የታሚል ታይገር አርፋጅ የሰላም ጥሪ እና ፍፃሜ


       የዓባይ፡ልጅ✍️

ከእንግሊዝ የ 133 አመታት ቅኚ ተገዢነት በኋላ፣ የቀድሞዋ “ሴሎን” ነፃነቷን የካቲት 4 1948 በተቀበለችበት በዚያው አመት ነበር በቁጥር አናሳ የነበሩት ታሚሎች አዲሱን የሀገራቸውን መንግስት ያማርሩና ይቃወሙ የጀመሩት። ይህ ስሜት እያደገ ቀጥለና አማፂ እስከማቋቋም ደረሰ። በወርሃ ሐምሌ 1983፣ የታሚል አማፂ በሲሪላንካ ሰሜን ጠረፍ የነበሩ ወታደሮች ላይ የደፈጣ ጥቃት ፈፅሞ 13 የመንግስት ወታደሮችን ገደለ። የታሚል ድርጊት በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ቁጣ ቀሰቀሰ። የታሚል አማፂያን ታዲያ ወረራውን፣ የደፈጣ ጥቃቱንና ግድያውን ቀጠሉበት።
[ያካተትኳቸው ዘመን መቁጠሪያዎች በሙሉ በፈረጆቹ ናቸው]

በወታደሮቹ ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ ከሁለት አመታት በኋላ የሲሪላንካ መንግስት ከታሚል ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር የመጀመሪያው የሆነውን ቀጥተኛ የሰላም ድርድር ለማድረግ ጥሪ አቀረበ፤ በሐምሌ 8፣ 1985 አመተ ምህረት)።

በዚህ የሰላም ሂደት ውስጥ ሀገረ ህንድ የድርሻዋን ለማበርከት ሐምሌ 29, 1987 ሰላም አስከባሪ ታስገባ ዘንድ ከስምምነት ተደረሰ። የሰላም ጊዜው ግን ከአጭር ጊዜ በስተቀር ሊሻገር አልቻለም። ታሚሎች ስምምነቱን አፍርሰው ውጊያውን እንደገና ጀመሩት። በዚህ ወቅት ትጥቅ እፈታለሁ ብሎ የኒውደልሂ ወታደሮች ገብተው እንዲያረጋጉ ፈቃዴ ነው ያለው የታሚል አማፂ  አፈሙዙን ወደ ሰላም አስከባሪው አዞረባቸው። ይተኩስና ይገድላቸው ገባ። መጋቢት 24 1990 የሕንድ ወታደሮች ቦታውን ለቀው ወጡ። የታሚል አማፂያንም በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠር ጀመሩ። ከ 1,200 በላይ ወታደሮችንም ገደሉ። የሕንድ ወታደሮች ቦታውን ለቀው ከወጡ ሶስት ወራት ቆይታ በኋላ የታሚል ታጣቂዎች ከስሪላንካ መከላከያ ሰራዊት ጋር ጦርነቱን አፋፋሙ። በውጊያውም አንድ ሶስተኛ የሀገሪቱን ግዛት በእጃቸው አስገቡ፤ ከባህር ዳርቻውም ሁለት ሶስተኛውን ተቆጣጥረው ጥቃታቸውን ቀጠሉ።

የቀድሞው የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ራጂቭ ጋንዲ በታሚል ሴት ታጣቂ፣ በደቡቧዊ ህንዷ ታሚል-ናዱ ግዛት ባደረሰችው የቦንብ ጥቃት ተገደሉ-ጊዜውም ግንቦት 21፣ 1991..። ታሚሎች በመቀጠል 1993 ግንቦት 1 ላይ የስሪላንካውን ፕሬዝዳንት ራናሲንግሄ ፕሪማዳሳ በአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ኮሎምቦ ውስጥ ገደሉ።

ከወቅቱ ፕሬዝዳንት ቻንድሪካ ኩማራቱንጋ ጋር የተስማማውን የ 100 ቀን ተኩስ አቁም በማፍረስም ታሚሎች ሚያዚያ 19, 1995 ላይ በስሪላንካ ሰሜን ምስራቅ ትሪንኮማሌ ወደብ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ።

በሲሪላንካ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ላይ በሰነዘሩት ጥቃት ቆመው የነበሩ ስድስት የሲሪላንካ አየር መንገድ አውሮፕላኖችን አወደሙ፤ ሰዎችንም ለህልፈት ዳረጉ። ይህን ጥቃት የፈፀሙት ሐምሌ 2001 ሲሆን፤ ይኸውም በኒውዮርክ ከደረሰው ጥቃት በመቀጠል በአለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ላይ የተሰነዘረ የከፋ ጥቃት ተባለ። በቀጣዩ አመት ማለትም የካቲት 23 2002፣ የሲሪላንካ መንግስትና የታሚል ታይገር አማፂያን በኖርዌይ አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራረሙ። ነገር ግን ታሚል ታይገር  በጥር 2008 ስምምነቱን አፍርሶ ወጊያውን ድጋሚ አስቀጠለ።

በየካቲት 22፣ 2009 የታሚል ታይገር አማፅያን ስሪታቸው በቼክ የሆኑ ባለ አንድ ሞተር አውሮፕላኖችን በመጠቀም በኮሎምቦ የቦምብ ጥቃት ፈፀሠ። በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍልም ጥቃቱን አጠናከረ። በዚህ ወቅት የሲሪላንካ መንግስት አማፂያኑን ለመደምሰስ ውሳኔ በማሳለፍ መጠነ ሰፊ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ጀመረ። በሂደትም በርካታ አካባቢዎችን ከአማፂው ማስለቀቅ ቻለ። ይህ ግስጋሴም ታሚል ታይገርን የሰላም ድርድር እስከመጠየቅ ያደረሰው ሆነ።
በዚህ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ወቅት አለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እየደረሰ ነው የሚል ጥሪ ማሰማት ጀመረ። በወርሃ መጋቢት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ሃላፊ “ሁለቱም ወገኖች በጦር ወንጀል ጥፋተኛ ሊሆኑ ይችላሉ።” በማለት ገለፁ። ተመድ መጋቢት 13 2009 ባወጣው ሪፖርቱ የስሪላንካ መከላከያ ሰራዊት በመልሶ ማጥቃት ዘመቻው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን ገድሏል በማለት አሳወቀ..። ይሁንና ስሪላንካ በተመድ የቀረበውን ክስ ውድቅ አደረገች። ይልቁንም ዘመቻውን አጠናክራ ቀጠለች..።

ታሚል ታይገር ከሲሪላንካ መንግስት ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነን በማለት ሚያዝያ 14፣ 2009 ላይ የሰላም ጥሪ አቀረበ። ይሁንና የመንግሰት ምላሽ  አሻፈረኝ የሚል ነበር..።

ግንቦት 18፣ 2009 የታሚል ታይገር አማፂያን ቡድን መሪ ፕራባካራን፣ መሽጎባት በነበረች አንዲት መንደር ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረገው ውጊያ በመንግስት ሃይሎች ተገደለ።
በቀጣዩ ዕለት… ስሪላንካ 37 ዓመታት የዘለቀውን የታሚል ታይገር አማፂ ቡድን ጥቃት፣ ሽብርና እምቢተኝነት መደምሰሷን ለመላው ዓለም በይፋ አወጀች – ግንቦት 19፣ 2009 – የዛሬ አሥራ ሶስት አመት..!

  #የዓባይልጅ Esleman Abay

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories