የአል-ሲሲ-ሳልቫኪር የሴራ ጠገግ እስከ የት?
ሚኒስትሩ ለምን ሞቱ?
✍️ እስሌማን ዓባይ ~ የዓባይልጅ
▪️ካይሮ በኢትዮ-ደቡብ ሱዳን መሀል
‹ደይሊ ኒውስ› የተባለው የግብፅ ጋዜጣ በ2016 ‹‹ደቡብ ሱዳን ጠንካራ ብሔራዊ የጦር ኃይል ለመገንባት የግብፅ ወታደራዊ ዕርዳታ ትሻለች፤›› የሚል ዘገባ ይዞ ወጣ፡፡ ጋዜጣው ያስነበበው የደቡብ ሱዳኑ መከላከያ ሚኒስትር ኮሌ ማንያንግ ጁክ፣ ከግብፁ አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ተገናኝተው መምከራቸውን ነበር፡፡
የደቡብ ሱዳን መከላከያ ሚኒስትር በወቅቱ፣ ‹‹ግብፅ በአካባቢው ብርቱ የጦር ኃይል ያላት አገር ሆናለች፤›› አሉ፣ ሀገራቸው ደቡብ ሱዳን የገጠማትን የርስ በርስ ግጭትና የደኅንነት ችግር ለመፍታት የግብፅ ድርሻ ከፍ ያለ እንደሆነም ሲገልፁ ነበር፡፡
በተመሳሳይ በ2007 ዓ.ም ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ካይሮ ተገኝተው ከግብፅ መንግሥት ጋር አንዳንድ ስምምነቶች መፈራረማቸው አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ የወጡ መረጃዎች መሰረት፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ግብፅ በአገራቸው የጋራ የውኃ ፕሮጀክቶች ለማከናወን ተስማምተው ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቶቹ ከመፈራረማቸው በፊት ወደ ጁባ ሁለቴም ሦስቴም ተመላልሰው የማግባባት ሥራ የሠሩት የወቅቱ የግብፅ ውኃና የመስኖ ሚኒስትር ሆሳም አል ሞግሃዚ፣ አልዋኒተር ለተባለ የአገሪቱ ጋዜጣ ጉዳዩን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡
‹‹የናይል ውኃን በጋራ ለመጠቀም ከደቡብ ሱዳን ጋር ይፋዊ በሆነ መንገድ ስንፈራረም የመጀመሪያችን ነው፤›› በማለት ግብፅ በናይል ላይ ያላት ታሪካዊ የሆነ የውኃ ድርሻን ለማስጠበቅ ያስችለናል ሲሉ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም “በሁለቱ አገሮች ስምምነት ሲፈጸም ይኼ የመጀመሪያ ቢሆንም፣ ደቡብ ሱዳን ከዋናዋ ሱዳን ስተገነጠል ግብፅ አንድ ትልቅ ቃል ገብታለች፡፡ ይህም ግድብ ለመገንባትና ንፁህ የመጠጥ ውኃ ለደቡብ ሱዳን ዜጎች ለማስገኘት ለታቀደው ፕሮጀክት ድጋፍ ማድረግ ነበር፡፡
በወቅቱ (ማለትም 2017) የፖለቲካ ተንታኞች ሲሉት የነበረው “ግብፅ በደቡብ ሱዳን ያላት ፍላጎት ቀደም ሲል በሱዳን ውስጥ በተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የተቋረጠው፣ ግብፅ በደቡብ ሱዳን የነበራትን ‹‹ጆንግሌ ካናል ፕሮጀክት›› የተባለውን ፕሮጀክት ከማስቀጠል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የግብፅ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ግን፣ አገሪቱ በደቡብ ሱዳን የምታከናውናቸው የውኃ ፕሮጀክቶች ከኢትዮጵያ የምታገኘውን ውኃ የማይተካ ቢሆንም አንድ አማራጭ መሆን ይችላል፡፡
2016 እኤአ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ሁከት የግብፅ እጅ እንዳለበት የሚያመለክቱ ማስረጃዎች በመንግሥት ሚዲያ የቀረቡ ሲሆን፣ የግብፅ መንግሥት ድርጊቱን እንደተለመደው መካዱ ይታወሳል።
ሁኔታዎች ይህን መልክ በያዙበት ወቅት ታዲያ የግብፁ ፕሬዚዳንት ከኢሳያስ አፈወርቂ፣ ከጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኦማር ጊሌ፣ እንዲሁም ከደቡብ ሱዳኑ ሳልቫ ኪር ጋር በካይሮ መክረው ነበር፡፡
በካይሮ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት አብደልፈታህ አልሲሲ ጋር ስምምነት የመፍጠራቸውን ወሬ ተከትሎ ሳልቫ ኪር፣ በግብፅ የሚደገፉ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች የደቡብ ሱዳን ምድርን እንዲጠቀሙ መስማማታቸው ሲወራ ነበር፡፡ ሬዲዮ ታሜዙጂ ስማቸው ያልተጠቀሱ የጁባ ባለሥልጣናትን በማነጋገር ባሠራጨው ዘገባ፣ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ለማስቆም የኢትዮጵያን መንግሥት መጣል በግብፅ እንደ አማራጭ ተይዟል፡፡ እንደ ዘገባው ይህን ለማሳካትም ከደቡብ ሱዳን ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡” ነበር ያለው።
በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተጠይቀው፣ ‹‹ይህ መረጃ መሠረት የሌለው ሐሜት ነው፤›› በማለት ነበር ለሪፖርተር ጋዜጣ የተናገሩት፡፡ አንድ ለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅርበት አላቸው የተባሉ ባለሥልጣንም፣ ‹‹ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን አትፈራም፤›› ማለታቸውን ዘገባው ጠቁሞ ነበር፡፡ ቃል አቀባዩ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በመርህ የምትመራ አገር በመሆኗ፣ በደቡብ ሱዳንና በግብፅ መካከል ሊደረግ የሚችል ግንኙነት አያሳስባትም፡፡ ‹‹ያ ማለት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ሊጎዳ የሚችል ማንኛውንም ስምምነት ሆነ ድርጊት ካለ ግን ሁሌም በጥንቃቄ እናየዋለን፤›› ነበር ያሉት።
▪️ነገረ ጆንግሌ
ግብፅ የአስዋን ግድብ ማጠናቀቋን ተከትሎ ከስምንት ዓመታት በኋላ ነበር በ1978 እኤአ፣ ጆንግሌ ቦይ የተባለውን ግዙፍ ፕሮጀክት በደቡብ ሱዳን በሚገኘው ጆንግሌ ግዛት ከካርቱም ጋር በጋራ ያስጀመረችው።
የደቡብ ሱዳኗ ጆንግሌ ግዛት ከ 2 ሚሊዮን በላይ የዲንካ፣ የኑዌር እና ሞርሌ ጎሳዎች መኖሪያ ሲሆን ፕሮጀክቱ ነዋሪዎቹን ለሁለት በመለያየት ከብቶቻቸው ምግብ ፍለጋ የሚያደርጉትን ጉዞ በማስተጓጎል እና አደጋ በመፍጠር ብዙ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑ በብዙ ጥናቶች ተመላክቷል። የግብፅ ለብቻ የመጠቀምና የሌላውን ጉዳት ያላገናዘበ አካሄድ በዓባይ ተፋሰስ ሀገሮች ተደጋጋሚ ቁጣ ሲቀስቅስ ይታወቃል።
የጆንግሌይ ካናል ፕሮጀክት እሳቤ በሱዳን የአንግሎ ግብፅ ቅኝ ግዛት አስተዳደር ዘመን 1898 ላይ የተጀመረ ሲሆን፤ የናይል ወንዝን የውሃ ፍሰት መጠን ከፍ ለማድረግ በማለም ነበር ስራዎቹ የተጀመሩት።
በ1945 እኤአ የሱዳን መንግስት የፕሮጀክቱን እቅድ የሚያጠና የምርምር ቡድን አቋቁሞ ነበር። በቀጣይ አመት 1946 ላይ ደግሞ የግብፅ የሥራ ሚኒስቴር የጆንግሊ ቦይን ለመቆፈር የቀረበውን ሀሳብ “የወደፊት የናይል ጥበቃ” በሚል ርዕስ አንድ ጥናት አሳትሞ ነበር። 1959 ደግሞ ግብፅ እና ሱዳን ለደቡብ ሱዳን ረግረጋማ ቦታዎች ጥበቃ ፕሮጀክቶች ዝርዝር ድንጋጌዎችን ያካተተ የናይል ውሃ አጠቃቀም ስምምነት ተፈራርመዋል። በ1969 የግብፅ-ሱዳን ጥምር የቴክኒክ ኮሚቴ ቦይውን ተግባራዊ ለማድረግ መቋቋሙን መረጃዎች ያሳያሉ።
በ 1971 ኮሚቴው ጥናቱን በማካሄድ ለግብፅና ሱዳን መንግስታት አቅርቧል። ጥናቱም የረግረጋማ አካባቢዎችን የውሃ ብክነት የመቀነስ ስራዎች እንዲፈቀዱ መክሯል።
የጆንግሌ ግዛት ሱድ ጨፌ እና ማቻር ረግረጋማ ቦታዎች መገኛ ነው። የሱድ ጨፌ ከሰሜን እስከ ደቡብ 500 ኪ. ሜትር እንዲሁም ከምስራቅ እስከ ምዕራብ 200 ኪ.ሜትር ሲሸፍን ከዚህ ውስጥ 60%ቱ ቋሚ የጨፌው አካል 40% ደግሞ እንደ ክረምቱ ክብደትና ቅለት የጨፌው አካል እንደሚሆን ይገመታል። ከዚህ ጨፌ ውስጥም ከ10-14 ቢሊዮን ሜትር ኩብ የሚደርስ ውሃ እንደሚባክን ብዙ ጥናቶች ያስረዳሉ። ግብፅ በዚህ ጨፌ ውስጥ ገብቶ ከሚባክነው የነጭ አባይ ውሃ ውስጥ እና ከ4.5 እስከ 5 ቢሊዮን ሜ.ኩብ ውሃ ማዳን የሚችለውን የጆንግሌ ቦይ ፕሮጀክት ከሱዳን ጋር ማስጀመሯ ተመልክቷል።
የጆንግሌ ቦይ 360 ኪ. ሜትር ርዝመት፣ 75 ሜትር ስፋት እና ከ4-8 ሜትር ጥልቀት ያለው መሆኑ ዲዛይኑ ያስረዳል። ሆኖም ግን ስራው ከ260 ኪ.ሜትር በላይ መጓዝ አልቻለም።
ደቡብ ሱዳን እንደ አገር ከተመሰረተች በኋላ ግብፅ የተቋረጠውን ፕሮጀክት ለማስጀመር በተለያየ ጊዜ ጥረት ብታደርግም የመሳካት እድሉ ግን አነስተኛ ሆኖ ተስተውሏል።
የጆንግሌ ቦይ ፕሮጀክትን ለማስጀመር ሱዳንና ግብፅ በጋራ Compagnie de Conatruction International – CCI ከተባለው የፈረንሳይ ተቋራጭ ጋር 1978 ባደረጉት ውል ነበር ስራው የተጀመረው። ነገር ግን የወቅቱ የሱዳን መሪ ጃፋር ኒሜሪ ከጆንግሌ ቦይ በተጨማሪ በደቡብ ሱዳን ያስጀመሩት የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮና የሼሪያ ሕግ ለመተግበር አዋጅ ማፅደቃቸውን ተከትሎ የደቡብ ሱዳንያውያንን አመፅ አቀጣጠለ። ወደ ርስበርስ ጦርነት እንዲያመራም ምክንያት ሆነ።
ሌላው ክስተት በኮ/ል መንግስቱ የሚደገፈውና ጦር ካምፑን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሚዛን አማን አቅራቢያ ያደረገው በጆን ጋራንግ የሚመራው የደቡብ ሱዳን አማፂያን ቡድን የጆንግሌ ቦይን ለመቆፈር የምታገልግለውን አምስት ፎቅ የምትረዝም ኤስካቬሽን ማሽን በሚሳይል ማውደሙ ነበር።
የኤክስካቬሽን ማሽኗ ሉሲ ወይም ሳራ ተብላ የምትታወቅ ነበረች። ባለ ሶስት ሜትር 180 ዲግሪ እየዞሩ የሚቆፍሩ 12 አካፋዎች የተገጠሙላት፤ የቆፈረችውን አፈር በኮንቬየር ቤልት ወደ ምስራቅ የቦይ ክፍል የምትተፋ፤ ይኸውም ከአጠገቡ ለሚሰራው መንገድ እንዲያገለግል የሆነ፤ በቀን 40,000 ሊትር ነዳጅ የምትወስድ ነበረች ሉሲ/ሳራ ኤክስካቬተር። ይሁንና የጆን ጋራንግ ሀይሎች ያስወነጨፉት ሚሳይል ማሽኗን አውድሞ የስራ ተቋራጩን ቢሮ ጨምሮ አራት ሰራተኞችንም ገደለ፤ ስራውም በዚሁ እንዲቆም ምክንያት ሆነ።
▪️ የጆንግሌ ቁፋሮ ለደቡብ ሱዳኑ ምኒስትር ቀብር?
ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት በጥቅምት ባለፈው አመት 2021፣ ከግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ጋር ተገናኝተው ስለደቡብ ሱዳን ፖለቲካዊ መረጋጋት፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፀጥታ ጉዳዮች ባካተተ አጀንዳ ላይ መምከራቸው ይታወሳል።
የግብፁ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት በመግለጫው “ጉብኝቱ የግብፅና ደቡብ ሱዳን ታሪካዊ ግንኙነትን ያደሰውን ምእራፍ የከፈተ ነው።” ማለቱን ግብፃዊ ሚዲያዎች ሲያራገቡት ነበር። የአልሲሲ ፅህፈት ቤት አክሎም “የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጉብኝት ተምሳሌታዊና ለአዳዲስ የትብብር መስኮች እድል ፈጣሪ ነው።” ብሎ ነበር በመግለጫው።
በዚህኛው ምክክር ደቡብ ሱዳን ለግብፅ ባለሃብቶች የእርሻ መሬት አቅርቦት፣ በደቡብ ሱዳን የትምህርት ማዕከላት በማቋቋም ግብፃውያን ለደቡብ ሱዳናውያን እውቀት እንዲሰጡ በመግባቢያ ስምምነት ላይ ተወያይተዋል። ለዘመናት ተቋርጦ የቆየውን የጆንግሌ ቦይ ፕሮጀክት ወደ ስራ የማስገባቱ ውሳኔም ከዚሁ እንደጀመረ ነው የሁለቱ ሀገራት ዘገባዎች የሚጠቁሙት።
በደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት “የጆንግሌይ ካናል ቁፋሮ እንደገና እንዲጀመር” በይፋ እና በከፍተኛ አፅንኦት ግንዛቤ መፍጠር ላይ የታዩት በተያዘው የፈረንጆች 2022 ነው። በዛሬው እለት በካይሮ መሞታቸው የተሰማው የደቡብ ሱዳን ሚኒስትር ስለ ፕሮጀክቱ ጠቀሜታ ስልጠና ሲሰጡ ነበር።
🔹በኤፕሪል 11 2022 የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር ክቡር ማናዋ ፒተር ጋትኩኦት እና የሚኒስቴሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት በጆንግሌይ ካናል ፕሮጀክት ፋይዳ ዙሪያ ገለጻዎች አድርገዋል።
ሚኒስቴሩም ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው የሚገልጽ ሀሳብ አቅርበዋል።
🔹የደቡብ ሱዳን ዜጎች ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ። በተለይም የጆንግሌ ግዛት ዜጎች ፕሮጀክቱን እንደቀደሙት ጊዜያት መቃወማቸውን ቀጠሉ።
🔹በዚሁ ሚያዚያ ወር የደቡብ ሱዳን ፖርላማ አባላት የጆንግሌ ካናል ፕሮጀክትን በተመለከተ ምኒስትሩን ለማብራሪያ ጠርተዋል። ምኒስትሩ ዛሬ በካይሮ የሞቱት ናቸው። ይህን ተከትሎ ደግሞ ርስ በርሱ የተምታታ ዘገባ ከደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ይሰጥ ጀመር።
🔹በእለተ ረቡ 01/Jun/2022፣
የደቡብ ሱዳን ቤቶችና መሬት ሚኒስትር ላም ቱንጉዋር ኩይኮንግ ይህን ገለፁ፣
“ነአም ወንዝን ለመቆፈር የሚውሉ ማሽኖችን ተቀብለናል። እኛ የአንድነት ግዛቷ ህዝቦችም ተጠቃሚዎች ነን ማለት ነው፤ ፕሮጀክቱ በመንግስት የተባረከ ነው።” ነበር ያሉት።
🔹በሳምንቱ ረቡ Jun 8 /2022, የደቡብ ሱዳን አካባቢ ሚኒስትር Josphina ይህን አሉ፣ “የጆንግሌ ፕሮጀክት በደቡብ ሱዳን ህዝብ መብት ላይ የሚፈፀም ወንጀል ሲሆን የወንዙ ቁፋሮም ህገወጥ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችንም ይህን ፕሮጀክት ያወግዛል።” ሲል መግለጫ አወጣ።
🔹በቀጣይ ቀናት ደግሞ የደቡብ ሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስትር ማናዋ ፒተር ጋትኩት (ዛሬ በካይሮ ያለፉት) የተናገሩት ደግሞ የጆንግሌ ቁፋሮ ፕሮጀክት ከፕሬዝዳንቱ የተሰጣቸው ትእዛዝ መሆኑን አስቀመጠ። በዚህም “እኛ እንደ ውሃና መስኖ ሚኒስቴር የተሰጠንን ትእዛዝ ለመፈፀም ፕሮጀክቱን እየተገበርን ነው።” ሲሉ ይፋ አደረጉ።
🔹የፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ፅህፈት ቤትም ቀጠለ፤ በፕሬስ ሴክሬታሪ አቴኒ ዌክ አቴኒ በኩልም ተከታዩን ሲናገር ተደመጠ፣
“ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ከግብፅ መጡ ስለተባሉት የጆንግሌ መቆፈሪያ ማሽነሪዎች ምም እንደማያውቁና ስለ ግንባታው መጀመርም ምንም እንዳልተነገራቸው ይፋ አደረገ – ይህ ከሆነ ከአስር ቀን በኋላ ነው ምኒስትሩ በካይሮ ህልፈተ ሞታቸው ተፈፃሚ መሆኑ በዛሬው እለት የተሰማው።
Esleman Abay #የዓባይልጅ