By, Esleman Abay የዓባይ ልጅ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከእንግሊዙ British airways ሰልጣኞችን ተቀብሎ፤ አሰልጥኖ፣ ብቁ አድርጎ ማስመረቅ የቻለው ያኔ ከአርባ አመታት በፊት እንደነበር ስመለከት ተገረምኩ። አፍሪካ በቅኚ ግዛት በወደቀችበት 1945 ተቋቁሞ የማሰልጠኛ ተቋም ባለቤት የሆነው በዚሁ ጥቁር ዘመን ከ 70 አመታት በፊት ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በከፈተበት ወቅት ኢትዮጵያ አንድም ዩኒቨርሲቲ ባልነበራት ዘመን ነበር። በአገሪቱ የነበሩ ሐይስኩሎች ቁጥር 10 ብቻ ነበር(1,700 ተማሪዎች የሚያስተምሩ)።
በወቅቱ ከ17 የአፍሪካ አገራት 300 ሰልጣኞችን በ Aircraft mechanics እና 32 ፓይለቶችን አስመርቋል። ለኬኒያ ጄቶች ጥገና እንዲሁም የ Zambia Airways ፣ በምዕራቡ አለም ለሚደገፈው የሰሜን የመን አየር መንገድ፣ ማርክሳዊ ለነበረው የደቡብ የመን አየር መንገድ ኮንትራት ወስዶ መስራት የቻለ ነው።
የአየር መንገዱ የከፍታ ጉዞ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲመሰረት ከአሜሪካዊው ግዙፍ የግል ኩባንያ Trans World Airlines ጋር ነበር። አሜሪካዊው ኩባንያ በሙሉ የኦፕሬተርነት ሚና እንዲኖረው እና በጥምረት ስራ ጀመረ። ጉዞው ስኬታማ ነበር።
ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ነሐሴ 19 ቀን 1985 የከተበውን ሰፊ ዘገባ መለስ ብዬ ስመለከት አየር መንገዳችን ያኔ ከ40 ዓመታት በፊትም የአፍሪካ ኩራት እንደነበር ያስረግጣል። አሜሪካዊው ጋዜጣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀልጣፋ፣ በደንበኞቹ እጅግ ምስጉን እና ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጥ ስለመሆኑ ሁሉም የሚመሰክሩለት ነው” ብሎ ፅፏል።
የኒዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛው ገለፃውን ቀጥሏል “ከአፍሪካዊ ባለሙያዎች አንፃር የተሻለ ደመወዝ የሚከፈላቸው ሠራተኞች ያሉት ኩባንያ ነው። ይህን ሁሉ ብቃት ያሟላ ኩባንያ በህሊናችሁ ሳሉ። ኩባንያው በዓለም ላይ በጣም ድሃ የሆነች አፍሪካዊት አገር ንብረት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው” ሲል ነበር የከተበው።
ዋሽንግተን ፖሥት ጋዜጣ ደግሞ በ1982 ዘገባው “Ethiopian Airline Prospers While Defying African Stereotypes” በሚል ርዕስ የፃፈው ቅኚ ግዛት በፈጠረው የአመለካከት መዛባት የተነሳ በቴክኖሎጂ ዘርፍ በነጮች መማር እንደታላቅ በሚቆጠርበት ዘመን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ ፓይለቶቹንና ሰራተኞቹን ሙሉ ለሙሉ በጥቁሮች ያከናወነ መሆኑን አትቷል። “የአፍሪካ አገራት ፓይለቶቻቸውን የኢትዮጵያው እንዲያሰለጥንላቸው ሲልኩ በከፍተኛ መተማመን እንዲሆን ማድረግ ችሏል። የኢንዱስትሪ አብዮት ፋና ወጊ ለሆነችው የእንግሊዝ British Airways ነፃ ስልጠና ለማቅረብ የቻለም ነው” Washington Post ከ40 ዓመታት በፊት ዕትሙ።
አየር መንገዱ በመንታ መንገድ ላይ
በ1974 በኢትዮጵያ የነበረውን አብዮት ተከትሎ መንበረ ስልጣን የተረከቡት ኮሎኔል መንግስቱ የመረጡት የሶቬት ሶሻሊስት ኮሚኒስት ርዕዮተ-ዓለም ከአሜሪካ ጋር ቅራኔ የፈጠረ ነበር። ይህም ለአየር መንገዱ አደጋን ደቀነ። አየር መንገዱን ከምስረታው ጀምሮ ገናና ስም እስካገኘበት ድረስ አሜሪካዊው Trans World Airways አብሮት ተጉዞ ነበር። አብዮቱን ተከትሎ ግን መቀጠል አልቻለም። በ1975 ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያለውን ጥምረት አቋረጠ።
አለምን በጎራ የከፈለው የሶቬትና አሜሪካ ፀብ በምዕራባዊያን ገበያ ላይ የተመሰረቱ ኢንቨስትመንቶችን የጎዳ ነበር። ሽኩቻው በአቪየሽን ዘርፉ ላይ ያደረሰው በደል ከገመትኩት በላይ መሆኑን የተረዳሁት ከማሌዢያው MH-17 አይሮፕላን አደጋ ጀርባ በቀዝቃዛው ጦርነት ሩሲያ በአሜሪካ ጫና “የአቪየሽን ገቢዋ ክፉኛ ከመጎዳቱ ጋር የሚያያዙ ቁርሾዎች የወለዱት ሊሆን ይችላል” የሚሉ ትንተናዎችን ከተለያዩ ምንጮች ካነበብኩ ስመለከት ነው። የያኔው የቀዝቃዛው ጦርነት ጦስ የተረፈው አየር መንገዳችን አጣብቂኙ ክፉኛ መታው። በወቅቱ በደርግ መንግስት የተላለፈ አንድ ያልተጠበቀ ውሳኔ አየር መንገዱ ዛሬ የአፍሪካ ሰማይ የንግስና ዙፋኑን ሳይነጠቅ ለመዝለቁ ዋነኛ ከሚባሉ መልካም ነገሮች ይጠቀሳል።
ጨዋታ ለዋጩ ውሳኔ
አየር መንገዱ አዲስ ስራ አስፈፃሚ ሾመ፤ በ 1980 እኤአ። ሰውዬው በኢትዮጵያ አየር መንገድ የ17 አመታት ልምድ የነበራቸው፤ በአሜሪካም ልምድ የጨበጡ የ53 አመቱ ካፕቴን ሙሐመድ አህመድ…።
ካፒቴን ሙሐመድ ሲሾሙ አየር መንገዱ በርዕዮተ አለሙ ሽኩቻ ከተሰተበት ኪሳራ በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችም ነበሩበት። ኒውዮርክ ታይምስ እንዳስነበበው “በአየር መንገዱ አላስፈላጊ ባለሙያዎች ተጠቅጥቆ ደሞዝ ። ቅጥር ከብቃት ይልቅ በዝምድናና ትውውቅ ነበር” የሚሉት ይገኙበታል።
አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ለአገልግሎት ጥራት መጠበቅና ብክነትን ለመቀነስ 3,700 ከነበረው ሰራተኛ ውስጥ 400 ዎቹን ቀነሱ። የአየር መንገዱን መዳረሻዎች ቁጥር ማብዛት ደግሞ ቀጣዩ ተግባራቸው ነበር። ይህ ግን ከባድ ነበር።
በአዋጭነታቸው የተመረጡ መዳረሻ ከተሞች ከምዕራብም ከምስራቅም አገራት የሚገኙ ናቸው። አንዳንድ አማካሪዎች ከሶቬትና ሌሎች ሶሻሊስት አገራት ትብብሩ ይቀጥል ብለዋቸው ነበር። ካፒቴኑ ግን አየር መንገዱ ቢዝነስ ተኮር ይሁን አሉ። የፖለቲካው ግምብ ይፍረስ ሲሉም አሰቡ። በሚገርም ሁኔታ የመንግስቱ ኃይለ ማርያም መንግስት ሃሳባቸውን ተቀበለ። ጉዳዩ አለማቀፍ ብዙኃን መገናኛዎችን አነጋገረ። በኮሚኒስቷ አገር የሚገኘው ስኬታማ ካፒታሊስት ኩባንያ እያሉ ፃፉለት። ” ETHIOPIA’S CAPITALIST AIRLINE ” በማለት 1985 ላይ የአየር መንጠዱን የአፍሪካ ንጉስነት የሚያትት ፅሁፍ ያስነበበው ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ነበር።
ይህን ተከትሎም አዳዲስ መዳረሻዎች ተከፈቱ። አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የመዳረሻው ቁጥር 31 ደረሰ። ወደ ሞስኮም በረራ ለመጀመር ስራ ተጀመረ። ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር በተጀመረ ግንኙነት 2 የቦይንግ 767 አይሮፕላኖች ግዢ ተፈፀመ። ከ Schweizer ኩባንያ ሞዴል B, AG-CAT ተርባይን በአዲስ አበባ እንዲገነባ ስምምነት ተደረሰ። በአጭር ጊዜም ወደ ቀደመ ትርፋማነቱ ተመልሶ የአፍሪካ ክብሩን አስጠብቆ ቀጠለ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰንደቃችንን እንዲሁም ድፍን አፍሪካን ከፍ እንዳደረገ አሁንም ቀጥሏል። በዬአመቱ ከሚያሳካቸው የከፍታ ሽልማቶችና የምርጥነት ደረጃዎች በተጨማሪ የሀብታም አገራት አየር መንገዶች በከሰሩበት የCovid19 ወረርሽኝ ወቅት በካርጎ አገልግሎቱ ያስመዘገበው ስኬት ከአለም ግምባር ቀደሙ አድርጎታል።
ህወሃት ወለድ የሆነው የሐሰት ወረርሽኝ በሱዳናዊት ጋዜጠኛ ኒማ ኢልባግር እና በ CNN አንዳንድ የኢዲቶሪያል አባላት ቅንጅት ገፅታውን ለማጠልሸት ቢሞክሩም የራሳቸው ውሸት የተስተባበለበት ሌላኛው የ CNN ዘገባ የቀረበው ከቀናት በኋላ ነበር። በአራት ዘርፎች የአለም ምርጥነት ዕውቅና በዚሁ ሳምንት ተጎናፀፈና በሱዳናዊት የጥላቻ ዘገባ ላይ ጥላውን ደቀደቀበት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ።
Esleman Abay የዓባይ፡ልጅ
ትዊተር