ስዩም ተሾመ
አባይ ምንድነው? አዎ…አባይ ወንዝ ነው። “የአባይ ወንዝ’ስ“ ምንድነው? በምድረ-በዳ ተራራና ሸለቆን አያቆራረጠ፣ በረሃ ሰንጥቆ የሚፈስ ተራ ወንዝ አይደለም። በውስጡ የሚፈሰው ዉሃ ብቻ አይደለም። በሰው-ልጅ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ነገሮች በሙሉ በአባይ ውስጥ ይፈሳሉ። አባይ ለኛ ወንዛችን፣ ወዛችን፣ ደማችንና ገመናችን ስለሆነ አባይ ለኢትዮጲያኖች ሁለመናችን ነው።
በሰው-ልጅ ስልጣኔ ቁልፍ የሆነው ነገር እርሻ ነው። ሰው እንደ ጦጣ ከዛፍ-ዛፍ እየዘለለ ፍራፍሬ ከመልቀም እህል ዘርቶ መቃም የተማረበት ቦታ በአባይ ወንዝ ዳርቻ ነው። የአባይ ወንዝን ድንገተኛ ሙላት በመረጃዎች ላይ ተመስርቶ ለመተንበይ በሚደረገው ጥረት ክስተቶችን በፓፒረስ ላይ መመዝገብ ተጀመረ። በዚህም የሰው ልጅን ምክንያታዊ ግንዛቤ በላቀ ደረጃ ያሳደገው “ፁኁፍ“ እና በመረጃ ላይ የተመሰረተ የግምትና ትንበያ ሳይንስ፣ ስታትስቲክስ (statistics) ተፈጠረ። በአባይ ዳር ያለን የእርሻ መሬት ግብር ለመተመን በሚደረገው ጥረት የጂኦሜትሪ (Geometry) ሳይንስ ተፈጠረ። በአጠቃላይ፣ ለእነዚህና ሌሎች መሰረታዊ የሳይንስ ዘርፎች መነሻ መሰረት እንደመሆኑ “የሰው-ልጅ ስልጣኔ የአባይ ዳር ቄጤማ ነው“ ማለት ይቻላል።
አባይ ለእኛ ለእትዮጲያዊያን ሁለመናችን ነው። አባይ ለኛ ወንዛችን ብቻ ሳይሆን ወዛችን ነው። የአባይ ወንዝ የሚደፈርሰው በኢትዮጲያ ገበሬ ላብና ወዝ የወረዛ አፈርን ጠራርጎ ስለሚሄድ ነው። በአባይ ውስጥ የሚፈሰው ወዛችን ብቻ ሳይሆን ደማችን ጭምር ነው። የአባይ ውሃ ዳለቻ የሚሆነው የእሱ ጦስ ባመጣው ጦርነት የፈሰሰው የሰማዕታት ደም ተቀላቅሎበት ነው።
አባይ ሌሎችን እያሰለጠነ እኛን ያሰየጥናል። እኛን አቅም ነስቶ ለሌሎች አቅም ይፈጥራል። አባይ የእኛን ገበና ያጋልጣል። የእኛን ወዝ እና ደም ጠርጎ በመውሰድ ለባዕዳን ውድቀታችንን ያሳብቃል። ለእኛ ባዶ ድንፋታ እያሰማን ለሌሎች የስልጣኔ ጥዑም ዜማ ያዜማል።
ትላንት አባይን ለመጀመሪያ ግዜ በዓይኔ አየኹት። ከቆምኩበት ድልድይ ዘልዬ ወንዙ ውስጥ መግባት አሰኝቶኝ ነበር።…አቅበጥብጦኝ፣ …ነፍሴን የእልህ ሲቃ ተናንቋት ነበር። ጆሬዬ አቅርቤ አዳመጥኩት። “ኧኸኸኸ….ኸኸኸ…“ እያለ የሚያናግረኝ መሰለኝ፣ የሚያዜምልኝም መሰለኝ። ያም ሆነ ይህ አንጀቴን ሲጨምቀኝ ከነበረውን ርሃብ አስታግሶልኛል ነበር።
የህዳሴው ግድብ ወዳለበት ስፍራ ጉዞው ቀጠለ። ርሃቡ አንጀቴ መጭመቅና ጨጓራዬን መቧጠጡን ቀጥሏል። አዎ…የሚበላ ነገር ከቀመስኹ 24 ሰዓታት አልፈዋል። ጉዞው አላልቅ ሲለኝ፣ የመከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በየቦታው የእያንዳንዱን ሰው (189 ተጓዥ ነበሩ) ስም እየጠሩ ሲፈትሹ’ማ ሁኔታዎችን መታዘብ ቀርቶ ማሰብ እንኳን ተሳነኝ። ጆሮዬ አይሰማም፣ አይኔን መግለጥ ከበደኝ፣ እግሮቼን ማንቀሳቀስ ተሳነኝ…።
የግድቡ ግንባታ ቦታ ደርሰን ኢንጂነር ስመኘው ገለፃ ሲያደርግ ለተወሰኑ ደቂቃዎች እንኳን መታገስ አልቻልኩም። ወደ አንዱ ክፍል ዘ…ው ብዬ ብገባ የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪዎች የአባይ ወንዝ አምጥቶ የተፋው ግንድ የሚመስል አጥንት ያለበት የሥጋ ቅቅል ይበላሉ። ወደ አንዱ ኢንጂነር ጠጋ አልኩና፤ “ርቦኛል! እህል ከቀመስኹ ከ24 ሰዓት በላይ ሆኖኛል። ወይ እሱን ምሳ አብረን እንብላ ወይም “እ..በ..ላ..ሃ..ው!“ አልኩት። ያልኩት ነገር በጣም እያሳቀው፤ “ና ብላ“ ብሎ ጋበዘኝ። እሁ…ሁ..ሁ…ሁ! ለካስ ያለምግብ ሰው ከንቱ… ደካማ ፍጡር ነው።
ኢንጂነር ስመኘው ገለፃውን እንደ ጨረሰ ግንባታውን ለማየት ሄድን። ለካስ በአካል ተገኝተው ሲያዩት በጣም የተለየ ስሜት ይፈጥራል። ፕሮጀክቱ፤ 1300 ሜትር ርዝማኔ ያለው፣ ከታች ስፋቱ እስከ 170 ሜትር የሚደርስ እና ወደ ላይ 140 ሜትር ከፍታ ያለው እጅግ በጣም ግዙፍ የሆነ ተራራን በመገንባት በወንዙ ማዶና ማዶ ያሉትን ሁለት ተራራዎች ማገናኘት ነው። ከዚያ በተረፈ፣ ዙሪያው በተራራ የተገደበ ስለሆነ አብዛኛውን የግድቡን አካል ሰው ሳይሆን ተፈጥሮ የገነባችው ነው።
እስካሁን ይህን ቦታ አይቶና ለይቶ ግድቡን አለመገንባት ሃገሪቷ ያሏትን ተፈጥሯዊ ሃብቶች ጠንቅቃ ያለማወቋ ማሳያ ነው። የተለያዩ ቅድመ-ዝግጅቶች እንዳሉ ሆነው፣ የህዳሴው ግድብ ሁለት ተራራዎችን ለማገናኘት የሚደረግ የተቀየሰ ፕሮጀክት ነው። በቦታው ወደ 8500 የሚጠጉ ሰራተኞች በየፊናቸው እየተሯሯጡ ቢሆንም፣ በቦታው 1000 ሰው እንኳን ያለ አይመስልም።
ከሁሉም ሰራተኞች በተለየ ቀርቤ የታዘብኩት ሰው ቢኖር ኢንጂነር ስመኘውን ነበር። ዝም ብዬ ሳየው፣ ሰውዬው ለቅንጦት ቦታ ያለው አይመስልም። በዚያ ተራራ መኪናውን የሚያሽከረክረው ራሱ ነው። ስለ ግንባታው ገለፃ ለማድረግ ከአንዱ ጥግ ወደ ሌላ ሲሯሯጥ፣ አለባበሱና ቀረቤታውን ላየው፣ አንድ ተራ አስጎብኚ እንጂ የሀገሪቱን ታለቅ ፕሮጀክት የሚመራ ኢንጂነር አይመስልም። ሰውዬውን አከበርኩት። ግን ደግሞ ሳስበው፣ ኢ/ር ስመኘው በጣም እድለኛ እንደሆነ ይሰማኛል። ከእሱ የማያንሱ ወይም የሚሻሉ ኢንጂነሮች እንዳሉ ግልፅ ነው። ነገር ግን፣ ከሁሉም በተሻለ በዚህ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ላይ አሻራውን እንደሚያርፍ ሳስብ፣ አክብሮቴ እንዳለ ሆኖ፣ እንዚያ ትጉህ ባይሆን ኖሮ ይገርመኝ ነበር።
ወደ አሶሳ ስንመለስ ከመኪናው ወርጄ አባይን ትኩር ብዬ አየኹት። ቃለአብ የተባለው ጓደኛዬ የአባይን ውሃ እንደ ቅዱስ ጠበል እየቀዳ ነው። እኔ ደግሞ ለማስታዎሻ የሚሆን ምን መያዝ እንዳለብኝ ግራ ገብቶኛል። ድንገት ጎንበስ ስል ግን አንድ የሚያምር ጥቁር ድንጋይ አየሁ። እሱን አንስቼ አቧራውን እያራገፍኩ ሳለ ሌላ ሁለት ድንጋዮች፣ እንደገና ሌላ…..። ሁለት ትላልቅ እና ስድስት ትናንሽ ጥቁር ድንጋዮች፣ አንድ ደግሞ ነጭ ድንጋይ ታቅፌ ወደ መኪናው ስገባ ያዩኝ ባልደረቦቼ በሙሉ በድንገት ወደ ድንጋይ ለቀማ ወረዱ። ከዛ ሁሉም ይሄን የአባይ ጥቁር ድንጋይ ለቅሞ…ለቅሞ ታቅፎ ገባ።
ድንጋዮቹን ለምን እንደሰበሰብኳቸው እንድነግራቸው ቢወተውቱኝም፣ እነሱ ምንም ሳያስቡ በመሰብሰባቸው ተገርሜ ምላሽ ነፈግኳቸው። በኋላ ሁሉም አየና፣ ድንጋዮቹን የያዘበት ምክንያት አልገባ ሲለው፣ ግማሹ መኪና ውስጥ ጥሎት ወረደ፣ ሌላው ድንጋዩን አውጥቶ ጣለ። እኔ ግን፣ ዘጠኙንም ደንጋዮች ማታ ሰውነቴን ስታጠብ በሙቅ ውሃ አጠብኳቸው። ውል…ውል አድርጌም በቦርሳዬ አስቀመጥኳቸው።
ዘጠኙን ድንጋዮች በስስት ይዤ የመጣሁበት ምክንያት የተለየ ውበትና ማማር ስላላቸው ብቻ አልነበረም። ከዚያ ይልቅ፣ ግድቡ ሲጠናቀቅ ድንጋዮቹን ያገኘሁበት ቦታ ሙሉ-በሙሉ በውሃ ስለሚሸፈን ነውና እነዚያን ድንጋዮች ከዚያ ቦታ ማግኘት ስለማይቻል ነው። የአባይ ግድብ ምክኒያት የሚፈጥረው ሰው ሰራሽ ሃይቅ እስከ 240 ኪ.ሜ ርቀት የሚደርስን ቦታ፣ ወይም ከአዲስ አበባ እስከ ሻሸመኔ የሚያክል ቦታን ይሸፍናል።
በዚህ ትልቅ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ውስጥ የኢትዮጲያ ገበሬ ወዝ፣ ላብና ደም ይታቆራል። አባይ ከሀገር ወጥቶ ገበናችንን ማጋለጥ ይሳነዋል። ውድቀታችንን እንዳያሳብቅ በኢትዮጲያ ውስጥ ይታገታል። እነዚያ ጥቋቁር ድንጋዮች፣ እኛ ኢትዮጲያዊያን ወንዛችንን ገድበን ወዛችንን በማስቀረት፣ አባይ ግብፅ ሄዶ ውድቀታችንን ማሳበቅ ሳይሆን አቅማችንን እንዲመሰክር
1 thought on “ዓባይ፣ የኢትዮጲያ ወንዝ እና ወዝ”
አስገራሚ ገጠመኝ እና ለልጅ ልጆችህ፡ ለኢትዮጲያውያን የወደፊት ትውልድ፡ እውነት ማስተማሪያ፣ መተረኪያ፣ ምናልባትም ትልቅ ዓለም-ዓቀፍ ዓውደ-ርዕይ አዘጋጅተህ ለጨረታ ብታቀርበው ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ ትልቅ የሀብት ምንጭ ሊሆን ይችላል እና አስብበት። ምናልባትም ሁሉንም በከፍተኛ ገንዘብ እንግዛህ የሚሉህ ግብፆች እንደሚሆኑ ርግጥ ቢሆንም እኔ ብሆን ግን “ለግብፃዊ አይሸጥም” የምል ይመስለኛል።