የአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካዊ ሽኩቻ ቀጥሏል


እስሌማን ዓባይ

ምሥራቅ አፍሪካ፣ ከሞቃዲሾ እሰከ አሥመራ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ሀርጌሳ፤ እንዲሁም በአዋሳኝ አካባቢዎቹ እያንዳንዱ ቀን በአዳዲስ ፖለቲካዊ ገቢር እየተገለጠና እያስገረመ ቀጥሏል። በዋነኛነት ደግሞ ዋሽንግተን ከሶማሊላንድ ጋር እስከ ደህንነት እና ወታደራዊ የሚደርስ ትብብር እንዲኖራት የሚጠይቀው ህግ እንዲተገበር አፅድቃለች። ይህ በቀጣናው ታሪክ የትልቅ ጂኦፖለቲካዊ ምእራፍ ጅማሮ የሚባል ነው።
“somaliland partnership act” የሚባለው “የሶማሊላንድ ትብብር ህግ” አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና፣ በቀይ ባህርና በኤደን ባሕረ ሠላጤ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ያለመ ሲሆን ከሶማሊላንድ ጋር በመከላከያና ዲፕሎማሲ ረገድ የምትመሰርተውን ግንኙነት የሚመለከት ነው። የትብብር ህጉ አሜሪካ የሱማሌላንድ ጦርን ታሰለጥናለች የሚል ይዘትንም የሚያካትት ሲሆን “American Institute of Somaliland” የተባለ ኮርፖሬሽን በሶማሊላንድ እንዲቋቋም የሚለውንም ይጨምራል። ህጉ በአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የፀደቀው በትናንትናው እለት ሲሆን ዋሽንግተን ለሞቃዲሾ የምትሰጣቸው ወታደራዊ ድጋፎችና አካሄዱን እንዲያጠናም ይጠይቃል።
በተያያዥ የቀጣናው ክስተት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ዛሬ ወደ አሥመራ ጉዞ ያደረጉ ሲሆን በፕሬዝዳንት ኢሳያስ ግብዣ መሠረት እንደሆነም ነው የተነገረው።
ሀሰን ሼክ ሞሐሙድ በፕሬዝደንታዊ በአለ ሲመታቸው ወቅት ፕሬዝደንት ኢሳያስ አለመገኘታቸው የሚታወስ ሲሆን የደስታ መግለጫም በተመሳሳይ አላስተላለፉም። ሀሰን ሼክ ቀደም ሲል ጉብኝት ያደረጉት የኤርትራ ጥብቅ አጋር ወደሆነችም ኢማራት እንደነበር ይታወሳል።

ከሶማሊላንድ ጋር ከአንዳንድ ድጋፍ በስተቀር መደበኛ ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ያልነበራት ዋሽንግተን አሁናዊ ተጨባጮች በአዲስ አካሄድ ትመጣ ዘንድ ግድ ያሏት ይመስላል። ‘single Somalia’ policy’ አሁን ላይ አልፎበታል ያሉት ረቂቁን ሲያዘጋጁ ከነበሩት ሴናተሮች አንደኛው ሲሆኑ በቀደሙ ጊዜያት ሞቃዲሾ ላይ ያዘነብል የነበረው የአሜሪካ ፖሊሲ ተለውጦ ሶማሊላንድን ማካተት ጀምሯል።

የበርበራ ወደብን አሜሪካ ለጦር ሠፈርነት ትጠቀምበት ዘንድ ሶማሊላንድ ሀሳብ ማቅረቧ የሚታወስ ሲሆን አሜሪካ ያፀደቀችው ህግ ገቢራዊነቱ እየታየ ከጦር ሰፈር መገንባት ለሶማሊላንድ ሉአላዊ እውቅናን እስከመስጠት እንደሚደርስም ተጠቁሟል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ፊርማቸውን ያኖሩበት አራተኛ አመት ዛሬ የደፈነ ሲሆን ይህን ተከትሎም የኤርትራ መንግስት ኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት ለኢትዮጵያና ለአጠቃላይ የቀጣናው ሀገራትና ህዝቦች በአንድነት እንቁም የሚል ጥሪ አቅርቧል።

አዲሱ የሶማሊያ መሪ በዋነኛነት ከኢማራት እንዲሁም ከቱርክ እና አሜሪካ ቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው ይገለፃል። ከቻይና ጋርም ቢሆን ደህና የሚባል ነው ቀደም ባለው የስልጣን ዘመናቸው ያንፀባረቋቸው አካሄዶች የሚያመላክቱት።
ይሁንና ኢማራት እና ቱርክ በአሁናዊው ተጨባጭ ለሩሲያ እና ቻይና አዲስ አሰላለፍ እያሳዩት ያለው ዝንባሌ እጅጉን እየጨመረ ይታያል። ፕሬዝደንት ኢሳያስም የቻይናውን belt and road initiative የፈረሙና ወደ ስራም ያስገቡ ናቸውና የሀሰን ሼክ የአስመራ መጓዝ የልውጠተ-ፖለቲካ ነፀብራቅ ነው ያስብለዋል። ህወሃት አዲሱ የሞቃዲሾ መሪ ፀረ-ኤርትራ ይሆንልኛል በሚል ተስፋ አድርጋ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ይሁንና በየትኛውም አመክንዮ ሊሆን የማይችል ምኞት ብቻ ስለመሆኑ ያኔም ለመረዳት የማይከብድ ጉዳይ ነበር።
በሀሰን ሼክ ሞሀሙድን የአስመራ ጉዞ ዙሪያ ለምእራባዊያን ጥቅም የሚያዘነብሉ የመረጃ ምንጮች አጀንዳውን በኤርትራ የሚገኙ የሶማሊያ ወታደሮችን ከመመለስ ጋር ቢያያይዙትም፤ ሶማሊላንድ ከአሜሪካ ያገኘችውን የትብብር ፊርማ ተከትሎ የቪላ ሶማሊያው ሰውዬ በማግስቱ ወደ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ይገሰግሱ ዘንድ አንገብጋቢው መግፍኤ ሰሞንኛው የአሜሪካ-ሶማሊላንድ ወረት ጋር ይገናኛል እላለሁ።

የዓባይልጅ Esleman Abay

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories