አፍሪካዊው G-4 እና የካይሮው ስትራቴጂክ ጥናት ተቋም የዓባይ፡ልጅ

የምሥራቅ እና ምእራብ አፍሪካዎቹ ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ በቀጣናቸውም ሆነ በአህጉራዊ ዲፕሎማሲ ላይ ብርቱ ተፅዕኖ ካላቸው በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ታሪክ አላቸው። በዛሬው እለት ጠቅላይ ምኒስትር አብይ ወደ ናይጄሪያ ጉዞ ያደረጉ ሲሆን የናይጄሪያው ፕሬዝደንት መሀመዱ ቡሃሪ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ጠቅላይ ምኒሰትሩ ለአቀባበሉ ምስጋናቸውን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስነብበዋል። የጉዞው ዋነኛ አላማ በተለዬ ባይገለፅም ከሁለት ወራት በፊት በብራሰልስ የተጠነሰሰውን አህጉራዊ ጥምረት ተመልሰን እንቃኘው። የጥምረት ጥንስሱ በብዙኃን መገናኛዎች G4 የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን በዚሁ ዙሪያ የግብፁ Egyptian Centre for Strategic Studies ከካይሮ ጥቅም አንፃር ያቀረበው ጥናት ላይ ዳሰሳ በማድረግ ተከታዩን አጋራኋችሁ።

የአፍሪካዊ ሀገራት የአራትዮሽ ግንባር ይፋ የሆነው በያዝነው አመት ወርሃ የካቲት ላይ ነበር። G4 በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ኢኒሸቲቭ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑና በአልጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ እና የኢትዮጵያ መሪዎች ስምምነት መሰረት እንደሆነ ተዘግቧል። የአራቱ ሀገራት መሪዎች በG4 ምስረታ ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ለሚዲያ የተገለጠው በናይጄሪያው ፕሬዝደንት በኩል ሲሆን በብራሰልስ በተካሄደው 6ኛው የአውሮፓ ህብረት-አፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አውድ ውስጥ እደነበር ነው ሙሀመዱ ቡሀሪ ይፋ ያደረጉት።

በG4 ቅድመ ምስረታ ላይ በአራቱ መሪዎች ከተደረሱ ስምምነቶች መካከል ጥምረቱ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ሥር ሚናውን የሚወጣ እንደሚሆን አንዱ ነጥብ ነው። ለማስተዋወቅ (AU) ይሰራሉ እና አፍሪካ ትይዩ የሚከተሉተን በመፍታት አስቸኳይ ጉዳዮች ወደ አቀማመጥ እና ምላሾችን የማስተባበር የአፍሪካ ህብረት አባል መንግስታት መካከል አገናኝ ሆኖ ያገለግላል, በዚህም ቀውሶች ከመከሰታቸው በፊትና በኋላ ተገቢውንዪፍትሄ ርምጃ ለመውሰድ የታለመ ነው።
በአፍሪካ በሚከሰቱ ቀውሶች ላይ የሚደረጉ ምላሾች የአፍሪካዊያንን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው ይላል ስትራቴጂክ ጥናት ተቋሙ። በዚህም የአውሮፓ ህብረትና ተመድ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም አሜሪካን ጨምሮ ሀያላን ሀገራቱ በአፍሪካ ቀውሶች ውስጥ ከሚኖራቸው ሚና አስቀድሞ የ G4 ጥምረት አፍሪካዊ ድምፅና አቅም እንዲሆን ያለመ ነው ያለው የግብፁ ስትራቴጂክ ጥናት ተቋም አለማቀፍ ድርጅቶች ሆኑ አሜሪካ ወይም ሩሲያና ቻይና የዚህን የG4 ጥምረት አቋም መሰረት አድርገው ቀአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ሚናቸው እንዲተገበር ማእቀፍ የመስራት እሳቤ ያለው ነው ሲል አብራርቷል።

የ G4 አሊያንስ ይፋ የሆነው አለማቀፋዊ የፖለቲካ ሁነቶች ጋር የተገናኘ መልክ ከነበራቸው አፍሪካ ውስጥ የተከሰቱ ቀጣናዊ ተጨባጮች መካከል ነው ይላል የስትራቴጂክ ጥናት ተቋሙ። በዋናነት ሁለት ቁልፍ ጉዳዮችን በተለየ ጠቅሷል። የመጀመሪያ ያደረገው የፈረንሳይ ጦር ከማሊ መውጣት የሚለውን ነው። ፈረንሳይ ጦሯ ከማሊ የመውጣቱን መግለጫ የካቲት 17 2022 ላይ ሲሆን G4 ከሶስት ቀን በኋላ በየካቲት 20 ላይ ይፋ መሆኑን በማውሳት። አስከትሎ የጠቀሰው እስራኤል በአፍሪካ ህብረት የታዛቢነት ቦታ ይኖራት ዘንድ የቀረበውን ጅምር በአህጉሪቱ አገሮች የአቋም መከፋፈል ከታየ በኋላ ከመሆኑ ጋር ነው ይለናል ግብፃዊው የጥናት ተቋም። በዚህ መነሻነትም ለ G4 ምስረታ ጎልተው ሊቀሰቅሱ ከሚችሉ መግፍኤዎች መካከል ናቸው በማለት የሚከተሉትን ጉዳዮች ያስቀምጣል።

▪️ኢትዮጵያ የቀደመ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን ለመመለስ ካላት ፍላጎት የሚለውን ጥናታዊ ተቋሙ EGCS አስቀምጧል።
በዚህም ኢትዮጵያ ከህወሃት ጋር የነበራትን ጦርነት ይጠቅሳል። ይህን ተከትሎ ከአሜሪካ የተለያዩ ጫናዎች እስከ ማእቀብ ድረስ ኢትዮጵያ ላይ መከተላቸውን አውስቷል EGCS። ከኢትዮጵያ ቀጣናዊ እና የጎረቤት አገሮች ጋር በተያያዘ ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አለመግባባት ግብጽ እና ሱዳን ካሳዩት የሁለትዮሽ የስጋት ተቃውሞ ጋር ያያይዘዋል።
በዚህም ጠቅላይ ምኒስትር አቢይ የ G4 አሊያንስን ለመመስረት ተነሳሽነቱን መውሰዳቸው የኢትዮጵያን ጉዳይ ከአለማቀፍና የአፍሪካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ነው ይላል። የጠቅላይ ምኒስትሩን ስሌት እነ አልጄሪያ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ መቀበላቸው ሀገራቱ በኢትዮጵያ የተከሰቱ ውስጣዊ ሁነቶችን እና የአዲስ አበባን የውጭ ፖሊሲዎች የመቀበላቸው ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ነው ያለው።
▪️አልጄሪያ ከሞሮኮ ጋር በምትወዛገብባቸው ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ካላት ፍላጎት ይመነጫል- በተከታይነት የሰፈረው ነው። ሞሮኮ ከእስራኤል ጋር ሰላም ለማውረድ ያሳለፈችውን ውሳኔ አልጄሪያ ትቃወማለች። ሞሮኮ በበኩሏ አልጄሪያ መስራች የሆነችበት G4 መረጃ ይፋ ሲሆን ጅምሩን አምርራ ነው ያወገዘችው። የሞሮኮ ፀር የሆነ ጥምረት ስትል መግለጿም አይዘነጋም።
የሞሮኮ እና አልጄሪያ ውዝግብ ከድንበር ጉዳይም ጋር የተያያዘ ሲሆን ሞሮኮን ከአልጄሪያ የሚያወዛግበውን የምእራብ ሰሀራ ግዛት አሜሪካ ለሞሮኮ እውቅና መስጠቷ ይታወቃል። በሌላ በኩል አልጄሪያ ፖሊሳሪዮ ግምባር የሚባለውንና በሞሮኮ ራስ ገዝ ለመሆን የሚንቀሳቀሰውን ሀይል በይፋ የምትደግፍ ናት።
ከዚህ ባሻገርም አልጄሪያ ከሞሮኮ ምጣኔ ሀቅብታዊ ሽኩቻ እንዳላት ይነገራል። በተለይም የአልጄሪያ-ናይጄሪያ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ወደ ስራ የገባ ሲሆን “ትራንስ-ሰሃራ በታች” በተባለው የጋዝ ቧንቧ የአልጄሪያ ነዳጅ ማስተላለፊያ መሰረተ ልማት በኩል ወደ አውሮፓ በርካታ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ በኒጀር በኩል ለማጓጓዝ ከ 4,000 ኪሎ ሜትር በላይ የማስተላለፊያ ቱቦ ለመገንባት ስራ ጀምረዋል።

▪️አፍሪካ ህብረት የአህጉሪቷን ችግሮች በራሱ በመፍታት ረገድ ያሳየው ደካማነት ለ G4 ምስረታ ምክንያትነት ሌላው ተጠቃሽ ነው። አፍሪካ ኅብረት በአህጉሪቱ የተከሰቱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና የደህንነት ተግዳሮቶች ብሎም በምዕራባዊ አፍሪካ ተከታታይ መፈንቅለ መንግስቶች ተከተስተዋል። ይሁንና ህብረቱ ለተጠቀሱ የደህንነት ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠትና መፍትሄ ለማቅረብ አልቻለም። ይህ ውስንነት የህብረቱ ሚና እንዲያድግና የአፍሪካ ሀገራትን አውድ ያገናዘበ አህጉራዊ የመፍትሄ ርምጃ መውሰድ ለማስቻል ይህ የ G4 ጥምረት እንዲመሰረት ምክንያት ነው። እንደ ግብፁ የስትራቴጂክ ጥናቶች ተቋም።

የG4 አሊያንስ ከአፍሪካ ጠቅላላ ህዝብ ከ30 በመቶ የሚበልጠውን የሚያቅፍ ሆኖ ይመሰረታል ማለት ነው። መልክዓ ምድራዊ ስብጥር ያለው ሲሆን ደቡብ አፍሪካ ከበስተ ደቡብ በሰሜን እና ምዕራብ አፍሪካ ናይጄሪያ እና አልጄሪያ በምስራቅ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን አቅፎ ሲመሰረት አራቱ መስራቾችም የአፍሪካ ህብረትን በጀት በማዋጣት ዋነኛውን ድርሻ የሚሸፍኑ መሆናቸውንም ይጠቅሳል EGCS።
የG4 ጥምረት እውን መሆን ላይ ተግዳሮት ይሆናሉ ከተባሉ ጉዳዮች መካከል ከአራቱ መስራች ሀገራት መካከል የተወሰኑት በአንዳንድ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አቋም ማንፀባረቃቸው ተሰምሮበታል። በዚህም እስራኤል በአፍሪካ ህብረት ታዛቢ አባል ትሆን ዘንድ ከደገፉ ሀገራት የG4 ጥምረትን የምትቃወመው ሞሮኮ ስትሆን G4 የመስራችነት ስምምነት የደረሰችው አልጄሪያ ደግሞ የእስራኤልን የህብረቱ ታዛቢ አባልነት ትቃወማለች። ይህ እና መሰል ተግዳሮቶችን ነው የ G4 እውናዊነትን ሊያስቀር ይችላል ሲል የግብፁ ስትራቴጂክ ጥናት ተቋም ድምዳሜውን አስፍሯል።

ጠቅላይ ምኒስትር ዓብይ ዛሬ ወደ ናይጄሪያ ያደረጉትን ጉዞ በተመለከተ ባሰፈሩት ፅሁፍ “ሁለት ታላላቅ የአፍሪካ ሀገራት እንደ መሆናችን፣ የኛ ትብብር መጠናከሩ ለሁለትዮሽ ግንኙነታችን እንዲሁም ለአህጉራዊ ትብብር ወሳኝ ነው።” ሲል ይነበባል።

Esleman Abay #የዓባይልጅ

የግብፁ ስትራቴጂክ ጥናት ተቋም EGCS ሙሉ ጥናት በሊንኩ ያግኙ ⬇️ https://eslemanabay.com/group-of-african-four-nations-context-and-motives/

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories