የዓባይ ልጆች እና ቁራዎቹ


እስሌማን ዓባይ

ዓባይ እና ኢትዮጵያ ላይነጣጠሉ ነገር ግን አንዱን ካሮት ሌላውን ዱላ አድርገው ፈረሶቻቸው የነበሩትን የግብፅ ሹማምንት በመረጡት መንገድ ለመግራት ሲጠቀሙባቸው ኖረዋል። የዚህ ጥልፍልፍ ሴራ ለኢትዮጵያ ረጂም የጭለማ ዘመንን አንብሮ ዘመናትን ሊሻገር ችሏል። ቄሳራዊያን ዓባይን ለግብፅ እንደ ካሮት ኢትዮጵያን ደግሞ ማስፈራሪያ ዱላ አድርገዋቸው ቆይተዋል።
ምክንያቱም ዓባይ በሚስጥራዊ ጉልበቱ ከወንዝነት ባሻገር የአለምን የጉልበት ማእከል ጠምጥሞ የያዘበት ስንክሳር ያለው በመሆኑ…። ይህም ተከታዩ ርእዮት ይጠነሰስ ዘንድ መነሾ ሆኗል..፤
“..ኢትዮጵያን የተቆጣጠረ ዓባይን ይቆጣጠራል፤ ዓባይን የተቆጣጠረ ግብፅን ይቆጣጠራል፤ ግብፅን የተቆጣጠረ ሜድትራንያንና ቀይ ባሕርን ይቆጣጠራል፤ ሜድትራኒያን የተቆጣጠረ ስዊዝ ቦይን ይቆጣጠራል፤ ስዊዝ ካናልን የተቆጣጠረ ዓለምን ይቆጣጠራል..”።

ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የተዳፈነ እውነት ይገለጥ ዘንድ የማያስቆሙት የተፈጥሮ ግዴታ ነውና ፈርኦኖቹ ተለጣፊ ቁራዎች የመሆናቸው ሀቅ ከአለም ከደባባይ መዋል ጀምሯል። ዘመን ተሻጋሪ ፀኃፍት በብእራቸው ስለጉዳዩ ያሰፈሩት ከረጂም ዘመናት በፊት ጀምሮ ነበር። ቤተሞን የተባለው ፈረንሳዊ ደራሲ ክታብ ውስጥ ተከታዩን እንምዘዝ..
“..ከማንም ሌላ ሀገር በበለጠ፣ የግብፅ የመኖር ዕድል የሚወሰነው በሙጥኝት ይዛ የቆየችው የመላ ሕይወቷ ዋስትና ምልክት የዓባይ ወንዝ ነው:: ይህም ከወንዙ ጋር በተለጣፊነት መቆየት፤ ከጊዜ ብዛት፣ ስለወንዙ ያላት አቋም በአጠቃላይ ዓይነ ሥውር ስላደረጋት በሕዝብ ምናብ፣ ወንዙ ከበረሀ በተአምር ፈልቆ፣ በወንዙ ከላይ ክፍል የውሃ ችግር እንደሌለ ተቆጥሮ፣ ችግርም ቢኖር ግብፅ ትኩረት የሰጠችው አቋሟ በማንኛውም አይነት ዘዴ ድርቀት ባጠቃው አፍሪካ እና ዝናብ በተቸረው አፍሪካ መካከል የሚገኘውን አካባቢ በቁጥጥሯ ሥር ማድረግ መቻል ነው።”
እናም፣ የዓባይን ምንጭ መቆጣጠር የሚለው የግብፅ ጥንታዊ ህልሟ ውላጅ ሁሌም ኢትዮጵያ ተሰውታ ወተቷ የሆነውን የዓባይ ውሃ ግን እወዳለሁ በሚል ተለጣፊ ከፍታ ላይ ዘመናትን ባጅታለች። ከድርሳናት ማህደር ማመሳከር የምንችለውም ይህንኑ ነው።
ናቢል አብደልፋታህ የተባለው ግብፃዊ የፖለቲካና ስትራቴጂ ጥናት ተመራማሪ ክታብ ውስጥ ተከታዩን እናጣቅስ።
“..በዓባይ ወንዝ እና በግብፅ ሀገራዊ ፀጥታ መካከል የውስጥ አካል ትስስር አለ። ይህም በግብፅ ሕዝብ ሕሊና በጥብቅ የተቀረፀውን ስሜት እንጂ ታስቦ የተደረሰበት ሁኔታ አይደለም። ዞሮ ዞሮ ሁሉም ነገር ከዓባይ ተነስቶ ተመልሶ ወደ ዓባይ ነው የሚመጣው የሚል እምነት አለኝ..”።

ከዚህ ሁሉ አዙሪት ለመውጣት የግብፅን ተለጣፊ ከፍታ መገንዘብ፤ የስካሁን ከፍታዋ የቁራ መሆኑን ለማስረገጥ ደግሞ ንስር መሆን፤ የራሳችን የሆነውን ከፍታ በተግባር እየተረጎሙ ወደ ላይ ከፍታው መውጣት። ትናንሽ አሳማሚ ተግዳሮቶችን ከሰነቅነው ራዕያችን በታች ደፍቀን ማሳነስ። ሀሰተኛ ከፍታ ለመሸመት ህሊናውን ገበያ ወስዶ ከሚቸረችረው ቁራ ጊዜ እና ጉልበትን አለማባከን። ተለጥፎ የሚነክስህን ቁራ ወደ ከፍታህ መውሰድ። በተለገሰህ የሀቅ ፀጋህ ቁራው መተንፈስ እስከማይችልበት የከፍታ ደረጃ መውጣትና በዚያም ብርቱ ሆነህ መዝለቅ።
የዓባይ ልጆች ሚስጥርም እንደዚያ ነው፤ የወንዙን ስንክዛር የተገነዘቡ፤ የመዳፎቻቸው ህብረታዊ ማእከል ላይ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚበጅ ነገርን ለማበርከት ብቻ የሚተጉ። እህልና ጉልበት የሚለግሱ ህዝቦች…የዓባይ ልጆች!

የዓባይልጅ Esleman Abay #GERD

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories