ከ60 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ግብፅን ስታሸንፍ እንዲህ ሆኖ ነበር፡ የ ‘ያ ትውልድ’ ትውስታ

ሐሙስ ሰኔ 02/2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በግብፅ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የተካሄደው ጨዋታ መነጋገሪ ሆኖ፣ ለኢትዮጵያውያን ደስታን ለግብፆች ደግሞ ድንጋጤን ፈጥሯል።

በማላዊ ሜዳ፣ ኢትዮጵያ በከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ በግብፅ ላይ ድል መቀዳጀቷ ያላስደነቀው የለም።

በተለይም በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ኳስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ‘የቅርብ ወዳጅ’ ነበረች ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ድንቅ ግቦች፣ ድንቅ የግብ ሙከራዎችም አሳይተዋል።

ድሉ የብሔራዊ ቡድኑን ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን ተቀናቃኟን ግብፅም ሳያስገርም አልቀረም።

በፊፋ የኳስ ብቃት መዝገብ ግብፅ 32ኛ ኢትዮጵያ 140ኛ መሆኗን አንዘንጋ።

ታዲያ ትላንት ምን ዓይነት ተዓምራዊ ቀን ነበር?

ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት 60 ዓመታት ወደኋላ እንሂድ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በታሪኩ ለመጨረሻ ጊዜ የግብፅ ብሔራዊ ቡድንን በሁለት ግብ ልዩነት የረታው በ1954 ዓ.ም. ነው። በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ።

60 ዓመታት ወደኋላ. . .

ለኢትዮጵያዊ ኳስ አፍቃሪ ግብፅን ከመርታት በላይ ምን ያስደስተዋል? ምንም።

የትላንቱን ዓይነት ድል ለማጣጣም ግን ምስኪኑ የኢትዮጵያ ኳስ ወዳጅ 60 ዓመታት ጠብቋል።

ያለ አኩሪ ድሎች፤ ፀሐይ፣ ዝናብ፣ ሰልፍ ወዘተ. . . ሳይበግረው ብሔራዊ ቡድኑን በመደገፍ ኢትዮጵያዊ አቻ ይኖረው ይሆን?

ለማንኛውም 60 ዓመታት ወደኋላ እንጓዝና የእነ መላኩ ተገኝ (ዶ/ር) ቤት ጎራ እንበል።

የኢሕአፓው መላኩ ያኔ ገና ፖለቲከኛ አልሆነም ነበር።

በሰንጋ ተራው ቤታቸው የኢትዮጵያ ራድዮ ተከፍቷል።

ቤተሰቡ ተሰብስቧል። የሰፈር ልጆችም ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል።

ሰለሞን ተሰማ ኳሷን እግር በእግር እየተከተለ ይተርካል።

ኢትዮጵያ ግብፅን ስትገጥም ነፍስ ውጪ ነፍስ ጊቢ ነበር።

መላኩ የዚያን ቀኑን ጨዋታ፣ በተለይ ግቦቹን ደቂቃ በደቂቃ ያስታውሳል።

የግብፅ ቡድን አንደኛና ሁለተኛ የአፍሪካ ዋንጫን ያሸነፈና የሚፈራ ቡድን ነበር።

በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታ ኡጋንዳን አሸንፎ ኢትዮጵያን ገጠመ።

ግጥሚያውን መላኩ እንዲህ ያስታውሳል. . .

“. . . ግብፆች ልምምድ ላይ ሲታዩ ፍጥነታቸው በጣም ያስፈራ ነበር። መቼም ኢትዮጵያ ዛሬ ካሸነፈች ተዓምር ነው ነበር የሚባለው። ጨዋታው እንደተጀመረ ሕዝቡ በጣም እየጮኸ ድጋፍ ይሰጥ ነበር። የመጀመሪያውን ጎል እንደተፈሩት ግብፆች አገቡ። ለረዥም ደቂቃ ጨዋታው አንድ ለባዶ ቀጠለ። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ኢትዮጵያ አገባችና አንድ ለአንድ ሆኑ።

“. . . ተክሌ ነበር ያገባው። የድሬ ዳዋው ኮተን ክለብ ተጫዋቹ፣ 7 ቁጥሩ ግርማ በእረፍት ተቀይሮ የቴሌው ተክሌ ገብቶ ነው ጎል ያስቆጠረው። ተክሌ ሲያገባ አገሩ ተገለባበጠ። የነበረው ደስታ ይህ ነው አይባልም። ትንሽ ቆይተው ግብፆች አገቡ። ጠሃ የሚባል ጎበዝ ተጫዋች ነበር ያገባው። በእኛ በኩል አሁንስ ‘ተስፋ የለም’ ተባለ። ግን እስከ መጨረሻው ድረስ ሕዝቡ በድጋፍ ይጮሀል፤ ያበረታታል።

በ1950ዎቹ አጋማሽ 3ኛውን የአፍሪካዋ ዋንጫ ያሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን
የምስሉ መግለጫ,በ1950ዎቹ አጋማሽ 3ኛውን የአፍሪካዋ ዋንጫ ያሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን

“. . . ጨዋታው ሊያልቅ 7 ደቂቃ ሲቀረው ሰው ሁሉ አዝኖ ነበር። ለግብፅ ቡድን የመልስ ምት ልትሆን የምትችል ኳስ ነበረች። 11 ቁጥሩ ጌታቸው ወልዴ እንደ ምንም ሮጦ ወደ ውጭ እንዳትወጣ ያጠፋትን ኳስ ሉቻኖ ደርሶ አገባት። ስታዲየሙ ተገለባበጠ! ከዚያ 2 ለ 2 ሆኑና 30 ደቂቃ ተጨመረ።

“. . . ያኔ የሕዝቡ ሞራል ጨመረ። ጩኸቱ በረታ። ሦስተኛዋን ጎል ያገባው የሉቻኖ ወንድም ኢታሎ ነው። ኢትዮጵያ ባገባች ቁጥር ከቤት መንገድ ድረስ ወጥተን እንጨፍራለን። ቤት ተመልሰን ደግሞ ራድዮ እናዳምጣለን። ኢታሎ ካገባ በኋላ ደስታ በደስታ ሆንን። ‘እነዚህ ሰዎች ተመልሰው እንዳያገቡ’ ‘አይዟችሁ’ ‘ዲፌንሱ’ የማይል ሰው አልነበረም።

“. . . ጨዋታው ሊያልቅ 5 ደቂቃ ሲቀረው መንግሥቱ ወርቁ ኳሷን ወሰደና፣ ብቻውን ሦስት አራት ተጫዋቾች አልፎ፣ ጎል አገባ። ያኔ የኢትዮጵያ ቡድን ማሸረፉ እርግጥ ሆነ። መንግሥቱ ራሱ ጎሉ ውስጥ ገብቶ ገመዱ ላይ ተንጠልጥሎ ጮኸ። መረቡ እጁን ቆርጦት እንኳ በደስታ ብዛት ህመሙ አልተሰማውም ነበር። በጣም ከፍተኛ ትዝታ ያለው ጨዋታ ነው። በጣም አስደናቂ ነበር።”

መላኩ ስለዚህ ግጥሚያ ሲያወራ ድምጹ ውስጥ 60 ዓመታት የተሻገረ ደስታ ይሰማል።

ጨዋታውን ስታዲየም ገብቶ አለማየቱ በጣም ይቆጨዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብፅን አሸንፎ የአፍሪካ ዋንጫን አነሳ። ከሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወዲህ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ዋንጫ በልታ አታውቅም።

እንዲያውም ግብፅን ካሸነፉ በኋላ ‘የማይበገሩት’ ተብለው እንደነበር መላኩ ያስታውሳል።

እስከ አምስተኛ የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ ቡድኑ በየሄደበት እያሸነፈ ይመለስም ነበር።

ኬንያ ሄደው ሲጫወቱ ኢታሎ ከተሰበረ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ‘ቀውስ ውስጥ ገባ’ ይላል መላኩ።

“ኳስን በቁም ነገር የያዝኩት ከዚያ ጨዋታ በኋላ ነው”

ወደ እግር ኳስ መሳብ

መላኩ ከ1954ቱ ጨዋታ በኋላ እግር ኳስን እንደ ሙያ በቁም ነገር መውሰድ እንደጀመረ ይናገራል።

ከሕጻንነቱ ጀምሮ ኳስ ይጫወት ነበር።

‘ብቸኛው የምናውቀው ጨዋታ’ የሚለውን እግር ኳስ ከመንደር ጨዋታ ባለፈ እንደ ሙያ ማየት የጀመረው ኢትዮጵያ ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ስትበላ ነው።

“እነዚህን ተጫዋቾች ለወደፊት የሚተካ መኖር አለበት በሚል ስሌት፣ ከመንደር ቡድን ወጥቼ መደበኛ የሆነ ቡድን ውስጥ መግባት አለብኝ ብዬ ራሴን አዘጋጅቼ እግር ኳስን በቁም ነገር የወሰድኩት ከዚያ በኋላ ነው። ትልቅ መነሳሳት የፈጠረ ነበር።”

ያኔ የአዲስ አበባ ልጆች በየሰፈራቸው የሚወዳደሩባቸው የሮተሪ ክለብ ሜዳዎች ነበሩ።

የእነ መላኩ ቡድን ‘ጥሩ’ ከሚባሉት ይጠቀሳል።

እንዲያውም አንድ ጊዜ ሲጫወቱ ይድነቃቸው ተሰማ አይተዋቸው “ሁሉንም እፈልጋቸዋልሁ” ብለው እንደነበር ያስታውሳል።

መላኩ እና አምስት ጓደኞቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን ተቀላቀሉ።

የገቡ ቀን የመጀመሪያውን ፎቶ ያነሷቸው ይድነቃቸው ነበሩ።

ያኔ ኳስ ተጫዋች ስታዲየም መግቢያ ትኬት በነጻ ይሰጠዋል። እነ መላኩም የድርሻቸውን ወሰዱ።

መላኩ ያሰበበት ሳይደርስ የሰፈር ሽማግሌዎች ቤታቸው ሄደው “ከጊዮርጊስ ወጥተህ የሰፈርህ ልጆች ያሉበት ‘ፈጣን ክለብ’ ግባ” አሉት።

ጫና ሲያሳድሩበት ከጊዮርጊስ ወጥቶ ፈጣን ገባ። ፈጣን ግን ደካማ ክለብ ነበር።

ጊዮርጊስ የቀጠሉ ጓደኞቹ የደረሱበት መድረስም ፈታኝ ሆነ።

ከዚያ የገባበት ዳኛው ክለብም ‘ችሎታ የሌላቸው የሚሰለፉበት’ ስለነበር ጥሎት ወጣ።

አለማያ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ ለድሬ ዳዋ ምድር ባቡር ክለብ ተጫውቷል።

ፖለቲካ ውስጥ እስከገባበት ጊዜ ድረስ ከትምህር ቀጥሎ ሕይወቱ ኳስ እንደነበር ይናገራል። ጎበዝ ኳስ ተጫዋችም ነበር።

ግብፅን ማሸነፍ ምን ምን ይላል?

ከግብፅ ጋር የሚደረግ ግጥሚያ ኳሳዊ ብቻ አይደለም። ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ተፈጥሮ ሀብታዊም ቀለም አለው።

ያኔ የግብፅ መንግሥት የኤርትራን ተቃዋሚዎች ይረዳ እንደነበርና እንዲያውም ኤኤልኤፍ መጀመሪያ የተቋቋመው ካይሮ እንደሆነ የሚጠቅሰው መላኩ፣ ከግብፅ ጋር የሚደረግ ፉክክር ፖለቲካዊ ገጽታው ይታየዋል።

ቀድሞ ኢትዮጵያ ጳጳስ ይሾምላት የነበረው ከአሌክሳንድሪያ መሆኑም ሳይጠቀስ አይታለፍም።

ይባስ ብሎ ግብፆች ዓባይን በተመለከተ ‘እኛ ብቻ እንጠቀምበት’ የሚመስል አቋም ያንጸባርቃሉ።

ሌላው ትችት ‘አፍሪካ ላይ ንቀት ያሳያሉ፣ ዘረኝነት ይታይባቸዋል’ የሚለው ነው።

በእነዚህና ሌሎችም ምክንያቶች ግብፅ የኢትዮጵያ ‘ወዳጅ አይደለችም’ ሲሉ ኢትዮጵያውያን ይደመጣሉ።

የትላንቱ ድል

ተሾመ ቀዲዳ ለ30 ዓመታት የስፓርት ጋዜጠኛ እና ተንታኝ ሆኖ ሰርቷል።

የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ በሦስት አገሮች መካከል በሱዳን ተካሂዶ ግብፅ ኢትዮጵያን 4 ለ 0 ማሸነፏን ያወሳል።

ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ በአገሯ ስታስቀር፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዋንጫውን ለአምበሉ ኢታኖ ቫሳሎ አስረክበዋል።

“ከዚያ ዘመን በኋላ ኢትዮጵያውያን ከኳስ ጋር ያላቸው ቁርኝት ጨመረ” ይላል ጋዜጠኛው።

ግብፅ ከመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ አንስቶ እስካሁን 10 ጊዜ ለዋንጫ ቀርባ 7 ጊዜ ወስዳለች።

ኢትዮጵያ ከ1954ቱ ግጥሚያ ወዲህ ግብፅን አሸንፋ አታውቅም።

አንድ ጊዜ ግን የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ቡድን የግብፅ አቻውን 5 ለ 0 አሸንፎ፣ ግብፅ በንዴት አሠልጣኟን ማባረሯን ተሾመ ያስታውሳል።

ወደ ትላንቱ አስገራሚ ጨዋታ እንመለስ . . .

ተሾመም በድሉ ተደንቋል። እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ግብፆች ያገባሉ ብሎ መጠበቁን አይክድም።

ዛሬ የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ‘እንዴት 2 ለ 0 ታሸንፈናለች!?’ ብለው ቁጣቸውን ሲገልጹ መዋላቸውን ይጠቅሳል።

ታዲያ ድሉ እንዴት መጣ?

“. . . መሐመድ ሳላህ ተገኘም አልተገኘም እኛ እናሸንፋለን ብለው ነበር አሠልጣኙ። ተጫዋቾቹም ይህንን ሰንቀው ነው የሄዱት። ከዚያማ የመጀመሪያውን ግብ በ21ኛው ደቂቃ፣ ሁለተኛውን በ40ኛው ደቂቃ አገባን። ይሄ ማለት ተጫዋቾቹ ከአሠልጣኛቸው ጋር አንድ ሆነው፣ አገራቸውን እና ሕዝባቸውን ታሳቢ አድርገው እናሸንፋለን ብለው በወኔ ነው የገቡት ማለት ነው። ምስጢሩ ይሄ  ነው።”

ኃያሏ ግብፅ ግን በ ‘እናሸንፋለን’ ወኔ ብቻ ትረታለች?

“. . . ደካማ ቡድን ነው ኢትዮጵያን በቀላሉ እናሸንፋታለን ብለው ነበር። ሜዳ ሲገቡ ግን ሌላ ታሪክ ተፈጠረ። በተከታታይ ሲገባባቸውና የእኛ ልጆች አይለው ሲጫወቱ ተደናግጠዋል። ደግሞ ግብፆች ቀልድ አያውቁም። የፈለገ ኃያል ቡድን ውጤቱ ሲቀየር ይደናገጣል። ትላንት ግብፆች ወደ መጨረሻ ላይ በመደናገጥ ኳስ መያዝ አቅቷቸው ነበር።

ኢትዮጵያ ለ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከማላዊ፣ ከጊኒ እና ከግብፅ ጋር የተመደበችበትን ቡድን መምራት ጀምራለች።

ከዚህ ቀደም በማላዊ 2 ለ 1 ተሸንፋለች።

ለወደፊትስ ምን ይጠብቃት ይሆን?

ተሾመ እንደሚለው፣ ግብፅን ማሸነፍ ታላቅ የሞራል ስንቅ ይሆናቸዋል። ምናልባትም ቀጣይ ድሎች ይመዘገቡ ይሆናል. . .

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories