አባይ የማን ሲሳይ? – የህዳሴ ግድብ ጣጣና የአሜሪካ እጅ ማስረዘም

አባይ ግንድ ይዞ ይዞራል!

የኢትዮጵያ 56 በመቶው ዜጎቿ ለኤሌክትሪክ ብርሃን ባይዳ ናቸው፡፡ 23 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ወለል በታች ኑሯቸውን ይገፋሉ፡፡ ስምንት ሚሊዮኑ ደግሞ የምግብ ዋስትና እርዳታ የሚሹ ናቸው፡፡ ይቺ የምስራቅ አፍሪካ ሀገር 11 ሚሊዮን (መንግስት ያመናቸው) ስራ አጥ ወጣቶች ባለቤትም ናት፡፡ የህዝብ ቁጥሯ መቶ ሚሊዮንን የተሻገረው ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነት መፍትሄ መዘየድን የግድ ብሏታል፡፡

እንደ ስሙ ለሀሪቱ ህዳሴ እንዲሆን የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንድ ይዞ በሚዞረው በአባይ ወንዝ እንዲገነባ ቁርጠኝነት መጋቢት 2003 ዓ/ም ታዬ፡፡ ይህ እርምጃም የሁለት ሀገራት ብሄራዊ ጥቅም ሆኖ አንገት ለእገት አያያዘ፤ አያይዞም እንደቀጠለ ነው፡፡

ኢትዮጵያና ግብፅ ጎረቤቷሞች፤ የጋራ ታሪክ ተጋሪዎች ነገር ግን የጥቅም ባላንጣዎች ናቸው ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ ሀገራቱ ግብግብ የገቡበት የአባይ ወንዝ፤ የኋላ ኋላ የውክልናም ቢሆን ጦር ሳያማዝዛቸው አይቀርም የሚባል የዘመናት ስጋትን ታቅፈዋል፡፡

በተለይም ይህ ስጋት ከለተወለደበት የአባይ ውሃ የጥቅም ፍላጎት አድጎና ተመንድጎ የጎረመሰው ከዘጠኝ ዓመት በፊት፤ ኢትዮጵያ ከጨለማ አውጥቶ ብርሃን ይሆነኛል ስትል ግንባታውን በጀመረችው የታላቁ የህዳሴ ግድቧ ነው፡፡ ታዲያ ግብፅ ከጥንስሱ ጀምሮ የኢትዮጵያ ህልም እውን እንዳይሆን ያልወረወረችው ድንጋይ፤ ያልሰበረችው ድልድይ የለም፡፡ ከአቅሟ ማነስ ጋር ተያይዞ እንደ ዓለም ባንክ ከመሰሉ የገንዘብ ተቋማት ተበድራ ግድቧን ለመገንባት የተንቀሳቀሰችው ኢትዮጵያ፤ አልሳካ አላት፡፡ ለዚህም ግብፅ መንገዱን በዲፕሎማሲያዊ ደርድሮች ስለመዝጋቷ ለማንም የተደበቀ አልነበረም፡፡

ወገቧን አስራ “አናፂውም እኛ፤ ግንበኛውም እኛ” ስትል በራስ ገንዘብና አቅም ህዝቧን ቀስቅሳ ግድቡን ጀመረችው፤ ኢትዮጵያ፡፡ በእነዚህ ዘጠኝ ዓመታት ከህዝቡ የአንደነት አቋም ጀምሮ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ስራ ማጓተትና ማጭበርበር፤ ከግድቡ ስራ አስኪያጅ ህልፈት ጀምሮ እውነታኛ ገሀዱ እስከወጣው አፈፃፀሙ፤ ከተቆረጠለት በጀትና የጊዜ ሰሌላ በላይ ከመጓዝ ጀምሮ የግብፅ አሻፈረኝ ባይነትና እኔ ብቻ ልጠቀም እስከሚል ራስ ወዳድነት ደረስ፤ ከተርባይን ቅነሳ እስከ ሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ድረስ፤  በውጥንቅጥ የተሞሉ ነበሩ፡፡

ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ድርድሩ

ግርማ ሞገሱ፤ ግንድ ይዞ ይዞራል፤ የሀገር ሲሳይ፣ የበረሀው ሲሳይ እና ሌሎችም ስንኞች የተቋጠሩለት የአፍሪካ ታላቁ ወንዝ አባይ፤ ለዘመናት ኢትዮጵያን የበይ ተመልካች አድርጓል እየተባለ ሲታማ ከርሟል፡፡ በውጭው ዓለም ናይል እየተባለ ለሚጠራው ረጅም ወንዝ ኢትዮጵያ 86 በመቶው ውሃ ታዋጣለች፡፡ ይህ ድንበር ተሸጋሪ ወንዝ 11 የሚደርሱ የአፍሪካ ሀገራትን የሚያስተሳስር በመሆኑ ውስብስ የብሄራዊ ጥቅም ማስከበሪያ ተደርጎ እንደሚወሰድም የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያም ከአባይ ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ከአፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ ጥረት ስለማድረጓም ይነገራል፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ በአባይ ወንዝ ላይ ምርምሮችን ከሚያደርጉ ኢትዮጵያዊን ሙሁራን መካከል ፊት ተጠቃሽ ናቸው፡፡  ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነታቸው ባሻገር የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውይይት አማካሪ ቡድን አባል ናቸው፡፡ የአባይ ወንዝ የውሃ ሃብት ባለቤት የሆነች ኢትዮጵያ ጎረቤቶቿ ደረቅ የአየር ንብረት ያላቸው መሆኑን ተከትሎ በውሃ ሃብቷ የመልማት እቅዷን ባነሳች ቁጠር ሽሚያና የእኔ ልቅደም ጫና ይመጣባታል ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሦስትዮሽ ድርድር በቴክኒክ ቡድን በኩል እንዲሆን ቢደርግም ውጤቱ እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም፡፡ ግብፅም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተበዳይ መስላ መታየት እና በየጊዜው የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጫና ብዙ ርቀቶችን እንድትጓዝ ስለማድረጓ ይነገራል፡፡

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ የተባለው ተቋም በወራት በፊት የአባይ ወንዝ ውኀ አጠቃቀምና የኢትጵያ የዉጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሚል አርዕስት ባዘጋጀው መድርክ ላይ የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ፕ/ር ተስፋዬ ታፈሰ ግብፅ በተለይም በአረቡ ዓለም ያለትን ተቀባይነት ተጠቅማ ጫና እያደረገች ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵም ለዚህ ምላሽ መስጠት አለባት የሚሉት ፕ/ር ተስፋዬ ለህዝቡ ወቅታዊ መረጃዎች መቅረብም አለበት ይላሉ፡፡

ለዓመታት በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ውይይት ያዝ ለቀቅ እያለ ፍሬ ሳያፈራ ዛሬ ላይ ለአሸማጋይ በሩን የከፈተ ይመስላል፡፡ በመስከረም ወር በካርቱም በተካሄደው የሀገራቱ የሦስትዮሽ ውይይት፤ ግብፅ፣ የህዳሴ ግድብ አሞላሉ ላይ እና ሦስተኛ ዓለም አቀፋዊ ወገን ይግባ የሚሉ ሀሳቦችን አቅርባ ነበር፤ ምንም እንኳ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሀሳቦቹ ውድቅ ቢደረጉም፡፡

በቅርቡ በአሜሪካ ኒዮርክ በተካሄደው 74ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ አለም አቀፉ ማህበረሰብ መላ እንዲላቸው መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ በዚሁ ጉባኤ በአማርኛ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሄር ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ በአባይ ውሀ አጠቃቀም ላይ ትብብር እንጂ ቅርምት እንደማያስፈልግ የገለፁ ሲሆን የአባይን ውሀ መጠቀም ለኢትዮጲያውያን የህልውና ጉዳይ መሆኑን መናገራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

የአልሲሲን የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጣልቃ ይግባልን ጥያቄ ተከትሎ አሜሪካ ሶስቱን ሀገራት ለውይይት ጋብዛ ከሰሞኑንም የሦስቱ ሀገራት መሪዎች በዋሽንግተን ከትመው ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሦስተኛ ወገን እና አደራዳሪ የሚባልን ጉዳይ እንደማይቀበለው ሲገልፅ ቢቆይም፤ በመጨረሻ በዋሽንግተኑ መድረክ ተሳትፏል፡፡

የግብፅ ስጋትና የአሜሪካ አሸማጋይነት

የግብፅ፣ የኢትዮጵያና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም ልዑኮቻቸው ከአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትርና ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ጋር ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ ጥቅምት 26፤ 2012 ዓ.ም ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ፤ የሚከተለውን የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ አሞላል እና ማንቀሳቀስ ላይ አጠቃላይ፣ የትብብር፣ የተቀናጀ፣ ዘላቂና ሁሉም ተጠቃሚ ለሚሆኑበት ስምምነት እንዲሁም ይህንን ፅኑ አቋማቸውን በ2008 ዓ.ም. የመርሆች መግለጫ መሠረት ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ግልፅ ሂደት ለመፍጠር ቁርጠኛነታቸውን ሚኒስትሮቹ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በውኃ ሚኒስትሮቻቸው ደረጃ የሚካሄዱ አራት መንግሥታዊ የቴክኒክ ስብሰባዎችን ለማድረግ የደረሱበትን ስምምነት አስታውሰዋል። የዓለም ባንክና ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ እንዲሰጡና በየስብሰባዎቹ ላይም በታዛቢነት እንዲገኙ ሚኒስትሮቹ ተስማምተዋል። ሚኒስትሮቹ በተጨማሪም ስምምነቱን እስከ ጥር 6/2012 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ለመሥራት፣ እንዲሁም ኅዳር 28/2012 ዓ.ም እና ጥር 4/2012 ዓ.ም ሂደቱን ለመገምገምና ለመደገፍ ዋሺንግተን ዲሲ ላይ በሚደረጉ ሁለት ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ተስማምተዋል። እስከ ጥር 6/2012 ዓ.ም ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ የ2008 ዓ.ምቱ የመርሆች መግለጫ አንቀፅ 10 ተግባራዊ እንዲሆን ሚኒስትሮቹ ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ልዑክ በዋሽንግተን በሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ የውይይቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጠው የግሉ መግለጫ ደግሞ ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ፍትሃዊና ሚዛናዊ የውሃ መብት እንዳላትም ማስገንዘቧን አስታውቋል፡፡

በውይይቱ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኝ ህዝቧ የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽ ለማድረግ እና ለድህነት ቅነሳ ጥረቷ እንጂ ማንንም አካል የመጉዳት ዓላማ እንደሌላት አስታውቃለች ነው የተባለው፡፡ እንዲሁም ለሶስትዮሽ ውይይቱ አሁንም ትልቅ ግምት እንደምትሰጥ እና በግድቡ ዙሪያ ያሉ ማናቸውም አለመግባባቶች በቴክኒክ ባለሙያዎች ሙያዊ ምክክር ብቻ እንደሚፈቱ እንደምታምን አስረድታለች። በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የነበሩ ብዥታዎችን ግልጽ ለማድረግና የኢትዮጵያ አቋም ገንቢ መሆኑን ለማስረዳትም የምክክር መድረኩ ጠቃሚ እንደነበር በመግለጫው ተገልጿል።

ሀገራቱ በ2008 ዓ/ም በተፈረመው የመርሆች ስምምነት (Declaration of Principles) መሠረት እስከ ጥር 06፤ 2012 ዓ/ም ድረስ በውሃ ሚንስትሮቻቸው አማካኝነት አራት የቴክኒክ ውይይቶችን በማድረግ ውጤት ላይ ለመድረስ መስማማታቸው ታውቋል፡፡ ሆኖም ስምምነት ላይ ካልተደረሰ የመርሆዎች ስምምነት አንቀፅ 10 ገቢራዊ እንዲሆን ተስማምተዋል ተብሏል፡፡

እንዲህ እንዲህ እያለ የካቲት 4 እና 5 2012 የደረሰው ድርድሩ በዋሽንግተን ረቂቅ ሰነድ ለማዘጋጀትቢካሄድም የነበረው ውይይት በዚህኛውም ዙር ሳይቋጭ ቀርቷል፡፡ ውይይቱ በግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለማዘጀት ሲካሄድ የነበረ ነው። ሆኖም ቢቢሲ ከውስጠ አዋቂዎች አገኘሁት ባለው መረጃ ሱዳን የአቋም ለውጥ አድርጋ ከግብጽ ጋር መወገኗን እንዲሁም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ለግብጽ መወገናቸውን በመጠቆም አሁን ላይ ድርድሩ “4 ለ 1” ሆኗል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እየተደረገ መሆኑን ምንጮቹ ተናግረዋል።

መደምደሚያ

የሦስትዮሽ ድርድሩ ከተጀመረ ከአራት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ አካል በአደራዳሪነት ተሳትፏል፡፡ ለዚህም የሀገራቱ ፍጥጫ ማየሉን ተከትሎ ስለመሆኑ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ የሆነው ሆኖ የ85 በመቶ የአባይ ወንዝ ባለቤት ኢትዮጵያ በውስጣዊ ጣጣዋ ውጥንቅጥ ውስጥ መግባቷ፤ ለግብፅ እንደሚጠቅማት እሙን ነው፡፡ በሀገሬው ዜጋ ጫና ውስጥ ያሉት አብዱልፈታህ አልሲሲ፤ የህዝባቸውን አመኔታ ለመመለስ የአባን ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የግድ ሊላቸው ይችላል፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም የሚል ትነበያ እየተሰጠ ነው፡፡

ግድቡ በ80 ቢሊዮን ብር ያልቃል ቢባልም 65 በመቶ ላይ ሆኖ እንኳን 98 ቢሊዮን ብር ወጭ እንደተረገበት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ በ2015 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎም ቀን ተቆርጦላት፡፡ ከስድስት ሽህ 500 ሜጋ ዋት የኃይል ማመንጨት ወደ አምስት ሽህ 150 ዝቅ እንዲል የተደረገው የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በፈተናዎች ታጥሮ እጣ ፈንታው ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ እየተጠበቀ ነው።

በሠላም ዓለሙ

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories