የብሔራዊ መግባባት ውይይት በቀጣይ ወር ሊካሄድ መታቀዱ ተነገረ

22 mins a

ከትጥቅ ትግል ውጪ ካሉ ውጪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሳትፋል የተባለለት የብሔራዊ መግባባት ውይይት በመጪው ወር ኅዳር እንደሚካሄድ ተነግሯል።

ሆኖም በውይይቱ ላይ ለመሳተፍ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኅዳር የመጀመርያ ሳምንታት ለማድረግ ግብዣ እንደቀረበላቸው ነግረውኛል ያለው ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ሌሎቹ ግን አልሰማንም እንዳሉ አስነብቧል።

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑሩ ወለላ “በኅዳር የመጀመርያ ወይም ሁለተኛ ሳምንት የሚካሄድ 500 ሰዎች የሚካፈሉበት ውይይት እንደሚኖር ጥሪ ቀርቦልናል” ማለታቸው ተመላክቷል።

ይሁን እንጂ የውይይቱ ዋና አመቻች ነው የተባለውና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ያቀፈው ማይንድ ኢትዮጵያ የተባለው ተቋም፣ የተቆረጠ ቀን አለመኖሩን ተናግሯል ተብሏል፡፡

የማይንድ ኢትዮጵያ የሥራ ኃላፊ ናርሶስ ብርሃን (ዶ/ር)፣ ‹‹ለማንም ፓርቲ የውውይ ጥሪ አላቀረብንም፤›› በማለት ለሪፖርተር ቢናገሩም፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን በመወከል ማይንድ በተባለው የውይይት አመቻች ጥምረት ውስጥ የሚካፈሉት የፓርቲያችን ሊቀመንበር ናቸው›› ሲሉ የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ገልፀዋል።

የብሔራዊ መግባባት ውይይትን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የባልደራስ ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻ በበኩላቸው፣ የደረሳቸው ጥሪም ሆነ ግብዣ አለመኖሩን በመጠቆም፣ ውይይቱ መቼና እንዴት ሊካሄድ እንደታሰበ እንደማያውቁ ገልጸዋል፡፡

ይህንኑ ፓርቲዎች ያቀረቡትን መረጃ በመመርኮዝ የብሔራዊ መግባባት ውይይቱ አንዳንዶችን አግልሎ ጥቂቶችን አካቶ ሊካሄድ ታስቦ እንደሆነ የተጠየቁት በሰላም ሚኒስትር የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ምግባሩ አያሌው፣ ‹‹የትጥቅ ትግል ከመረጡ ኃይሎች ውጪ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሳተፋሉ›› ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡ አቶ ምግባሩ አክለውም፣ ‹‹በምርጫ ሒደቱ የተካፈሉ ሁሉም ፓርቲዎች ይጋበዛሉ፤›› ያሉ ሲሆን፣ ግብዣ ያልቀረበላቸው ፓርቲዎች ወይም የተገለሉ ካሉ ድርጊቱ አግባብነት የሌለው መሆኑን በመጠቆም የሰላም ሚኒስቴር እንደማይቀበለው አስታውቀዋል፡፡

የውይይት ግብዣ እንደደረሳቸው ያረጋገጡት የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑሩ፣ የብሔራዊ መግባባት ውይይቱ ጉዳይ የአካሄድ ግልጽነት ያለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኦነግን፣ ኦብነግን፣ ኦፌኮን፣ ባልደራስንና ሌላውን ትተህ ብሔራዊ መግባባት አመጣለሁ ብሎ ማሰብ ተገቢነት የለውም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የብሔራዊ መግባባት አጀንዳን ከምሥረታው ጀምሮ አጠንክሮ ፓርቲያቸው ሲጠይቅ  መቆየቱን የተናገሩት አቶ ኑሩ፣ ‹‹የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ሆደ ሰፊነትና ሁሉንም አካታችነት ይፈልጋል›› ብለዋል፡፡ አሁን ግን በመንግሥት በኩል የራሱን ፍላጎት የሚያስፈጽሙ ኃይሎችን የማሠለፍና አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የመጓዝ አዝማሚያ መኖሩን አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ መግባባት ውይይት ገና መሆኑን የተናገሩት የማይንድ ኢትዮጵያ ሥራ ኃላፊ ናርዶስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በቅርብ ሊኖር የሚችለው ቅድመ ውይይት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹እኛ የውይይት አመቻች ነን፣ ማን እንደሚሳተፍ፣ በምን አጀንዳዎች ላይ፣ እንዴት እንደሚካሄድ አንወስንም፡፡ ውይይቱ ገና ነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ለሕዝብ ይፋ ስለምናደርግ እንነግራችኋለን፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የውይይቱ ጋባዥ ማን ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ ማይንድ ኢትዮጵያ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡

በቅርቡ ካቢኔያቸውን ያቋቋሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአገሪቱ ብሔራዊ ውይይት እንደሚኖር ጠቁመው፣ ውይይቱ ሰላማዊ ትግል የመረጡትን ብቻ የሚካትት መሆኑን መግለጻቸው አይዘነጋም።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች በተለይ በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ ባልተሳተፈው ኦፌኮ እና ሌሎችም ሲቀርብ ቆይቷል።

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories