ዘመነ ኢሕአዴግ በሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች መነፅር

ክፍል አንድን ለማንበብ:-  ⬇️ https://eslemanabay.com/%e1%8b%98%e1%88%98%e1%8a%90-%e1%8a%a2%e1%88%95%e1%8a%a0%e1%8b%b4%e1%8c%8d-%e1%89%a0%e1%88%bc%e1%88%85-%e1%88%81%e1%88%b4%e1%8a%95-%e1%8c%85%e1%89%a5%e1%88%aa%e1%88%8d-%e1%89%b5%e1%8a%95%e1%89%a2-2/

ዘመነ ኢሕአዴግ በሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች መነፅር

ክፍል ሁለት 

ሰሎሞን ዳውድ (ኤም.ኤ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

ወይ እንደ ቀበሮ አልገባሁ ተጉሬ፤

ታገሬ ላይ ሆኘ ናፈቀኝ ሃገሬ፡፡

ትንቢተኛው ሼህ አስከትለው እሳቸው የሚያዩበትን የትንቢት (የጊዜ) መነፅር ርቀት እስከ ሰማኒያ አመት የሚደርስ መሆኑንና መንግስት ለበርካታ አመታት ማሰብ ሲገባው ለዕለት ብቻ አስቦ መጋለብና እንደ ልቡ መፏነን መገለጫው የሆነውን የዘመኑን መንግስትም እንዲህ ሲሉ ይሞግቱታል፤  

እናንተ የምታዩት የለቱን የለቱን፤

እኛ የምናየው፤ የሰማንያ አመቱን፡፡

ታሪክ አዋቂው ትንቢተኛ ሼህ የዘመናችን ትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ነን ባዮች በተግባር የትግራይን ህዝብ የማይወክሉ ሽፍቶች በአገር አስተዳደርና ጀግንነት በትንቢት አቅርቦ ማሳያ መነፅር ተመልክተው አውርደው አውጥተው፤ ከዐጼ ዮሐንስ በኋላ ትግሬ ነኝ ብሎ ተነስቶ የሃገርን አንድነት የሚሰብክ በዘመኑ አጠራር ወንድ፤ ሃገርን አንድ የሚያደርግ አካል አይወጣለትም ያሉት ከዚህ በታች በቀረበው ስንኛቸው ነበር፡፡

የትግሬ ሕዝብ ውክልና የሚመለከቱ ግጥሞች

ምድር ተዘርግታ እስክትከተት

እንግዲህ ለትግሬ የለው ወንድነት

ትንቢተኛው ገጣሚ ሸዋን በቅመም፤ ትግሬን በበርበሬ መስለው ያቀረቡበት ሌላው ግጥም የሚከተለው ሲሆን ብያኔውም የሽምብራ ዘር በምድር ላይ ጥለን በርበሬ ማብቀል ወይም ማፍራት ማለት አንድም ደገኛ ዘር ተዘርቶ ሳለ የሚያቃጥል፤ የሚለበልብ ፍሬ ማፍራትን የሚያመላክት ሲሆን፤ ነገሩ የግርንቢጦሽ ወይም የማይሆን፤ የማይደረግ ነገር መፈጸሙን የሚሳይ ነው፡፡ ሁለትም ይህም የሆነው ቅመሙ፤ አንዳች ፋይዳ ያለው ነገር (የተዘራው ፍሬ) ከሸዋ ሆኖ ሳለ፤ ጭብጫቦው ቅጠል እንዲያወጣ ወይም የማጀፍጀፍ ስራው የተሰራው በትግሬ ስለሆነ ነው ይሉናል ሼህ ሁሴን ጅብሪል፡፡

ሽምብራ ብዘራው፤ ሆነ አሉ በርበሬ፤

ቅመሙ ተሸዋ፤ ጭብጨባው ተትግሬ፡፡    

ከዚህ ጋር በተያያዘ (ዶ/ር) ጌቴ ገላየ ያጠኑት አንድ የጎጃም ጥናት ላይ የተካተቱ አራት ስንኞችን ብንመለከት ይህ የትንቢት ቃል ከዘመኑ ማህበረሰባዊ ትችት ጋር እንዲዛመድ ያደርገዋል፤

በቅሎ ግዙ ግዙ ግራጫ ግራጫ

ወትሮም ተትግሬ ነው የነገሩ መምጫ፡፡

እኛ መች ፈለግነው የትግራይን ጠጅ፤

እየበጠበጡ ያፋጁናል እንጅ፡፡

የጎጃሙ ገበሬ ቃል ግጥሞችና እና የትንቢት ተናጋሪው ሼህ ትንቢት ግጥሞች፤ በዘመንና በቦታ ተለያይተው ሳለ ተመሳሳይ ጭብጥ ያለው ሃሳብን ያስተላልፋሉ፡፡ ይህም ገበሬው የግጥሞቹን ይዘት ቀድሞ ያውቅ ኖሯል፤ አልያም አንዳች መንፈስ አዛምዷቸዋል፡፡ ትግሬን እንወክለዋለን (የትግሬ ነፃ አውጭ) ተብየ ሃይሎች መልካም ፍሬን እንዳይዘሩ፣ ማጨብጨብ ወይም የልፋትን ዋጋ መንጠቅ እና ማበጣበጥና መፋጀት ዋነኛ ስራቸው ነው ይሉናል፡፡ ዶክተሩ ቃል በቃል እንዳስቀመጡት ስነቃሎቹ “ከጥንት ጀምሮ የመከራው መምጫ ከየት እንደሆነና ለችግሩ ተጠያቂዎቹ እነማን እንደሆኑ በግጥማቸው በግልፅ ያወሳሉ፡፡”  

ሌላው ከዚህ የትግሬ ወኪል ነኝ ባይ አስተዳደር ጋር የተያየዘ ግጥማቸው፤ በአሁኑ ወቅት መንግስት ተብየዎቹ አካላት እሳቱን አጋግመው ለፈጠሩት ነዲድ ወይም ችግር መፍትሄ ሰጭ አካላቱ ራሳቸው በመሆናቸው መፍትሄ አለን ቢሉም፤ በእጃቸው የያዙት መፍትሄ በእሳት ላይ ነዳጅ እንደ መጨመር ወይም ቅጠል ይዘው ወደ እሳት እንደመጠጋት እንደሆነ ያስጠነቅቃሉ ትንቢት ተናጋሪው፡፡ ለዚህም በአሁን ሰዓት (2009 ዓ.ም) በአማራና ኦረሚያ ክልሎች እየተከወነ ያለውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡  

ጎጃም ተቃጠለ ታባይ እስታባይ፤

ትግሬ ቅጠል ይዞ ሊያጠፋው ነወይ፡፡

  • የመሬት ይዞታና ተያያዥ ነገሮችን የሚመለከቱ ግጥሞች  

ለገበሬ በተለይም ለታዳጊ ሃገሮች አርሶ አደር መሬት የማይደራደርበት ብቸኛ ሃብቱ ነው በመሆኑም መሬቱን ሲነኩበት ያመራል፤ ምሬቱም ለከት አይኖረውም፡፡ ሼህ ሁሴን ጅብሪልም ይህን ያውቃሉና፤ መሬት ገበሬውን አቅል የሚነሳ ጉዳይ መሆኑንና መንግስት ግን በሰበብ አስባቡ ከመሬት ባለቤትነቱ እንደሚነጥቀው ያሳዩበት ትንቢታዊ ግጥም የሚከተለውን ይመስላል፤

በሮቸን አምጡልኝ አርጀ እበላቸው፤

ደሞ እንደ መሬቱ ሳይካፈሏቸው፤

ሌላው ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ገበሬውን ዕረፍት የነሳ ጉዳይ የመዳበሪያ ዕዳ መሆኑና አቅምን ያላገናዘበ፣ የግዳጅ ማዳበሪያ እዳ ለዚህ ዘመን ገበሬዎች መቆሚያ መቀመጪያ ያሳጣ ጉዳይ መሆኑን ቀድመው የተረዱት እኒሁ ሼህ እንዲህ ብለው ነበር፤    

ጊደሯም ተሸጠች፤ መሬቱም ተነዳ፤

አላስቀምጥ ቢለኝ፤ የማዳበሪያ ዕዳ፡፡

ከመሬት ይዞታ ባሻገር ገበሬው በምርቱም እንደማያዝ ያሳዩበት ግጥም ሲተነተን አምራች ገበሬ ወይም አካባቢ ያመረተውን በመኪና ጭነው ወስደው የሚቀለቡበትንና በስመ የውጭ ንግድ ወደ ውጭ ሃገር የሚጭኑትን ምርት በሚመለከት ደግሞ እንዲህ ብለው ነበር፤  

እናበቅል ነበር ሰርገኛ ከነጭ፤  

መኪና ወሰደው በላው ተቀማጭ፡፡

ተቀማጭ ማለት አንድም ቁጭ ያለ የተጎለተ ወይም ስራ የማይሰራ፤ የሚበላበት ዘመን በተቃራኒው የሰራ የደከመ ደግሞ ከምርቱ ተጠቃሚ የማይሆንበት ዘመን እንደሆነ ለማጠየቅ ነው፤ “ተቀመጥ በወንበሬ፤ ተናገር በከንፈሬ” እንዲል ስነ ቃል ባለስልጣን ወይም ወንበር የያዘ ሰው የሚበላበት ዘመንንም ይጠቁማል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ትንቢት ተናጋሪው የድሮን ገበሬና የዘንድሮ መንግስት ያነፃፀሩዋቸው ሲሆን የድሮው ገበሬ ቃል ኪዳነኛ የዘንድሮ መንግስት ግን ወራሽ እና ቀማኛ ናቸው ሲሉ እንዲህ ይገልጹታል፡፡

የድሮ ገበሬ አርሶ ይለምናል፤

የዘንድሮው መንግስት ወራርሶ ይበላል፡፡

ትንቢተኛው ሼህ የወያኔን መንግስት አሁን በህይወት ያሉ ያህል ያውቁታል እንሰኪባል ድረስ በእያንዳንዱ ጉዳይ ትንቢታቸውን አስቀምጠው አልፈዋል፤ መሬት ስሪቱ ጋር በተያያዘ የሚከተለውን ግጥም ብንመለከት መሬት የሚሰጣቸው በርካታ እንደሆኑና መሬት ስሪቱም የማይፀና መሆኑን በመግለፅ ምክራቸውን እንዲህ ነበር ለግሰዋቸው ያለፉት፤   

በወያኔ ጊዜ መሬት ያገኛችሁ፤

ድቡን አታርሱ ይረጋ መስሏችሁ፡፡

በተጨማሪም በርካታ የሃገሪቱ የመሬት ይዞታዎች በየመንደሩ፤ በየድንበሩ ለሃገር በቀልና ባዕዳን ቱጃሮች እንደ ዕቃ የሚቸበቸብበት እና መሬት እንደ ጓዝ ታስሮ ተቀርቅቦ የሚሰጥበትን ይህን ዘመን በትንቢታዊ ቃላቸው አልዘነጉትም፡፡   

መሬትም እንደ ዕቃ ሄደ ተወደነ፤

የኛ የነበረው ዛሬ የሰው ሆነ፡፡

  • የካድሬና ኮሚቴ ሥርዓት የሚመለከቱ ግጥሞች    

ሰው እጅግ ሲከፋው የፈጣሪ እርዳታን ይሻል፤ ይለምናል፤ ይማፀናል፤ ነገር ግን መከራው አላባራ ሲለው ምነው ፈጣሪ አንተ በመኖርያህ፣ በመንበርህ የለህም ሲል ይጠይቃል፤ እንዲያውም በጣም ሲያዝን ፈጣሪውን በበረታ ቃል ይገስፃል፤ ለዚህም ሼህ ሁሴን ጅብሪል ባልኖሩበት በዚህ ኮሚቴ እና ካድሬ እንደ አሸን ፈልቶ ህዝቡን ቁም ስቅል ስለአሳየበት ስለዚህ ዘመን በምሬት ለፈጣሪ ግሳጼ ያቀረቡበት ግጥም እንዲህ የሚል ነበር፤

ኮሚቴና ካድሬ ጣለብን እግዜር፤

አምላክ የለም መሰል ታለበት አገር፡፡

ቅኔያዊ ይዘት ያላቸው በርካታ ስንኞችን መቋጠር የተካኑት ሼህ ሁሴን በዚህ በዘመናችን ሰውን ያስመረረውን “በእግርህ መጣህ፤ በእጅህ” የሚሉትን የጉቦ አሰራር የሚያስረዳ ግጥምን የሰደሩ ሲሆን ይኸውም “ታለ ብር አይሄድም የኮሚቴ እግር” ሲሉ ላይ ላዩን ኮሚቴዎች ያለ ብር አምባር እግራቸው አይታይም ያሉ አስመስለው እግራቸው ከፅህፈት ቤታቸው የሚፈታው ገንዘብ (ብር) ይዘህ ከሄድክ ብቻ መሆኑን እንዲህ ገልጸውታል፤  

አንዱን ብንሾም አንዱን ብንሽር፤

ታለ ብር አይሄድም የኮሚቴ እግር፡፡

በተጨማሪም የዚህን ዘመን የኮሚቴ አሰራር እጅግ በበረታ ቃል ሲገልፁት በአሳማ ኮሚቴ፣ በጅብ ሊቀመንበር እና በጦጣ ፀሃፊ ይገልፁታል፤ ይህም ማለት ሆዳም ኮሚቴ፣ ጉልበተኛ ዳኛ (ሊቀመንበር) እና ብልጣብልጥ ፀሃፊ የሰፈነበት መሆኑን በሚከተሉት ስንኞች እንዲህ አሳምረው ገልፀውታል፡

ያሳማ ኮሚቴ፣ የጅብ ሊቀ መንበር፣ የጦጣ ፀሃፊ፤

አረ ተይ አንቺ ቀን ቶሎ ቶሎ እለፊ፡፡

አስከትለውም የዚህ አይነት አገዛዝ ወይም ዳኝነት መስፈን ፍፃሜውም የድሃውን ማህበረሰብ  መንከራተት፣ ስደትና ፍልሰት የሚያስከትል መሆኑን ትንቢት አዋቂው እንዲህ ተንብየው አልፈዋል፡፡  

እጅ መንሻ ፈላጊ ክፉ ዳኛ መጥቶ፤

ድሃው ተሰደደ የሚከፍለው አጥቶ፡፡

በመጨረሻም የዚህ ስርዓት ተጠባቂው ውጤት የህዝብ ዕልቂትና ሰላም መጥፋት መሆኑን እና በአሁኑ ወቅት በእጅጉ ሰፍኖ ስለምናስተውለው መንግስት አልባነት፤ ማን ሃገሪቱን እንደሚመራ እና ማን ችግሮቹን እያቀጣጠለ እንደሆነ በማይታወቅበት ሁኔታ ህዝባዊ ትግል (በቃኝ አልገዛም ባይነት) የተጧጧፈበት ይህ ዘመን ቀድሞ የተገለፀላቸው ትንቢተኛ ሼህ በግጥማቸው እንዲህ ብለው ገልፀውት ነበር፤

አቃጣዩ አይታይ በማዕና ክብሪት፤

ቲቀጣጠል ድራል ቀንና ሌሊት፤

አላህ ይጠብቀን ተንዲህ ያለው እልቂት፡፡

እርግጥ ነው፤ በዚህ ማህበራዊ ሚዲያው፣ መገናኛ ስጣኔዎቹ በተስፋፉበት ዘመን ማን ምን አደረገ ማለት እስኪከብድ ድረስ በመንግስት ተብየዎቹ ላይ በተነሳ ተቃውሞ ሰበብ በርካታ እልቂት እየተፈፀመ የሚገኝበትን ሁኔታ፤ ከትንቢቱ ጋር የሰመረ ትክክለኛው ወቅት ይህ ወቅት ስለመሆኑ አሌ አያሰኝም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የዚህ ዘመን መንግስት ሌላው መገለጫ ሰውን ሆድ ለሆድ እንዳይገናኝ የተደረገበትና ወንድማማች ህዝብ መካከል መጠራጠር፣ አለመተማመን እንዲሰፍን መደረጉን አስቀድመው ያወቁት ሼህ እንዲህ አሉ፤  

ውሸት ዘረዘረ ሃቅ እድሜ ጨረሰ፤

አሟጠው ቀበሩት ሰባት ጉድጓድ ምሰው፤

እንግዲህ ሆድ ለሆድ አልተገናኘም ሰው፡፡

ትንቢተኛው ሼህ በእንዲህ ያለ ወቅት የተገኘውን አቅርቦ መብላት እንደሚገባ የገለፁ አስመስለው በውስጠ ወይራ አነጋገራቸው ወቅቱ ያልተረጋጋ መሆኑን የገለጹት፡፡  

አተር ሽምብራውን ዝም ብለሽ አቅርቢው፤

እኛም አይተነዋል፤ የታመሰው ቀን ነው፡፡  በማለት ነበር፡፡

  • የቀደመውንና የዘመኑ አስተዳደር የሚነፃፅሩ ግጥሞች

“የወደዱትን ሲያጡ፤ የጠሉትን ይቀላውጡ” እንዳለ ስነቃል፤ ገበሬው (ህዝቡ) ብሎት ብሎት አልሆን ሲለው፤ አንቅሮ ተፍቶት የነበረውን መንግስቱ ሃይለ ማርያም መልሶ የሚመኝበት ግዜ እንደሚመጣ የሚያሳይ የትንቢት ግጥሞቻቸው ደግሞ ከዚህ በታች የቀረቡ ናቸው፡፡

እንደ ኮራ ሄደ እንደ ተጀነነ፤

አንድነት ወይም ሞት እንደተማጠነ፤

ስንዴው በሄልኮፕተር፤ በቆሎው በጀት፤

መንጌ ሃይለ ማርያም የድሆች አባት፡፡

መንጌ ሃይለ ማርያም አይሙት አይበላሽ፤

ለተራበው ስንዴ፤ ለጠገበው ክላሽ፡፡

መንጌ ሃይለ ማርያም ምን ምንህ ይረሳል፤

ብርድ ልብስህ አልቆ ኬሻህ ይለበሳል፡፡

ሼህ ሁሴን ጅብሪል ተስፋ ያደረግንበት ነገር ሁሉ መና ከቀረ የመጣውም የሄደውም ለሃገሪቱ ተስፋ ቢስ (ሁሉም ዝንጀሮዎች) ከሆኑ ምኑን ምርጫ አስገባን አደራውን ለፈጣሪ ሰጥቶ ቁጭ እንጅ ያሉበት ግጥማቸው ደግሞ የሚከተለው ነው፡፡

የመጣውም መጥቶ ተስፋ ካስቆረጠን፤

ከዝንጀሮ ቆንጆ ምኑን አስመረጠን፤

በመጨረሻም ያለፉትን አመታት ከያዝነው ወቅት ጋር፣ አምናን ከዘንድሮ አነፃፅረው ያምና የታች አምናውን እንደነገሩ እንዳሳለፍነው በመግለፅ መጭውን ዘመን ወይም አስተዳደር ደግሞ ምን አይነት ይሆን ሲሉ የህዝቡን ተስፋ የገለፁበት ስንኝ ደግሞ እንዲህ ይላል፡፡

አምናንም አለፍነው እንዳይሆን እንዳይሆን፤

ደሞ መክረሚያችን ዘንድሮ እዴት ይሆን፤

ማጣቀሻ፡ ቦጋለ ተፈሪ፣ 2007 ዓ.ም፣ ትንቢተ ሼህ ሁሴን ጅብሪል:: 7ኛ ዕትም አዲስ አበባ፡፡

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories