ኢትዮጵያ ከቻይ፣ ሩሲያ እና ህንድ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጥቂቱ

ኢትዮ- ቻይና

ላለፉት 60 ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ፣ በባህል እና በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ በርካታ
የጥናትና የምርምር ጽሁፎችን ያበረከቱት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፤ የቻይና እና የኢትዮጵያ ግንኙነት እኤአ ከ618 እስከ
907 ባሉት ዓመታት ውስጥ እንደተጀመረ ይገልጻሉ። ይሁንና የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሰያዊ ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ የተጀመረው እኤአ
በዴሴምበር 1970 እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

እኤአ በ1971 ቻይና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ ኢትዮጵያ
ድጋፍ ስለማድረጓም የታሪክ ድርሳናት ይገልጻሉ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያን በሀይል ለወረረችው ጣሊያን እውቅና ከነፈጉ አምስት መንግስታት
መካከል ቻይና ትጠቀሳለች። እ.አ.አ በ1964 የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዞው ኢንላይ ኢትዮጵያን
የጎበኙ ሲሆን በተመሳሳይ አፄ ሀይለስላሴ እኤአ በ1971 ቻይናን በጎበኙበት ወቅት የቻይና አባት በሚባሉት ማኦ ዜዱንግ ደማቅ አቀባበል
እንደተደረገላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኢትዮጵያ
እና ቻይና የረጅም ጊዜ ግንኙነታቸውን በማጠናከር እስካሁን የዘለቁ ሲሆን በንግድ፣ በመሰረተ-ልማት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስኮች
ጠንካራ ግንኙነት መፍጠራቸው ይታወቃል። ኢትዮጵያ የቻይና ሮድ ኤንድ ቤልት ትብብር ማዕቀፍን ከፈረሙ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ቀዳሚዋ ስትሆን፤ የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መንገድ ግንባታም የዚሁ ትብብር ማሳያ ነው። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በፈረንጆቹ
2018 በቤጂንግ በተካሄደው የቻይና- አፍሪካ ጉባዔ ላይ እንዲሁም በ2019 በተካሄደው ቤልት ኤንድ ሮድ ትብብር ጉባዔ ላይ ያደረጉት
ጉብኝት የሁለቱ ሀገራት ዘላቂ ግንኙነት አንዱ ማሳያ ነው።

በቤጂንግ
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ድረገጽ ላይ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እኤአ ከ2016-2018 ድረስ በነበሩት ዓመታት ብቻ የቻይና ቀጥተኛ
ኢንቨስትመንት 4 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። በእነዚህ ዓመታት የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፤ በየዓመቱ የ22 በመቶ እድገት እያሳየ መሆኑን መረጃው ያመለክታል። የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ጠቅላላ ዋጋቸው ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚያወጡ ከ1 ሺህ
500 በላይ ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፉ ሲሆን
በዚህም በኢትዮጵያ ከ60 ሺህ በላይ የስራ እድል መፍጠር የቻለ መሆኑንም መረጃው ይጠቁማል።

ኢትዮ-ህንድ

ኢትዮጵያና ህንድ ከሁለት ሺህ አመታት የተሻገረ ሁለንተናዊ ግንኙነት እንደነበራቸው የተለያዩ መዛግብት ያስረዳሉ። ከ19ኛው መቶ ክፍለ
ዘመን
ጀምሮም በርካታ የህንድ ተወላጆች ኢትዮጵያን የኑሮ ምርጫቸው እንዳደረጉ የሚያመለክቱ ማሳያዎችም ብዙ ናቸው። በአንደኛውና በሁለተኛው የአለም ጦርነት መካከል በነበሩት አመታት በርከት ያሉ የህንድ ዜጎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው ስለመቆየታቸው የሚያስረዱት መዛግብት በአጼ ሃይለስላሴ ስትመራ የነበረችው ኢትዮጵያ ከህንድ ጋር መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረተችው እኤአ በ1948 ሲሆን በአምባሳደር ደረጃ ግንኙነታቸውን ያሳደጉትም እኤአ
ከ1952 ጀምሮ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

በወቅቱ በርካታ ህንዳውያን መምህራን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በየጠቅላይ ግዛቱ በርካታ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በማስተማር ላይ ቆይተዋል። ሲኒማ ቤቶች ከመስፋፋታቸው በፊት በርካታ የህንድ ፊልሞች በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ለተመልካች ሲቀርቡና በባህል ግንባታ ረገድም የራሳቸውን ተጽእኖ ሲፈጥሩ እንደነበር የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ።

ህንዳውያን ከእንግሊዝ ነፃ ለመውጣት መራራ ትግል ባደረጉበት ወቅት ለትግሉ የሚሆኗቸውን መርሆዎች ከኢትዮጵያውያን ስለመውሰዳቸው አንዳንድ ሰነዶች ይጠቁማሉ። በዚያን ወቅት
መደበኛም ባይሆንም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንደነበርም መረጃዎቹ ያመለክታሉ። 

ከሁለት ትውልድ በላይ የተሻገረው የሃገራቱ የትምህርት ዘርፍ ትብብር የኢትዮጵያን የከፍተኛ ትምህርት አቅም ለማሳደግ ያስቻለ ሲሆን፤ በርካታ ኢትዮጵያውያንም በህንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን እንዲያገኙና የሃገራቸውን የተማረ የሰው ሃይል ክፍተት እንዲያሟሉ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። በታክስ አስተዳደር፣ በሃይል ልማት፣ በቴክኒክ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በባህልና በሌሎች ዘርፎች በርካታ ስምምነቶችን ያደረጉት ሃገራቱ የንግድ ልውውጣቸው ከ1.3 ቢሊየን ዶላር በላይ ስለመድረሱ የህንድ ኤምባሲ ይፋዊ ድረ-ገጽ ያመለክታል።

የብሄሮች፣ የሃይማኖቶች፣ የባህሎችና የመልክአ-ምድር ስብጥሮች ኢትዮጵያና ህንድን እንደሚያመሳስላቸውና ያሉበት ጂኦፖለቲካዊ ቀጠናም ሃገራቱን በፖለቲካና በውጭ ግንኙነቱ በኩል እንዲተባበሩ እንዳስቻላቸው ምሁራን ያስረዳሉ።

ኢትዮ-ሩሲያ

በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ክፍለ
ዘመን
የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ሃይሎች አፍሪካን፣ ላቲን አሜሪካን ብሎም አንዳንድ የኤሽያ ሃገራትን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ በተንቀሳቀሱበት ወቅት በንጉሳዊ የአስተዳደር ስርአት ስትመራ የነበረችው ሩሲያ ከቅኝ ግዛት ጋር ተያይዞ ስሟ አልተነሳም። በወቅቱ እንግሊዝ ፈረንሳይና ጣሊያን ኢትዮጵያ ላይ በአንድም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ጫናቸውን ሲያከብዱ ከኢትዮጵያ ጋር በመቆም አጋርነቷን ያሳየችው ሩሲያ ከታላቁ የሩሲያ የቦልሼቪክ አብዮት በኋላም ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙነት እንዳልተለወጠ ይነገራል።

የፋሽስቱ ሞሶሎኒ አስተዳደር ግዙፍ የጦር ሃይል አሰልፎ ዳግም ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በርካታ ሩሲያውያን ሃኪሞች፣ የጦር ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞችና የታሪክ ጸሃፊዎች ከኢትዮጵያውያን አርበኞች ጎን ሆነው ድጋፍ ከማድረጋቸውም በላይ የሩሲያ ባለስልጣናት በሊግ ኦፍ ኔሽንስ ጉባኤዎች ላይም ለኢትዮጵያ ወግነው ክርክሮችን ሲያደርጉ እንደነበር  በርካታ መረጃዎች ያሳያሉ።

የሁለተኛው የአለም ጦርነት እንዲጠናቀቅ ጉልህ አስተዋጽኦ የነበራት ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ይበልጥ የሚያስተሳስራትን እርምጃዎች የወሰደች ሲሆን በ1966 ዓ.ም
በኢትዮጵያ
የተከሰተው አብዮትን ተከትሎ የተከሰተው የሶማሊያ ወረራ የሃገራቱን ግንኙነት በደምና በህይወት የተቆራኘ እንዳደረገው ብዙዎች ይገልጻሉ።

ከወታደራዊና ደህንነት ዘርፍ ባለፈም ሩሲያ ለኢትዮጵያ በርካታ ድጋፎችንና እርዳታዎችን ያደረገች ሲሆን ሃገራቱ በባህል፣ በስፖርት፣ በትምህርት፣ እንዲሁም በግብርናና በህክምና የሚታዩ ተሞክሮዎች አሏቸው። በወቅቱ በታላላቅ የሩሲያ ደራሲያን የተጻፉ በርከት ያሉ ምርጥ የስነ-ጽሁፍ ስራዎች ተተርጉመው ለኢትዮጵያ አንባቢያን እንዲደርሱ በመደረጉ የንባብ፣ የንግግርና የጽሁፍ ባህልን በኢትዮጵያ በማሳደግ በኩልም የሃገራቱ ግንኙነት ጉልህ ድርሻ ነበረው።

በርካታ ኢትዮጵያውያን በሩሲያ ልዩ ልዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን በሩሲያውያን የሚመራው ባልቻ ሆስፒታልና የሩሲያ የባህልና የሳይንስ ማእከል ለትስስሩ አብነቶች ናቸው።  ከሶቪየት ህብረት መፈረካከስ በኋላ ሩሲያ በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ ላይ ያላት ፍላጎት የቀዘቀዘ ቢመስልም ፕሬዝዳንት ቦሪስ የለሲንን ተክተው ሃገሪቱን እየመሩ ያሉት ቭላድሚር ፑቲን በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸው ግንኙነት አዲስ መልክ ይዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርጉ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።

ሶስቱም ሃገራት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያመሳስሏቸው በርካታ ነገሮች ያሉ ቢሆንም
በዋናነት የሚጠቀሰው  የሀገራት ሉአላዊነትና ክብር መጠበቅ መቻላቸው፤
ከሌሎች ሃገራትና ቅኝ ገዥዎች የሚመጣባቸውን ወረራ መከላከላቸው፤ በከፍተኛ መስዋእትነት ነጻነታቸውን ማግኘታቸው፤ የህዝባቸውን ህይወትና
ብሄራዊ ክብራቸውን በራሳቸው መንገድ ለማስጠበቅና የልማት ውጥናቸውን ለማሳካት ጥረት ማድረጋቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ መመሳሰለ
እና ትብብራቸው የአለም አድራጊ ፈጣሪ ነን ለሚሉት አንዳንድ ምእራባውያን የሚዋጥ አልሆነላቸውም።

የሃገራቱ ህዝቦች እና መሪዎቻቸው “በራሳችሁ እንዲደርስ የማትፈልጉትን በሌሎች ላይ አታድርሱ”
ለሚለው ወርቃማ መርህ በመገዛት አሜሪካ እና የተወሰኑ ምእራባውያን ሀገራት በደሃ ሃገራት ላይ የፈቀዱትን እንዳያደርጉ ከሞራልና
ከታሪክ ተጠያቂነት የሚያድናቸውን እርምጃዎች ከመውሰዳቸውም በላይ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው
ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ሊወሰድ የታሰበውን ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ በመቃወም የሁልጊዜ አጋርነታቸውን ለአለም አሳይተዋል፡፡

ሶስቱም ሀገራት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና የህግ ማስከበር ዘመቻን
ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ በሰብአዊ እርዳታ ሽፋን ኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ጫናዎችን እንደማይቀበሉና ኢትዮጵያም የውስጥ
ችግሮቿን በራሷ መንገድ የመፍታት ተሞክሮም አቅሙም እንዳላት በተደጋጋሚ በመግለጽ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories