(ለአሁናዊ ሁነቶች መደላድል የነበሩ ቅድመ ተግባራትን በጨረፍታ ለመመልከት ከስምንት ወር በፊት ያሰፈርኩትን ፅሁፍ ልጋብዝ)
በፀጥታው ም.ቤት ሩሲያ ኢትዮጵያን በግልፅ መደገፏና ማንኛውም የምዕራባዊያን ጫና እንዳይደርግባት ስታስጠነቅቅ መታየቷ የግብፅንና ሩሲያን ግንኙነት በቅርበት ለሚታዘቡት የሚጠበቅ እና “በምክንያት ነበር የሆነው” ይላሉ ግብፃዊው የፖለቲካ ሰው። ለዚህ የሩሲያ አቋም በተለይም ከወራት ጊዜ ወዲህ የተከሰቱ ጂኦ-ፖለቲካዊ ክስተቶችን ማሳያ ያደርጋሉ፤ ግብፃዊው።
“ሩሲያ እንደምን ፊት ልትነሳን ጨከነች” በሚል ርዕስ ግብፃዊው ባቀረቡት ትንተና ላይ በቅርቡ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ም.ጠ.ምኒስትር ደመቀ መኮንን በሞስኮ ተቀብለው ሞቅ ያለ አቀባበል ማድረጋቸውን ያወሳሉ። ይህን ተከትሎ ላቭሮቭ የሰጡት መግለጫ እንግዳ በሆኑ አቋሞች ተሞልተዋል ሲሉ ይገልፃሉ ተንታኙ። ላቭሮቭ በትግራይ ግጭት ዙሪያ የኢትዮጵያን አቋምና የመረጠችውን ፖሊሲ አድንቀዋል፡፡ በትግራዩ ቀውስም ሆነ ከሱዳን ጋር ለተፈጠረው የድንበር ግጭት መፍሄው ኢትዮጵያ የምትከተለው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ እና ፖሊሲ እንጂ ማስፈራሪያዎች አይደሉም የሚለው የላቭሮቭ መግለጫም ሞስኮ በከፍተኛ ፍላጎት ወደ አዲስ አበባ ማዘንበሏን አመላካች ነበር ይላሉ።
“የሊቢያን ጉዳይ በሚመለከት ጀርመን ላይ በታቀደው ስብሰባ ዋዜማ ላይ ሌላ አስደንጋጭ መግለጫ በሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተላለፈው መልዕክት አስደንጋጭ ነበር ካሉ በኋላ “የውጭ ኃይሎች እና ቅጥረኞች ከሊቢያ መውጣታቸው አሁን ሳይሆን ቀስ በቀስ ተተግባሪ እንደሚሆን ጠቀሱ” ብሏል። ሩሲያ የቱርክን ፍላጎት በመደገፍ በጉዳዩ ዙሪያ ሁለቱ የተስማሙበት ይመስላል” ያሉት ግብፃዊው በዚያው በጀርመን በተደረገው ኮንፈረንስ ላይ ተሳታፊ መሆናቸውንም እግረ መንገዴን ልጥቀስ። ”ህብረቱ በኮንፈረንሱ ላይ ሐሳቡን የነ ሩሱያን አቋም መቀበሉ ቱርክ ኃይሏን ከሊቢያ እንድታስወጣ ማስገደድ ተስኖታል”። ይህም ካይሮ ከቱርክ ጋር ተገዳ እርቅ እንድታደርግ አስገደዳት። ሩሲያ በሊቢያ ጉዳይ የቱርክን አቋም መቀበሏን ተከትሎ ካይሮ በአንካራ ተይዞባት የነበረውን ብርቱ አቋም አለዘበላት።”
መንከባለሉን የቀጠለው የምዕራባዊያኑ ሽኩቻ ከጥቁር ባህር ተሻግሮ በአፍሪካ ምድር የቀይ ባሕርን ከለላ ይቀዝፈው ዘንድ በኢትዮጵያና ግብፅ ሰሞንኛ ፍጥጫ ላይ ጨዋታ በመለወጥ ጀመረ። “ታሪኩ የጀመረው ከአንድ ወር በፊት ነው” ይላሉ ግብፃዊው “አሜሪካ ከኔቶ ጋር በመሆን በጥቁር ባህር ከዩክሬን ጋር በሩሲያ የውሃ ድንበሮች አካባቢ የባሕር ኃይል ልምምድ ሲያደርጉ ሞስኮ አደገኛ አዝማሚያ ነው ስትል አስጠንቅቃለች፡፡ በዋሽንግተን የሩሲያ ኤምባሲም በይፋ የተቃውሞ መግለጫውን ማቅረቡ ይታወሳል። ይህ ፍትጊያ እየተንከባለለ የግብፅን ጉዳይ ተቀላቀለ። የአሜሪካ ጉዳይ እስከሆነ ድረስ ወደ ኋላ የማትለው ካይሮ እንደለመደችው አሚን አለች።”
“ሩሲያን ያስገረመው ሌላው ነገር የግብፅ መግለጫ ነበር። ይኸውም የአረብ አገራት ከሆኑት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሞሮኮና ቱኒዚያ ጋር የባህር ኃይል ልምምድ ተሳታፊ እንደምትሆን ማሳወቋ ነው። ሩሲያ በእነዚህ ይዞታዎች ላይ የሚደረጉ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ከትንኮሳዊ ርምጃ እንደምትቆጥረው ገልፃ ግብፅ እንዳትሳተፍ በግልጽ ነግራታለች። ግብፅ አንገቷን አዙራ ወደ ኋላ እንድትመለከት በማስታወስ ጭምር ሩሲያ አስረድታታለች።”
“ለዓመታት የግብፅን ጥቅም እንዳልነካችባት፤ በሁሉም መስኮች እንደደገፈቻት ነገረቻት። በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በኢኮኖሚ፣ በቱሪዝም፣ በወታደራዊ፣ በኢንዱስትሪና በጦር መሳሪያዎች ሽያጭ በተለይም በዳባአ የኑክሌር ፕሮጄክት እና ግብፅ የላቀውን SU – 35 የጦር አውሮፕላኖች እንዳቀረበችላት ዘርዝራላታለች”
“ግብፅ ለሩስያ ጥያቄ ይሁንታዋን ለመግለፅ ተቃርባ ነበር። ይሁንና የጋዛውን ግጭት ተከትሎ ለግብፅ ተሳትፎ እውቅና ሲሰጡ የተደመጡት ፕሬዝዳንት ባይደን ከፕሬዚዳንት ሲሲ ጋር ባደረጉት ውይይት የፈጠሩት ጫና ካይሮ ለ 12 ቀናት በወታደራዊ እንቅስቃሴው እንድትሳተፍ ሆነ”
በሌላ በኩል አሜሪካ በሱዳን ባሳደረችው ጫና ከአንድ አመት በፊት የተፈረመው የሱዳን-ሩሲያ የጦር ሰፈር ማቋቋም ስምምነት ለመሰረዝ ከሱዳናዊው ሉዓላዊ ወታደራዊ ምክር ቤት ውሳኔ ማግኘት ቻለ። እዚጋ ነው ሩሲያ ወደ ቀይ ባህር የምትመለስበትን አጋጣሚ ተስፋ ማድረግ የጀመረችው፡፡
ታዲያ “ወርቃማውን ዕድል በመጠቀም በሱዳን እና ግብፅ ፋንታ ኢትዮጵያን ለመተካት ወዲያውኑ ወሰነች” ሲሉ ሁነቱን ግብፃዊ ቁጭ አደረጉት።
“በርግጥም የአሜሪካ ልማዳዊ ባላንጣ የሆነችው ቻይናም ከሩስያ አቋም ጎን ለጎን ኢትዮጵያን ለመደገፍ መርጣለች” የሚሉት የካይሮ መንግስት የፖለቲካ ሰው “ከአስፈሪው ሁሉ የከፋው አደጋ የሩስያና የቻይና ድምፅን በድምፅ ሽረው ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ድጋፍ መስጠታቸው አይደለም” ይላሉ፤
እንደ’ሳቸው ገለፃ “ከሁሉም ፍርሃቶች ይበልጥ የሚያስፈራው አደጋ ሩሲያና ቻይና ኢትዮጵያን ላቅ ያሉ ዘመናዊ የአየር የራዳርና የሎጂስቲክስ ድጋፍ መስጠታቸው ነው” ሲሉ ይደመድማሉ።
🇪🇹esleman ABAY | የዓባይ፡ልጅ 🇪🇹