አፍሪካውያን ዘላቂ ሰላማቸውን ለማስጠበቅ በራሳቸው የገንዘብ አቅም የሚደገፍ ተቋምን ለማጠናከር 480 ሚሊየን ዶላር ከአባል ሀገራቱ እያሰባሰበ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ገለጸ፡፡

የሕብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ደኅንነት ኮሚሽን ባለፉት 9 ወራቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሕብረት ታዛቢነት የተካሄዱ 11 ምርጫዎች ስኬታማ ነበሩ ብሏል፡፡ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዴዌየ በአህጉሪቱ ሰላም እና ደኅንነትን ለማስጠበቅ አምስት መሰረታዊ ምሰሶዎችን ለይቷል ብለዋል፡፡ ይህም ሰላም እና የተቀናጀ የአቅም ግንባታን ማሳደግ፤ ወዳጅነትን መገንባት፤ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ማደራጀት፤ እንዲሁም የእርቅ መንገድን ማስፋት ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን በተመለከተ የተጠየቁት ኮሚሽነሩ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት ቆሞ ሰላም እንዲሆን ሕብረቱ ከፍተኛ ፍላጎት አለው ብለዋል። ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የሱዳን ግጭትም ቆሞ ምሥራቅ አፍሪካ የተረጋጋ እና ሰላም መሆን አለበት፤ እነዚህን ጉዳዮች እንዲመራ ደግሞ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ የምሥራቅ አፍሪካ ዋና ተወካይ ሆነው በዋና ጸሐፊው መሾማቸውን አስታውሰዋል፡፡ ይህን ኀላፊነት ወስደው ይከውናሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ነው የተናገሩት፡፡

ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ላሉ ንጹሃን ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደረስ ማመቻቸት አለባቸው ነው ያሉት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ።

አፍሪካ በኀያላን ሀገራት ጣልቃ ገብነት እየተቸገረች ስለመሆኑ እና በየዓመቱ እንደ ንግድ ሊዝ ለጦር ሰፈርነት መሬቷን እያከራየች ነው ይህ ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳዮች የሰላም እና ደኅንነት ኮሚሽን ከቀጣናው ሰላም አኳያ እንዴት ያየዋል ተብሎ ለቀረበላቸው ሀሳብም አምባሳደር ባንኮሌ አዴዌየ በዚህ ጉዳይ ላይ ሕብረቱ የየሀገራቱ ውሳኔ ነው ብሎ እንደሚያምን ነው የተናገሩት፡፡ የኀያላኑ ሀገራት የጦር ሰፈር ጉዳይ የሚወሰነው በአባል ሀገራቱ ፍላጎት ነው፤ ይህን የመወሰን ሉዓላዊ መብታቸው ነው ብለዋል፡፡ ይሁን የፈቀዱት ሀገራት የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና ደኅንነት ፕሮቶኮልን ማክበር አለባቸውም ብለዋል፡፡

ይህም አፍሪካውያን ችግር ሲያጋጥማቸው በጋራ የሚከላከሉበት መንገድ ነው፤ ይህን አቅጣጫ የሚያሲዘው የሕብረቱ የሰላም እና ደኅንነት ምክርቤት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በዚህ አማካኝነት አፍሪካውያን ይተባበራሉ፤ ያጋጠማቸውን አለመረጋጋት በመፍታት ለተረጋጋ መንግሥት ይሠራሉ ብለዋል።

አፍሪካ ምንም ቢሆን የራሷን አቅም ማጠናከር ካልቻለች ከውጭ በገንዘብ እየተደጎመች ሰላሟን ልታረጋግጥ አትችልም ነው ያሉት፡፡ አፍሪካ ሰላሟን በራሷ የማስጠበቅ ሃሳብ አንዱ የጀንዳ 2063 እቅድ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ በራሷ የፋይናንስ አቅም የሚቆም የደኅንነት ተቋም ያስፈልጋታል፤ በውጭ እረዳታ ሰላምን ማረጋገጥ ያስቸግራል ነው ያሉት፡፡

ልማት እና ሌሎች ሥራዎች በረጅ ሀገራት እና ተቋማት ቢደገፉ ችግር የለውም፤ ይሁንና አፍሪካ ለደኅንነቷ እራሷ ፋይናንስ ማድረግ አለባት፤ ለዚህም እስከ 2022 ድረስ አባል ሀገራቱ 480 ሚሊዮን ዶላር የማወጣት ግዴታቸውን እየተወጡ እንደሆነ አምባሳደር ባንኮሌ አዴዌየ አስረድተዋል፡፡

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories