አሜሪካን ያዋረደ የጣልቃ ገብነት ዘመቻ-ቴሕራን: OPERATION EAGLE-CLAW


?እስሌማን ዓባይ፣ የዓባይ፡ልጅ?

የዛሬ አርባ ሁለት አመት ነበር። 1980 እኤአ። በኢራን አብዮተኞች ቁጥጥር ስር የነበሩ አሜሪካዊ ሰላዮችን ለማስለቀቅ ፕሬዘደንት ጂሚ ካርተር (የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዘደንት “Operation Eagle Claw” የተሰኘውን ወታደራዊ ዘመቻ አዘዙ። ዘመቻ ከመደረጉ በፊት የነበረው አንድ አመት የክስተቱ ገፊ ምክንያቶች የተጠነሰሱበት ነበር።

1979፣ አብዮተኞቹ የኢራን የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች የአሜሪካን ፀረ-ኢራን ፖሊሲ በመቃወም በቴህራን የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ በተቃውሞ አናወጡት።


በቴህራን የአሜሪካን ኤምባሲ የናጡት የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች በተለይም የአሜሪካ መንግስት በኢራን ህዝብ የተመረጠው መሪ ሞሳዲቅ በሀይል እንዲወገድ የሞከረችበት ሴራ አቀሳጭቷቸዋል። ከዚህ ባሻገርም በኢራን ህዝባዊ አብዮት ከስልጣን የተባረሩትንና በኢራናውያን አብዮተኞች ደም የተጨማለቁትን ሻህ፣ ረዛ ፓልቫሲ ማስጠለሏና አሳልፌ አልሰጥም ማለቷም ሌላኛው የቁጣ መንስኤ ነበር።


ፕሬዘደንት ጂሚ ካርተር አሜሪካውያንን ለማስለቀቅ እስካፍንጫቸው የታጠቁ አይሮፕላኖቻቸውንና ልዩ ወታደሮችን ወደ ኢራን ላኩ። ጂሚ ካርተር “ዘመቻው ኢራንን ከአለም ካርታ ማጥፋት የሚችል ነው ” ሲሉ አሞካሽተውት የነበረ ነው። ሸብ እረብና ሰፊ ዝግጅት የተደረገበት ዘመቻ ሳይሳካ መቅረቱ ታዲያ የጂሚ ካርተርን አስተዳደር ቀውስ ውስጥ የከተተ፤ አለማቀፍ የጣልቃ ገብነት ፖሊሲን የለወጠ እንዲሁም ለዋሽንግተን ውርደትን ያከናነበ ነበር።
እንደ ጠበብቶች አስተያየት ጂሚ ካርተር 52 አሜሪካውያን እንዲለቀቁ ለማድረግ የተጔዘበት መላ ፍሬ አልባ መሆን ነገሮችን አበለሻሽቶባቸዋል። በቀጣዩ አመት (በ1981 የተደረገውን ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ እንዲሸነፉም ምክንያት ሆነ። ኢራን ያገተቻቸውን 52 አሜሪካዊያን በድርድር የለቀቀችው ባገባደድነው ሳምንት የዛሬ 41 አመት ነበር።

ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር ወደ ካቢኒያቸው ቁልጽ ትዕዛዛቸውን ሰጡ፣ ጊዜው ሚያዚያ 11 1980፤ እንዲህም አሏቸው።
“ክቡራን! በኢራን ቁጥጥር ስር የሚገኙ ዜጎችን ለማስለቀቅ ያለ የሌለ አቅማችንን መጠቀም ግድ እንደሚለን ላሳውቃችሁ እፈልጋለሁ” ሲሉ አስረገጡ። ይህም አለም አማቀፉን ህግ በተፃረረ መንገድ በኢራን ምድር አንዳች ዘመቻ እንደሚያደርጉ ለካቢኔዎቹ ግልፅ ነበር። ይህን ተከትሎ “Operation eagle claw” የተሰኘ ወታደራዊ ዘመቻ ይደረገ ዘንድ የፕሬዘደንት ጂሚ ካርተር ትዕዛዝ ሆነ።

የአሜሪካ ጦር ለዘመቻው የሚገኝበት ብቃት አርኪ ስለመሆኑ ፕሬዘደንቱን ለማሳመን ለተከታታይ 5 ወራት ልዩ ዝግጅት ተደረገ። ዝግጅቱ ላይ በምክረ ሐሳብ ተሳትፎ የነበራቸው ሰው እንደገለፁት “አየር ሃይሉ አባላት ልዩ ልምምዳቸውን በፍሎሪዳ ኢግሊን ኤ.ኤፍ.ቢ. እና ኸልበርት አድርገዋል። እንዲሁም ጉዋም አንደርሰን አየር ጣቢያ ላይ ዝቅ ብሎ ስለ መብረርና አዬር ላይ ነዳጅ መሙላት እንዲሁም ከራዳር እይታ ውጭ መብረር፣ በምሽት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እና በኢራን ምድር ያካባቢው ቅጥረኞች እንዲያጠፉት የሚሆነውን መብራት በሚፈጠር ፅልመት ውስጥ በጎግል ካሜራ እየተመለከቱ ዘመቻቸውን መተግበር፣ ወዘተ… ለ 5 ወራት ሲሰለጥኑ አሳልፈዋል።” አሉ።
አሜሪካ ከዚህ ጊዜ በፊት መሰል የዜጎቿ እገታ አጋጥሟት አያውቅም። ለመሰል ወታደራዊ ዘመቻ የተለያዩ አገራት ጥምር ጦር ጋር የመተግበር ተሞክሮውም አልነበራትም። ይሁንና የጂሚ ካርተር ሁለተኛ ዙር ምርጫ  አሸናፊነት በዚህ ዘመቻ ስኬት ላይ የተንጠለጠለ ነበር። በዚህም “Delta Force” የተባለው ልዩ የተልዕኮ ወታደራዊ ቡድን በዚህ ዘመቻ ይጀመር ዘንድ ሁኔታዎች ለጂሚ ካርተርን አስገዳጅ ሆኑ።

ሚያዚያ 24 1980፣ የአሜሪካ ጦር ብሔራዊ እዝ ዘመቻውን ጀመረ። operation eagle claw።
ሶስት የአሜሪካ አዬር ሃይል MC-130 በተባሉ ወታደራዊ ጀቶች እጅግ ጠንካራና ስልጡን የሆኑ 130 ላዩ አባላትን በኦማን አየር ሃይል ጣቢያ አቅራብክያ ከሚገኘውና ማሲራህ ከሚባል ቦታ አሳፈረ፤ ጉዞውም ከቴህራን 200 ማይል ርቀት ላይ ወደምትገኘው የፋርስ ባህረ-ሠላጤ ሰርጥ ለማድረስ ነው፤ ቦታው desert-one የሚል የኮድ ስም ተሰጥቶታል።

Hostage crisis Iran America

ዘምቻው የታቀደው በስምንት የባህር ስታልዮ ሄልኮፕተሮች ከUSS Nmitz እና C-130 ሄሪክሎስ አይሮፕላኖች በአዬር ላይ ነዳጅ ከሚሞሉበት የዴዘርት-ዋን ከሚባለው የመካከለኛው ምስራቅ በረሃ ለማድረስ ከሚደረግ በረራ እንዲጀመር ነበር።
የዘመቻው የትግበራ ንድፍ በትንሹ 6 ወታደራዊ ሄልኮፕተሮችን በማሰማራት ነው የተጀመረው። ይሁን እንጅ 4 ሰዓታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ 2 ሄልኮፕተሮች ባጋጠማቸው ሜካኒካዊ ብልሽት ከአገልግሎት ውጪ ሆኑ። ሌሎች ሄልኮፕተሮችና ደጋፊ ጀቶች ደግሞ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ገጠማቸው፤ ይህ እስኪስተካከል እየጠበቁ መቆየት ግድ ነበር፤ ሴኮንዶች ግን መቁጠራቸውን ቀጥለዋል። አየር ሁኔታው እስኪስተካል ከሚጠባበቁት መካከል አንደኛው ሄልኮፕተር በሃይድሮሊክ ችግር ከአገልግሎት ውጪ ሆነ።


ሶስቱ ሄልኮፕተሮች ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል። በመቀጠልም ሌላኛው ሄልኮፕተር (ቁጥር 6) ተሽከርካሪ ምላጩ ላይ ባጋጠመ ብልሽት እሱም ከአገልግሎት ውጭ ሆነ። አምስተኛውም ሄልኮፕተር (ቁጥር 5) ድቅድቅ በሆነ የአሸዋ ማእበል ተከበበ። ሄልኮፕተሩ ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ለመጠበቅ የቀረው ከ25 ያልበለጡ ደቂቃዎች ብቻ ናቸው። ከዘመቻው የጊዜ ሰሌዳ አንፃር ጉዳዩን መፈፀም የማይችል መሆኑን በመገንዘብም ሄልኮፕተሩ ወደተነሳበት ጣቢያ መመለስ ግድ አለው። ዴዘርት ዋን በተባለው ምስጢራዊው የኢራን በረሃማ ምድር መድረስ የቻለው ሄልኮፕተር 2 ብቻ ነበር። እሱም በተመሳሳይ የሃይድሮሊክ እክል ገጥሞት ቀጣዩን ተልዕኮ መከወን በማይችልበት ሁኔታ ላይ ራሱን አገኘ።


እዚህ ላይ፣ ዘመቻው ይሰረዝ ዘንድ አስገዳጅ ሁኔታዎች ተከስተዋል። operation eagle claw ግቡን ለመምታት ያለው የወረደ ሎጅስቲካዊ ቁመናና ያልተጠበቁ ሁነቶች ምክንያት ነበሩ። አሁን ከዴዘርት ዋን ወጥተው መመለስ አለባቸው። ለመመለስ አንደኛው የ C-130 ሄሩክለስ ጀት እና ለአንደኛው ሄልኮፕተር ነዳጅ ሊሞላለት ይጠበቃል። ሄልኮፕተሩ በዝቅታና በዝግታ እየበረረ ነዳጅ ለመሙላት ተጠጋ። ነገር ግን ፓይለቱን ግራ ያጋባ የአሸዋ ማዕበል ተነሳና ለሄልኮፕተሩ ነዳጅ ሊሞላ ከተጠጋው ጄት ጋር ተላተሙ። ሁለቱም ጀቶች በእሳት ተያያዙ። በውስጥ የነበሩትን የአሜሪካ Delta Force ልዩ ኮማንዶዎች ጨምሮ 8 ሰዎች ሞቱ።


አሜሪካ ያቀደችው Operation eagle claw ሳይሳካ ቀረ። የዚህ ዘመቻ አለመሳካት ያስከተለው ጣጣ እስረኞችን የማስፈታቱ እቅድ ቅዠት በማድረግ የተወሰነ አልነበረም። ከጂሚ ካርተር በፊት የነበሩት ሪቻርድ ኒክሰን በአንድ ወቅት የአሜሪካን ጦር “የአለማችን ሃያል” በማለት ሁሉን ቻይ አድርገው የገለፁበት ንግግራቸውን አለም ያስታውሰው ነበር። Operation Eagle Claw በውድቀት ሲቋጭ ለዋሽንግተን ያልተጠበቀ ሃፍረትና ውርደትን  ያዘነበ ክስተት ሆነ።
ከዚህ በተጨማሪም ጂሚ ካርተር ለሁለተኛው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የነበራቸው ህልም አብሮ ተደመደመ። ሃምሳ ሁለት ታጋች ዜጎችን ለማስለቀቅ የተደረገው ኦፕሬሽንም ተጨማሪ ደርዘን አሜሪካዊያንን ህይወት በመቅጠፍ ተዘጋ።

ዘመቻው የከቸፈበትን ምክንያት የወቅቱ የኢራን መሪ ኢማም ሆሚኒ 2010 ላይ ለኢራን ተማሪዎች ባደረጉት ንግግራቸው የአምላክ ተአምር መሆኑን አስረገጡ።
“ፈጣሪ ሴራውን አከቸፈ!” ያሉት ኢማም ሆሚኒ፤ ቀጠል አርገውም፣ “ሰላዮቻቸውን በአገራችን አሰማሩ፣ ሴራቸውን የሚፈፅሙበት ቦታ መረጡ፣ የአገራችንን ልዕልና በሄልኮፕተሮቻቸው ደፈሩ፣ የታሰሩ ሰላዮቻቸውን ማስለቀቅ ነበር የነሱ ዕቅድ። ይሁንና ተአምራዊው ክስተት ተፈጠረ። ጀቶችና ሄልኮፕተሮቻቸው በእሳት ተያያዙ፣ የቀሩትም ወደ መጡበት ተመለሱ።”

?Esleman Abay?

ለፅሁፉ ግብአት ካገኘሁባቸው ምንጮች መካከል⬇️

  1. BusinessInsider.
    http://www.businessinsider.com/jimmy-carter-i-could-have-wiped-iran-off-the-map-2014-10?IR=T.
  2. UsaToday.
    http://usatoday30.usatoday.com/news/washington/2010-09-17-iran-hostages-jimmy-carter_N.htm.
  3. Concannon, Diana M. Kidnapping: An Investigator’s Guide. Amsterdam : Elsevier/Academic Press, 2008. p. 135: https://books.google.fr/books?id=-KdueQed_sgC&pg=PA135&lpg.
  4. The Atlantic.
    http://www.theatlantic.com/magazine/archive/2006/05/the-desert-one-debacle/304803/.
  5. Project Gutenburg
    http://self.gutenberg.org/articles/operation_evening_light.
  6. U.S. Air Mobility Command.
    http://www.amc.af.mil/news/story.asp?id=123174343.
  7. Global Security.
    http://www.globalsecurity.org/military/ops/eagle_claw.htm.
  8. The American Presidency Project.
    http://www.presidency.ucsb.edu/ws/?pid=2490.
  9. en.imam-khomeini.ir. [Online]
    http://en.imam-khomeini.ir/en/NewsPrint.aspx?ID=7819.
  10. U.S. Force Historial Support Division.
    http://www.afhso.af.mil/topics/factsheets/factsheet.asp?id=19809.

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

1 thought on “አሜሪካን ያዋረደ የጣልቃ ገብነት ዘመቻ-ቴሕራን: OPERATION EAGLE-CLAW”

  1. I read that too much interesting to see how they’re not good at all God is great , that’s the reason they stacked died in the desert
    I want extend my greatful to you after all

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories