የጦርነት ማግስቱ ‘ስኳር-ለበስ’ መሳሪያ

Esleman abay

ለቻይና ሰላማዊ ሽግግር በሚል CIA የቀረፀው ሰነድ ነበር አሉ – ያኔ፡ የማኦ ዚዶንግ ቻይና የሶሻሊስት አብዮት ድሏን ባከበረች ማግስት የተጠነሰሰ። የሲአይኤ “How to do manual” በሚል ዛሬ ድረስ የቻይናውያን መሳለቂያ የሆነው ኢምፔሪያሊስታዊው የአሜሪካ ፕሮጀክት “ከህዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ የሚኖራትን ትብብር” የሚመለከት በሚል ሰይመውታል። መጀመሪያ የተጻፈው 1951 እኤአ ሲሆን ወቅቱ የሲኖ-አሜሪካ ግንኙነት በጣም የሻከረበት ነበር። የግንኙነታቸውን መለዋወጥ እየተከተለ በየጊዜው ሲከለሰም ነበር – እስካሁን ድረስም ይከልሱታል። “አስርቱ ትእዛዛት” ተብሎ ይጠራም ጀምሯል። ይፋ የሆነው በቅርቡ ሲሆን “ተገርመናል” ይላሉ ያን ሁላ ሴራ ዛሬ ላይ የሚታዘቡ ቻይናዊያን። ከአስሩ መካከል የመረጥኳቸው አምስቱን እንቃኛቸው ዘንድ ወደድኩ።
▪️አንድ፦ ወጣቱን በቁሳዊ ነገሮች የማባበልና አይምሮውን የማበላሸት corrupt የማድረግ ተግባራትን ማከናወን ነው። በዚህ ዘዴ የቻይና የሆነውን ርዕዮተ ዓለምና አስተምህሮ በተለይም ኮሚኒዝምን እንዲንቁ እና የበለጠ እንዲቃወሙት ማበረታታትና የመሳሰሉ ተግባራትን ያቅፋል።
▪️ሁለት፦ የመዝናኛውን፣ የመጻሕፍትን ይዘት፣ ብዙሃን መገናኛውን፣ አሜሪካዊ ቀለም ማላበስና በዘርፉ ውስጥ በስውር ሰርጎ መግባት።
በዚህ ዘዴ የምንለብሰውን፣ የምንመግበውን፣ የምንኖርበትን ቤት፣ የምንጓዝበትን፣ የምንዝናናበትና የምናስተምርበትን መንገድ እንዲመርጡት ካደረግናቸው ይህ የጦርነቱ ድል ግማሹን ያክላል ይላል።
▪️ሶስት፡ ወጣቶች ከሀገራቸው መንግስት ጋር ተቀናጅተውም ሆነ ተማክረው ለሀገራቸው የሚኖራቸውን አበርክቶ የማምከን ግብ ነድፎ መስራት የሚለው ነው። የወጣቱን አእምሮ በስፖርታዊ ትእይንቶች፣ በብልግና ቪዲዮዎች፣ በተድላ፣ በጨዋታዎች፣ በወንጀል ፊልሞችና በአጓጉል መናኛ አተያዮች ላይ እንዲተኩር ማድረግ።
▪️አራት፡ ህዝቡ በይፋ የማይነጋገርባቸው ጉዳዮችን እንዲወያዩባቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት። ይህ በተለይም ንቁ ባልሆነው subconcious አእምሯቸው መከፋፈልን ሳያስቡት መትከል ይጀምሩ ዘንድ ያነጣጥራል። አናሳ የሚሏቸው ብሔረሰቦች በተለየ ኢላማ ይደረጋሉ። በሀገሬው መካከል በክልል፣ በብሔረሰብ፣ እንዲሁም በስሜታቸው ሁሉ መከፋፈልን በመፍጠር ለዚህም የቆዩና አዳዲስ የጥላቻ አጀንዳዎችን ለመፍጠር መልካም አጋጣሚዎችን ማማተር።
▪️አምስት፡ ተከታታይ ዜናዎችን በመስራት መሪዎቻቸውን ማጥላላት። በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የአሜሪካን የዴሞክራሲ ፍልስፍና ማነብነብና ማቀንቀን።
“ባገኘነው በዬአጋጣሚው ሁሉ፣ ትልቅም ይሁን ትንሽ፣ የሚታይም ሆነ የማይታይ፣ ዕድሉን ተጠቅመን ዴሞክራሲያዊ የሚባል ስም የተሰጣቸው ንቅናቄዎችን ማበረታታት። ይህን ሲደጋግሙት ህዝባቸው እኛ የምንናገረውን እውነት ነው ብሎ በእርግጠኝነት ያምናል። እኛ የምንይዘው ሰዎችን ነው።” የሚል ይገኝበታል።
የቀድሞ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን “ያለ ጦርነት ድል መቀዳጀት-Victory Without War” መጽሐፍ ደራሲ ይሆኑ ዘንድ የቻይናዊው Sun Tzu ዝነኛ መፅሐፍ “Art of War” የገፋፋቸው ሰበብ ነበር። ታዲያ ኒክሰን በዚያ መፅሐፋቸው “ወጣት ቻይናውያን በአባቶቻቸው አስተምህሮና በባህል እሴታቸው ላይ ያላቸውን እምነት መናድ ስንችል ያኔ አሜሪካ ቻይናን ያለ ጦርነት ታሸንፋታለች..።” ሲሉ ማስፈራቸውንም እዚጋ ልብ ይሏል።
በሌላ በኩል ማኦ ዜዶንግ የአሜሪካን ሴረኛ ፖሊሲ ከረጅም ጊዜ በፊት ገምተው እንደነበር የሚገልፁም አሉ። ለዚህም አንድ ዝነኛ ንግግራቸው ይወሳላቸዋል። የማኦ ንግግር በዋነኛነት ህዝባዊ ድል አይቀሬነቱን ነገር ግን ከድል ማግስት ላለመሸነፍ ምን ይደረግ የሚለውን የሚመልስ ነው። የቻይና አብዮትን ምእራባዊያን ላይቀለብሱት ይባስ ብሎም ኢምፔሪያሊዝምን አሁን ሊቀብረው ከጫፍ ለመድረሱ የማኦ ዚዶንግ እሳቤ ወሳኝ ነበር። ተከታዩ የማኦ ንግግር የእሳቤያቸው አብነት ነው፣
“ድሉን አሳክተናል። ተኩራርተን መቆም ግን የለብንም። ጠላት በአውደ ውጊያ አያሸንፈንም። ለመሳሪያ ያልተበገሩት ጀግኖቻችን በጠላት ፊት የጀግና ማዕረግ ይጎናፀፉ ዘንድ የተገባ ነው። እነዚህ የጦር ሜዳ ጀግኖችቻን ታዲያ በስኳር የተለወሰ ሰዎች የሚከፍቱባቸውን ዘመቻ ግን ሊደመስሱት የሚመቻቸው አይሆንም።” ማኦ ዚዶንግ።
ወደ ሀገራችን ስንመለስ በኢትዮጵያ ህወሃት ከከፈተው ጦርነት በፊት፣ በጦርነቱ ወቅትና ማግስት ምእራባዊያን ተደርበው ወግተዋታል። በጦርም በወሬም ነበር የዘመቱባት። የምእራባዊያን የውጊያ ተሳትፎ የህወሃትን የእስትፋስ ማጣት ተከትሎ አሁን ላይ ጋብ ለማለት ተገዷል። በቅርቡ ደግሞ ርዳታቸውና ብድራቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል። ስም ሲያጠፉ የነበሩ አለማቀፍ ሚዲያዎቻቸው መልክ ለውጠው በጎ በጎውን ስለኢትዮጵያ ማውራት ጀምረዋል። “በአዲስ አበባ የሚታየው ለውጥ የመሪዎቿ ራእይ ውጤት ነው።” የሚለውን መጣጥፍ ዘኢኮኖሚስት የተባለው የኒዮሊበራሊዝም እርኩስ መፅሐፍ ለማስተናገድ የፈቀደው በዛሬው እለት ነው። የምእራባዊያን ፖሊሲ ለውጥ ማሳያ መሆኑ ነው። “የመሪዋ” ወይም “የአብይ” በማለት ፅሁፉ ያልተስተናገደው ይህን አዲስ ስያሜ ለመልመድ ትንሽ ቀን ስለሚያስፈልጋቸው ነው። በቀጣይ ግን ያደርጉታል። ሌሎች ሚዲያዎቻቸውም ይህንኑ ይከተሉታል። ታዲያ የቀራቸው ካርታ ምን ሊሆን ነው? ከላይ ከቻይና ታሪክ ያጣቀስነው አይነት በስኳር የተለወሰው ውጊያ መሆኑ ቀጣዩ መሳሪያቸው። ኢትዮጵያን ከመርዳት ጋር ተቀላቅሎ የሚገባ ጣጣ እንደማለት…። በዚህ አውድ ከትልቅ ድል ማግስት ላለመሸነፍ የቤት ስራ ይጠብቀናል ማለት ነው።
መሰል አደጋዎችን ለመመከት ቻይና እንዲሁም ቱርክ (በዘመነ ኤርዶኻን) ከወሰዷቸው ርምጃዎች መካከል የአለማቀፍ NGOዎችን ሚና የሚገድብ ህግ ማውጣት፣ ዲጂታል volunteers አይነት የዜጎች የመረጃ ሰራዊት ማሰማራት፣ ለፖለቲካ ፖርቲዎች እና ለጋዜጠኞች/አክቲቪስቶች በሚል ምእራባዊያን የሚያቀርቡትን ፈንድ መከልከል ይገኙበታል።

ከድል ማግስት ድጋሚ ማሸነፍ፤ ተከታታይ ባለድሎች መሆን ይቻላል✊
Esleman Abay #የዓባይልጅ

https://eslemanabay.com/the-u-s-tiananmen-papersnew-documents-reveal-u-s-perceptions-of-1989-chinese-political-crisis/

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories