የአቶ ልደቱ አያሌው “የአፍ ወለምታ” ሐቲትና የፓስተር ኤድሞንድ ብርሃኔ ስልታዊ ቃለመጠይቅ

ጌታሁን ሄራሞ

አቶ ልደቱ አያሌው ከቀናት በፊት ኢድሞንድ ብርሃኔ ከተባሉ ጠያቂ ጋር ያደረጉትን ቃለመጠይቅ ለመከታተል ዕድሉን አግኝቼ ነበር፤ ወደ አቶ ልደቱ ምልልስ ከመሄዴ በፊት ግን ስለ ጠያቂው የተወሰነ ነገር እንደመግቢያ ልበል።

ካልተሳሳትኩ አሁን ባለኝ መረጃ ጠያቂው ካናዳ ውስጥ የሚኖሩ መጋቢ(ፓስተር) ናቸው። ከሚያነሱት ጥያቄዎችም ፓስተሩ የሕወሓት ደጋፊ መሆናቸውን መገንዘብ ከባድ አይደለም፤ በኋላ አቶ ልደቱ ሚዛናዊ ሊያደርጓቸው ጣሩ እንጂ ፓስተር ኤድሞንድ በጦርነቱ ውጤት ዙሪያ ፈፅሞ ሚዛናዊ እይታ የላቸውም። ለምሣሌ ፓስተሩ በአንዱ ጎራ ተፈፀመ ስለሚሉት በደል በተደጋጋሚ ያንሱ እንጂ በሴኩ ቱሬ እንደተገለፀው ጦርነቱን ቀድሞ ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ስለመጀመሩ ፤ በሕወሓት ጦር እንደተፈፀሙ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጭምር በጥናት ስለተረጋገጠው የማይካድራንና ሌሎቹን ብሔር ተኮር ጥቃቶችን በተመለከተ አንዲት ቃል እንኳን ሲተነፍሱ አይስተዋልም። ይህም ብቻ አይደለም፤ ፓስተሩ ከጦርነቱ መንስኤ ይልቅ ውጤቱ ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል። ለትግራይ ሕዝብ መጎዳት የጦርነቱ ጫሪ የነበረችውን ሕወሓትን በመንስኤነት ተጠያቂ ከማድረግ በእጅጉ ተቆጥበዋል። አቶ ልደቱ ግን ይህን ኢ-ሚዛናዊ የፓስተሩን አካሄድ ለማቀናት ከአንዴም ሁለቴ ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል።

ጠያቂው ፓስተር ኤድሞንድ አቶ ልደቱ እንዲልሉላቸው የሚፈልጉትን ለማስባል የተጠቀሙት ስልት ግን ለየት ያለ ነው፤ በሚገርም መልኩ የአቶ ልደቱን ሥነ ልቦና ለመቆጣጠር ረዥም መንገድ ተጉዘዋል፤ በተወሰነ ደረጃም የተሳካላቸው ይመስላል። በአጭር ቃል ፓስተር ኤድሞንድ ብርሃኔ አቶ ልደቱ ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት ረዥሙን ጊዜ የፈጁት አቶ ልደቱን በማደናነቅ ነበር፤ በተለይም በቃለመጠይቁ ከ1:00 ጀምሮ የነበረውን ጥያቄ ከማቅረባቸው በፊት “ፖለቲካ በናንተ ጊዜ ምክንያታዊ አሁን ግን በጥላቻ የተሞላ” በሚል ንግግር ልክ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ በር ካስከፈቱ በኋላ ቀጥሎ በሚጠይቁት ጥያቄም አቶ ልደቱ ምክንያታዊ እንዲሆኑ በገደምዳሜ መልዕክት አስተላልፈዋል፣ እንደኔ ግምት ፓስተሩ አቶ ልደቱ በብዙዎች ዘንድ “ምክንያታዊ ፖለቲካን” በማራመድ እንደሚታወቁ መረጃው ስላላቸው ይህን ምክንያታዊነታቸውን በመድረኩ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ተማፅዕኖ የሚያቀርቡም ይመስሉ ነበር። እስቲ ፓስተር ኤድሞንድ ብርሃኔ የአቶ ልደቱን ሥነ ልቦና ለመስለብ የገበሩትን ግብር ቃል በቃል እንደሚከተለው ላስቀምጥ፦

“ድሮ እናንተ ፖለቲካ ውስጥ ስትቀላቀሉ በሐሳብ በምክንያት ትሞግቱ ነበር። አሁን ግን እርሱ ቀርቷል፣ አሁን ጥላቻ ነው…የሚነገረው ምክንያታዊ ፖለቲካ ሳይሆን ጥላቻ ነው… መቼም ከነርሱ በላይ በዕድሜም በዕውቀትም በፖለቲካም በመቆየት እነዚያ ሰዎች ከአቶ ልደቱ የተሻሉ ስላልሆኑ አቶ ልደቱን መጠየቅ ከሕወሓትም ከኢሕአዴግም ጋር ብዙ ሙግት እንዳሳለፉ በደንብ ያውቁታል፤ እኔ እርስዎን መጠየቅ የሚፈልገው አቶ ልደቱ በሕወሓት ማኒፌስቶ “የአማራ ሕዝብ ጠላት ነው” የሚል ተፅፎ አንብበዋል ወይ ሰምተዋል ወይ? እሄንን ከእርስዎ ቢሰማ ይሻላል፤ ምክንያቱም ከነዚህ ከወጣት እክቲቪስቶች ከምሰማ ይልቅ…እርስዎ ምን ይላሉ?”

በዚህ አቶ ልደቱን አደናንቆ ወደ ወጥመድ ለማስገባት በተደረገው ሙከራ ውስጥ  ጠያቂው አቶ ልደቱ ሙግት አዋቂ እንደሆነ፣ ከሌሎች ይልቅ  በዕድሜ፣ በፖለቲካና በዕውቀት የተሻለ እንደሆነ ሌላኛው ከአቶ ልደቱ በተቃራኒ የተፈረጀው ጎራ ግን ወጣቶችና አክቲቪስቶች መሆናቸው ተጠቅሷል። ይህን ቀድሞ ተጠያቂውን አደናንቆ የሚፈለገውን እንዲናገር የመገፋፋት ስልትን አንዱ ወዳጄ "The Argument from Appreciation" በማለት ሰይሞታል፣ የ"Argument from Intimidation" ግልባጩ ወይም ተቃራኒው መሆኑ ነው። የመጀመሪያው ተጠያቂን አሸንፎ ወደ ራስ ጎራ ለመጎተት የተጠያቂን "Intellectual Capability"ን ደጋግሞ የመጥቀስን ስልት ሲጠቀም፣ ሁለተኛው የተሟጋችን "Intellectual Impotence"ን በማጉላት በዝረራ ለማሸነፍ የሚነደፍ ዕቅድ ነው(በነገራችን ላይ ፓስተሩ ሁለቱንም ስልት ተጠቅመዋል፣ በእሳቸው ሚዛን "ወጣት አክቲቪስቶቹ" intellectually impotent  ናቸው)።*እንደዚያም ሆኖ ፓስተር ኤድሞንድ የመጀመሪያውን ዘዴ ከሁለተኛው ይልቅ  በቃለ መጠይቃቸው ውስጥ በተደጋጋሚ ለመጠቀም ሲሞክሩ ተስተውለዋል፤ ከዚህም የተነሳ የፅሁፌን ይዘት ከአቶ ልደቱ ምላሽ ይልቅ በፓስተሩ የአጠያያቅ ስልት ላይ ለማተኮር መፈተኔን እዚህ ጋ ግልፅ ማድረግ ይጠበቅብኛል። ይሁንና ተጠያቂን በአድናቆት በመሸላለም ሥነ ልቦናውን ስለ መስለብ ስልት ከኔ ይልቅ የሥነ ልቦናና የሪቶሪክ ምሁራን ቢመራመሩበት ይሻላል የሚል አቋም አለኝ።

አቶ ልደቱ ከዚህ ሁሉ የአድናቆት ጎርፍ በኋላ ሚዛኑን ጠብቆ ተገቢውን ምላሽ ይሰጥ ይሆን? በአጭር ቃል የፓስተር ኤድሞንድ ጥያቄ “ሕወሓት በማኒፌስቶው የአማራ ሕዝብ ጠላት እንደሆነ አድርጎ አስቀምጧል ወይ?” የሚል ነበር። ፓስተር ኤድሞንድ ይህ አባባል የትግራይን ሕዝብ ለመውጋት እንደ ስትራቴጂ ጥቅም ላይ ውሏል የሚል አቋም አላቸው። ታዲያ አቶ ልደቱ ለዚህ ጥያቄ በቃለ መጠይቁ 1: 03:18 ሰዓት ላይ ምላሽ መስጠት የጀመሩት የስላቅ በሚመስል ሳቅና ፈጋግታ ነበር(ከሥር ፎቶውን ይመልከቱ)። በመቀጠልም የፓስተር ኤድሞንድ ጥያቄ የራሱም ጥያቄ መሆኑን አሳወቀ። ጥያቄውን በተመለከተም ከ20 ዓመታት በፊት ለማጣራት መሞከሩንና ባለውም መረጃ …ሕወሓት በማኒፌስቶው የአማራ ሕዝብ ጠላት ስለመሆኑ ያሰፈረው ነገር እንደሌለ፣ ነገር ግን በመጀመሪያው ማኒፌስቶው የተፈረጀው የአማራ ገዥ መደብ እንደሆነ እና የሕወሓት ትግል ዓላማና ግብም የትግራይን ሪፐብሊክ መመስረት እንደሆነ… ገልጿል። በመቀጠልም አቶ ልደቱ በሕወሓት ማኒፌስቶ ስድስተኛው ጉባኤ ላይ እነዚህ ሁለቱም ይዘቶች መወገዳቸውን አሳውቋል። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ በአፍ ወለምታነት የአማራ ገዥ መደብ ለማለት ተፈልጎ የአማራው ብሄር እየተባለ እንደሚፈረጅ አቶ ልደቱ ጠቀስ አድርጓል። እዚህ ጋ ለአቶ ልደቱ ሁለት ጥያቄዎችን ላንሳ፦

  1. ከፅሁፍ መረጃነት አንፃር በ1968 ዓ.ም. የተለቀቀ “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት መግለጫና የትግሉ መመሪያ” እንደሆነ የተነገረለት አንድ ባለ 28 ገፅ ሰነድ(ማኒፌስቶ) አለ( ፋይሉን ለሚጠይቁን ማካፈል እንችላለን)። በዚሁ በአማርኛ ቋንቋ በተዘጋጀው ሰነድ ገፅ 15 እና 16 ላይ የአማራ ብሔር ጨቋኝ ከመሆንም ባለፈ የትግራይ የሶስት ሺህ ዓመታት ታሪክን እንደሰረቀ በተደጋጋሚ ተፅፏል። አቶ ልደቱ ይህን ሰነድ በተመለከተ ለምን ዝምታን መረጠ? ወይስ አያውቀውም? ሰነዱስ ትክክለኛ ካልሆነ ለምን ትክክለኛውን ጥቆማውን አልሰጠም?
  2. ሌላው “የአፍ ወለምታ” ከተባለው ጋር የሚቆራኝ ጥያቄ ነው። አቶ ልደቱ አንዳንድ የሕወሓት ሰዎች የአማራ ገዥ ለማለት ፈልገው የአማራ ብሔር እያሉ መግለፃቸውን በማይገባን መልኩ በአፍ ወለምታነት ፈርጇል። በእኔ እምነት አንድን የፖለቲካ ሐቲት ከመሬት ተነስቶ በአፍ ወለምታነት መፈረጅ በራሱ የአፍ ወለምታ ነው፤ ምክንያቱም Identification of a political discouse(speech) as a “slip of tongue” requires indepth psycholinguistic research and analysis. አቶ ልደቱ መቼና የት ጥናት አድርጎ ነው የአማራ ብሔር ጨቋኝ እንደሆነ በየመድረኩና በየቃለመጠይቆቹ የተነገረውን በአፍ ወለምታነት የፈረጀው? ስለ አፍ ወለምታ ንግግሮች ከተነሳ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ቃለመጠይቆች ውስጥ በተስተዋሉ የአፍ ወለምታ ንግግሮች ዙሪያ “Professional Journal of English Education” በተሰኘ ጆርናል ላይ ማርች 2021 የተለቀቀ ጥናት አለ። የጥናቱ ርዕስ ” SLIP OF THE TONGUE IN BARACK OBAMA INTERVIEW AT THE AXE FILE” ይሰኛል። ይህን ጥናት በተመለከተ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም። ነገር ግን “Siti Zulaihah” እና “Rohmani Nur Indah” የተባሉ የዘርፉ ምሁራን ከባራክ ኦባማ ንግግሮች ውስጥ በአፍ ወለምታነት የተፈረጁ ንግግሮችን ነቅሶ ለማውጣት የሄዱበትን ጥልቀትና ርቀት መጠቆም ግድ ይላል። እነዚህ ምሁራን ለጥናቱ ግብዓትነት ወደ 36 ማጣቀሻ መፅሐፍትን ተጠቅመዋል፤ በጥናታቸውም የኦባማ የአፍ ወለምታ ንግግሮችን በየፈርጁ ከፋፍለው ስድስት ዓይነት(The types of Slip of tongues) መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል። እነዚህም “anticipation, perseveration, transposition, substitution, blend, and haplologies” ናቸው። ሙሉ ጥናቱን በተጠቀሰው ርዕስ ገብቶ ከጎግል ማውረድ ይቻላል። እናም አቶ ልደቱ ለዚያውም እጅግ አደገኛ የሆነውን ሌሎችን ለማህበራዊ ድርጊትና ፍረጃ (Social action and prejudice” የሚዳርገውን የሕወሓትን ሰዎች ንግግር በአፍ ወለምታነት ለመመደብ አቅሙ ካለው ራሱ ከሌለውም ሌሎች የዘርፉ ሰዎች ያጠኑትን ጥናት በዋቢነት መጥቀስ አለበት። ከሁሉም የሚገርመው አቶ ልደቱ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች የአማራውን ብሔር በጅምላ ላለመፈረጅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር ያለው ነው። እኛ የምናውቀው ደግሞ ከሕወሓት የበታች አመራሮች ይልቅ ከፍተኛ አመራሮች በንግግራቸው ይህን የጅምላ ፍረጃ ሲከውኑ ነው። ለምሣሌ፦

2.1. አቶ መለስ ዜናዊ አዲስአበባ ከመግባቱ ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ በ1990 ዓ.ም. ከጋዜጠኛ ፖል ሄንዝ ጋር በነበረው ቃለ መጠይቅ ቀጣዩን የፖለቲካ ፕሮግራሙን ያስቀመጠው እንደዚህ በማለት ነበር፦

“The country will have to be a federation and there will have to be recognition of the right of every people in it to have autonomy. We can no longer have Amhara domination.”

አዚህ ምላሽ ውስጥ መለስ “የአማራውን በላይነት” እናክስማለን ያለውን አስምሩልኝ። እዚህ ጋ ምናልባት የገዥውን መደብ እያለ እንደሆነ ልንገምት እንችላለን። ነገር ግን ንግግሩ በጣም ግራ አጋቢ ነው፤ ለዚህም ነበር ጋዜጠኛ ፖል ሄንዝ “What do you mean by AMHARA domination? በማለት የጠየቀው። በመቀጠልም ጋዜጠኛው ንግግሩ በአማራው ገዥው መደብ ላይ ሳይሆን ሕዝብ ላይ ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ እንደሚኖር የጠቆመው እንደዚህ ነበር፦

“What do you mean by AMHARA domination? If this is your message, how do the people in the regions where you have recently advanced – – Lasta, Gaynt, Saynt, Manz, Merhabete, etc., all of which are inhabited predominantly by Amhara – – look on your movement?”

ለእኔ ይህ የጋዜጠኛ ፖል ሄንዝ ጥያቄ ከ"political phenomenology" እና "Discursive Theory" አንፃር መቃኘት የሚችል ግሩም ጥያቄ ነው። ንግግሮች ከላይኛው የፖለቲካ ሹማምንት ወደ ሕዝቡ በሚወርዱበት ወቅት የሚይዙት የትርጉም ብያኔ የራሱ የሆነ ኢቮሉሽን አለው። የአንድ ቃል ትርጉም ለብቻው ሳይሆን በወቅቱ ካሉ ተቋማት ድባብ፣ ተዛማጅ ቅጥያዎችና ተቃርኖዊ ፅንሰ ሐሳቦች ይቀዳል። በዚህም ሂደት የትርጉሙ ማህበራዊ ስሪት(Social construction) እውን ይሆናል፤ ይህም ማህበራዊ ስሪት ለማህበራዊ ድርጊት (Social Action) ጉልበት ይሆናል። ለምሣሌ መለስ ዜናዊ የአማራን የበላይነት ማክሰም ያለው ታች በሌላው ተቃርኖ ጎራ (እንደተጨቆነ በሚሰማው ዘንድ) የአማራ ዘር ገና ከማህፃን ሳይወጣ በሽል ደረጃ ከእናቱ ሆድ ተቀድዶ እንዲወጣ እርምጃ እንዲወስድ አቅም ይሰጠዋል። በገሃድ ያየነውም ይህን ነው። በዚህ ረገድ ከፖለቲከኞች ወደ ሕዝብ የሚለቀቁ አሉታዊ የፍረጃ ንግግሮች ትርጉም የቱን ያህል "evolve" እያረጉ መልካቸውን እንደሚለውጡ ለማጤን እ ኤ አ በ2014 ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አርጄንቲናዊው የፖለቲካ ንድፈ ሐሳብና የሪቶሪክ ፈላስፋ ኤርኒስቶ ላክላው (Ernesto Laclau)  በፖለቲካዊ ሐቲቶች (Political Discourses) ትርጓሜ ዙሪያም ያካሄዳቸውን ጠለቅ ያሉ ጥናቶቹን አስሶ ማንበብ ጠቀሜታ አለው። 

እናም ፖል ሄንዝ የመለስን የአማራ የበላይነትን የማክሰም ፕሮጀክት ከሰማ በኋላ ግራ ገብቶት ለጠየቀው ጥያቄ ከመለስ የተሰጠው ምላሽ ይህን ይመስላል፦

“These Amhara are oppressed people. When we talk about Amhara domination, we mean the Amhara of Shoa, and the habit of Shoan supremacy that became established in Addis Abeba during the last hundred years.”

መለስ ዜናዊ በፖል ሄንዝ ጥያቄ የተደናገጠ ይመስላል፤ እኔ ያልኩት ሁሉንም አማራ ሳይሆን “የሸዋ የበላይነትን ነው” በማለት መለሰለት፤ ይኼ ምላሹ ደግሞ ሌላ መሠረታዊ ጥያቄ የሚጭር ነው። ማለትም እ ኤ አ በ1990 አዲስ አበባ የሸዋ የበላይነት ነበር እንዴ? እሱ የሚጠቅሰው የፊውዳሉ ሥርዓት ከወደቀ 16 ዓመታት አልፏል እኮ፤ ደርግ እኮ ነበር ሥልጣን ላይ የነበረው። እናም መለስ ዜናዊ ታሪክን 16 ዓመታት ወደ ኋላ rewind ማድረግ የፈለገበት ምክንያቱ ምን ነበር? የሆነ ያላወራረደው የምኒልክ/ዮሐንስ ቁርሾ ይኖር ይሆን? የምር ይህ በጣም ጥናት የሚያሻው ጉዳይ ነው። እንደዚያም ሆኖ አቶ ልደቱ የአማራ ገዥ መደብ በሚለውም እንደማይስማማ በለሆሳስ ጠቀስ አድርጓል። በወቅቱ የገዥ መደብ ውቅር ውስጥ ሌሎች ብሔሮችም ስላሉበት መሠለኝ። እንዲሁም ዋላልኝ መኮንን ሕወሓት ራሱ በሚያደንቅለት ፅሁፉ የትግራይ ገዥን መደብ ከአማራው ገዥ መደብ ጋር አንድ ላይ መጥቀሱ ትዝ ብሎትም ይሆናል። ምክንያቱም መለስ ቃለመጠይቁን በሚያደርግበት ወቅት “ሁለቱም ገዥ መደቦች” ወደ ታሪክነት ተቀይረው ነበር።

ዋናው ጥያቄ… ይህ የመለስ የፖለቲካ ሐቲት በአቶ ልደቱ ዘንድ በአፍ ወለምታነት ይመደባል ማለት ነው? ከሆነ ነገሩ አስቂኝ ነው የሚሆነው። በነገራችን ላይ ዕውቁ የሥነ ልቦና ተመራማሪ ሲግመንድ ፍሮይድ በአፍ ወለምታ ላይ ጥናት አድርጎ ነበር፤ በእሱ ጥናት መሠረት የአፍ ወለምታዎች አንዳንዴም በተናጋሪው “subconscious” ውስጥ ተደብቀው አጋጣሚውን ሲያገኙ አፈትልከው የሚወጡ ስውር ፍላጎቶችና ዕቅዶች ናቸው…ሆድ ያባውን የአፍ ወለምታ ያወጣዋል እንደማለት መሠለኝ። እናም አቶ ልደቱ የአፍ ወለምታውን በፍሮይድ ላይ ተመስርቶ እየነገረን ከሆነ በከፊል ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል። ግን…ግን መለስ ለምን ታሪክን 16 ዓመታት ወደ ኋላ “rewind” አድርጎ “Play” የሚለውን ተጭኖ የሸዋ “supermacy” እንጉርጉሮ ሊያሰማን ፈለገ? ለምን? እንደዚህ ዓይነት የአፍ ወለምታ ብሎ ነገር የለም።

2.2. ልድገመውና አቶ ልደቱ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች የአማራን ሕዝብ በጅምላ ላለመፈረጅ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር ብሎናል። ታዲያ በአንድ ወቅት የሕወሓት ዋናው ሰውዬ የሆኑት አቦይ ስብሃት በብሔራዊ ትያትር በፕሮፈሰር መስፍን ወልደማርያም መፅሐፍ ምረቃ ላይ “አማራውን ኦርቶዶክሱን አከርካሪውን ሰብረናል” ብለው ነበር። ውድ አቶ ልደቱ ይህ ከአፍ ወለምታነት ይልቅ መሬት ላይ በገሃድ የተሞከረ ድርጊት ስለመሆኑ እኛ ለአንተ መንገር አለብን? በነገራችን ላይ በወቅቱ የፍትሕ ጋዜጣ የመጀመሪያው ዕትም ይህን የአቦይ ስብሃትን ንግግር ዘግባ ነበር።

2.3 አሁን ደግሞ ወደ ዶ/ር ደብረፅዮን ልወስዳችሁ ነው፤ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ከጦርነቱ በፊት የአማራን ጉርብትና በተመለከተ “ከትምክህተኛው ይልቅ የሱዳን ሕዝብ ይሻለናል” ብለው ነበር። አስፈላጊ ከሆነ የቪዲዮ መረጃ ይኸው፦https://fb.watch/cBPs3u4xwr/
እናም ይህ የአፍ ወለምታ ነው ማለት ነው? የሚገርመው ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ይህን ገልብጦ ወደድንም ጠላንም አማራ ጎረቤታችን ነው በማለት ተናግሯል…ይልቁን ይኼኛው የአፍ ወለምታ እንዳይሆን መስጋት ይሻላል።

2.4. ሌላው የትግራይ የመጀመሪያው ጦርነት እንደተጠናቀቀ የጌታቸው ረዳ የ”ሂሳብ እናወራርዳለን” ንግግሩ ነው። ቆይቶም ጌታቸው ይህን ንግግሩን ለማከም ብዙ ርቀት ተጉዟል፤ ንግግሩ ብዙ ዋጋ በማስከፈሉም እኔ ያልኩት የአማራ ሊህቃንን እንጂ የአማራን ብሔር አይደለም በማለትም ተናዝዞ ነበር። ይህም ቢሆን የሚያስኬደው አልነበረም። ለእነርሱ ሲሆን ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው፤ ለሌላው ሲሆን ግን ሊህቃኑና(ጌታቸው “ወጠጤዎች” እያለ የሚሰድባቸውን የአብን አመራሮችኝ ጨምሮ) ሕዝቡ ለየቅል ናቸው። እናም ከአማራ ሕዝብ ነጥሎ የአማራን ሊህቃን ማጥቃት በአማራው ሥነ ልቦና ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አይኖርም? አቶ ልደቱም በዚህ ሐሳቤ የሚስማማ ይመስለኛል፤ ችግሩ ይህንን የጌታቸውን ንግግር በአፍ ወለምታነት መመደቡ ላይ ነው። በነገራችን ላይ አንድ ንግግር ተደጋግሞ ከተነገረ የአፍ ወለምታ አይባልም። ትክክለኛ የአፍ ወለምታ ወዲያው ነው የሚታረመው፤ ይቅርታም ይጠየቅበታል።

በመጨረሻም የዚህ ፅሁፍ ዋና ዓላማ የፖለቲከኞችን ሽፍጥና ሴራ መግለጥ እንጂ ብሄሮችን እንደ ብሔር ፖለቲከኞቹ ማቃቃር አይደለም። ለምን እንደሆነ ባይገባንም ብልፅግናም ሆነ ሕወሓት አሁን ደግሞ አቶ ልደቱ የሕዝቡን ንቃተ ሕሊና አሳንሶ የማየት ችግር አለባቸው። በቃ በእነርሱ ግምት…ሕዝብ በሌላ ነገር ላይ ስለተወጠረ የምንለውን ሁሉ እንደወረደ ሰምቶ ያምነናል… የሚል ስሁት አረዳድ አላቸው፥ በኔ አተያይ የአብዛኞቹን የኢትዮጵያን ፖለቲከኞች ሕፀፅ ለመንቀስ ሽርፍራፊ ጊዜ በቂ ነው፤ የመሉ ጊዜ ፖለቲከኛ አሊያም የፖለቲካ ሳይንስ ሊቅ መሆን አይጠበቅብንም፤ ምክንያቱም ስህተቶቹ በጣም ተራ ናቸው፤ ውስብስብ አይደሉም፤ እንዲያውም ያለቃቅሱብናል እያልን አይተን እንዳለየን የምናልፋቸው ሕፀፆች ለቁጥር ያታክታሉ። የአማራም ሆነ የትግራይ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ ንቃተ ሕሊናው ፖለቲከኞቹ እንደገመቱት የወረደ አይደለም። ስለዚህም ውሸት አያስፈልግም። ሳትሸፋፍኑ እውነቱን ተናገሩ፤ ውሸት ሰልችቶናል መርሮናል። እናም ለፖለቲካ ሥልጣን ስትሉ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ከመጋጨት ተቆጠቡ። ይቅርታ መጠየቅ እንደ እሬት አይምረራችሀ። ትናንት “የሱዳን ሕዝብ ይሻለናል” ዛሬ ደግሞ ላለፈው ምንም ይቅርታ ሳትጠይቁ “አማራ ጎረቤታችን ነው” አትበሉ።

ሌላው የማሳስበው ፅሁፉ በሚመለከታው የፖለቲካ ሊህቃን ላይ ብቻ የፃፈ ነው፤ በተለይም ሕወሓት በተሄሰ ቁጥር “ይህ የትግራይ ሕዝብ ጠላትነት ነው” የምትሉ እባካችሁ አደብ ግዙ፤ በቃለመጠይቁ ፓስተር ኤድመንድ ብርሃኔ የትግራይ ሕዝብ በስመ ትግራዋይነቱ ብቻ ሲታሰር ከልደቱ በቀር የጮኸለት የለም ያለው በጣም ስህተት ነው፤ በበኩላችን ትግራዋይ በመሆናቸው ብቻ ያለጥፋታቸው በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንግልት ለደረሰባቸው በወቅቱ ድምፃችንን በገፃችን ላይ በሰፊው አሰምተናል(ሊንክ መስጠት ይቻላል)። እሑድ በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 በየልጆቻችን ኢትዮጵያ ፕሮግራም ላይ ከባልደረቦቼ ጋር በግልፅ አውግዘናል። ከማውገዝም ባለፈ ለትግራይ ሕዝብ ሀገር አቀፍ ቴሌ ቶን እንዲዘጋጅ ድምፃችንን በሶሻል ሚዲያ ስናሰማ ነው። ለዚህም የሐኪሞችን ቡድን ወደ መቀሌ ለመላክ ሙከራ ባደረግንበት ወቅት ከዚያው ከትግራይ በኩል ያሉ ፅንፈኞች “እስቲ መቀሌን አንድ ሰው በእግሩ ይርገጣት? እያሉ ያስፈራሩን ነበር። ትንሽ ቆይተው ደግሞ ይኸው ቡድን ለትግራይ ሕዝብ ድምፅ አልሆናችሁም የሚለውን ወቀሳ ለማዝናብ ይሽቀዳደም ነበር። ከኔ ጋር በተገናኘም ሕወሓት የት እንዳለ እንኳን የረሳው አንድ የቀድሞ ሕወሓት ተጋደላይ ከ10 ዐመታት ወዲህ እስከ ዛሬም ደረስ ሰው መሆናችንና ኢትዮጵያዊነታችን አጣምሮን ከእኔ ጋር አብሮ እየሰራ ይገኛል። ሕዝብን ከሥልጣን ጥመኛው የብሔር ፖለቲከኛ የመለየት ችግር የለብንም።
አመሠግናለሁ ።

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories