“…በኢትዮጵያ ዘመናትን የዘለቀው የብሔር ችግር አሁንም ነገሮችን ለውጦ የግብፅን ጥቅም ሊመልስ ይችላል”
- ግብፃዊ ‘ምሁር’
……………………………………………………………………….
“ኤርትራ በሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ የነበራት አቋም ፀረ ኢትዮጵያ ነበር፤ የግብፅ ደግሞ ደጋፊ..። አሁን ኤርትራ የአቋም ለውጥ ማምጣቷን መገንዘብ ተችሏል። ከቀናት በፊት oct. 13, ፕሬዘዳንት ኢሳያስ በሕዳሴ ግድቡ ባደረጉት ጉብኝትም ተገልጿል” Al-Monitor, ጋዜጣ በድረ ገፁ ዛሬ ላይ እንዳስነበበው…።
አል-ሞኒተር አስከትሎም, የኢሳያስ ያሁኑ ጉብኝት ግብፅ በግድቡ ዙሪያ አጎራባች አገራት ድጋፍ እንዲቸሯት በምታደርገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ እክል መሆኑን ገልጿል።
የአል-ሞኒተር ዘገባ ብዙ ጉዳጉድ ጨማምሮ ያመላክተናል…
የሕዳሴ ግድቡ በጠ.ሚ መለስ ዜናዊ አመራር ዘመን ጀምሮ ኤርትራ ኢትዮጵያን ስትቃወምና ግብፅን ስትደግፍ እንደነበር ያወሳው ሞኒተር በጥር 2016 በቴሌቪዥን በተሰራጨ ቃለ መጠይቅ ላይ “የህዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመጥቀምም፣ ሀይል ለማመንጨትም ሳይሆን ለሌላ ፖለቲካዊ አላማ የታሰበ ነው” ብለው እንደነበርም አስቀምጧል።
ኢትዮጵያና ኤርትራ ከሁለት አመት በፊት ለሰላም ፊርማ ቢያኖሩም ስምምነቶቹን ለመተግበር ባለመቻሉ ኤርትራ በግድቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ተፃራሪ ነበረች። ይህ አቋምም እስከ ሐምሌ 2020 የፀና ነበር፤ እንደ አልሞኒተር። ይሁን እንጂ ኢሳያስ በጉባ ተገኝተው ግድቡን ከጎበኙበት ዕለት ጀምራ አቋሟን ለውጣለችም ይላል ጋዜጣው። ኢሳያስ ባለፈው ሐምሌ 2020 በካይሮ ያደረጉት ጉብኝት አል-ሲሲ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ብቻ ለ 5ኛ ጊዜ መሆኑና ዋነኛ አጀንዳ የነበረውም የግድቡ አለመግባባት ነበር ይላል።
ፕሮፌሠር ታሬክ ፋህሚ በካይሮ ዩኒቨርሲቲ የአለማቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሠር ናቸው፤ በጉዳዩ ዙሪያ ለአል-ሞኒተር የገለፁት አተያያቸው “አፍሪካዊ አገራት አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን ያመላክታል። ከሁሉም በላይ በግድቡ ላይ ኢትዮጵያን ስትፃረር የነበረችው ኤርትራ ኢትዮጵያን መደገፏ…” የሚል ነው።
“ግብፅ በአፍሪካ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ከኤርትራ ጋር ተወዳጅታ መስራት አሁን ቀዳሚው ጉዳያችን ነው” ያሉት ደግሞ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ባለስልጣን ናቸው።
ኢትዮጵያዊውን ጋዜጠኛ አንዋር ኢብራሂምን አነጋግሯል አል-ሞኒተር። አንዋር በአረብኛ ቋንቋ በሚሰራቸው ዘገባዎቹና በታላላቅ ቴሌቪዥኖች በአረብኛው ቻናላቸው እየቀረበ ለኢትዮጵያ ከሚሞግቱት ውስጥ ነው። አንዋር “
የኢሳያስ ጉብኝት በዋናነት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የሠላም ስጋት ከደቀነው የህወሃት ጉዳይ ጋር ነው የሚያያዘው” ሲል አስተያየቱን ገልፆላቸዋል። “ኢሳያስ በቀደሙት የኢትዮጵያ መሪዎች ዘመን ግድቡን ሲፃረር ቢቆይም አሁን ግን ከግድቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ስራዎች በመጀመራቸው በግድቡ ድርድር ላይ ኢትዮጵያም በአቋሟ ፀንታ የምትቀጥል ይሆናል” ሲልም አክሏል።
በሌላ በኩል “ኤርትራ ስለ ግድቡ አለመግባባት ቁልፍ ሚና የሚኖራት በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ነው” ያሉት ደግሞ
በአፍሪካ ጉዳዮች የ Al-Ahram Center for Political and Strategic Studies ባለሙያ ናቸው። ሐኒ ረስላን የተባሉት እኒህ ባለሙያ “ግብፅ በግድቡ ችግር ላይ የጦርነት አማራጭን ብትወስን ኤርትራ የሚኖራት ጠቀሜታ መተኪያ የሌለው ይሆን ነበር” ብለዋልም። ሌላው የገረመኝ የሐኒ ረስላን አስተያየት ኢሳያስ ዛሬ ላይ ግድቡን ቢደግፉም የመጨረሻ አቋማቸው እንደሆነ መወሰድ የለበትም የሚለው ነው፤ ምክንያት ያደረገው ደግሞ በኢትዮጵያ ያለው የብሔር ችግር ውስብስብ ነው፤ ላለፉት ዘመናት የነበሩት እነዚህ የብሔር ችግሮች አሁንም ነገሮችን ተለዋዋጭ የማድረግ እድል ያላቸው ናቸው” የሚል ነው።
በመጨረሻም “በኢትዮጵያ ዘመናትን የዘለቀው የብሔር ችግር አሁንም ነገሮችን ለውጦ የግብፅን ጥቅም ሊመልስልን ይችላል” የምትለዋን ምኞት ምን አንድምታ እንዳላት ልብ እንበላት!
የዓባይ ልጅ | እስሌማን ዓባይ