ያለው ዛሬ ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም. ከሰዓት ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት እንደ አዲስ ማገርሸቱ አሳስቦኛል ባለበት መግለጫው ነው።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ግጭቱን በዘላቂው ለመግታት እና ሰላም እና መረጋጋትን በአገሪቱ ለማስፈን ተዋጊ ኃይሎች ወደ ንግግር እንዲያመሩ ጋብዟል።

በመካከለኛው ምሥራቅ በምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆነችው ቱርክ፤ ከኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ጋር ተያይዞ ስሟ በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።

አንካራ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጥቅም ላይ የዋሉ ዘመናዊ ባይራክታር ቲቢ-2 የተሰኙ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በሽያጭ የፌደራሉን መንግሥት ስማስታጠቋ በስፋት ተዘግቧል።

ምንም እንኳ ቱርክ ሰራሽ ድሮኖች በኢትዮጵያው ጦርነት ጥቅም ላይ ስለመዋላቸው በቱርክም ሆነ በኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ ባይገለጽም፤ ጦርነቱ ተፋፍሞ በነበረበት ወቅት የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ቱርክ ለኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ድጋፍ ታደርጋለች ብለው ነበር።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ 2013 ዓ.ም. ላይ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋንከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ወቅት ፕሬዝዳንቱ፣ ቱርክ ለኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች ስለማለታቸው በፕሬዝዳንቱ ይፋዊ የትዊተር ገጽ ላይ ሰፍሮ ነበር።

ከቱርክ በተጨማሪ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የአፍሪካ ኅብረት ተፋላሚ ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቱርክ ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ሁለቱ አገራት ወታደራዊ እና ፋይናንስን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ትብብር ለማድረግ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

‘ጊዜው የጦርነት አይደለም’

በተያያዘ ዜና የዩናይትድ ኪንግደም የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካ እና የካረቢያን ሚንስትር ቪኪ ፎርድ ግጭት እንደ አዲስ መቀስቀሱ አሳሳቢ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሯ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ማገርሸቱ የሰብዓዊ ቀውሱን እንደሚያባብሰው አመልክተው፤ ህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥት ጦርነት አቁመው ያለ ቅምድ ሁኔታ በመነጋገር ፖለቲካዊ መፍትሄ ማፈላለግ አለባቸው ብለዋል።

ሁለት ዓመት የተጠጋው ደም አፋሳሽ ጦርነት ዳግም መቀስቀሱ እንዳስደነገጣቸው የተገለጹት ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ናቸው።

“በኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት የመቀስቀሱን ዜና ስሰማ በጣም ደንግጫለሁ፤ እንዲሁም አዝኛለሁ” ያሉት ዋና ፀሐፊው ተፋላሚ ወገኖችም ጦርነቱን በሰላም እንዲቋጩት ጥሪ አቅርበዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው ወታደራዊ ግጭቱን አስመልክቶ በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነ ገልጸው፣ ጦርነቱ እንዲቆም እንዲሁም ተፋላሚ ወገኖች ሰላማዊ መፍትሄን በመሻት ወደ ድርድሩ እንዲመለሱ ጠይቀዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ እና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል፣ ደግሞ ወቅቱ ለሰላም ውይይት የሚደረግበት ጊዜ እንጂ የጦርነት አለመሆኑን ገልጸዋል።

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories