የዓባይ፡ልጅ✍️Esleman Abay
ዶክተር ሞሐመድ ሐፌዝ በውሃ ምርምርና ከግድቦች ጋር በተያያዘ እውቅ ምሁር ሲሆኑ አሁን ላይ ኳላላምፑር በሚገኝ ዩንቨርሲቲ ውስጥ ፕሮፌሰር ናቸው። በፖለቲካዊ አቋማቸው የአልሲሲ ተቃዋሚ ሲሆኑ በህዳሴ ግድቡ አለመግባባት ዙሪያ ግን ለአገራቸው በመወገን ምሁራዊ በሆነ ትንተናቸው ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ሲያንፀባርቁ የምናውቃቸው ናቸው። በአልሲሲ አስተዳደር እንደ ስርዓት የሚበሳጩ ናቸው። በተለዬ ደግሞ የግድቡን ጉዳይ በተመለከተ አልሲሲ ግብፅን እያዋረዱ ናቸው ሲሉ ነው የቆዩት። ይሁንና የሁለተኛው ዙር ሙሊትን መጨረሻ እስከሚመለከቱ አልሲሲን ከመውቀስ መቆጠብ ሲመርጡ ተስተውለዋል። ከህወሃት ጋር የሚደረገው ጦርነት የፈጠረባቸው የተስፋ ጉጉት ለዝምታቸው መራዘም ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ ነበር። ከግድቡ ድርድርም ሆነ ከአልሲሲ አስተዳደር ብሎም ከትግራይ ጦርነት የጠበቁት ተስፋ እንደ ጉም ተኖ ሲጠፋ መራራው ሐቅ የካይሮ ልሂቃን እርስ በርስ እንዲፋጠጡ ያስገደደ ሆኗል።
ለግብፅ መንግስት ቅርበት ያለው አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ግብፅ በ 2021 ክረም ያገኘችውን የውሃ መጠን በተመለከተ አሃዛዊ መረጃዎችን ማቅረቡ የውዝግቡ መነሾ ነበር። የግብፅ መንግስት እጥረት እንዳይኖር የሚያከናውናቸው የተባሉ ተግባራትን ዘረዘረ፤ በዚህም ግብፅ ባለፈው ክረምት ከናይል የደረሳት የውሃ መጠን 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው በማለት ቴሊቪዥን ጣቢያው እወቁት አለ፤ በዚህ ጊዜ ነበር ግብፃዊው ፕሮፌሰር ሙሐመድ ሐፌዝ ወትሮውንም የማይደግፏቸው አልሲሲ ሲነዙት የነበረው ውሸት ቋቅ አላቸው መሰል ንዴታቸውን መቆጣጠር የተሳናቸው…።
ጉዳዩን አስመልክቶ ከሚሊዮኖች በላይ ተከታይ ያለው የአልሲሲ ተቃዋሚ አክቲቪስት ዩቲዩብ ቻናል ፕርፌሰሩን ከማሌዢያ ኳላላምፑር በዙም ቃለ መጠይቅ አደረገላቸው፤ ፕሮፌሰር ሐፌዝ ባቀረቡት ማብሪያ የአልሲሲ መንግስትን “ውሸታሙ እረኛ” ያስባለ ትንተና ነበር ያቀረቡት።
ሙያዊ በሆነ አቀራረብ ተጨባጭ አሀዞችን እያቀረቡ የአልሲሲን መንግስት ውሃ አባካኝነት ገላለጡት። የውሃ እጥረት የሚሉት ችግር አለመኖሩንና ይልቁንም አልሲሲ ችግሮችን ለመቀነስ የሚጠበቅበትን የቤትስራ እንዳላከናወነ ማስረጃዎች እያስቀመጡ ገላለጡት።
ፕሮፌሰር ሙሐመድ ሐፊዝ ካጋለጡት መረጃ አንደኛው፣ በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ግብፅ 40 ቢሊዮን ሜትሪክ ኩብ ውሃ ወደ በረሃና ወደ ሜዲትራኒያን በከንቱ መድፋቷን ነው። የ2021 ክረምት ከተለመደው በላይ ከፍተኛ የጎርፍ መጠን የተመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ መንግስት በአስዋን ግድብ ከተጠራቀመው ውሃ ለገበሬው ቀናንሶ በማዳረስ ግድቡ ነፃ ቦታ እንዲኖረው አድርገው መጠባበቅ ነበረባቸው። ይህንን ግን አላደረጉም ነበር። ዘንድሮ ከፍተኛ ጎርፍ መምጣት የጀመረው በ June 27 ጀምሮ ነው። በዚህ ወቅት 182 ሜትር ከፍታ ከባህር ወለል በላይ ያለው አስዋን ግድብ ከያዘው ውሃ ላይ ቀንሰው ወደ ገበሬዎቹ ማሳ እና ኩሬ ማድረስ ሲገባቸው አለማድረጋቸው የሚመጣው አዲስ ውሃ በግድባቸው ማቆየት ሳይችሉ ቀርተዋል። የግብፅ ውሃ እና መስኖ መስሪያ ቤት የአስዋን ግድብን እስከ 179.9 ሜ. ከፍታው ድረስ ጢም እንዳለ ነበር አዲሱን የክረምት ውሃ የጠበቁት።
በወርሃ ነሐሴ ብቻ በዬቀኑ በአማካይ 800 ሚ.ሜ.ኩብ ውሃ ወደ ግብፅ ገብቷል ያሉት ፕሮፌሰሩ በነሐሴ ሱዳንም ድርሻዋን ቀድማ በመያዟ ሙሉው ወደ ግብፅ እንዲገባ ሆኗል። በዚህም በወርሐ ነሐሴ 25 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ሄዶላቸው ነበር። ነገር ግን በአስዋን ግድብ የውሃ አስተዳደርና የስርጭት ተግባራት ባለመስራታቸው የግብፅ ባለስልጣናት ውሃውን የበረሃና የሜዲትራኒያን ሲሳይ አድርገውታል። እስከ መጨረሻው ከፍታው በሞላው የአስዋን ግድብ ሰላሳ በሚደርሱ ማስተንፈሻዎች እያለፈ ተድፋፍቷል።
ፕሮፌሰሩ አክለውም በሐምሌ ወር ከጥቁር አባይ 5 ቢሊዮን ከአትባራ 4 ቢሊዮን ከነጭ አባይ 14 ቢሊዮን ደርሷቸዋል። በሐምሌና ነሐሴ በድምሩ 45 ቢኩሜ ውሃ ሄዶላቸው ነበር። ይሁንና ባለስልጣናቱ ቀድመው ባለመስራታቸው ይህ ውሃ በከንቱ ወደ ባህር ተደፍቷል።
ፕሮፌሰሩ ያቀረቡት መረጃ የግብፅ ባለስልጣናት ሊያስተባብሉ በፍፁም የማይቻል ነው። “20 ሚሊዮን ዶላር በዬአመቱ የምናወጣበት ሳተላይት አለን። በህዳሴ ግድቡ ውስጥ እንደሚገኝ ግብፃዊ የሚቆጠረው ሳቴላይታችን እያንዳንዷን የግድቡን ሙሌትና ግምባታ በየቀኑ እንቃኝበታለን። የጎርፍ መጠን መረጃም ልቅም ብሎ ይደርሰናል። ታዲያ ይህን ሳተላይት ተጠቅመው ካልሰሩበት አልሲሲ የማንን ጎፈሬ ያበጥራሉ” ፕሮፌሰሩ ይወቅሳሉ።
በተጨማሪነትም “ከሱዳን መስኖ ሚኒስቴር የውሃ ፍሰት ሪፖርት መቀበላቸውን በመግለፅ አልሲሲ ከዚህ በኋላ ሊርቅብን ሊቀልድብን አይችልም” ነው ያሉት። በዚህም ከሁለት ቀን በፊት ቀ August 29 አስዋን ሙሉ 182 ሜትር ድረስ ሞልቶ ነበር። በእለቱ ብዙ ጎርፍ ቢመጣም በከንቱ ባክኗል። ሙግታቸውን ከሱዳን ባገኙት መረጃ ያጠናከሩት ፕሮፌሰር ሙሐመድ ሐፌዝ በ August 27,28,29 ባሉት ቀናት ከጥቁር አባይ 664mcm ከነጭ ዓባይ 130mcm ከተከዜ/አትባራ 134mcm ሲሄድላቸው ነበር። ሱዳን ደግሞ ሁለተኛውን ሙሌት በመስጋት ቀድማ ግድቦቿን ሞልታ ነበር። ውሃ መያዝ ትታ ነበር። በዚህም ሱዳን ድርሻዋን ስትለቀው ነበርና ይህ ተደምሮ በዬቀኑ 1 ቢሊዮን ሜትሪክ ኩብ በድምሩም ነበር ከ 27 እስከ 29 August በ 3 ቀናት ውስጥ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ነበር የደረሳቸው። ታዲያ በዘንድሮው ክረምት 4 ቢሊዮን ውሃ ነው ያገኘነው የሚለው የግብፅ ውሃና መስኖ መስሪያ ቤት 45 ቢሊዮኑን የት አድርሶት ነው? ብለዋል። 4 ቢሊዮኑማ በሶስት ቀን ብቻ ያገኙት ነው በማለት።
ፕሮፌሰሩ ለአልሲሲ የማስተዛዘኛ ቅናሽ አስቀምጠውም ነበር። በዚህም ከ 45 ቢሊዮን ውሃ ውስጥ ለገበሬዎች 7 ቢሊዮን ሰጥተናል ያላችሁት ውሸት ቢሆንም ይያዝላችሁ፣ ተጨማሪ 10 ቢሊዮን ይቀነስላችሁ። ታዲያ ከ 45 ቢሊዮን ኪዩቢክ የተረፈው ውሃ የት ገባ?” ብለዋል። ፕሮፌሰሩ በአረብኛው “ፌራሁ? ፌራሁ? ፌራሁ?” በማለት የት ደረሰ የት ደረሰ…ሲሉ ጠይቀዋል።
በፕሮፌሰሩ ንዴት የፈነዳው መረጃ የተለያዩ ዕውነታዎችን ይፋ አድርጓል።
ፕሮፌሰሩ እንዳረጋገጡት ግብፅ በያመቱ የምታገኘውና ለ 85 አመታት የዘለቀው አማካኝ መጠን 84 ቢሊዮን ኪዩቢክ ነው። በሌላ በኩልም ግብፅ በአመት የምታገኘው ውሃ 55 ቢሊዮን ኪዩቢክ ብቻ አይደለም። ይልቁንም በእጅጉ ከፍ ያለ እና ሰርክ የሚናገሩት 55 ወይም ከዚያ በታች የሚለው መጠን ወደ ግማሽ የሚጠጋውን ውሃ ቀንሰው/ክደው ነው ማለት ነው።
በሌላ ማስረጃቸውም በሐምሌ ወር 6BCM በነሐሴ እስከ 20BCM በመስከረም 19BCM በድምሩ 45 ቢሊዮን በሶስቱ ወራት እናገኛለን ብለዋል። ይህ በ 3 ወራት ብቻ የሚያገኙት የውሃ መጠንም ለ 85 አመታት የዘለቀ አማካይ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ሐፊዝ ቀሪው 38 ቢሊዮን በቀሪዎቹ 9 ወራት እንደሚደርሳቸው ወደ ድምዳሜ ይወስዳል። በዚህም በክረምት 53 በመቶውን ያገኛሉ። ውሃውን ወደ ባህር ላለመልቀቅ ቢሰሩ ኖሮ ቀንሰውም ቢሆን ከሚናገሩለት አመታዊ የ 55BCM ውሃ 80 በመቶው በሶስት ወራት ብቻ የሚያገኙት ነው። በወጠኙ ወራት ውስጥም ለውሃው ከልብ ቢጠነቀቁለት ኖሮ ከ 55BCM ተጨማሪ 28 ቢሊዮን ውሃ በእጃቸው ነበር።
Esleman Abay #የዓባይልጅ