የዓለምን ታሪክ ከቀየርክ በኋላ ተራ ሆነህ መታየት አትችልም: አምባሳደር ሪድዋን ሁሴን

ኢትዮጵያ ዓባይን ስትገድብ የዓለም ታሪክ እየተቀየረ ነበር፡፡ ዓባይ ከኢትዮጵያ ይመነጫል፣ ወደ ሱዳንና ወደ ግብጽ ይፈስሳል የሚለው ትርክት ከሰው ልጅ መፈጠር ጋር አብሮ የኖረ ትርክት ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅና በአውሮፓ እንደ ዓባይ ያለ ረዥም ወንዝ ባለመኖሩ ስለ ዓባይ የማያወራ ጥንታዊ ሕዝብ አልነበረም፡፡ ግብጽ የአፍሪካ፣ የአውሮፓና የእስያ መገናኛ ናት፡፡ ለግብጽ ሕይወት የሚሰጠው ደግሞ ዓባይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የእስያ፣ የአውሮፓና የአፍሪካ ሰዎች ስለ ዓባይ የሚተርኳቸው ጥንታውያን አፈታሪኮች አሏቸው፡፡

የዓባይ መነሻው የት ነው? ይሄን ጥያቄ የጥንት ሥልጣኔ የነበራቸው ሕዝቦችና መሪዎች ሁሉ ጠይቀዋል፡፡ የግሪክና የሮም አማልክት ጠይቀዋል፡፡ መነሻውንም ለማየት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ የባቢሎንና የአሦር ነገሥታት ወደ ግብጽ ከመጡ በኋላ ወደ ደቡብ ለመውረድ ባይሳካላቸውም እስከ ታኅታይ ግብጽ ድረስ ፍለጋ ወርደዋል፡፡ የግሪኩ ንጉሥ እስክንድር ወደ ኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል መጥቶ ነበር፤ የሮም ነገሥታትም እስከ ሜርዌ ድረስ መጥተዋል፡፡
ከሮም ሥልጣኔ በኋላ ኃያላን የነበሩት ስፔንና ፖርቹጋል የመጀመሪያ አሠሳቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያደርጉ ከገፋፏቸው ነገሮች አንዱ የዓባይን ምንጭ ለመፈለግ ነው፡፡ በመካከለኛው ዘመን ሕንድ፣ ከዚያም ደቡብ ዓረቢያ፣ በመጨረሻም ደቡብና ሰሜን አሜሪካ በአውሮፓውያን እንዲታወቁ ያደረጋቸው ኢትዮጵያን ፍለጋ የተደረገው ጉዞ ነው፡፡

እስከ ቅኝ ግዛት ዘመን ድረስ የዓባይ ጉዳይ በአብዛኛው የኢትዮጵያና የግብጽ ጉዳይ ነበር፡፡ ግብጻውያን ኢትዮጵያ ዐቅም ያገኘች ቀን ዓባይን ትገድበዋለች ብለው እንደሠጉ ነው የኖሩት፡፡ በዐፄ ይስሐቅ ዘመን ዓባይን የሚገድቡ ባለሞያዎችን ፍለጋ ወደ አሪጎን(ምዕራብ አውሮፓ) ተጉዞ የነበረው የንጉሡ መልእክተኛ ጣብሪዚ፣ 13 የጥበበ ዕድ ባለሞያዎችን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ግብጾች የካቲት 20 ቀን 1421 ዓም ያዙት፡፡ ጣብሪዚ ተሰቃይቶ እንዲሞት ነው የተደረገው፡፡ የግብጹ ንጉሥ ጣብሪዚን ከገደለ በኋላ ‹ بينما تصعد إثيوبيا ستسقط مصر› ብሎ መናገሩ ይተረካል፡፡ ‹ኢትዮጵያ ከፍ ከፍ ካለች ግብጽ ትወድቃለች› ማለቱ ነው፡፡ በዚህም የተነሣ በሃይማኖትም፣ በንግድም የሚመጡ ሰዎቻቸው ነገሩን ሲከታተሉ ኖረዋል፡፡ ግብጽ በ18ኛውና 19ኛው መክዘ ራሷ ጦር ሰብቃ ዘምታ ኢትዮጵያን ለማዳከም ሞክራለች፡፡ አልተሳካላትም እንጂ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያን ጠላቶች በማገዝ ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ዕድገቷ እንዳትመልስ ስታደርግ ከርማለች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈለፈሉ ‹ነጻ አውጪ› ድርጅቶች ውስጥ የግብጽን ርዳታ የማያገኝ ድርጅት አልነበረም፡፡ ሕወሐት ደርግን ባሸነፈ ጊዜ መጀመሪያ ከጥቅም ውጭ የሆኑት በዓባይ ተፋሰስ ላይ የተሠሩ ሥራዎች ናቸው፡፡ የፓዌ ፕሮጀክትና የጣና በለስ ፕሮጀክት ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረጉ የእርስ በርስ ጦርነቶች ውስጥ ግብጽ አንደኛውን ወገን በመደገፍ ሀገሪቱን ለማዳከም ተጠቅማበታለች፡፡ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ያሏትን ዜጎችና ደጋፊዎች በመጠቀም ኢትዮጵያ የተሻለ ድጋፍ እንዳታገኝ ስታደርግ ኖራለች፡፡ ግብጽ ኢትዮጵያን በተመለከተ ሁለት ፖሊሲዎችን ስትከተል ነው የኖረችው፡፡ ከተቻለ ኢትዮጵያን ወደ ብዙ ትንንሾች መከፋፈል፤ ካልተቻለ ተጽዕኖ እንዳትፈጥር አድርጎ ማዳከም፡፡

አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት መያዝ ሲጀምሩ የዓባይ ጉዳይ የኢትዮጵያና የግብጽ ጉዳይ ብቻ መሆኑ ቀርቶ – የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የአውሮፓ ጉዳይ ሆነ፡፡ አውሮፓውያን ወደ ዓባይ ጉዳይ የገቡት በሁለት ምክንያት ነው፡፡ የመጀመሪያው በኢትዮጵያ አካባቢ የሚገኙ የታችኛውና የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮችን በቅኝ ግዛት ስለያዙ የዓባይ ተፋሰስ ጉዳይ ባለቤቶች ነን አሉ፡፡ ኢትዮጵያ የሌለችበትን ስምምነት እያዘጋጁ በቅኝ በያዟቸው ሀገሮች ስም መፈራረም ጀመሩ፡፡ አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀች በኋላም የቀድሞ ቅኝ ተገዥዎቻችን ጉዳይ ያገባናል ማለት ቀጠሉ፡፡

ሁለተኛው ምክንያታቸው የኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ካለመገዛት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአውሮፓ ያልተገዛች ብቸኛ የአፍሪካ ሀገር ሆና መውጣቷ ለአውሮፓውያን መልካም ምሳሌ አልሆነላቸውም፡፡ አፍሪካውያን፣ ላቲን አሜሪካውያን፣ እስያውያን፣ ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ እንዲችሉ ኢትዮጵያ የሞራል፣ የዲፕሎማሲ፣ የቁስና የሥልጠና ድጋፍ አድርጋላቸዋለች፡፡ በዚህ የተነሣ አንዲት በቅኝ ግዛት ያልተያዘች ሀገር ራሷን ችላ ስታድግና የሞራል ልዕልናዋን ስትጠብቅ መመልከት ለምዕራቡ ዓለም ሐፍረት ሆነበት፡፡ በዚህ የተነሣ ኢትዮጵያ ታሪክ የሚለውጥ ሥራ እንዳትሠራ ሲያደናቅፉ ኖረዋል፡፡ የዓባይ ግድብ ከእነዚህ አንዱ ነው፡፡

የምዕራቡ ዓለም በሁለት መንገድ የኢትዮጵያን የዓባይ ፕሮጀክቶች ሲያደናቅፍ ኖሯል፡፡ በአንድ በኩል በዓባይ ላይ የሚሠራ ፕሮጀክት በቂ የገንዘብ ድጋፍ እንዳያገኝ በማድረግ፤ ሁለተኛ ደግሞ ኢትዮጵያን በአሣሪ ስምምነቶች ለመጥለፍ በመሞከር፡፡ ኢትዮጵያ ይሄን ፈተና ለመወጣት በራሷ ገንዘብ ዓባይን ለመገደብ ተነሣች፡፡ በዚህ ጊዜ የምዕራቡ ዓለምና ግብጽ የግድቡን ፕሮጀክት ለማጓተትና ለማስቀረት ሦስት መንገዶችን ተከተሉ፡፡ አሣሪ ስምምነቶችን ማምጣት፣ የፕሮጀክቱን ጥራት መቀነስ እና የፕሮጀክቱን ሥራ ማጓተት፡፡

የመጀመሪያው ስትራቴጂ የፕሮጀክቱን ጥራት መቀነስ ነው፡፡ ለዚህ ዓላማ መሳካት ሜቴክ የሠራውን አሳፋሪ ሥራ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ የግድቡ ብረቶች አዲስ አበባ ውስጥ እየተቸበቸቡ ግድቡ በማይሆኑ ብረቶች እንዲሠራ የተደረገው ባለማወቅ አልነበረም፡፡ ፕሮጀክቱ ከመጠናቀቂያ ጊዜው በዘገየ ቁጥር የዋጋ መናር ይከሠታል፡፡ ከዚያም አልፎ ሥራቸውን ያጠናቀቁ ኮንትራክተሮች ወደ ሌላው ተግባር ባለመሸጋገራቸው የሚጠይቁት ከፍተኛ ክፍያ ይኖራል፡፡ ይሄም እስከ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች የሚደርስ ነው፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት መንግሥት በብልሐት የፈታቸው ሁለቱን ፈተናዎች ነበር፡፡ እነዚህ ሁለቱ ካልተሳኩ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲ ጫና ሥር አስገብቶ አሣሪ ስምምነት እንድትፈርም ማድረግ የመጨረሻው አማራጭ ነበር፡፡ ባለፉት ዓመታት በአሜሪካ መንግሥት፣ በአውሮፓ ኅብረት፣ በጸጥታው ምክር ቤት፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ምክንያት የተጠራውን ስሟን ማስታወስ ብቻ ለዚህ በቂ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዓባይን ለመገደብ የተከተለችው ስትራቴጂ ለግብጽ ምቹ አልሆነም፡፡ ‹እየተዋጋን እናመርታለን› ዓይነት ሆነባት፡፡ የግድቡ ሥራ አይቆምም፤ ውይይትምም ድርድርም፣ ምክክርም ካለ ጎን ለጎን እናስኬደዋለን፡፡ ገንዘብም ከራሳችን እንመድባለን፡፡ እንደምንም ብለን እንጨርሰዋለን፡፡ የሚለው አካሄድ ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ለመክተት የማይመች ሆነ፡፡

ይሄኔ የኢትዮጵያ ጠላቶች ወደለመዱትና ወደሚችሉት መንገድ መጡ፡፡ ኢትዮጵያን ከተቻለ መከፋፈል ካልተቻለ ማዳከም፡፡ አንድ የአፍሪካ ዲፕሎማት ባለፈው ሰሞን ‹ከአጠገብህ የነበረ ዛፍ ዋርካ እየሆነ ሲሄድ ዝም የምትለው የአካባቢ ጥበቃ ሰው ከሆንክ ነው፡፡ ፖለቲከኛ ከሆንክ ግን ዝም አትልም› ብሎ ነበር፡፡ ዓባይ ለ5000 ዓመታት በአካባቢው የነበረውን ታሪክ ነው ኢትዮጵያ እየለወጠችው ያለችው፡፡ ዓባይ የኢትዮጵያን አፈርና ዕጽዋት እየያዘ ወደ ሱዳንና ግብጽ ሲፈስ ኖሯል፡፡ ታሪኩ ይሄ ነው፡፡ አሁን ግን ዓባይ ተገድቦ ሊጠናቀቅ ነው፡፡

የዓለም ታሪክ ሊቀየር ነው፡፡ የዓባይ መገደብ አምስት ነገሮችን ቀይሯል፡፡

  1. የኢትዮጵያን የማድረግ ዐቅም አሳይቷል፣ ጨምሯል፡፡
  2. የዓባይን የ5000 ዘመን ታሪክ ቀይሯል፡፡
  3. የ5000 ዘመን የአፍሪካን፣ መካከለኛው ምሥራቅንና የአውሮፓን አፈ ታሪክ ለውጧል
  4. የኢትዮጵያን የአሠራር ባህል ቀይሯል፡፡
  5. የአካባቢውን ጂኦ ፖለቲካ ለውጧል

ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ዓባይን ገድባ ልትጨርስ ነው፡፡ ዓባይ በደለል እንዳይሞላ ቢልዮን ዛፎች እየተከለች ነው፡፡ ዓለም ስለ ስንዴ ችግር እያወራ በመስኖ ስንዴ አምርታ ወደ ውጭ እልካለሁ ማለት ጀምራለች፡፡ በቅርቡ የድንጋይ ከሰል አላስገባም፤ በቅርቡ ማዳበሪያ አመርታለሁ፤ በቅርቡ የብረት ድፍድፍ ከራሴ እጠቀማለሁ እያለች ነው፡፡ ወደብ ባይኖረኝም ባሕር ኃይል እገነባለሁ እያለች ነው፡፡ የፖለቲካ ስብራቶቿን ለማረምና የተሻለ ሀገረ-መንግሥት ለመገንባት ብሔራዊ ምክክር አካሂዳለሁ እያለች ነው፡፡ እናም ‹ከአጠገቡ ያለ ዛፍ ዋርካ ሲሆን፣ ዝም ብሎ የሚያይ ፖለቲከኛ ማነው?› ‹ዛፉ ዋርካ ከመሆኑ በፊት ስበር› ነው መመሪያው፡፡

እየቀየርን ያለነው ታሪክ ከባድ ስለሆነ የሚገጥመን ፈተናም ከባድ ነው፡፡ ትልቅ ሥራ ትልቅ ፈተና ያመጣል፡፡ ጠላቶቻችን የመጡት ሊያሸብሩን ነው፡፡ የምንመክታቸው ባለመሸበር ነው፡፡ ጠላቶቻችን የመጡት ሊያዳክሙን ነው፡፡ የምንመክታቸው በመጠንከር ነው፡፡ ጠላቶቻችን የመጡት ሊከፋፍሉን ነው፤ የምንመክታቸው አንድ ሆነን በመቆም ነው፡፡ በተለይም ሦስተኛው ሙሌት እስኪጠናቀቅ “ሁሉም በቦታው ዘብ ይቁም!” በተለይ ቤተ-ዕምነቶችን አማኞች ነቅተው ይጠብቁ። የኢትዮጵያ የጸጥታ ተቋማት አባላት በምድር፣ በባሕር፣ በአየር እና በሳይበር የሚመጡትን ጥቃቶች በየቀኑ እያከሸፉ ናቸው፡፡ በትራፊክ ፖሊስ ሪፖርት አንመራ፡፡ ከ1.3 ሚልዮን በላይ መኪኖች በሠላም ትናንት ወደ ቤታቸው ገብተዋል፡፡ ዜናው ግን አደጋ ስለደረሰባቸው 100 መኪኖች ብቻ ይናገራል፡፡

ፈተናው የሚቀጥል ቢሆንም በዋናነት ግን የዓባይ ግድብ እስኪጠናቀቅ ድረስ ጠላቶቻችን አሉን የሚሏቸውን ዱላዎች ሁሉ መሰንዘራቸው አይቀርም፡፡ ዓላማቸው መርሮንና ሰልችቶን ‹ከአሁን በኋላ ትተነዋል› እንድንል ነው፡፡ አንዳንዱ ጎረቤት በጠላትነት፣ አንዳንዱ ጎረቤት በቅንዐት፣ አንዳንዱም ‹ይህቺ ባቄላ ካደረች..› እያለ፣ ቢነሣብን አይግረመን፡፡ አምባሳደር ሬድዋን እንደሚለው ‹የዓለምን ታሪክ ከቀየርክ በኋላ ተራ ሆነህ መታየት አትችልም›
በዲያቆን ዳንኤል ክብረት✍️

GERD4All #ItsAfricanDam

የዓባይልጅ

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories