▪️የዓባይ፡ልጅ ✍️
ዓለማችን በቀደሙት ዘመናት ያስተናገደቻቸው ስልጣኔዎች ሲወጡ እንዲሁም ሲወድቁ ጠቅለል ያሉ መገለጫዎች እንደታዩባቸው የዘርፉ ልሂቃን ብዙ የከተቡበት ርዕሰ ጉዳይ ነው። በዋናነትም የስልጣኔው መሪ ሀገር/መንግስት የሆነች አንድ ከተማ የአለም ንግድ ማእከል መሆን፤ የሀገሪቷ ገንዘብ አለማቀፍ መገበያያነት፣ የሀገሪቱ አለማቀፍ የንግድ ድርሻ እንዲሁም ወታደራዊ አቅም ተገዳዳሪ የሌለው መሆን ዋነኞች ናቸው። ዶላር፣ ኒዮርክ የአሜሪካ ጦር እና የንግድ ድርሻ በቀደሙት ዘመናት የነበረውን ቦታ እዚጋ ልብ ይሏል።
ዘመነ ጉልቤነቷ የማብቃቱ ማሳያዎች ውስጥም መገበያያ ገንዘቧ ሌላ ተገዳዳሪ ሲመጣበት፤ የሃያል ጦሯ አስፈሪነት መቀነስ፤ የንግድ አለማቀፍ ድርሻዋ ብልጫ ሲወሰደበት ተያያዥ ዝለቶች ምልክት ይሆናሉ ማለት ነው።
▪️አሜሪካ መራሹ የአለም አሰላለፍና ዘመነ ክስመት
ዓለማችን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ በመጣችበት የአንድ ሀገር የበላይነት አትቀጥልም” በማለት በርካታ መሪዎች ሲናገሩ ይደመጥ ነበር። ሩሲያ ቻይና የተለያዩ የእስያ ላቲን አሜሪካና ጥቂት አፍሪካዊ መሪዎች ይህን ሲያስተጋቡት ይገኛል። የቱርኩ መሪም ከዚህ ውስጥ ነበሩ።
ይሁንና ሩሲያ ከተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በታገደችበት ድምፀ ውሳኔ ውስጥ ቱርክ ከቃሏ በተቃራኒው ድምፅ ሰጥታለች። ኤርዶጋን የትኛውንም ቀጣናዊ ስሌት ቢቀምር ተመድን በተመለከተ ሲናገሩ የነበረውን የመረረ ተቃውሞ ላስታወሰ ዛሬ የሰጡት ፀረ ሩሲያ ደምፅ ከሀገራዊ ጥቅማቸው ቢመዘን ውሃ የማንሳቱ ነገር ግን ሊያሳምን አይችልም።
ሩስያን ከተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አባልነት ለማስወጣት በተደረገ ድምፅ አሰጣጥ ላይ 93 ድጋፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ 24 ተቃውሞ እና 58 ተአቅቦ በማግኘት ሩሲያ እንድትታገድ የሚያደርግ አብላጫ ድምፅ ተመዝግቧል። የእገዳውን ድምፅ ከሰጡ ሀገራት በተለይም ኤርዶጋን የተካተቱበት መሆኑ በርግጥም የዩክሬይን ቀውስ የአለምን አሰላለፍ ብቻም ሳይሆን እንደ አለት የጠነከረ ሲባልላቸው የነበሩ ሀገራትን ፖሊሲ እንደ ቃሪያ መልክ መለወጥ ጀምሯል።
“ዓለም ከአምስት ሀገራት ተፅዕኖ በላይ ግዙፍ ናት” በማለት
የቱርኩ መሪ ጣይብ ኤርዶጋን በቅርቡ በአህጉረ አፍሪካ ጉብኝታቸው ወቅት ድጋሚ አንፀባርቀውት ነበር።
ኤርዶጋን አክለውም አፍሪካ በተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ማግኘት ሲገባት ውክልና እንዳይኖራት መሆኑ ተመድ ውስጥ ከፍተኛ ኢ-ፍትሃዊ አሰራር የመኖሩ ማሳያ ነው።” ሲሉ ነበር ኤርዶጋን የሚታወቁት።
▪️ተመድ ላይ አዲስ ተገዳዳሪ ወይም ሌላ ተመድ?
ሊግ ኦፍ ኔሽንስ(በህይወት የሌለ ተቋም) የመጀመሪያ ስብሰባውን በጄኔቭ ያደረገበት 101ኛ ዘመን ያስቆጠረበት የያዝነው አመት፣ የአለም ህዝብ አንድ ኮርስ ሰልጥኖ የጨረሰበት ከመሆኑ ጋር ተገጣጥሟል ቢባል አልተጋነነም። ይኸውም አሜሪካ መራሽ ሰሰለሆነው UN የተባለ “የምእራባዊያን አክሲዮን ማህበር” ከሁሉም የአለም ኮርነሮች የሚስተጋቡ ድምፆችን ላዳመጠ ምድራችን “የተመድ ቅኝ አገዛዝ – 101” ተብሎ ሊጠራ የሚችለውን ኮርስ ያጠናቀቀችበት ነው ሊባል ይችላል።
ድርጅቱ በአንደኛው አለም ጦርነት መገባደጃ ላይ ሲቋቋም ሰላም ያመጣልናል ተብሎለት ነበር። ይሁን እንጂ በሁለት የአለም ጦርነቶች መሀል በተቆጠረው እድሜው ከ1913 እስከ 1939/1920-1946) ከ26 አመታት በኋላ ሥራና ኃላፊነቱን ለተመድ አስረክቦ እንዲከስም ሲሆን አንዳች ነገር ሳይፈይድ የመሆኑ እውነታ ሁሉንም ያስማማል።
ለአብነትም ናዚ ጀርመን ሩሲያን፣ ጃፓን ቻይናን እንዲሁም ጣልያን ኢትዮጵያን ሲወርሩ ሊግ ኦፍ ኔሽን ሃላፊነቱን አልተወጣም። መርሆችንም አላስከበረም ነበር። ተቋሙ የጉልበተኞች አክሲዮን ነው የሚለው ትልቁ ትችት የነበረውም ከመሰል ገፅታዎቹ በመነጨ ነበር።
ፋሺስት ኢጣሊያ ሃገራችንን ሲወር አባል የሆንበት የመንግስታቱ ማህበር ማዕቀብ የመጣል ሀሃላፊነት ቢኖርበትም ድርጊቱን እንኳን ለመቃወም አልፈቀደም ነበር። ይባስ ብሎ ጣልያን ከናዚ ጀርመን ጋር ያላትን ትብብር የምታቋርጥ ከሆነ ኢትዮጵያን በስጦታ ሊለቁላት እንደሚችሉ ማህበሩን የሚዘውሩት እንግሊዞች ቃል ገብተውላቸው ነበር( “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ ቁ-2 ላይ እንደሰፈረው።) በወቅቱ ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ በሊጎፍ ኔሽን ያስደመጡት ንግግር የተቋሙን የመፍረስ ፍፃሜ ያመላከተ ሆኖ በታሪክ ይወሳል።
የሶማሊያን ወረራ በዝምታ ያለፈው ደግሞ የዛሬው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ነው፡፡ ሶማሊያ በጦርነት ኢትዮጵያን እንድታፈርስ እንግሊዝና አሜሪካ ፍላጎታቸው ስለነበር ይኸው የግል ኩባንያ United Nations ያወጣው መግለጫ እንኳን አልነበረም፡፡ ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች ከሩሲያ ኩባ እና ቻይና ካገኙት ድጋፍ ጋር ተዳምሮ የዚያድ ባሬና ጭፍሮቹ እቅድ ህልም ሆኖ ሊቀር ችሏል፡፡
ሊግ ኦፍ ኔሽንስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት United Nations ቢተካም ይህኛውም ተቋም ከውልደቱ ጀምሮ የእንግሊዝና አሜሪካ አክሲዮን ማህበር ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ ተቋም ስለመሆኑ ተጨባጭ ሆኗል። በዘረኝነት የተተበተበና የሃያላን ሃገራትን ፍላጎት ለማሟላት ሌት ተቀን የሚተጋ ሰንካላ ተቋም ስለመሆኑም በርካታ አባል አገራት መሪዎች ያስደመጡት ቅሬታ ነው።
ኢትዮጵያ በዚሁ በተመድ ተቋም ታሪካዊ የአባልነት ሚና ቢኖራትም በተቋሙ መበደልና መጎዳቱ የቀረላት አይመስልም፡፡
ሱዳን በአል-ፋሻቃ አካባቢ ስለፈፀመችው ወረራ፣ ህወሃት ሉዓላዊውን የኢፌዴሪ መከላከያ ስለማጥቃቱም ሆነ ከህግ ውጭ ተናጠላዊ ጫና ለማድረግ ያሰፈሰፉ አገራት እረፉ ሲል አይደመጥም። ይልቁንም የነሱኑ የቤት ስራ ለማስፈፀም ላይ ታች ሲል ነው የሚታየው።
በአንፃሩ የማይመለከተው በሆነው ህዳሴ ግድቡ ጉዳይ ደጋግሞ ሲመክር ታዝበነዋል። በጠላት አገራት ድጋፍ ላይ ተስፋውን አድርጎ ሃገራችንን ለማፍረስ እየታገለ ያለውን ወያኔን ድራሹን አጥፍቶ ህግና ሥርዓትን ለማስከበር በምናደርገው ትግል በውስጥ በተለያዩ ጫናዎች ወንበዴውን ለመርዳትና እንዲያሸንፍ ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ሲያደርጉ ቢታዩም ህልማቸው ውሃ እየበላው ይገኛል፡፡
ለሊግ ኦፍ ኔሽን ውድቀት መግፍኤ የነበረውን ቅሬታ ያኔ ካሰሙት መካከል ኢትዮጵያ ቻይና ሩሲያ ዋነኞች ነበሩ። በተመሳሳይ በዛሬው የተመድ አድሏዊ አካሄድ ላይም ትችት ያቀርባሉ። ከዚህ አልፎም ተቋሙ ሪፎርሙን እንዲተገብር ደጋግመው እየጠየቁ ናቸው።
የሊግ ኦፍ ኔሽን የውድቀት ታሪክ በተመሳሳይ ገፁ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገምበት ዘመን ቀርቧል የሚለው እሳቤም ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እየጨመረ ነው የሚገኘው።
ታዲያ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ የገጠመው የረከሰ ዕጣ ፋንታ በተመድ ሊደገም ይሆን? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ብዙም የተወሳሰበ የሚሆን አይመስልም።
አለማችን በቀደሙት ዘመናት ያስተናገደቻቸው ስልጣኔዎች የየራሳቸው መገለጫ ቢኖራቸውም ሲወጡና ሲወርዱ በታዩባቸው መገለጫዎች ግን ስለመመሳሰላቸው ነው የዘርፉ ጠበብት የሚገልፁት። ይኸውም ያለፉ ስልጣኔዎች የሃያልነት መሰረቶቻቸው ለጉልበታቸው እንዲሁም የእነዚያ መሰረቶቻቸው መዳከም ለውድቀታቸው ዋነኛ ሰበብ ነበሩ። በአጭሩ ለመጥቀስም የስልጣኔው መሪ ሀገር የሆነች አንድ ከተማ የአለም ንግድ ማእከል መሆን፤ የሀገሪቷ ገንዘብ አለማቀፍ መገበያያነት፣ የሀገሪቱ አለማቀፍ የንግድ ድርሻ እንዲሁም ወታደራዊ አቅም ተገዳዳሪ የሌለው መሆን ዋነኞች ናቸው።
የስልጣኔ መሪ ሃገር ከጉልበታዊ ከፍታዋ ወድቃ ስትከሰከስ እምጂ ከዙፋኗ መውረድ ስለመጀመሯ በውል ሲታይ አይስተዋልም የሚሉም አሉ። የሆነ ሆኖ ውድቀቱ እውነት ሆነ ለማለት የሃያሏ ሀገር መገበያያ ገንዘብ ሌላ ተገዳዳሪ ገንዘብ ይመጣበታል። የሃያሏ ሀገር ጦር ተዋግቶም ሆነ አስፈራርቶ ጥቅሙን በአለም ዙሪያ ማስጠበቅ እየተሳነው መምጣት፤ አለማቀፍ የንግድ ድርሻዋ በአዳዲስ መንግስታት ብልጫ እየተወሰደበት መምጣት ይሆናሉ ማለት ነው።
አሜሪካና አጋሮቿ በአፍጋን በሊቢያ በማሊ በክሪሚያ በቻይና ባህር ወዘተ ጥቅማለውን ለማስከበር ጉልበታቸው እምደ ድሮው አልፈቀደላቸውም። ዶላር በሩብል በዩዋን እና ቢትኮይን እየተዘረረ ይገኛል። ሰርክ የዋሽንግተን አገልጋይ የነበሩት የገልፍ ሀገራት የተጠቃቀሱ ይመስል አሜሪካን በቃሽኝ ብለዋታል። ወዘተ ወዘተ…
የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን ሀገራቸውን ከፀጥታው ምክር ቤት ለማስወጣት ውሳኔ ከተሰጠ ሊመጣ የሚችለውን አፃፋ በተመለከተ ከሳምንታት በፊት አስጠንቅቀው ነበር። ፑቲን እምዲህ ነበር ያሉት፦ “ሩሲያ ከፀጥታው ምክር ቤት አባልነት የማገድ ውሳኔ የሚተላለፍ ከሆነ ያኔውኑ የፀጥታው ምክር ቤት የሚባል ተቋም አለመኖሩ እውን ይሆናል። በየትኛውም የአለም ክፍል የፀጥታው ምክር ቤት ሚና እንዳይኖረው ሩሲያና አጋሮቿ ሚናቸውን መወጣት ይጀምራሉ።” ነበር ያሉት ፑቲን
በሌላ በኩል ፕሬዝደንት ኤርዶጋን “ዓለም ከአምስት በላይ ናት” ከሚለው ዝነኛ ንግግራቸው በተጨማሪ “A fairer world is possible.” “ፍትሃዊ ዓለምን እውን ማድረግ ይቻላል” በማለት ጭምር ነበር የምዕራባዊያኑን አድልዖና ኢፍትሀዊነት ሲያወገዙ የሚታወቁት። በዛሬው ዕለት ከተደረገው ድምፅ አሰጣጥ አስቀድሞ ቱርክ የሩሲያን ሰብአዊ ጥፋት ማውገዝ አለባት በማለት አውሮፓ ህብረት ሀገረ ጀርመንና አጋሮቻቸው ከሌላው ጊዜ በተለዬ መንገድ ሲለምኑ ሲያግባቡና ሲማልዱ የተደመጡት ከአንድ ቀን በፊት ትላንት ነበር። ኤርዶጋን “fairer world is possible” በማለት ሲመኙት የነበረውን የአለም ፍትሃዊ አሰላለፍ ለማሳካት መላው እነዚያን አምስት ጨቋኝ ሀገራትን ደግፎ ሩሲያን በማውገዝ? ወይስ ሌላ ያልተገለጠ ሚስጥራዊ ቀመር ይኖር ይሆን?
Esleman Abay #የዓባይልጅ