ዓባይ- ከ “እናትክን በሉልልኝ” እስከ “የደም ሐረግ ሆነ”፡ አባይ ተኮር ግጥሞች እና ዘፈኖች አጭር ቅኝት

Zerihun Abebe Yigzaw

አባይ የኢትዮጵያ ድጓ ነው… መቀነቷ ነው… ከላይ ትገራይን በተከዜ ሲያስገብር… ጎንደር እና በእነ አንገረብ እና ጓንጉ፣ በእነ ርብ እና በራ፣ በእነ ቲሽከና እና በእነ ዛሪማ ያሰገብራል… ጎጃም በግልገል አባይ.. በእነ ቢኮሎ እና ጩሞጋ እጅ ይነሳል… ወሎ በሽሎን ግብር አስጭኖ ይልካል… ሸዋ በደብረሊባኖስ አስባርኮ ጀማን ይገብራል… ደቡብ ለባሮ አኮቦ ይገብራል ከጋመብላ ጋር ተባብሮ… ቤንሻነጉል-ጉምዝ አባይን ያስተናግዳል በበለስ እጅ እየነሳ….ኦሮሚያ ስንቱ ተቆጥሮ… እነ ዲንደር፣ ጉደር፣ ሙገር፣ ፊንጫ፣ ዲዴሳ… ወዘተ ይገብራል…
አባይ በቃኝን አያውቀም.. አይጠረቃ.. ዝም ብሎ ያገኘውን መጫን ነው.. የመጣውን ሁሉ መቀበል ነው.. እረፈትን አያውቀም.. ዝም ብሎ መፍሰስ.. ዝም ብሎ መጋብ.. ዝም ብሎ በረሐን መናፈቅ… ዝም ብሎ መሄድ… መሄድ…

ታዲያ በዚህ የግብዝ ጉዞው.. ውጭ በመናፈቁ ለዘመናት የገጣሚዎቻችን፣ የባለቅኔዋቻችን እና የዘፋኞቻችን ቀጥታ ይሁን አሽሙር ስድብን እና ዘለፋን አስተናግዷል አባይ፡፡ ሙገሳውም አልቀረለትም ደጉ ነገር… ይገባዋላ… አባይ አደል እሱ ለውበትማ… እውቅ ገጣሚያን ወርፈውታል… ንቀውታል… ሰድበውታል.. እሱም እረኛው የሚያሰማውን ዋሽንት እያጣጠመ.. እምቢልታውን እያደመጠ… አሸንዳ እና እስክስታውን እያየ.. ቅኔውን እየተመገበ… ደርት መደቃቱን እየታዘበ.. ረገዳውን እያጣጣመ… ሀገር ሙሉ አፈር አንደ ቅጠል እና እንደ ደንገል ተሸክሞ መሄዱን አላቆመም… ይህ የሆነው ግን እንደ ሰካራም በሰኔ፣ በሐምሌ እና በነሐሴ እየደነፋ… እያጓራ… በተቀሩት ወራቶችም በለሆሳስ እና በእርጋታ ቢጣራ ሰሚ አጥቶ ነው.. ስሙ እዩኝ እያለ እሚያይ አልነበረውምና… ስድብን እንደ ቅቤ እየተቀባም ቢሆን ግን መሄድ ነው እሱ.. ማን ከልክሎት…

ብታሰረፉኝ ደግ በመደብ አድራለሁ

ሂድ ካላችሁኝም ስጓዝ እኖራለሁ

ምርጫችሁ ምርጫየ እኔ ሰው አይደለሁ… (ዘአ)

እያለ እንደሚሄድ ያስታውቅበታል….

እጅግ ተቆጥተው ከሰደቡት ደማምነቱን.. ውበቱን እንኳ ለመናፈቅ እና ለማድነቅ ጉሮሯቸው ያልከፈተላቸው እጅግ ብዙዎች ነበሩ… ምክንያቱም አባይን የጎሪጥ እያዩ… በውሃ ጥም የሞቱት.. ተርበው በአባይ ዳቦ ለመጋገር ባለመቻሉ.. እንጀራ ለማብሰል ባለመድፈሩ ብዙዎች በረሀብ አለንጋ ተገርፈዋልና…. ከመጀመሪያዎቹ ሰዳቢዎቹ መካከል ገጣሚ እና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሀንስ (ገሞራው) ዋነኛው ነው.. እጅግ ሰዋዊ በሆነ አተራረክ አባይን ከእነ ወላጁ ይወርፈዋል ገሞራው… እንዲህ ሲል…

«እናትክን!» በሉልኝ

ይፈሳል ይሉኛል፣ አባይ ዐይኑ ይፍሰስ
ያን ስንቱን ወገኔን የውሃ እጦት ሲያምስ
የድርቀት ጋንጩራ ሲበላ ስንቱን ነፍስ፣
ውሃ ውሃ እያለ ለጋው ሲቀነጠስ
ናይል አባያችን . አለ ነበር ሲፈስ
ለፈፀመው ደባ ለሰራውም ግፉ
«እናትክን!» በሉልኝ በዚያ የምታልፉ

እርግጥ ነው አባይን እስከ እናቱ መሰደቡ አግባብ ነው… እስማ ግዑዝ አይደል ሀገሩ ነበርቻ ማልማት የነበረባት… ሰው ሀገር ናትና.. ሀገርም ሰው ናትና… “ቢያ ጀቹን ቢየ ሚቲ ቢያ ጀቹን ነማ”-ሀገር ማለት መሬት አይደለም ሀገር ማት ሰው ነው እንዲሉ ኦሮሞ አባቶቻችን… በርግጥ ደ/ር በድሉ ዋቅጅራ ለልጁ ለኬር ሰላም እንዲህ ብሏት የለ…

ልጄ ሀገር ማለት ሰው ነው

አትሰሚው አትናገሪው…

አባይ-ግዮን እንደ ያሬድ ዘጨጎዴ ያሉት ታላላቅ ባለቅኔዎችንም ዱላ ተቀብሏል.. በመዝባሪነት እና ክፉ ወላጅ አስለቃሽ፣ ወላጅን አሳዛኝ፣ እንባ አራጭ የሌባ የዘራፊ ተምሳሌት ሆኖ ተስሏል… እንደሆነም ተነግሮበታል… ባለቅኔው እንዲህ ብለውታል ዘመን በማይሽረው ፍልስፍና…

ፅሩዕ ምግባረ ግዮን ልቡናሃ ለኢትጵያ አንደደ

አምጣነ ቤታ ከረየ ወንዋያቲሃ ወሰደ፡፡ (ግዕዝ)

ብለውታል፡፡

ትርጉሙም

ምግባረ ብልሹ አባይ የኢትዮጵያን ልብ አሳዘነ

ቤቷን በርብሮ ንብረጾቿን ወስዷልና፡፡ ማለት ነው፡፡

ጋሽ ጸጋዮ ገብረመድህንም በእሳት ወይ አበባ አባይን ተራቅቆበታል፡፡ የስልጣኔ ምንጭነቱን፣ ውበት ሀብቱን፤ ቅርስነቱን፤ የኩራት ምንጭነቱን፤ የካም ሀበትነቱን፤ ለሀገሩ መከራነቱን ብሶትነቱን ወዘተ በውብ ቋንቋ ተርኮታል፡፡ እንዲህ ሲል

አባይ የምድረ ዓለም ሲሳይ

የቅድመ-ጠቢባን አዋይ

አባይ የጥቁር ዘር ብስራት

የኢትዮጵያ ደም የኩሽ እናት

የዓለም ስልጣኔ ምስማክ

ከጣና በር አስከ ካርናክ

በእቀፍሽ ውስጥ እንዲላክ

እያለ አውድሶ አንዲህም ወርፎታል…

በመመለክ በመመስገን

ጽላትሽ ከዘምን ዘመን

በአዝዕርትሽ አበቅቴሽ ሲታጠን

አቤት አባይ ላንቺ መገን፡፡

እያለ ገማናነቱን ይገልጥበታል፡፡ የአለሙን ፍረደ ገምድልነት፣ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትን ውለታ ቢስነት እና የኢትዮጵያ ብቻ መቆም ከስልጣኔ መሰረትነቷ እያነሳና እየጣለ የጥንታውያን ኩሽ ግብጽ አጥኝ እና ገጣሚው ጋሽ ጸጋዮ እንዲህ ይቀጥላል

አድርጎሽ ቅድመ ገናና

ዛሬ ወራቱ ራቀና

ምድረ-ዓለም ያነችን አድናቆት

ፈለጉን መሻት ተስኖት

እንዲህ ባንቺ መንከራተት

ታሪክ ወሮታሽ ጠፍቶበት

ትላንት በባዕድ ጩኸት

ዛሬም ባላዋቂ ሁከት

ቋንቋ ለቋንቋ ቢራራቅ

የቅድሚያሽ ንድፍ ላይፋቅ

እዚህ ደማም እዚያ ተማም

መበልሽ ብቻ ባይበቃም….

እያለ ውስጠ ሚስጥሩን ይገለጽበታል፡፡ በምንጩ ያለው ክብር ከደማምነቱ እና ውበቱ ሳይዘል ተማም ተብሎ አለመበላት አለመጠጣቱ አቤት አባይ ያንች መገን እንዲባል.. ጉድ እንዳስባለ.. ራስ እንዳስያዘ እንዳስነቀነቀ ይገልጽበታል ጋሽ ጸጋዮ፡፡

አባይ ያላቃጠለው የለም… የመለያየት ምሳሌም ሆኖ በዘፋኞቻችን ነግሶ ቆይቷል…

አባይ ወዲያ ማዶ ዘመድ አሉኝ ማለት

ዋ…! ብሎ መቅረት ነው ውሃው የሞላ እለት….

እንዲሉ በሀገረኛ ዘፈን፡፡

አበበ ብርሃኔም

ዓሳው እያማራት

ውሃው እየጠማት

አባይ ዳር ነው ቤቴ

ብትል ማን ሊሰማት

ብሎ የኢትዮጵያን ጩኸት ጩኋል፡፡

እጅግ ውብ በሆነ አራረክ እና ፍልስፍና በሙዚቃ አባይን እንደ እጅግአየሁ ሽባባው የተራቀቀበት አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ጂጂ የአባይን ምንነት… ገመናውን… ውስጠ ሚስጢሩን ብሶቱን ችግሩን.. ፍትጊያውን አሳምራ ገልጻዋለች፡፡ እንዲህ ስትል የሚያምረው ውበቱን እና ሰማያዊነቱን አጥንት በሚሰረስር ዜማ ታዜመዋለች…

የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና

የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የጠና

ከጥንተ ከጽንሰ አዳም ገና ከፍጥረት

የፈሰሰ ፈልቆ ከገነት…

ግርማ ሞገስ የአገር ጸጋ የአገር ልብስ

በማለት ወረድ ትልና እጅግ ውስጥን በሚያም እና በሚያሳምም.. እንዴት ለእነሱ ብቻ ሆንክ በሚል ቁጭት የበረሐ ሞገስ ብቻ ሆንክ.. ለምን ተውከን እኛን በሚል ቅላጼ እንዲህ ተለዋለች

ግርማ ሞገስ አባይ…..

የበረሐው ሲሳይ

የበረሐው ሲሳይ…

ብነካው ተነኩ አንቀጠቀጣቸው

መሆንህን ሳላውቅ ስጋና ደማቸው

የሚበሉት ውሃ

የሚጠጡት ውሃ

አባይ ለጋሲ ነው በዚያ በበረሐ…

በማለት እልም ባለው በሰሐራ በርሐ ህይወትን መዝራቱን አሳምራ ትገልጸዋለች… አባይ ሲነካ ተነካን የሚሉትን ግብጾችን ከላይ የነካካችው ጅጅ ወረድ ብላም በሀገራቱ መካከል ያለው አተካራ እና ከወንዙ ጋር የተያያዘውን ፍትጊያ እንዲህ ትለዋለች….

አባይ አባይ አባይ

አባይ ወንዛ ወንዙ

ብዙ ነው መዘዙ፡፡

ጅጅ አባይን ለግብጾች ብቻ ስጋና ደም መሆኑ ከነከናት.. ምንጩን ሳይስብ መብረሩ አሳረራት.. እናም ዝም ልትለው አልፈለገችም… እንደ ሰው አናገረችው… እንደ ሰው ጠየቀችው… እንዲህ ስትል…

አባይ የወንዝ ውሃ አትሁን እንድ ሰው

ተራብን ተጠማን ተቸገርን ብለው

አንተ ወራጅ ውሃ ቢጠሩህ አትሰማ

ምን አስቀምጠሀል ከግብጾች ከተማ? አባይ ግን የሰማት አይመስልም ነበር ዝም ብሎ መሄድን ስራየ ብሎ ይዞ ነበርና… አልጋ የሚሰራለት ያጣው አባይ… መደብ የሚያበጅለት ግዮን… በዋሽንት እንጉርጉሮ የተሸኘው ታላቁ ወንዝ.. አባይ ማደሪያ የሌው ግንድ ይዞ ይዞራል ካላችሁኝ.. ልበራራ ወደ ማደሪያ በሚል ግልፍተኝነት እና ብስጭት ቁልቁል ወደ ምስር መስገሩን አላቆመም ነበር….

በዚህም በዚያም የተጀመረው የድርድር ሂደት እና የስምምነት ጭላንጭል መገራገጭ ሲያጋጥመው የተመለከተ… በተፋሰሱ የግርጌ እና የራስጌ ሀገራት ስምምነት መጥፋቱን ያስተዋለው ደግሞ የድምጻዊ ግዛቸው ተሾመ ጎጃም የሚል ዜማ ነው…. እንዲህ ሲል…

ኧረ ነይ ኧረ ነይ ኧረ ኧረ በመስኩ

የአባይማ ነገር አልታወቀም ልኩ፡፡

ውጣ ውረዱን.. ያልተፈታውን ችግር.. መዘዙን.. ውስብስበነቱን ሲገለጽ ነው እንዲያ ማለቱ… ነይ እስኪ በመስኩ እንነጋገር… እያለ ያባብላታል ፍቅሩን… መልክቱ ግን ለስምምነት እየተጠራች ነበር በግርጌ ያለቸው እህት ሀገር… አሁንም እየተጠራች ነው መስማቷን ግን እንጃ….

በዚህ መሐል ነው እንግዲህ እጅግ ግሩም የሆነው የገነት ማስረሻ ጪስ አልባው ነዳጄ ብቅ ያለው… እስካሁን ከላይ ያየናቸው ግጥሞች እና ዘፈኖች ቁጭትን እና ብሶትን አለመስማማትን መጥራትን የሚገልጹ ናቸው፡፡ የገነት ማስረሻ ዜማ ግን ለየት ይላል፡፡ ምንም ቅኔ የለውም.. ግልጽ ያለ መልዕከት ነው… ግልጽ ያለ ጥሪ ነው..
ይህ ሙዚቃ የወጣው የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከመጣሉ በፊት ነው…. የጣና በለስ ሀይል ማመንጫ ከተገነባ ማግስት… የናይል ተፋሰስ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ ጉዳይ በጦዘበት ሰሞን… ገነት ማስረሻ በዚህ ግጥም.. አባይ ለኢትዮጵያ ምን እንደሆነ.. ከፍ ሲልም ለተፋሰሱ ሀገራት ምን ማድረግ እንደሚችል እና እንዴት እንደሚበቃ.. የሰላም ዋስትና እንደሚሆን ትገልጽና… ይህ የማይጥመው ካለ ግን በሊማሊሞ እንዲያቋርጥ በግልጽ ትናገራለች…. እስኪ በምዕራፍ በምዕራፍ የተወሰኑትን ስንኞች እንሂድባቸው…

ገነት የሀበት ምንጭ ነውና ጭስ አልባው ነዳጄ አልዋለሁ ትልና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይን ለሌሎችም እንደሚተርፍ እንዲህ ትገልጻለች…

ጭስ አልባው ነዳጅ-አባይ

እንኳን ለእኛ ቀርቶ ለሰውም ይተርፋል

ጭስ አልባው ነዳጄ ብለው ምን ያንሰዋል፡፡

…..

አባይ አንተ እያለህ ታላቁ ወንዛችን

መሳለቂያ አንሆንም በድህነታችን፡፡

ቁጭት በቃን ተግባር ነው አሚያሻው ስትልም እንዲህ ትላለች… በማስቀጥልም ጥሪዋን ታቀርባለች.. እንፋቀር.. እንተባበር ትላለች…

አባይ ወርዶ ወርዶ ወርዶ ሲሰለቸው

ዛሬስ ለወገኑ ስለ ሀገሩ ቆጨው

…..

አባይ አንተ እያለህ ጭስ አልባው ነዳጅ

አልመለከትም እኔስ የሰው እጅ…

….

አባይ እኔ አንተ ያለነው ቅርብ ነው

ከተስማማንማ ሙያ በልብ ነው፡፡

ከተፋቀርንማ ሙያ በልብ ነው፡፡

ከተግባባንማ ሙያ በልብ ነው፡፡

ገነት አባይ አልጋ ሊሰራለት እንደሆነ.. እንግዲህ እየዘለሉ ግንድ ይዞ መዞር እንደሚቀርለትም እንዲህ ታበስራለች…

ማደሪያ ሳይኖረው ግንድ ይዞ ይዞራል

የሚባለው ተረት ከእንገዲህ ይቀራል…

….

የገነት ማስረሻ ሙዚቃ ልዩ የሚያደርገው አንድ ነገሩ የሚከተለው ስንኙ ነው… ለዘመናት የቆየውን የኢትዮጵያን ለጋስነት እና ዝም ባይነት እንደ ፍርሃት የቆጠሩ ወገኖች እንዳሉ በዚህም መፎከሪያ ሆንን ትላለች ገነት… ባለቤትነቱንም በጣም ታመጣው እና የማንም አይደለህም የእኛ ነህ.. አንተን ሳንጠቀም ስልለቀቅንህ… እነሱ ተጠቅመውህ.. አስተኝተውህ ስጋና ደማቸው ሆነህ በእኛ ረሐብ ተሳለቁ ብላ ትቆጫለች…

አባይ እኔ እና አንተን ሳይሉን ቸር ሆነን

ፎከሩብን እንጅ ማን አመሰገነን

በራሳችን ውሃ በራሳችን አፈር

ተዘባበቱብን ተመጠጠ ከንፈር፡፡

የቁጭት ዘመን አብቅቷል እንደልብህ ሁን አባይ … አልጋ ይሰራልሃል አለችው… እንደ ልብህ ፍሰስ.. ለምን የሚል ካለም ያው ሜዳው ያው ፈረሱ.. ውረድ እንውረድ ትለዋለች…

ስንት ዘመን ቁጭት

ስንት ዘመን ፍጭት

ስንት ዓመት በጣሳ

ስንት አመት በወጭት

ፍሰስበት እና በሀገርህ ሜዳ

የሚቆጣን ካለ ያበጠው ይፈንዳ፡፡፡

የነገር ሁሉ ማሰሪያ.. የሰላም ሁሉ መንገድ ሰላም መሆኑን ያልረሳችው ገነት ጥሪዋን በድጋሚ ታስተላልፋለች… ኑ እንተባበር ትላለች…

በፍቅር ብንይዘው አባይ ያገር ዋርካ

ለዓለም ይበቃ ልእንኳን ለአፍሪካ፡፡

ይህን የገነት ማስረሻን ሙዚቃ ልብ ብሎ ላደመጠ ሰው አንድ ነገር ይረዳል… ሙዚቃው ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ኦፊሴላዊ አቋም በግልጽ ያለምንም ጉድለት ያስቀምጣልና…

የገነት ማረሻን ሙዚቃ ተከትሎ እጅግ ብዙ ሙዚቃዎች ወጥተዋል… እጅግ ብዙ ግጥሞችም ተገጥመዋል… ማሰሪያው ግን አርቲስት ጌትነት ነው-በአባይ ሀረግ ሆነ…

አርቲስት ጌትነት የጥንታዊውን የስልጣኔ መሰረትነቱን፣ ስረብዙነቱን… መከራብዙነቱን.. አስለቃሽነቱን… እንዲህ ሲል በትዝታ ይገልጸዋል….

ለአዕላፍ ዘመናት ስንት ታሪክ ሰርቶ

ስንት ተውልድ አይቶ

ስንት ዓመት ተጉዞ እዚህ የደረሰው

ግዮን ስረ ብዙው

አባይ ስመ ብዙው

ናይለ ገጸ ብዙው

የፈለቀበቱን የቃልኪዳን ስሩን መሬቱን ፈንቅሎ

ጥቁር አፈር አዝሎ

ሀገር አንጠልጥሎ

ውሃን አፈር ጭኖ ከሰው ቋት ማፍሰሱን

የወነዝ እንባ ሆኖ ሀገር ማስለቀሱን

በሀዘን በቁጭት የሀገር ፊት መጥበሱን

አንጀት መበጠሱን….

በመቀጠልም የአባይን መቀየረ.. የግዮንን ውስጥ ልብ ቤቱን መመልከት መጀመሩን መጸጸቱን እንዲህ በሰወኛ እያዋዛ ይገልጸዋል… ጸጸቱን ተከትሎም ጥለቅ ስርነቱን እና ከደም መወፈሩን አበሰረ ጌትነት እንዲህ ሲል…

በአገር ግፍ መዋሉን መበደሉን ትቶ

ባለፈ ተግባሩ በጎደፉ ስሙ አፍሮ ተጸጽቶ

በጊዜ ንስሃ ከዘመናት መርገምት ከበደሉ ነጽቶ

ከቆየ ልማዱ ከኖረ ምግባሩ ከባህሪው ወጥቶ

ውሃነቱን ትቶ

ወንዝነቱ ቀርቶ

እንዳንዳች ምትሀት ከቃልኪዳን ስሩ እየተመዘዘ

በአንድ የስሜት ግለት በአንድ የስሜት ሲቃ

ሀገር ጫፍ እስከ ጫፍ ሰቅዞ እየያዘ

ትውልድን ከታሪክ ታሪክን ከሀገር ስቦ እያዋደደ

አስማምቶ እያሰረ

ስሩ የጠለቀ

ግብሩ የረቀቀ

ውሉ የጠበቀ አባይ ሀረግ ሆነ ከደም የወፈረ

ይሄው ከዓናችን ስር ዘመን መሰከረ

ይሄው ከእጃችን ላይ ግዮን ተቀየረ

ጌትነት የአባይን መቀየር በዚህ ብቻ አላስቆመውም… ሸፍጡ ብረት ማንሳቱ… ጥሉ በዚሁ መድረቅ እንዳለበትም ጥሪውን እንዲህ ሲል አቀረበ…

ከእንግዲህ ባገሩ ሳቅ እና መስኖ እንጅ እንባ ሆኖ ላይገርፍ

ከእንግዲህ ላገሩ እጁ ላይታጠፍ

ጸጋው ላይገፍ

ግቱም ከቶ ላይነጥፍ

ከእንግዲህ ፍቅር እንጅ ሸፍጥ እና ድለላ ስሩን ላያስረሱት

ከእንግዲህ ምክር እንጅ ብረት እና ሴራ ውሉን ላያስረሱት

ያገር ውርስ እና ቅርስ እራት እና መብራት

ዋስ ጠበቃ ሊሆን መከታ እና ኩራት

“የሀገር ውርስና ቅርስ ራትና መብራት፣

ዋስ ጠበቃ ሊሆን ክብርና ኩራት፣

ይኸው በአዲስ ዘመን አዲስ ቃል ዘመረ፣

ከራሱ ታረቀ ካፈሩ መከረ፣

ለሀገሩ ቆመ በሀገሩ አደረ፣

ዜማና ቅኝቱ ረገደ ምቱ፣

ከግዜ ከትውልድ ከሀቅ ሰመረ፣

ሃገርን ባንድ ነዶ ባንድ ልብ አሰረ

ይኸው ካይናችን ስር ከእውነት የነጠረ ከእምነት የጠጠረ፣

አባይ ሃረግ ሆነ ከደም የወፈረ፡፡

በማቀጠልም ጌትነት የሀገሪቱ ህዝብ ብሄሩን በመላ እንዲህ ሲል ይጣራል…

የአንድ ወንዝ ልጅ ሁሉ ይህን የአባይ ሀረግ ከእምነትህ ጋር ቋጥረህ

ከጋራ አንገት መድፋት ከጋራ መሳቀቅ ከጋራ አፍረት ወጥተህ

በያለህበቱ በየዓለማቱ ጥግ በአንተነትህ ኮርተህ

አንተ ማነህ ሲሉህ

ከወዴት ነህ ሲሉህ

በሙሉ ራስነት አንገትህ አቅንተህ

ድምጽህን ከፍ አድረገህ

ደረትህን ነፍተህ

የአባይ ልጅ ነኝ እኔ

ጦቢያ ናት ሀገሬ በል አፍህን ሞልተህ….

ርግጥ ነው.. ጌትነት በዚህ ግጥም አባይ ለኢትዮጵያ እንደተቀየረ በገልጽ አስቀምጧል… አባይ ከደም የወፈረ ሐረግ ስር ሆኗል.. ወደ ውስጡ ተመልክቷል… የተቀረውን የቤት ስራ መስራት የእኛ ፋንታ ነው…. ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር…!!!

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories