“ናሚቢያ፣ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት የጀርመን ቅኝ ግዛት ነበረች። መጠሪያዋም ደቡብ ምዕራብ አፍሪካ (South West Africa) ነበር። ጀርመን በ1ኛው የዓለም ጦርነት ስትሸነፍ ቅኝ ግዛቷ በሙሉ በእንግሊዝና ፈረንሳይ ስር ተከፋፍለው በሞግዚትነት እንዲተዳደሩ ተደረገ። ይህንን ያደረጉት አሸናፊዎቹ ያቋቋሙት የመንግስታቱ ማህበር ወይም ‘ሊግ ኦፍ ኔሽንስ’ ነው። ስለዚህ ደቡብ ምዕራብ አፍሪካ (የዛሬዋ ናሚቢያ) በደቡብ አፍሪካ ሞግዚትነት (ማንዴት) ስር እንድትተዳደር ሆነ። ደቡብ አፍሪካ ደግሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነበረች።
“ከ20 ዓመታት በኋላ፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲቀሰቀስ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ (ማህበር) ፈረሰ። ኢትዮጵያም የዚያ ማህበር አባል ነበረች። ከጦርነቱ በኋላ ተመድ (United Nation) የተባለው ሌላ የዓለም ማህበር እንደተቋቋመ፣ ቀድሞ በእንግሊዝና በፈረንሳይ ሞግዚትነት ስር የቆዩት እንደ ደቡብ ምዕራብ አፍሪካ (ናሚቢያ) ያሉት አገሮች ‘ማንዴት’ ከመባል ፋንታ “Trust Teritory” እንዲባሉ በተመድ ተወሰነ። ይሄኔ፣ ሳውዝ አፍሪካ ውሳኔውን አልቀበልም አለች። ውሳኔው ወደነፃነት የሚወስድ አንድ እርምጃ በመሆኑ ነው። ተመድም የደቡብ አፍሪካን እምቢተኝነት አወገዘ። ኢትዮጵያና ላይቤሪያ የቀድሞው የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል ስለነበሩ፣ በወቅቱ ለደቡብ አፍሪካ ማንዴቱ የተሰጠው በአደራ ነው በማለት፣ ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት (International Court of Justice) ደቡብ አፍሪካን ከሰሱ። በተለይ ኢትዮጵያ የራሷ ጉዳይ አድርጋ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ላይ ለናሚቢያ ተከራከረች። ኔዘርላንድ ያለው ይህ ፍርድ ቤት፣ ጉዳዩ አግባብ ያለው ጥያቄ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያና ላይቤሪያን አይመለከታችሁም። የሚያገናኛችሁ ጥቅም የለም በማለት ፈረደባቸው።
“ኢትዮጵያ ይህንን ክርክር ለናሚቢያ ስታካሂድ ገንዘቧንም ጉልበቷንም አቃጥላ ነበር። ከዚያም የተባበሩት መንግስታት ደቡብ አፍሪካን በመቃወም በፖለቲካው የያዘውን አቋም ገፋበት። ኢትዮጵያም የፖለቲካ ትግሏን አጠናከረች። ከብዙ ትግል በኋላ ደቡብ አፍሪካ የራሱ የአፓርታይድ ችግር እየከበደውና ግፊቱ እየበዛበት ሲመጣ፣ ሸክሙን ለማቅለል ሲል፣ ልገላገል ብሎ ደቡብ ምዕራብ አፍሪካን ነፃ ለቀቀ። አገሪቷም ነፃ እንደወጣች ናሚቢያ ተባለች።…”
ከላይ ያለውን የተናገረው የመጀመሪያው የናሚቢያ ፕሬዚዳንት የነበረው የሳም ኒዮማ የቅርብ ወዳጅ እና ከአበበ ቢቂላ ጋር ዝምድና ያለው ዶ/ር ግርማ አበበ ነው
(ምስሉን ከታች ይመልከቱ) በጊዜው ዶ/ር ግርማ አበበ የተመድ የሞግዚት ምክር ቤት (Trusteeship Council) ፀሃፊ ሆኖ ያገለግል ነበር።
ምንጭ: “ታላቁ ጥቁር” በንጉሤ አየለ ተካ