የእስራኤል ኤምሬትስ ስምምነት በግብፅ የደቀነው አደጋ (2021)

የግብፁ Egyptian Centre for Strategic Studies, ECSS, ኦክቶበር ስድስትን የግብፅ “የድል በዓል” በማውሳት እንኳን አደረሳችሁ ያለው በዛሬዌዋ ዕለት ነው። ይህ ተቋም በተለይም የአገራችንን ገፅታና የዲፕሎማሲ ትግል አጠልሽቶ ለዓለም ለማሳየት ሲፍጨረጨር የምናውቀው ነው። በዛሬው ዕለትም “እንኳን ለኦክቶበር 6 የግብፅ ድል ቀን አደረሳችሁ” ብሎ ሲፅፍ ሴፕቴምበር 15,2020 በእስራኤልና UAE የተፈረመውን ስምምነት ተከትሎ ግብፅ ለአመታት የነበራት የዲፕሎማሲ አቅም ሊከስም ቁልቁል መንደርደር መጀመሩን ባላየ አልፎታል። ለነገሩ ለሀሰት የተቋቋመ ድርጅት ዕውነት “ለአህያ ማር” አይነት አይደል የሚሆንበት!

የእስራኤል UAE ስምምነት

አረብ አገራት UAE የእስራኤል ዋነኛ የንግድ አጋር የምትሆንበት ስምምነት ባለፈው Sept. 15 ተፈርሟል። ባሕረይንም የ UAE ን ጎዳና ተከትላለች። ይህ ለውጥ ለመካከለኛው ምስራቅ አዲስ ብርሃን የፈነጠቀ ነው ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው። ይህች በትራምፕ “አዲስ” የተባለችው የመካከለኛው ምስራቅ ፀሐይ ለግብፅ ጨለማን እንጂ ብርሃን አትሆንም። በርካታ ተንታኞችም ይህንኑ ነው እያሉ የሚገኙት። ግብፅ በአጭርም ሆነ በረጂም ጊዜ መረር ያለ ችግር የሚገጥማት ይሆናል። የትራምፕ “አዲስ ፀሐይ” ያደሉላት ግብፅን ሲያጨልም የበደሏት ኢትዮጵያን ግን በዘወርዋራው ፀዳል የሚያጎናፅፍ መፃኢ ፍሬ የመስጠቱ አዝማሚያ በርካቶችን የሚያሳምን-የሚያስተማምን እየሆነ ነው።

የእስራኤል-ገልፍ አዲስ የግንኙነት በገፅ-አንድ ላይ የሚፈጥረውና እየፈጠረውም ያለው ነገር የመካከለኛው ምስራቅ ጂኦ-ፖለቲካን መለወጥ ነው። የአሜሪካ አጋሯ እስራኤል በቀጠናው የባጀችበትን የስጋትና የባይተዋርነት ዘመናት ለውጦ የንግድና ዲፕሎማሲ አጋር አገር ያስገኘላት ሆኗል። የ Guardian ጋዜጣው ዕውቅ ተንታኝ David Hearst, እንደፃፉት ካይሮ አረብ አገራትን ከእስራኤል ጋር በማደራደር ለበርካታ አስርት አመታት ብቻዋን በበላይነት ስትዘውረው የነበረውን የመካከለኛው ምስራቅን ፖለቲካ ከጇ ነጥቆ ለሌሎች የሚሰጥ ነው የሚሆነው። የካይሮን ተፈላጊነት ወደ ኢምንትነት የሚቀይረው ምክንያት ደግሞ ካርዱን የሚረከቧት እነ UAE እንደ ግብፅ በነ አሜሪካ ርዳታ ጥገኛ አለመሆን ነው። ቁጥራቸው የበዛ እስራኤላዊ ኩባንያዎች በኢምሬትስ የተፈጠረላቸው ዕድል ካሁኑ ጮቤ እንዳስረገጣቸው Times of israel ማስነበቡም ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ በርግጥም ግብፅን የምታስረሳ አገር መሆኗን ያስረግጣል።
    በቀደሙት ጊዜያት ግብፅ የፍልስጤም ጉዳይ ዘዋሪ ነበረችና በጋዛ የእስራኤልና ሐማስ ተኩስ አቁም ስምምነትን፤ እንዲሁም የፋታህና ሐማስን ድርድር በካይሮ ታስተናግድ ነበር። እዚጋ ፋታህና ሐማስ የቅርቡን ጊዜ ድርድር ያደረጉት በባላንጣዋ አንካራ መሆኑም ታሳቢ ይሁን።

በ Shorouk News ፀሐፊና ተንታኝ የሆኑት ሙሐመድ ኢስማት ግብፅ ብዙ በጣም ብዙ ነገር የምታጣበት ሁኔታ እየመጣ ነው ብለዋል። “The entire Arab national security system, with all its military, political and economic dimensions, will be utterly dismantled” በማለትም ከትበዋል።

በዱባይና እስራኤል የሚገነባው የቱቦ መስመር የሚነጥቃት እልፍ ቢሊዮን ዶላር ሌላኛው የግብፅ አይቀሬ እጣ ሆኗል። የግብፁ ስዊዝ ካናል 193 k.m ርዝመት አለው። ኤሺያና አውሮፓን ለማገናኘት ተመራጩ ቦይ ነው። የዓለማችን 10 በመቶ ንግድ በዚሁ ካናል ያልፋል። በስድስት ወር ውስጥ ብቻ ከ 9 ሺህ በላይ መርከቦችን (581 ሚሊዮን ቶን ጭነት) ያስተናገደው ባለፈው 2019 ነበር። የዱባይ-እስራኤል ቱቦ መስመር መገንባት ታዲያ ግብፅ ከስዊስ ካናል የነዳጅ ድፍድፍ ማጓጓዝ የምታገኘውን ገቢ ይወስደዋል። ምክንያቱም ከአረብ አገራት ወደ አውሮፓ ድፍድፍ ለማድረስ ይህኛው አጭርና የተሻለ ዋጋ ስለሚኖረው። በሌላ ጎንም የዱባዩ DP world የሚገነባቸው በቀይ ባሕር ኢይላት, በሚዲትራኒያን ጫፍ ደግሞ አሽዶድ የተሰኙት የንግድ ማዕከል ከተሞች አሉ። በነኚህ ከተሞች መካከል የሚዘረጋው የባቡር መስመር ከአውሮፓ ወደ አረብ አገራት በስዊዝ ካናል በኩል ይገባ የነበረውን እልቆ ቢስ ጓዝ ይህኛው አማራጭ የሚሰጠው ሁለገብ ጥቅም ደምበኛ እንዲሆን ያስገድደዋል።

ከድፍድፍ ማስተላለፍ የስዊዝ ካናልን 20 በመቶ የሚጠጋ ገቢ የሚሸፍን ነው። “በእንቅርት ላይ” እንዲሉ አል-ሲሲ ካናሉን በ 12 በመቶ ለማስፋት ከ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ የግብፅ ባለሃብቶችን አጨናንቀው ቦንድ በማስገዛትና ገንዘብ በመቀበል በከንቱ መድከማቸው ነው።

እስራኤል የጋዝ export ምርቷን ለማዘጋጀት Liquefaction ማዕከሎቿን በግብፅ ማቋቋም አማራጭ የሌለው ምርጫ ነበር። ግብፅ ከዚህ ታገኝ የነበረው ገቢ እስራኤል ከ UAE ጋር የሚገነቡትን የንግድ መስመር ተከትሎ የራሷን ልትገነባ ነውና ይህም ሌላው የግብፅ ኪሳራ መሆኑ ነው።

ሳዑዲ አረቢያና UAE ያቀርቡት የነበረውን ፈንድ ማቋረጣቸው ደግሞ ከድጥ ወደ ማጥ አይነት መከራ በግብፅ ደቅኖ ነው የሚገኘው። Middle East Eye ይህን ክስተት ጨዋታ ለዋጭ ያለው ሲሆን የአቡ-ዳሐቢው መሪ ሙሐመድ ቢንዛይድ “የማይሞላ ባልዲ ላይ ገንዘቤን መፈጥፈጥ መቆም ያለበት ጨዋታ ነው” ማለታቸውንም አውስቷል።

በግብፅ ሁሉም አካባቢዎች የተነሳው ፀረ-አልሲሲ ተቃውሞም መዘንጋት የሌለበት ነው።

   በመጨረሻም፦ ግብፅ የመካከለኛው ምስራቅ ዲፕሎማሲ መዘውሯ ዘመን ሲያልፍበት ለአሜሪካም የሚኖራት ጠቃሚነት አብሮ እየከሰመ ይመጣል። ትራምፕ “deal of the century” ብለው የሠየሙት የእስራኤል-ፍልስጤም ጉዳይ አለማቀፍ ፊርማ የታከለበት ስምምነት አስተገብራለሁ ማለታቸው አሜሪካዊ ፖለቲከኞችም በስፋት ያወገዙት ነበር። ይሁንና ትራምፕ ይህን ውጉዝ የወረራ ውል ማስፈፀም እችላለሁ ብለው ሲነሱ የተማመኑት በግብፅ ነበር። በዚህ ቀመር የተሯሯጠችው ግብፅ ዓለም ጉድ እስኪል ድረስ ትራምፕ በግድቡ ድርድር ላይ “ገገማ አድሎ” ባገራችን ላይ በይፋ እስከማራመድ የደረሰ ተፈላጊነትን ከትራምፕ አግኝታ ነበር። ውጤት ባያመጣላትም። ግና የትራምፕ “deal of the century” ጉዳይን እስራኤል እንድታቆም በመስማማት ፊርማቸውን ያኖሩት እስራኤልና ኢምሬትስ፣ ግብፅ የተሠጣትን የቤት ስራ “በቃ ተይው…ቀርቷል” የሚል ውጤትን ይዞ ከተፍ አለ። ግብፅ የቀራት ነገር የለም። ሌሎች በርካታ አቅሞቿንም እያጣች ነው ይባላል።

የቀራት ነገር ካለም፣ ‘ከሐቁ ጋር ታርቃ በላቧ መብላት’

የዓባይ ልጅ | እስሌማን ዓባይ

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories