(እስክንድር ከበደ )
ኢትዮጵያ ፋይናንስ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራው ልኡክ ከአለም ባንክ፣ከአለምአቀፉ ገንዘብ ተቋም፣ከዩኤስ ኤድ ፣ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፤ ከአፍሪካ ቀንድ ረዳት ኃላፊዎች ጋር መነጋገሩ ተሰምቷል። እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ጋር የተደረገው ውይይትም በጦርነቱ የተጎደሐ በትግራይ፣በአማራና አፋር ክልሎች እንዲሁም በድርቅ ለተጋለጡ የሶማሌና ኦሮሚያ አርብቶ አደሮች እገዛ የሚደረግበት ሁኔታዎች መግባባታቸው ተሰምቷል።
የጠላትነት ሁኔታን ማርገብ ጨምሮ የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት የሚያስጠብቁ የሰላምና እርቅ ሂደቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መነጋገራቸው ተሰምቷል።
የሰብአዊ እርዳታ ያለምንም ገደብና ክልከላ እንዲደርስ ብልም መልሶ የማቋቋምና የተቋረጡ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መልሶ ማስጀመር ዙሪያ መነጋገራቸውን የሚኒስቴሩ ድረ ገጽ ይጠቁማል።
የአሜሪካ ባለስልጣናቱ ከኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ጋር በነበራቸው የአንድ ሳምንት ስብሰባዎች ፤በኢትዮጵያ እየደረሰ ያለውን የኢኮኖሚ ቀውስ መቋቋም የሚያስችል አዎንታዊ ድጋፍ እንደሚደረጉ ተጠቁሟል።
የልኡካን ቡድኑ ከገንዘብ ተቋማቱና የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር የተደረገው ውይይት ብዙ ሚስጥራዊ ነገሮች ቢኖሩትም፤ ኢትዮጵያ በጦርነት ምክንያት የደረሰባትን ቀውስ በአፋጣኝ መወጣት የሚያስችል ከፍተኛ የበጀት ድጋፍ ሊሰጡ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ከተፋላሚ ወገኖች ተወካይ መገኘት አለመገኘታቸው የተባለ ነገር የለም።
የኢኤምኤስ እለታዊ ኘሮግራም በትላንት ስርጭቱ ከትግራይ አንድ ባለስልጣን በአውሮኘላን መውጣታቸውና አሜሪካ እንደገቡ ጭምጭምታ መኖሩን የተናገሩ ሲሆን ይህ መረጃ ከእነ አህመድ ሺዴ ልኡክ ስብሰባ ጋር ስለመያያዙና እውነተኛነቱ አልተረጋገጠም። አሜሪካ በማአቀብ ስም “ዱላዋ”ን የምታሳርፍባት ኢትዮጵያ አሁን አካሄዷን መቀየር ያለመች ይመስላል። ከ”ዱላ” ይልቅ “ካሮት” መጠቀም አዝማሚያ እያሳየች መሆኗን እርግጠኛ ለመሆን ቀጣዮቹን ሳምንታት ወይም ወራት መጠበቅ ይኖርብናል።