
✍️ Getahun Heramo
ኬሪ ቤቲ ሙራንጋይ በዜግነት ኬንያዊት ነች፣ በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኤክስፐርቶች ቡድን ሊ/መንበር እንደመሆኗ፣ በአሁኑ ወቅት በጄኔቭ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግስታት አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመውን ሪፖርት በዋናነት የቀመመችው እሷ ነች። ይህች ሴት ገና ከማለደው ጀምሮ ለትህነግ ወግና ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲገባ አፅንኦት ሰጥታ ስትወተውት ነበር። ለዚህም አፕሪል 2 2021 ላይ በራሷ የቲውተር ገፅ ላይ “If there was ever time for application of R2P, it is now.” በማለት የለጠፈችውን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል። ሌሎች ልጥፎቿንም ከሥር ካሰፈርኩት ምስል መመልከት ይቻላል(ምስሉን ያገኘሁት ከ”Esleman Abay” ገፅ ነው) ሴትየዋ ለትህነግ ባላት ውግንና በፀረ-ኢትዮጵያዊ አቋማቸው በሚታወቁ በእነ ራሺድ አብዲ ዓይነት አክቲቪስቶች ዘንድ “Compatriot” ተብላም ተሞካሽታለች።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊያን አክቲቪስቶች የካሪ ቤቲ ሙራንጋይን የከረመ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋሟንና የትህነግ ውግንናዋን ማጋለጥ በመጀመራቸው ሴትየዋ በቲውተር ገጿ የለጠፈችውን በሙሉ አጥፍታና ገጿን አምክና(Deactivate አድርጋ) ተሰውራለች። ካሪ ቤቲ በግልፅ ለትህነግ ያላትን ውግንና የሚያሳብቁ ልጥፎቿን መሰረዟ በራሱ የሚያስተላልፈው መልዕክት አለ። ከላይ እንደጠቀስኩላችሁ ኬንያዊቷ ካሪ ቤቲ በ"R2P" መርህ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዲተገበር በቲውተር ገጿ ይፋ ካደረጋች ከወራት በኋላ የትህነጉ አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳም The African Report ላይ በዲሴምበር 21,2021 "Ethiopia: UN Commission is a Victory for the Cause of Justice and Accountability" በሚል ርዕስ ሥር የ"R2P" መርህ ሳይተገበር በመዘግየቱ "...justice delayed is justice denied." የሚለውን ጥቅስ በብስጭት ለመጥቀስ ተገድዶ ነበር። ይህ ካሪ ቤቲም ሆነች ጌታቸው ረዳ በኢትዮጵያ ላይ ይተገበር ዘንድ ቀን ከሌት የሚማፀኑት የ"R2P" መርህ ምን ይሆን?
R2P..Responsibility to Protect...የተባበሩት መንግስታት በሰው ልጆች ላይ የዘር ፍጅት፣ ጄኖሳይድ፣ የጦር ወንጀሎችና የሰብዓዊ ቀውሶች ጥቃቶች በሚፈፀሙበት ወቅት ተጠቂዎቹን እስከ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በሚደርስ እርምጃ የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት የሚያስገነዝብ መርህ ነው። ታዲያ የ"R2P" መርህ ተፈፃሚ በሚሆንበት ወቅት የተባበሩት መንግስታት ቻርተር ዘብ የሚቆምለትን የሉዓላዊነት አጥር እስከመጣስ ይደረሳል። ይህ መርህ በተባበሩት መንግስታት የፀደቀው እ.ኤ.አ በ20ዐ5 ዓ.ም. ነው። ጌታቸው ረዳ በኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋቱ የሉዓላዊነት ፅንሰ ሐሳብ ስለመሆኑ በፅሁፉ አምርሮ ገልጿል፤ እውነት ነው፤ የR2P ጣልቃ ገብነት መርህና የተባበሩት መንግስታት የተቋቋመበት የአባል ሀገራትን ሉዓላዊነት የማስከበር መርህ በእርስ የሚጣረሱ ፅንሰ ሐሳቦች ይመስላሉ። ጌታቸው ረዳ የተባበሩት መንግስታት የሉዓላዊነት መርሁን አለዝቦ የ"R2P" መርህን ይተገብር ዘንድ በፅሁፉ ያቀረበው መከራከሪያ አለ። የሙግቱ ይዘት ይህን ይመስላል፦
“Those that objected to the resolution couched their objection in terms of its inconsistency with the principle of state sovereignty. In reality, the invocation of sovereignty cannot serve as an all-purpose defense against external scrutiny of a state’s actions within its domestic jurisdiction. This rigid interpretation of sovereignty is radically at odds with normative shifts that have taken place in the international system over the past 3 decades, particularly with regards to the principle of responsibility to protect (R2P).”
ለጌታቸው ረዳ ለሉዓላዊነት ፅንሰ ሐሳብ ግትር ሆኖ መገዛት ኋላ ቀሪነት ነው፤ ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህም በሉዓላዊነት ፅንሰ ሐሳብ ላይ የሙጢኝ ብሎ ከጣልቃ ገብነት መታቀብ ጊዜ ያለፈበት አስተሳሰብ ነው በማለትም ለመሞገት ይሞክራል። እውነታው ግን ከዚህ ይለያል።
ጌታቸው ረዳም ሆነ ኬንያዊቷ አፍቃሪ-ትህነግ ካሪ ቤቲ አሁን ባለው ነባራዊ እውነታ የ”R2P” መርህ በራሱ ከፍተኛ የትግበራ እክል እንደገጠመው ለመገንዘብ የዘገዩ ይመስላል። የተባበሩት መንግስታት አንዳንድ አባል ሀገራት ኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቱ እንዳይተገበር የሚቃወሙት ለሉዓላዊነት ካላቸው አቋም ብቻ ሳይሆን በታሪክ ውስጥ በስመ “R2P” መርህ በምዕራባውያን የሚደረገው ጣልቃ ገብነት ለከትየለሽ በመሆኑም ጭምር ነው። ስለዚህም በአሁኑ ወቅት በስመ “R2P” ጣልቃ መግባት ጋዜ ያለፈበት አካሄድ ወደ መሆን እያዘነበለ ነው፤ ራሳቸውን ከወቅቱ ሁኔታ ጋር “Update” ያላረጉት በኢትዮጵያ ላይ ጣልቃ ገብነቱ ዕውን እንዳይሆን የተቃወሙ ሀገራት ሳይሆኑ ጌታቸው ረዳና ካሪ ቤቲ ናቸው።
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በአሁኑ ነባራዊ ሁኔታ የ”R2P” መርህ ትግበራ በራሱ ፈተና ላይ ወድቋል። ለዚህም “R2P” በተባበሩት መንግስታት እ ኤ አ በ2005 ከፀደቀ በኋላ የፎረሸባቸውን ሁለት ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፤ (One can call such assessment…pragmatic evaluation of R2P principle)። የመጀመሪያው የሊቢያ የ2011(እ ኤ አ) የኔቶ ወረራ ሲሆን ሁለተኛው የሶሪያው የ2012(እ.ኤ.አ.) የእርስ በእርስ ዕልቂትና ስደት ነው። እስቲ ሁለቱንም ዓለም አቀፍ ሁነቶች ለየብቻ እንመልከታቸው።
የተባበሩት መንግስታት ኔቶ በአሜሪካ ፣ በእንግሊዝና በፈረንሳይ አጋፋሪነት ሊቢያን እንዲወራት የይለፍ ፈቃዱን የሰጠው በ”R2P” መርህ ነው። እናም የወቅቱ የአሜሪካ መሪ ባራክ ኦቦማ፣ ሂላሪ ክሊንተንና የኔቶ መሪ ካናዳዊው ሻርል ቡሻር ሊቢያን በአየር ድብደባ ዶግ አመድ ከማድረጋቸው በፊት የጣልቃ ገብነታቸው ብቸኛው ሰበብ “Responsiblity to Protect” የሚል ነበር። ከላይ ስማቸውን የጠቀስኳቸው የአሜሪካና የኔቶ ባለሥልጣናት ከ”R2P” ግብና ዓላማ ውጭ የመንግስት ግልበጣና የሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ላይ እጃቸው እንደማይኖር መተማማኛ እስከመስጠት ደርሰው ነበር። ነገር ግን በገሃድ የሆነው ኔቶ በሊቢያ ከ”R2P” መርህም በዘለለ ጋዳፊን ከሥልጣን የማስወገድ ድብቅ ዓላማ እንደነበረው ያሳበቀ ነበር። የአሜሪካና የእንግሊዝ ወታደሮች ለአማፂያን ወታደራዊ ሥልጠና ከመስጠትና የጦር መሳሪያን ከማስታጠቅ ባለፈ በውጊያውም ተሳታፊ እንደነበሩ የሚያመላክቱ አያሌ መረጃዎች ነበሩ፤ የማታ ማታም የሊቢያ ሉዓላዊነት መቀመቅ ወርዶ በጥቂቱም በሊቢያ የውስጥ ጉዳይ ከ12 ሀገራት በላይ እጃቸውን ለመክተት
በቁ(በዚህ ጉዳይ ቀደም ሲል ዘርዘር ያለ ፅሁፍ ማካፈሌን አስታውሳለሁ።) ይህ ሁሉ የሆነው ግን በስመ “R2P” ነው። እናም ኦባማ ዋሽቷል፣ ሂላሪ ክሊንተንም ዋሽታለች፤ ሌተናል ጄኔራል ቡሻርም ዋሽቷል። ከነዚህ ውስጥ ቢያንስ ኦቦማ ከሥልጣኑ በወረደ ማግስት በሊቢያ ላይ በወሰነው ውሳኔ ተፀፅቷል። በ”R2P” ሰበብ የተጀመረው ጦርነት የሊቢያን ሉዓላዊነት በማፈራረስ በመጠናቀቁ ነው ኦባማ በውሳኔው የተቆጨው። በእርግጥ ከውሳኔው ጀርባ ከሂላሪ ክሊንተን በተጨማሪ የሱዛን ራይስና የሳማንታ ፓዋር ስውር እጆች እንደነበሩ ይነገራል። እናም ጌቾ እነ ቻይናና ራሺያ በስመ “R2P” እነ አሜሪካ የሚፈፅሙትን ደባ ቢቃወሙ…30 ዓመታት ያህል ወደ ኋላ ቀርታችኋል… በማለት መውቀሱ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት ያለው አይደለም። እነርሱ ጣልቃ ገብነቱን መቃወማቸው የሚጠቅመው ኢትዮጵያን ነው፤ ቢያንስ ውሳኔአቸው ኢትዮጵያ እንደ ሊቢያ እንዳትፈራርስ ያግዘታል። በእርግጥ ይህ ኢትዮጵያን ከመፈራረስ መታደጉ ቀደም ሲል….እስከ ሲዖልም ድረስ ወርደን ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን… ይሉን ለነበሩ መልካም ዜና አይደለም። የነጌታቸው ዓላማ ኢትዮጵያን ማፈራረስ እስከሆነ ድረስ አፈራረሷ እንደ ሊቢያ በአሜሪካ ጣልቃ ገብነትም ሆነ በኔቶ እነርሱ ግድ አይሰጣቸውም። ያም ሆነ ይህ የሊቢያው ወረራ የ”R2P” መርህን ገደል ውስጥ ከከተቱት ዓለም አቀፍ ሁነቶች አንዱ መሆኑ ይሰመርልን። ይህንኑ የሊቢያን ቀውስ ከግምት በማስገባት ብራዚል ለተባበሩት መንግስታት በR2P ላይ አንድ የማሻሻያ ሐሳብ እንዳቀረበች ይነገራል፤ ይኸውም R2P ወደ RWP ይቀየርልን የሚል ነበር…ማለትም ወደ “Responsibility while Protecting!” በነገራችን ላይ አሜሪካ በስመ ሰብዓዊ ጣልቃ ገብነት በሲ አይ ኤ አማካይነት በታሪክ ውስጥ
በብዙ ሀገራት ላይ (በተለይም በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ) የፈፀመችውን ሽፍጥ በማጋለጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች አሜሪካዊያን የፖለቲካና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሐያሲያን ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ዊሊያም ብሉም፣ ሐዋርድ ዚንና ኖኣሚ ቾምሲኪ ተጠቃሽ ናቸው። ከሶስቱም ፀሐፍት የዊሊያም ብሉምን “Killing Hope U.S. Military and CIA Interventions Since World War II, 2004” መፅሐፍ ማንበብ አሜሪካ በስመ ሰብዓዊ ጣልቃ ገብነትና ዲሞክራሲ ከ50 በላይ በሚሆኑ ሀገራት ላይ የሸረበችውን ሴራና በውስጥ ጉዳይ ጓዳ ድረስ ዘልቃ የፈበረከችውን መርዝ ስፋትና ጥልቀት ባለው መልኩ ለመገንዘብ ይረዳል።
“R2P” በትግበራው ሂደት ወገቤን ያለበት ሌላው ዓለም አቀፍ ሁነት የሶሪያው ጦርነት ነው። የሚገርመው በሶሪያ ጦርነት የጦርነት ወንጀሎችና ሰብዓዊ ቀውሶች ቢስተዋሉም “R2P” በተባበሩት መንግስታት አልተተገበረም። ብዙ አጥኚዎች ዘግይቶ የገባቸው የ”R2P” መርህ የሚሰራው እንደ ሊቢያ ላሉ ደካማ ሀገራት መሆኑን ነው። “R2P”ን ፈርጣማ ወታደራዊ ጡንቻና በልዕለ ኃያላን መካከል አሻሚ ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎት ባላቸው ሀገራት ላይ መተግበር የሚታሰብ አይደለም። በሶሪያም ጦርነት “R2P” የገጠመው ፈተና ይኸው ነው። ሶሪያ እንደ ሊቢያ ዘው ተብሎ የሚገባባት ሀገር አይደለችም። ይህ እውነት ለአውስትራሊያው የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦብ ካር ገብቶት ነበር፤ እንደዚህ ነበር ያለው፦ “This is (Syria) militarily strong regime. There isn’t an appetite, and not a budget , in the western world for the sort of intervention that would be involved here.” ለምን ቦብ ካር ብቻ! የR2P ፅንሰ ሐሳብ ቀማሚ እንደሆነ የሚነገርለት ጋሬት ኤቬንስም R2Pን ሶሪያ ላይ መሞከር አደጋ እንዳለው አስምሯል፦ “”Syria has a …a very different geopolitical environment …no Arab League unanimity is in favour of tough action; a long Russian commitment to the Assad regime , and strong Syrian armed forces with a credible air defense system, meaning that any intervention would be difficult and bloody…it is too much now for such renewed consensus to help much now in Syria.” የኦቱዋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፈሰሩ ኤሮል ሜንጅስ ደግሞ እንደዚህ ይላል፦ “Syria is a very hard case for current R2P intervention, due to the tri-level proxy war unfolding there.”
ከሶሪያ ጦርነት አንፃር የ"R2P" መርህን የሚተቹ አጥኚዎቹ የመርሁን ወጥ ያለመሆንን(Inconsistency) በጉልህ ያሳምራሉ። እስቲ አስቡት፦ ለምሣሌ ቻይና ላይ "R2P"ን እንዴት መተግበር ይቻላል? ኔቶም ሆነ አሜሪካ ሊቢያ ገብተው ጋዳፊ ላይ የፈፀሙትን ቻይና ላይ መፈፀም ይችላሉ? ወይም ራሺያ አሁን በዩክሬን ላይ በምታደርገው ጦርነት አሜሪካ በR2P መርህ ወታደሮቿን ዩክሬን ውስጥ ማስፈር ትችላለች? መልሱ "ፈፅሞ" የሚል ነው፤ ምክንያቱም ሩሲያ ሊቢያ አይደለችም። እንኳንስ ሩሲያ ላይ ሶሪያም ላይም አሜራካ የR2P መርህን አልሞከረችውም።
ሲጠቀለል R2P የሚተገበረው በሚሊተሪና በኢኮኖሚ አንፃራዊ ዝቅተኛ አቅም ባላቸው ሀገራት ላይ ብቻ ነው። እናም ጌታቸው ረዳም ሆነ ካሪ ቤቲ ማወቅ ያለባቸው ከሉዓላዊነት ፅንሰ ሐሳብ ይልቅ የ”R2P” ፅንሰ ሐሳብ “Shift” ማድረጉን ነው። “R2P” ከላይ እንደተመለከትነው ኃያላን ሀገራት የታዳጊ ሀገራትን ሉዓላዊነት ለመግፈፍ ሰበብ መሆኑንና ወጥነትን ባለማስተናገዱ ከየአቅጣጫው ሂሶችን ማስተናገድ ከጀመረ አሥር ዓመታት ያህል አልፈዋል። ለዚህም በአስረጅነት ከሥር በዋቢነት የጠቀስኳቸውን መፅሐፍትና መጣጥፎችን ማሰስ ይቻላል።
በመጨረሻም አንድ እውነት ላስቀምጥ፦ በየትኛውም ሀገር ሰብዓዊ ጥቃትና የዘር ፍጅት እንዳይፈፀም ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ የሚደገፍ ነው፤ ሌላ ስውር የጂኦፖለቲካ ዓላማን በጉያው እስካልሸጎጠ ድረስ “R2P”ን የሚቃወም የለም። ከዚህ አንፃር ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ አየርላንድ ፣ የአውሮፓ ሕብረት ግጭቱ በሕወሓት ጠብ ጫሪነት ከተከሰተ ጀምሮ የሚያሳዩት ኢ-ሚዛናዊ ምልክቶች ስውር አጀንዳቸውን የሚያጋልጥ ነው። ለምሣሌ ቀደም ሲል የተባበሩት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(OHRC) እና በዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (EHRC) በጣምራ ባደረጉት ምርመራ የጄኖሳይድን ማስረጃዎችንና ምልክቶችን ያገኙት በትግራይ ውስጥ ሳይሆን በኢትዮጵያ እንደማይካድራ ባሉ አካባቢዎች ነበር። ትግራይ ውስጥ ጄኖሳይድ ስለመፈፀሙ ምንም ማስረጃ እንዳላገኙ ይፋ ከማድረጋቸውም ባለፈ ሪፖርቱ በነአሜሪካ ሳይቀር ተቀባይነትን አግኝቶ ነበር። በእርግጥ ወቅቱ የትህነግ ሠራዊት ወደ አዲስ አበባ እየተቃረበ ስለነበር ምዕራባውያን በወያኔ ድል አይሉት የዕውር ድንብር ተሳክረው ለሪፖርቱ ብዙም ትኩረት አልሰጡም ነበር። ይህ የትህነግ ጉዞ በኢትዮጵያ ጣምራ ጦር የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ተገትቶ የወያኔ ሠራዊት ጀርባውን ለአዲስ አበባ ፊቱን ግን ለመቀሌ ሰጥቶ መፈርጠጥ ሲጀምር ግን ምዕራባውያኑ ከስካራቸው ነቅተው የተውትን የጄኖሳይድ ዜማን “ሪሚክስ” አድርገው ማቀንቀን ጀመሩ…ግልፅ ወገንተኝነትና ኢፍትሐዊነት ዳግም አንሰራራ። ጌታቸው ረዳም በፅሁፉ በዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሚመራውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን(EHRC) እንደ በቀቀን የዶ/ር አብይ መንግሥት የሚለውን ከመድገም ባለፈ ሌላ ሚና እንደሌለው አድርጎ መሳለቅ ጀመረ። እንደዚህ በማለት፦ “The EHRC’s involvement in the joint investigation team (JIT) had seriously undermined the integrity of the investigative process and the credibility of the findings. Indeed, the EHRC’s parroting of the Abiy regime’s prepackaged talking points confirmed the peril of involving a state-appointed entity in the investigation of crimes allegedly committed by the appointing state.” ታዲያ ጌታቸው “EHRC”ን በ-ሚዛናዊነት ከከሰሰው በእጥፍ አስበልጠን እኛም አሜሪካን፣ የአውሮፓ ሕብረትን፣ እንግሊዝን፣ አየርላንድን ጦርነቱ በወያኔ ከተጫረበት ጊዜ ጀምሮ ባሳዩአቸው ይፋዊ ምልክቶች ተንደርድረን በወገንተኝነት የመክሰስ መብታችን የተጠበቀ መሆኑን ጌቾ ሙሉ በሙሉ የዘነጋው ይመስላል። እሱ የ”EHRC”ን ሚዛናዊነት ከጠረጠረበት ልክ በላይ እኛም በዘረዘርኳቸው ሀገራት የሚዘወረውን የ”OHRC”ን ፍትሐዊነት እንጠራጠራለን። እሱ የሉዓላዊነት ትርጓሜ ግትርነትን ባወሳበት መጠን እኛም የ” R2P”ን ትርጓሜ ግትርነትን ለዚያውም ታሪካዊ ማጣቀሻዎች እያነሳን እንሞግታለን። ጌታቸው ረዳ ሌሎች ሀገራትን በሉዓላዊነት ትርጓሜ ግትርነት በከሰሰበት የክስ ወጥመድ እሱ ራሱም የR2P ትርጓሜ ላይ በያዘው ግትር ትርጉም ተይዟል። ቢያንስ በ”R2P” ሰበብ ሉዓላዊነት እንዴት እንደሚገረሰስ ማሳየት አልፈለገም፣ ባለማወቅ ወይም ሆን ብሎ…By ignorance or by omission!
መልካም ቅዳሜ!
ዋቢ መፅሐፍት
- THE OXFORD HANDBOOK OF THE RESPONSIBILITY TO PROTECT Edited by ALEX J. BELLAMY and TIM DUNNE,2016 2. The Question of Intervention: John Stuart Mill and the Responsibility to Protect, Michael W. Doyle, 2015
- Reviewing the Responsibility to Protect Origins, Implementation and Controversies Ramesh Thakur, 2019
4.. THE RESPONSIBILITY TO PROTECT The Evolution of Humanitarian Intervention or a new way of Protecting Human Rights?, 2021 3.Gareth Evans on ‘Responsibility to Protect’ after Libya, Interview with Gareth Evans by Alan Philips for The World Today, October 2012 4. Event Report: Discussion on the Will to Intervene, CIPSBlog, October 1, 2012, accessed October 4, 2012,
- The Battle for Syria’, ABC Four Corners, accessed October 4, 2012
- A critique of the theory and practice of R2P Nicholas Glover Sep 27 2011 (Article)
- The Weakness of the Responsibility to Protect as an International Norm, 2014 by Kim R. Holmes, Ph.D. (Article)
- The Responsibility to Protect doctrine: between criticisms and inconsistencies , Fiammetta Borgia, 2015