በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ምክትል ልዩ መልዕክተኛ የነበሩት ፔይተን ክኖፍ ከኃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ተዘገበ።
ፔይተን አሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ መሰየም ከጀመረችበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ምክትል በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተው ነው በዚህ ሳምንት ኃላፊነታቸውን የለቀቁት።
ይህም በሰባት ወራት ውስጥ ብቻ ከአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ቡድኑ ሥራቸውን የለቀቁ ሦስተኛው የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት ያደርጋቸዋል።
ፔይተን ከምክትል ልዩ መልዕክተኝነታቸው ባሻገር ከሦስት ወራት በፊት ዴቪድ ሳተርፊልድ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ በጊዜያዊነት የዋና ወኪልነት ቦታውን ሸፍነው ሲሰሩ ቆይተዋል።
“እነዚህ ሦስት በርካታ ልምድ እና ብቃት ያላቸው ዲፕሎማቶች ይህንን ወሳኝ ኃላፊነት ወስደው በማገልገላቸው ደስተኞች ነን” ሲሉ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በአፍሪካ ቀንድ ያለው ያለመረጋጋት እንዲሁም በቀጠናው ያሉት የፖለቲካ፣ የፀጥታ እንዲሁም የሰብአዊ ጉዳዮች ፈተናዎች የአሜሪካን ያልተቋረጠ ትኩረት ይፈልጋሉ” ሲሉም ፕራይስ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ፔይተን ክኖፍ ከአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ እንዲሁም ከመንግሥት ሥራ መልቀቃቸውን አረጋግጠዋል።
ነገር ግን ለፔይተን ከኃላፊነታቸው መልቀቅ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ከእራሳቸውም ሆነ ከሌሎች ምንጮች የተባለ ነገር የለም።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ነበር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮችን በቅርበት የሚከታተሉ ልምድ ያላቸው ዲፕሎማቶችን የሰየሙት።
በጥር 2013 ዓ.ም. የመጀመሪያው የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ጄፍሪ ፌልትማን በቦታው ላይ ለአንድ ዓመት ገደማ ከቆዩ በኋላ ነበር ከኃላፊነታቸው የለቀቁት።
በዚህ ዓመት ጥር ወር ተሹመው ወደ ኃላፊነቱ መጥተው የነበሩት ዴቪድ ሳተርፊልድም ከአራት ወራት በኋላ በተመሳሳይ ራሳቸውን ከኃላፊነቱ አግልለዋል።
ከዋና መልዕክተኞቹ በተጨማሪ ለልዑኩ ምክትል በመሆን ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት ክኖፍ ፔይተንም አሁን የቀደሙ አለቆቻቸውን መንገድ ተከትለው ሥራቸውን ለቀዋል።
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚከሰቱ ቀውሶችን በሚከታተለው በዓለም አቀፉ ክራይስስ ግሩፕ ውስጥ ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ዊሊያም ዳቪሰን፣ ፔይተን “በቀጠናው በርካታ ልምድ እና ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ዲፕሎማት” ነበሩ ሲል ይገልጿቸዋል።
“እንደ እርሳቸው ያለ አቅም፣ ዕውቀት እና ልምድ ያለው ሰው አዲሱን ልዩ መልዕክተኛ ለመደገፍ መሾም አለበት ብዬ አምናለሁ” ሲል ዳቪሰን ይናገራል።
በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን፣ ማይክ ሐመርን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርገው መሾማቸውን ገልጸው ነበር።
“ይህ ሹመት በቀጠናው ላለን የዲፕሎማሲ ጥረቶች ቁርጠኝነት ማሳያ ነው። በተለይም አንገብጋቢ በሆነው የጋራ ሰላምን እና ብልጽግናን ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማምጣት የሚደረገውን ሁሉን አካታች ሂደት ለመደገፍ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል” ሲሉም ስለ አዲሱ መልዕክተኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መናገራቸው ይታወሳል።
ክኖፍ ፔይተን እጅግ ተቀያያሪ እና ፈታኝ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ መልክተኛ ሆነው ለተሾሙት ለሦስቱም መልዕክተኞች ምክትል ሆነው ያገለገሉ ሲሆን አብረዋቸውም በቀጠናው አገራት በርካታ ጉዞዎችን አድርገዋል።