ኢትዮጵያ የፋና ቴሌቪዥን ንብረት አይደለችም። የዜጎቿ እንጂ። ለሀገር ጠንቅ የሆነውን ስህተቱንም በጋዜጠኝነት ሙያዊ አተያይ መተቸት ግዴታየ ነው። የጋዜጠኝነት ውግንናው ለህዝብ ነውና ጣቢያው እልቂትን ለማስወገድ በሚል ያሰራጨው ይዘት ለተቃራኒው ውጤት የሚዳርግ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
ፋና ፋውል የሰራው በማን ላይ ነው? ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ “ኢላማውን ስቶ በራሱ የገቢ ምንጮች እና በራሱ አመራሮች ቆይታ ላይ ቃታ የሳበ ያህል ቀዩን ተላልፏል።” ተብሎ ሊመለስ ይችላል።
“ግጭት መቀነስ” harm minimization የሚለው የኤዲቶሪያል መርህ በተለይም በኢትዮጵያ ሚዲያዎች ቀዳሚው የይዘት መረጣ ሚዛን ነው። የዚህ መርህ ጥሰት የሚያመጣው ቀውስ ከፍተኛ መሆኑም ቢታመንም ፋና ቴሌቪዥን በቅርቡ ያሰራጨውና አሁን ላይ ከዲጂታል ማድረሻዎቹ ዝርዝር የማይገኘው ቪዲዮ ቀዩን መስመር ተላልፏል።
ፋና ብሮድካስት “በኃይማኖት ካባ የሽብር ተግባር” በሚል ርዕስ ባስተላለፈው ቪዲዮው ከደቂቃ 4 እስከ 5 ተኩል ገደማ ድረስ ሽብርተኝነትንና ፅንፈኝነትን በተለይም ፋና በኢትዮጵያ “ተደገሰ” ላለው ስጋት የሁለት ሰዎች ንግግርን በማሳያ ማስረጃነት አቅርቧል። በዚህም አንድ ወጣት በአማርኛ ቋንቋ (በቲክቶክ የቀረበ ቪዲዮ የሚመስል) ሙስሊሞችን ለበቀል ርምጃ ሲቀሰቅስ ይታያል። በመቀጠል ደግሞ ማንነቱ በምስል የማይታይ ሰው አሁንም ሙስሊሙን ለጥቃት ሲቀሰቅስ ይደመጣል። ሁለቱም ሰዎች ሙስሊም ስለመሆናቸው አመላካች የለም።
(ማንነታቸው ያልታወቀ) የሁለት ሰዎችን የበቀል ቅስቀሳ ተከትሎ የሚታየው ኡስታዝ አቡበክር ነው። የኡስታዝ አቡበክር ንግግር ይዘት ከሁለቱ ሰዎች በተቃራኒው ነው። ፋና ያሰራጨው ቪዲዮ ግን ሁለቱ ሰዎችና ኡስታዝ አቡበክር በይዘት ተመሳሳይ ቅስቀሳ አለማድረጋቸውን ነጥሎ ለማስቀመጥ ድንበር አለበጀላቸውም። የኡስታዙን ንግግር በእማሬው ይሁን ፍካሬ ፍቹ ብቻ ግን በፕሮዳክሽኑ የቅርፅ አደረጃጀት ውስጥ ከሁለቱ ሰዎች የበቀል ቅስቀሳ ጋር በአንድ ፈርጅ ተመድቦ ቀርቧል።
እኩይ ተግባራት ከአንድ ማህበረሰብ የሚመነጭ የሚያስመስለው አቀራረቡ የፋና ብሮድካስት ቪዲዮ ሌላኛ አደጋ ነው። ይህ ደግሞ በተለያየ ማንነት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ርስ በርሳቸው ጣት እንዲቀሳሰሩ ብሎም አጥፊ ወደ ሆነ ደረጃ ግፊት የሚፈጥር የተንጋደደ አቀራረብ ነው።
“ጉዳትን መቀነስ” የሚለውን የኤዲቶሪያል ቀይ መስመር በመተላለፍ የፋና ብሮድካስቱ ፋና ቴሌቪዥን አደገኛ ፀረ ሀገር ፋውል ፈፅሟል።
ፋና ቀይ ካርድ ይሰጠዋል አያሰጠውም የሚሉ ውዝግቦች የኢንስትራክተሩን ውሳኔ ይጠብቃሉ።
እስሌማን ዓባይ #የዓባይልጅ