ጀኔራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል – ክፍል ሁለት

By ባይለይኝ ጣሰው (ዶ/ር)

ለባርነት የተሸጡት ኢትዮጵያዊ የጀኔራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል (1696-1781) አጭር ታሪክ፡- ክፍል ሁለት

ባይለየኝ ጣሰው (ዶ/ር)

የአብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል የትምህርት ዓለም፣ ሙያና የሥራ ዘመን

“በይበልጥ ‹የታላቁ ጴጥሮስ ባሪያ› ወይም ‹የጴጥሮስ ባሪያ› በመባል የሚታወቀው አብርሃም ሀኒባል በአሥራ ስምንተኛው ምዕተ-ዓመት የሩሲያ ታሪክ ከሚታወቁት ታላቅ ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ ልዩ ዕጣ ፈንታው ከባርነት ወደ ጌትነትና ባለፀጋነት መርቶታል፡፡ (አልበር ፓሪ 1923)፡፡

“ቮልቴር አብርሃም ጋኒባልን ‹የዘመነ-አብርኆት ጥቁሩ ኮከብ› ብሎ ይጠራው ነበር፡፡” (አሌክሳንደር ፑሽኪን (1837፣ አልበር ፓሪ 1923)፡፡ .

ማስታዎሻ፡- ታዛ መጽሔት ቅጽ 3፣ ቁጥር 30 ዕትም የጀነራል አብርሃም ጋኒባልን ታሪክ የመጀመሪያውን ክፍል ለአንባያን በሚከተለው ፍ…… ነገር ላይ በማተኮር አቅርቤ ነበር፡፡ ለማስታወስ ያህል በመጀመሪያው ክፍል፡- 1ኛ/ አብርሃም በ18ኛው ምዕተ-ዓመት መባቻ ላይ (በ1703 ዓ. ም. (እኤአ)) በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በኤርትራ ክፍለ ሀገር፣ በመረብ ወንዝ ዳርቻ በምትገኝ፣ ላጎን ሳርዳ ተብላ በምትጠራ ቀበሌ፣ በእድሜ የ7 ዓመት ልጅ ሲሆኑ ከትልቅ ወንድማቸውና ከትልቅ እህታቸው እንዲሁም ከአንድ የጎረቤት ልጅ ጋር በጨዋታ ላይ በድንገት በቱርኮች ታፍነው ለባርነት ተዳርገው ወደ ምጽዋ መወሰዳቸውን፣ 2ኛ/ ከምጽዋ በመርከብ ተጭነው ሲጓዙ እህታቸው ቀይባህር ዘላ በመግባት መሞቷንና እነርሱም በሰንሰለት ታስረው በዘመኑ የኦቶማን ቱርክ ኢምፓየር ዋና ከተማ ወደ ነበረችው ወደ ቆንስጣንጢኖፕል (ወደ ዛሬዋ ኢስታንቡል) ተወስደው ለአንድ ዓመት ያህል በባሪያ ማጎሪያ ውስጥ በመሰቃየት ላይ ሳሉ በሩሲያ ዲፕሎማቶች አማካይነት በሚስጢር ተሰርቀው ወደ ሞስኮ መወሰዳቸውን፣ 3ኛ/ በመጨረሻም ህፃኑ አብርሃም ዕጣ ፈንታቸው ተቀይሮ በሩሲያው ዛር (ንጉሥ) በታላቁ ቀዳማቂ ጴጥሮስ ቤተመንግሥት ውስጥ መልካም አስተዳደግ መቀጠላቸውን ነበር ያቀረብኩት፡፡ በዚህ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል ስለተሰጣቸው የትምህርት ዕድል፣ ሙያና የሥራ ዘመን፣ ስለገጠማቸው ውጣውረድና ስለተቀዳጁት አስደናቂ ድል ላይ በማተኮር ይዤላችሁ ቀርቤአለሁ፡፡ ወደ አብርሃም ታሪክ በቀጥታ ከማምራታችን በፊት ግን በቅድሚያ ስለ ታላቁ የሩሲያው ዛር (ንጉሥ) ቀዳማዊ ጴጥሮስ በጥቂቱ ማውሳ ት አስፈላጊ ይሆናል፡፡

የታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ የሥልጣን ዘመን የሩሲያ ተሀድሶ መጀመሪያ ዘመን ጋር በማያያዝ ታሪክ ሲያወሳ ቆይቷል፡፡ እርግጥ ነው! ታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ ከ1680 እስከ 1725 ዓ.ም በሥልጣን ላይ በቆየበት ዘመን በሩሲያ ውስጥ እጅግ ግዝፈት ያላቸውን ተከታታይ ለውጦች በማካሄድ ኋላ ቀሯን ሞስኮቭስካይ ወደ ዘመናዊት የአውሮፓ መንግሥትነት ቀይሯታል፡፡ ታላቁ ጴጥሮስ የሩሲያን አሮጌ የዛሩ አስተዳደራዊ ሥርዓት በማሻሻል ሀገሪቱን ወደ አዲስ አቅጣጫ በማምራት ከዘመናዊ የአውሮፓ መንግሥታት ይከተሉት ከነበረው ዘመናዊ አስተሳሰብና አሠራር ተርታ አስይዟታል፡፡ ታላቁ ጴጥሮስ ሀገሩን ወደተሻለ ደረጃ ለማሰለፍ ከነበሩት ቀናዒነት የተሞላባቸው ጥረቶች መካከል ሀገሪቱ ዘመኑ በደረሰበት በማንኛውም የዕውት መስክ ብቃት ባለው የተማረ የሰው ኃይል መገንባት አንዱ ነበር፡፡

በመሆኑም የሩሲያን ወጣቶች ወደተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች፣ በተለይም ወደ ፈረንሳይና እንግሊዝ፣ በብዛት በመላክ እንዲማሩና ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ በማበረታታት ያልተቆጠበ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ወጣቱ አብርሃምም ያገኙት ዕድል ከዚህ ውጭ አልነበረም፡፡ አብርሃም የተለየ ተሰጥኦ ነበራቸው፡፡ በመሆኑም “ንጉሡ ታላቁ ጴጥሮስ ከመጀመሪያው ዕይታ አንስቶ በአብርሃም ልዩ የሆነ ብሩኅ አእምሮ የተሰጠው ልጅ እንደሆነና በተለይም የወትድርና ተሰጥኦ እንዳለው በመገንዘብ ትኩረቱን እጅግ በጣም ስቦት ሰለነበር ልጁን ወደ መኖሪያ አፓርታማው የወሰደው መሆኑን ጸሐፍቱ (ፑሽኪንን ጨምሮ) በአጽንኦት ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ ቴሌቶቫ (2006)፡- “ንጉሡ (ዛሩ) ከመጡት አብረውት ከሌሎቹ ልጆች ይልቅ አብርሃምን በቀላሉ ሊገኝ የማይችል ብርቅ ስጦታ አድርጎ ገና ከጅምሩ አንስቶ ለይቶ አውቆ ስለነበር ከራሱ ጋር በቅርብ እንዲኖር አደረገው” ብላለች፡፡ ሻው (2006) ደግሞ፡- “ትንሹ ልጅ (አብርሃም) ከዕድሜው አኳያ ሲታይ ፈፅሞ ለማመን የሚያዳግት ብሩኅ አእምሮ ነበረው፡፡ የሩሲኪን ቋንቋ አቀላጥፎ መናገርና ፊደሎችን ለይቶ መፃፍ የቻለው እጅግ በጣም በአጭር ጊዜ (በስድስት ወራት ውስጥ) ነበር፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የፒትስቡርግን ቤተ-መንግሥትም የገዛ ቤቱ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ታላቁ ጴጥሮስም አብርሃም ያለውን ልዩ ተሰጥኦ በመረዳትና በማድነቅ ከራሱ የመኖሪያ አፓርትመንት እንዲቀመጥ አደረገው” ሲል ገልፆታል፡፡ የልጅ ልጃቸው አሌክሳንደር ፑሽኪን (1837) እና አልበርት ፓሪም (1923) በተመሳሳይ ይህን የአብርሃምን ልዩ ተሰጥኦ አስፍረውት እናገኛለን፡፡

አብርሃም ከክርስትና አባታቸው ከሩሲያው ዛር (ንጉሥ) ጋር  እንደ ልጅ አብረው በመኖር ላይ እንዳሉ መደበኛ ትምህርታቸውን በቤተመንግሥት አቅራቢያ ለመማር ችለዋል፡፡ በትምህርታቸውም ተወዳዳሪ አልነበራቸውም፡፡ በዘመኑ ከመደበኛው ትምህርት በተጓዳኝ ተማሪዎች የውጭ ቋንቋዎችን ፈረንሳይኛን፣ ላቲንን፣ እንግሊዝኛን፣ ወዘተ፣ ጨምረው እንዲማሩ ይደረግ ነበር፡፡ አብርሃምም ከመደበኛ ትምህርታቸው በተጨማሪ ላቲንን፣ ፈረንሳይኛንና እንግሊዝኛን ጠንቅቀው ለመማር አስችሏቸዋል፡፡ አብርሃም በትምህርት ላይ ሳሉ ታላቁ ጴጥሮስ በሀገር ውስጥ በየጊዜው ያደርጋቸው በነበሩት ጉብኝቶች ሁሉ ይዟቸው ይጓዝ ነበር፡፡ ይህም ብዙ ትምህርት ለመቅሰም እድል ሰጥቷዋል፡፡ በኋላም በውጭ ሀገራት በሄደባቸው ሀገሮች ሁሉ አብርሃምን ትቷቸው የሄደበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡ ታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ በጀርመን ባደረገው ጉብኝት አብርሃምን ይዟቸው ሄዶ ነበር፡፡ በ1717 ዓ.ም. ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች ባደረገው የብዙ ወራት ጉብኝት እንደዚሁ ይዟቸው ነበር የተጓዘው፡፡ በዚህ ዙር ንጉሡ ከጎበኛቸው ሀገሮች መካከል ፈረንሳይ አንዷ ነበረች፡፡

Description: F:\Gannibal\256131-1330622238.jpg

በዚህ በፈረንሳይ ጉብኝት ጊዜ ነበር ታላቁ ጴጥሮስ  አብርሃምን በዛሩ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የውትድርና ትምህርት እንዲማሩ ፈረንሳይ ውስጥ ትቷቸው የተመለሰው፡፡ በዚህ ጊዜ አብርሃም የ18 ዓመት እድሜ ወጣት ነበሩ፡፡ አብርሃምም ከጅምሩ አንስቶ ክርስትና አባታቸው የሩሲያው ንጉሥ ቀዳማዊ ጴጥሮስ ያደርግላቸው የነበረውን ቤተሰባዊ ዝምድና ለመፃኤው የሕይወት ጉዞና ዕጣ ፈንታ ምን አንድምታ እንደነበረው መረዳት አላቃታቸውም፡፡ እናም በፈረንሳይ ሀገር ልዩ ሥፍራው ሜትዝ (Metz) ከተባለ ቦታ ይገኝ በነበረ ወታደራዊ ምህንድስና (ኢንጂነሪንግ) አካዳሚ ውስጥ የአምስት ዓመት ትምህርት ለመማር (እኤአ) በ1717 ዓ. ም. ገቡ፡፡ ከዚያም ወታደራዊ ምህንድስና፣ ወታደራዊ ምሽግ ቅያስና ግንባታ፣ ሂሳብ፣ ጂኦሜትሪና ፊዚክስ በተጨማሪም የፈረንሳይኛ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሥነጥበብና ማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ለሁለት ዓመት ያህል ቀጠሉ፡፡ ወደ ወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት ከመግባታቸው በፊትም በርካታ ቋንቋዎችን ችለው ነበር፡፡ በመሆኑም የውትድርና ሳይንስ፣ የፍልስፍና እና የሥነጽሑፍ መፃሕፍትን በማንበብ ይታወቁ ነበር፡፡ በትምህርትም አብርሃም ተወዳዳሪ ተማሪ አልነበራቸውም፡፡

(እኤአ) በ1718 የንጉሡን ፍላጎት የማሟላት ቀቢፀ-ተስፋ በመያዝ የፈረንሳይን ጦር በመቀላቀል (በፎርቲፊኬሽን) እና በወታደራዊ ምህንድስና ልምድ በማስፋት መቅሰም ጀመሩ፡፡ ተመዝግበው የገቡትም እኤአ በ1720 ዓ. ም. ላ ፈሬ (La Fëre) ይገኝ ከነበረው የፈረንሳይ ሮያል መድፈኛ ጦር አካዳሚ ነበር፡፡

ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳሉ ግን በፈረንሳይና በስፓኝ መካከል ከባድ ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡ ጦርነቱ (እኤአ) ከጥር 9 ቀን፣ 1719 እስከ የካቲት 17 ቀን፣ 1720 ዓ. ም. ድረስ ቀጠለ፡፡ አብርሃም የስፔኑን ንጉሥ የፊሊፕ 5ኛውን ጦር ለመውጋት በእድሜ 10 ዓመት የነበረውን የፈረንሳዩን ንጉሥ የሉዊስ 15ኛውን፣ በሞግዚቱ በኦርሊያኑን መሥፍን – በፊሊጵ –  ይመራ የነበረውን ጦር ተቀላቀሉ፡፡ ጋኒባል በብዙ ውጊያዎች ተካፍለዋል፡፡ በተደረጉት ውጊያዎች ሁሉ ችሎታ ያለው ኢንጂነርና ብቁ ኮማንደር መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ በተለይም ከእነዚህ ውጊያዎች መካከል አንዱ የፈረንሳይ ጦር በ1719 ዓ. ም. በስተሰሜን ስፔን የፉንተራቢያን የጦር ምሽግ ለመቆጣጠር የተካሄደው ከባድ የምድር ውስጥ ውጊያ ነው፡፡ በዚህ ውጊያ ጋኒባል ከራሳቸው ላይ ቆሰሉ፡፡ ቁስሉ ቀላል ነበር፡፡ እንደቆሰሉም ለህክምና ወደ ፓሪስ ተወስደው በቀላሉ ድነዋል፡፡ የቆሰሉበት ቦታ በፉንተራቢያ ሠፍሮ የነበረውን የስፔን ግዙፍ ጦር ለመምታትና ለመቆጣጠር የሚያስችል ቁልፍ የሆነ የምድር ውስጥ ድልድይ (ቱነል) ነበር፡፡ ከዚህ ላይ አብርሃም አስደናቂ ጀብድ ፈጽመዋል፡፡[1] ለፈፀሙት ጀብድም በፈረንሳይ መንግሥት የሻለቃነት ማዕረግ ሊሰጣቸው ችሏል፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ታላቁ ጴጥሮስ ሁኔታቸውን በቅርብ ይከታተሉ ነበር፡፡ “ጋኒባል” የሚለውን ስም የሰጣቸው ራሱ ታላቁ ጴጥሮስ ነው፡፡ ስሙ የተሰጣቸውም በፈረንሳይ ሀገር በትምህርት ላይ እያሉ የፈፀሙትን ጀብድ ምክንያት በማድረግ የካርታዥኒያውን (Carthaginian) ወደር የሌለውን ታሪካዊ ጀግና የጀኔራል ሀኒባልን የጀግንነት ገድል ለማስታዎስ መሆኑን የታሪክ ማኅደሮች አስፍረውታል፡፡

ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ጋኒባል በ1720 ዓ. ም. ላ ፈሬ (La Fëre) በሚገኜው “ሉዊስ 5ኛ ሮያል መድፈኛ አካዳሚ” ተብሎ ይጠራ ወደነበረው ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ገቡ፡፡ ከዚያ ፈረንሳይ ለጦር መኮንኖች አዲስ የመድፈኛ ሥልጠና ፕሮግራም መስጠት እንደምትጀምር ሉዊስ 15ኛው በሞግዚቱ በኦርሊያኑ መሥፍን አማካኝነት አዋጅ አወጀ፡፡ በዚህ ጊዜ በ1722 ዓ.ም. የጋኒባል ጓደኞች መጀመሪያ ለማማር የመጡበትን የ5 ዓመት ተኩል የትምህርት ፕሮግራም ጨርሰው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡ ጋኒባል ግን አዲሱን የጦር መኮንኖች የመድፈኛ ትምህርት ለአንድ ዓመት ያህል ለመከታተል ፈለጉ፡፡ ተጨማሪ የአንድ ዓመት ቆይታ ለማድረግ ግን የታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስን ፈቃድ ማግኝት ነበረባቸው፡፡ በመሆኑም ታላቁ ጴጥሮስን በደብዳቤ ጠየቁ፡፡ በጠየቁት መሠረትም የንጉሡን ፈቃድ አግኝተው አዲሱን የመኮንኖች የመድፈኛ ሥልጠና እስከ 1723 ዓ. ም. መጨረሻ ደረስ በዚያው በሉዊስ 15ኛ ሮያል መድፈኛ አካዳሚ ውስጥ ቆዩ፡፡

ጋኒባልና ጓደኞቻቸው በፈረንሳይ ውስጥ በነበራቸው የትምህርት የቆይታ ዘመን ውስጥ ከሩሲያ መንግሥት ይሰጣቸው የነበረው የገንዘብ ድጋፍ በቂ እንዳልነበረና ከባድ ችግር ገጥሟቸው እንደነበር ጸሐፍት አስፍረውት ይገኛል፡፡ ይህን በሚመለከትም ጋኒባል ለሩሲያ የገንዘብ ሚኒስትርና ለራሱ ለታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ የፃፏቸው ደብዳቤዎች በፒትስቡርግ ውስጥ በሚገኜው ቤተ-መዘክር በመረጃነት ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ አብርሃም በደብዳቤዎቻቸው እንደገለፁት “ፈጽሞ ስለረሳችሁኝ በከባድ ችግር ውስጥ በረሀብ እየተሰቃየሁ እንድኖር ተገድጃለሁ፡፡ … የምንኖርበት እንዲህ ያለው የድህነት ሁኔታ አባት ሀገርን የሚያሳፍር ውርደት የሚያመለክት ነው” የሚል የብሶት ቃል ይገኝባቸዋል (ፓሪ 1923፡- 362)፡፡  ለምሳሌ መጋቢት 5 ቀን፣ 1722 ዓ.ም. ወደ ሞስኮ ለማካሮቭ በጻፉት ደብዳቤም ስለችግሩ ክብደትና በፓሪስ ውስጥ ይኖር የነበረው ካውንት ፕላቶን ኢቫኖቪች ስላደረገላቸው ድጋፍ እንዲህ በማለት ገልጸውታል፡፡

እዚህ ሁላችንም በዕዳ ውስጥ ነን፡፡ በዕዳ ውስጥ የምንገኘውም በሀገራችን ገንዘብ የመግዛት አቅም ድክመት ምክንያት እንጂ ከአባኝነታችን የተነሳ አይደለም፡፡ እንደማምንበት ይህን ከካውንት ሙሲን-ፑሽኪን የነገረዎት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባለው የሀገራችን ገንዘብ የመግዛት አቅም ውድቀት አኳያ ሲታይ ፕላቶን ኢቫኖቪች ባይኖር ኖሮ እስካሁን የርሀብ ጠኔ በገደለኝ ነበር፡፡ በእውነቱ እርሱ ቸርነቱን ስላልነፈገኝ በየቀኑ ምሳም ራትም ከእርሱ ጋር እበላለሁ፡፡ … የእርሱን ድጋፍ ባላገኝ ኖሮ  ከፓሪስ እስከ ሞስኮ ድረስ በእግረ መንገድ ምጽዋት እየለመንኩ ወደ ሞስኮ በእግሬ ለመምጣት እገደድ ነበር (ፓሪ 1923፡- 360)፡፡

Description: F:\Gannibal\gannibal images.jpg

ከዚህ በተቃራኒ ግን ፑሽኪን “የዛሩ ኔግሮ” በሚለው መጽሐፉ ያሠፈረው ከዚህ የተለየ ሆኖ እናገኛለን፡፡ በመሆኑም እንዲህ ሲል ገልጾታል፡- “ታላቁ ንጉሥ ጴጥሮስ በቂ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግለት ነበር፡፡ ይደረግለት የነበረው ድጋፍም ከተለያዩ የፈረንሳይ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እንደ ልብ ሰፋና ጠለቅ ያለ ግንኙነት ለመፍጠር ያስቻለውን ዕድል ሰጥቶታል፡፡ ገጽታው የሰዎችን ትኩረት ይስብ ነበር፤ ጥቁር የተጎነጎነ ግልስልስ ጸጉሩ የሰዎችን ዓይን ይስብ ነበር፤ ከቅጽበታዊ አስተውሎት የሚፈልቁ  ጥዑመ ቀልዶቹና አስደሳች ተረቦቹ፣ ትምህርቱና የጦር ሪኮርዱ በሰዎች ዘንድ አክብሮትን ችሮታል፡፡ ከነጭ ቴክኖራቶች ጋር እጅግ በተዋቡ የፓሪስ ሳሎኖች ይስተናገድ ነበር፤ በየትኛውም የደረሰበት ቦታ በሁሉም ዘንድ ‹የንጉሡ ባሪያ!› እየተባለ ታዋቂ አድርጎታል፡፡”

ያም ሆነ ይህ የታሪክ ፀሐፍትም ሆኑ ፑሽኪን ራሳቸው ጋኒባል ከፃፉትና በመዘክርነት ተጠብቀው ከሚገኙት ደብዳቤዎች የበለጠ ተአማኒነት ያላቸው ምስክር ሊሆኑ የሚችሉ ማረጋገጫዎች አይገኙም ማለት ተገቢ ይሆናል፡፡

የወታደራዊ ትምህርትና ልምምድ ውጤታቸው ከሁሉም ሰልጣኞች በአስደናቂ ሁኔታ የላቀ ነበር፡፡ የወጣቱ ንጉሥ ሞግዚት የኦርሊያኑ መሥፍን ጋኒባልን ፈረንሳይ ውስጥ እንዲቀሩ በመፈለግ “እድገትህ ያለ ምንም መሰናክል ተጠብቆ በፈረንሳይ ውስጥ ባለው እስከ መጨረሻው ከፍተኛ ወታደራዊ የደረጃ ማዕረግ እናደርስሀለን፡፡ እዚህ ቅር” በማለት በተደጋጋሚ ጠይቋቸው እንደነበር ፀሐፍት አስፍረውታል፡፡ ፑሽኪንም በበኩሉ፡- “በጊዜው የወጣቱ ንጉሥ ሞግዚት ሆኖ ፈረንሳይን ይገዛ የነበረው የኦርሊያኑ መሥፍን ፊሊጵ የተለየ ትኩረት በመስጠት ሀኒባልን ያደንቀው ነበር፡፡ እና ታላቁ ጴጥሮስ አብርሃምን ወደ ሩሲያ እንዲመጣ በጠየቀው ጊዜ የፈረንሳዩ ወጣት ንጉሥ ሞግዚት ሀኒባልን ወደ ሩሲያ መመለሱን ትቶ ፈረንሳይ ውስጥ እንዲቀርና አንፀባራቂ የወታደራዊና ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን እንደሚሰጠው ቃል በመግባት አጥብቆ ይወተውተው ነበር” ሲል ጽፏል፡፡

አብርሃም ጋኒባል ይህ ጥያቄ በተደጋጋሚ ቢቀርብላቸውም እሽም እምቢም ሳይሉ  በፈረንሳዩ መሥፍን በኩል የቀረበላቸውን ሀሳብ ገልፀው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለታላቁ ጴጥሮስ በደብዳቤ አሳወቁ፡፡ ታላቁ ጴጥሮስም “በፈረንሳይና በሩሲያ መካከል የምትወስደውን ምርጫ ለአንተ ለራስህ ብተወው ይሻላል” የሚል አጭር መልስ ሰጣቸው፡፡ መልእክቱ ግልጽ ነበር፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ጋኒባል መሥፍኑን “ከዚህ መቅረት እንደ ክህደት ይቆጠርብኛል፡፡ ወደ ሀገሬ ለመሄድ ወስኛለሁ” ብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ አመስግነው ይቅርታ ጠየቁት፡፡

አብርሃም በፓሪስ ውስጥ በነበራቸው የቆይታ ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ እንደ ዴኒስ ዲደሮት፣ እንደ የባሮኑ ዴ ሞንትስኪዩ እና እንደ ቮልቴር ከመሳሰሉ ዕውቅ የዘመነ-አብርኆት አቀንቃኝ ምሁራን፣ የፍልስፍና፣ የቅኔ፣ የሥነ-ጽሑፍ፣ ጠበብትና ሊቃውንት ጋር የጠበቀ ግንኙነትና ጓደኝነት ፈጥረው ነበር፡፡ ለምሳሌ የሕይወት ታሪካቸውን ከፃፉት መካከል ኤ. ኬ. ሮትኪርክ (1782) ፣ ፑሽኪን (1837)፣ ቴሌ ቶቫ (2006)፣ አልበርት ፓሪ (2003) እንዳሰፈሩት “ቮልቴር ጋኒባልን፡- ‹የዘመነ-አብርኆት ጥቁሩ ኮከብ›” በማለት ሰይሟቸዋል፡፡

ጋኒባል በ1723 ዓ. ም. ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የተለያዩ ርዕሶች ያሏቸውን 400 መፃሕፍት ቅፆችን ገዝተው በማስጫን ነበር፡፡ ወደ ሩሲያ በተመለሱ ጊዜም ራሱ ታላቁ ጴጥሮስ ከሞስኮ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ወጣ ብላ ከምትገኝ ፕርዮበራዜንስካይ ከተባለች ቦታ ላይ ከፓሪስ አብሯቸው ከመጣው ከውድ ጓደኛቸው ከቫሲሊ ሉኪች ዶልጎሩስኮቭ ጋር እንደተቀበላቸው በሕይወት ታሪካቸው ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በመጨረሻም አብርሃም ለቀዳማዊት ንግሥት ካቴሪን ከፈረንሳይ ወደ ሩሲያ መመለሳቸውን በሚከተለው ሁኔታ በደብዳቤ ገልጸውላታል፡፡ ይህንም ቴሌ ቶቫ (2006፡47)፡-

በ1723 ዓ. ም. ወደ ሩሲያ ተመልሼ ከጃንሆይ፣ ከታላቁ ንጉሥዎ፣ ጉልበት ሥር ወድቄ ለመገናኜት በመብቃቴ እና ንጉሡም እንደ እኔ ወላጅ ለሌላቸው ምስኪኖች በሚያደርጉት በዚያው በተለመደው ቸርነታቸው በደስታ ተውጠው በተቀበሉኝ ጊዜ በቦምባርዲር ብርጌዳቸው ውስጥ እንዳገለግል በሌፍትናንት ማዕረግ ሲሾሙኝ እና በጥበቃ ብርጌዱ ውስጥ በሥልጠና ላይ የሚገኙ ወጣት መኮንኖችንና ወታደሮችን ወታደራዊ ሥነ-ሕንፃ (አርክቴክት) እንዳስተምር በቃል ትዕዛዝ በሰጡኝ ጊዜ እጅግ በጣም ትልቅ ደስታና ክብር ተሰምቶኛል፡፡

በማለት አስፍራዋለች፡፡ ከደብዳቤው ይዘት መገንዘብ እንደሚቻለው አብርሃም ከፈረንሳይ ወደ ሩሲያ ተመልሰው ፒትስቡርግ ከገቡ በኋላ ራሱ ታላቁ ጴጥሮስ የውትድርና ትምህርት በተማረበትና የሻለቃነት ማዕረግ በተሰጠበት በፕርዮብራጀንስካይ የጥበቃ ረጂመንት ቦምባርዲር ብርጌድ በኢንጂነር ሌፍትናንት ማዕረግ ኦፊሰርና አሰልጣኝ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ጋኒባል የንጉሡ ፀሐፊ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ጋኒባል በማስተማር ላይ እንደነበሩ ንጉሡ ወደ ሪጋን ከተማ በ1724 ዓ/ም. ለሥራ ላኳቸው፡፡ የተላኩትምየከተማዋን ወታደራዊ ምሽግ አሻሽለው እንዲቀይሱና ተጠናክሮ እንዲገነባ በመፈለጉ ነበር፡፡ በተመደቡበት ሥራ ላይ እንደነበሩ ፈጽሞ ይፈጠራል ብለው ያልጠበቁት እጅግ በጣም አሳዛኝ ዱብእዳ መርዶ ደረሳቸው፡፡

Description: F:\Gannibal\peter I.jpg

እሱም ታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ ከዚህ ዓለም በሞት በድንገት የመሞቱ ዜና ነበር፡፡ ቀዳማዊ ጴጥሮስ ሳይታሰብ የሞተው ጥር 28 ቀን፣ 1725 ዓ.ም. ሲሆን የሞተው ህመም በተሰማው በአንድ ስዓት ውስጥ ነበር፡፡ ታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ ሲሞት ሥልጣኑን ለማውረስ የኑዛዜ ጊዜ አላገኘም፡፡ በመሆኑም በቤተ-መንግሥቱ ምስቅልቅል ተፈጠረ፡፡ ከዘውዱ ለመቀመጥ ይቋምጡና ይሻሙ የነበሩት ሁሉ በተንኮልና በሤራ መሻኮት ጀመሩ፡፡ ጋኒባል ግራ የተጋቡበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ወደ ሩሲያ ከመጡበት ጊዜ አንስቶ የምታውቃቸው የታላቁ ጴጥሮስን ሚስት፣ የቀዳማዊት ንግሥት ካቴሪንን፣ መንግሥት ለማስቀጠል በግንባር ቀዳሚነት ለመምራትና ለመቆጣጠርና የቀጣዩን ንጉሠ ነገሥት ጴጥሮስ ሁለተኛው፣ ማለትም፡- የዛሮቪች ጴጥሮስ አሌክሲቪች አስተማሪ ሆነው ተመደቡ፡፡

                                                                              ታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ

አልበርት ፓሪ (1923) እንደፃፈው አሌክሳንደር ዳኒሎቪች ሜንሽኮቭ የታላቁ የቀዳማዊ ጴጥሮስ የረዥም ጊዜ አማካሪና ቢትወደድ ነበር፡፡ አብርሃም ጋኒባል ካሰለጠኗቸው መኮንኖች አንዱ ነው፡፡ ፀባዩን ጠንቅቀው ያውቁጣል፡፡ ይህ ሰው በሙስና የዘቀጠ ባለሥልጣን ነበር፡፡ ፖላንድን ሙጥጥ አድርጎ ዘርፏታል፡፡ በፒተርስበርግ የራሱን ቤተ,መንግሥት አሠርቷል፡፡ የሜጀር ጀነራልነት ማዕረግ ተሰጥቶታል፡፡ ላይክስ አይበድልም እንዲሉ ድንቅ ስትራቴጂስት ነው፡፡ አምጡ ድገሙ ቢባል እንደ ሜንሽኮቭ ያለ አድርባይ፣ እንደ እርሱ ያለ ስሉጥ አሳሳች ሰው ለማግኘት ያዳግታል፡፡ የሚቀናቀኑትን ሰዎች እንዴት አድርጎ እንደሚያስወግዳቸው ለማመን ያስቸግራል፡፡ ታዲያ ታላቁ ጴጥሮስ ለምን ይህን ሰው ከጎኑ አስጠግቶ አማካሪ አድርጎት እንደሚኖር ከልብ በሚደግፉት ታማኝ ባለሥልጣናቱ ሳይቀር ይታማበት ነበር፡፡ አንዳንዶች ምን አልባት ብልህ ስትራቴጂስት በመሆኑ ምትክ እስከሚያገኝ በትዕግሥት መጠበቅን መርጦ ሊሆን ይችላል የሚሉ ነበሩ፡፡

ሜንሽኮቭ ከማንኛውም የሩሲያ መሣፍንት ወገን ተወላጅ አይደለም፡፡ በትውልድ ፊንላንዳዊ በዜግነት ሩሲያዊ ነው፡፡ በመሆኑም ዘውዱን መቀናቀን አይችልም፡፡ ምኞት እንኳን ቢያድርበት የመሣፍንት ወገኖች ወይም የሥርዓቱ ጠባቂዎች በቀላሉ የልቡን እስቲያደርስ እድል አይሰጡትም፡፡ ይሁን እንጂ ገና ለአቅመ-አዳም ያልደረሰውን ልጇን እስቲነግሥ በሞግዚትነት በማሳደግ የዛሩን ሀገረ መንግሥት በበላይነት በመምራት ላይ የነበረችው የሟቹ ንጉሥ ሚስት የቀዳማዊት ንግሥት ካቴሪን አማካሪ ሆኖ መቀጠል ብቻ ሳይሆን ራሱን የሩሲያ ገዥ አድርጎ በመሠየም ፈላጭ ቆራጭ ለመሆን ቻለ፡፡

ስዕል፡-  አሌክሳንደር ዳኒሎቪች ሜንሽኮቭ

ሜንሽኮቭ መንገሥ እንደማይችል ያውቃል፡፡ ስለዚህ ሩሲያን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚገዛበትን አቋራጭ ስልት ነደፈ፡፡ ይኸውም ሜሪ የምትባል እጅግ በጣም ቆንጆ ልጅ ነበረችው፡፡ ይህችን ልጁን ለወጣቱ አልጋ ወራሽ (የዛሮቪች ጴጥሮስ አሌክሲቪች)፣ ለወደፊቱ ዛሩ (ንጉሠ) አጋብቶ ሩሲያን በመዳፉ ውስጥ በማስገባት እስከ ዕለተ ሞቱ ድርስ በብቸኝነት መግዛት የሚል ነው፡፡ ይህን ለማሳካት ደግሞ “መሰናክል ይሆናሉ” ብሎ የሚጠረጥራቸውን የታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስን የተሀድሶ ጅምር እናስቀጥላለን የሚሉትን እውነተኛ ደጋፊዎች “ድራሻቸውን ማጥፋት” የሚል እኩይ ሀሳብ አደረበት፡፡ የዚህ አደገኛ ሤራ ዒላማዎች መካከልም አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባልና ሌሎች ታላቁ ጴጥሮስ ያራምደው የነበረውን ሩቅ የተሀድሶ ራዕይ በማስቀጠል እውን ለማድረግ ይታትሩ የነበሩት ከፍተኛ የወታደራዊና የሲቢል ባለሥልጣናት ነበሩ፡፡ እነርሱም የሜንሽኮቭን ተንኮል ደርሰውበታል፡፡

በተለይም አብርሃም ጋኒባል አልጋ ወራሽ ይሆናል ተብሎ ይጠበቅ የነበረውን ወጣት ጴጥሮስ ሁለተኛውንና ልጃቸውን ኤልሳቤጥን ሟች አባታቸው ሩሲያን ለማዘመን ይከተለው የነበረውን የተሀድሶ መርህና እርምጃ፣ የሀገሪቱን ታሪክ፣ የቤተመንግሥት ሥርዓትና ደንብ፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነትና ወታደራዊ አደረጃጀት፣ ወዘተ. የማስተማር ኃለፊነት ጨምረው በመያዝ ንግሥት ካቴሪንን ከልብ ያግዙ ነበር፡፡ በመሆኑም የሜንሽኮቭ ሤራ ዋነኛ ኢላማ ሆነው ሳለ ንግሥት ካቴሪን ግንቦት 6 ቀን፣ 1727 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች፡፡ እርሷ እንደሞተች አልጋ ወራሽ ጴጥሮስ ሁለተኛው ዲነግሥ ተደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ ወጣቱ ንጉሠ ሜንሽኮቭ ልጁን እንዲያገባለት በግልጽ ያባብለው ጀመረ፡፡ እርሷም እስከምታገባው ድረስ እንቅልፍ አጣች፡፡ ውሎና አዳሯም ከእርሱ ጋር ሆነ፡፡ “ወይራ ዶግ ይወልዳል፡፡” እውነት ነው! ወጣቱ ንጉሠ እንደ አባቱ ጠንካራ አልሆነም፡፡ ልፍስፍስ ሆነ፡፡ አርቆ ማየት አልቻለም፡፡ ቢመክሩትም አልሰማቸውም፡፡ ልጅቱም ክፉኛ ልቡን ሰርቃዋለች፡፡ በዚህም አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባልና ሌሎች የአባቱ ተቆርቋሪዎችና ታማኞች ደስተኛ አልሆኑም፡፡

ሜንሽኮቭ የዋዛ ሰው አይደለም፡፡ እነዚህን ሰዎች አንድ ጊዜ በጠላትነት ፈርጇቸዋል፡፡ እርሱ ብቻ አይደለም፤ ልጅቱ ሜሪም በተለይም እጅግ በጣም ቅርበት ያላቸውና አስተማሪው የነበሩት አብርሃም ጋኒባል በቤተመንግሥቱ ውስጥ እስካሉ ድረስ ወጣቱን ንጉሥ ማግባት እንቅፋት እንደሚሆኑባት በመገመት በተቻለው መንገድ ሕይወታቸው እንዲጠፋ ታልም ስለነበር አባቷን አዘውትራ ትወተውት ነበር፡፡ በሌላ በኩል ጋኒባል ከንግሥት ካቴሪን ሞት በኋላ ይህን የመሰለውን አደገኛ ሤራ የሚከላከልላቸው የኋላ ደጀን አልነበራቸውም፡፡ በመሆኑም በሜንሽኮቭ ምኅረት ወይም ሥልጣን ጥላ ሥር ወደቁ፡፡ ስለዚህ ወደ ሳይቤሪያ በግዞት ቤተመንግሥቱን እንዲለቁ አደረገ፡፡ ይህን ፓሪ በሚከተለው አገላለጽ አስፍሮታል፡-

‹ሜንሽኮቭ አብርሃም ጋኒባልን የሰው አገር ሰው ወይም የባዕድ ሀገር ሰው ነው፡፡ ለሩሲያ ታማኝ ሊሆን አይችልም› በሚል ስማቸውን ማጥፋት ጀመረ፡፡ ከዚህ በላይ በትምህርት ከእርሱ ይልቅ በእጅጉ የመጠቀ ስለነበር በጥርጣሬና በስጋት ዓይን ይመለከታቸው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ሜንሽኮቭ በእርሱ ላይ ሤራ ማውጠንጠን ቀጠለ፡፡ በመጨረሻም ጋኒባልን በ1727 ዓ.ም ከምሥራቃዊ ቅዱስ ፒተርስበርግ በ4000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኜው ወደ ሳይቬሪያ ምድር በግዞት እንዲሄዱ አደረገ፡፡ የላከቸውም ሰለንጊንስክ በምትባል ከተማ የወታደራዊ ምሽግ ዲዛይን እንዲያወጡና በበላይነት እንዲያስገነቡ በሚል ሰበብ ነበር፡፡ ጋኒባል በግዞት እንዲሄድ ሲደረግ በኦፊሴል አልታሰረም፤ ከሥልጣን ደረጃውም አልተሻረም፤ ንብረቱም አልተወረሰም ነበር፡፡ ከሰለንጊንስክ ከተማ በመውጣትም ሩሲያን የሚያዋስነውን ታላቁን የቻይና ግንብ ርዝመት በትክክል እንድትለካ የሚል ትዕዛዝ ተሰጠው፡፡ ይህን ከማከናወን ወደ ውጭ ሀገር አምልጦ እንዳይሄድ ሰላዮችን መደበበት፡፡ በወሰን ለሚገኙ ሀገረ ገዥዎችም ‹ጋኒባል ወደ ውጭ ሀገር አምልጦ ከሄደ ከሚያውቀው የሀገር ሚስጢር አኳያ እጅግ በጣም አደገኛ ችግር ስለሚያስከትል ቁጥጥር እንዲደረግበት› የሚል ጥብቅ የማስጠንቀቂያ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ 

Description: F:\Gannibal\sayberia images.jpg

ፓሪ ጨምሮ እንደሚገልጸው ‹ሜንሽንኮቭ የሳይቤሪያ ቆርጣማ ቅዝቃዜ ፈጠነም ዘገየ ወጣቱን ኢትዮጵያዊ ይግድለዋል› የሚል እምነት ነበረው፡፡ ዳሩ ግን እንዳሰበው አልተሳካለትም፡፡ ምክንያቱም ጋኒባል በአካልም ሆነ በመንፈስ ጠንካራና ጤነኛ ሰው ነበሩ፡፡ በመሆኑም ሜንሽንኮቭ እንደገመተው አልሞቱም፡፡ ሰውየው ከልጅነታቸው አንስቶ ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታዎችን ተላምደዋል፡፡ በመሆኑም የሳይቤሪያን አደገኛ ቅዝቃዜ ተቋቁመው በሕይወት መቆየት ችለዋል፡፡

ጋኒባል በ1729 ዓ. ም. ከሰለንጊንስክ ወደ አውሮፓ አምልጠው በመግባት ጥገኝነት ለመጠየቅ ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ ሆኖም አውሮፓ ከመግባታቸው በፊት ወሰን ላይ ተይዘው ታሰሩ፡፡ በእጃቸው የያዟቸው ሠነዶችና ገንዘቦች ተወረሱ፡፡ ከዚያም ተይዘው በምዕራብ ሳይቤሪያ ውስጥ ወደምትገኝ ‹ቶምስክ› ወደምትባል ቦታ ተወሰደው ለጥቂት ጊዜ ታስረው ቆዩ፡፡

ስዕል፡- አብርሃም ጋኒባል በሳይቤሪያ በግዞት ላይ እንደነበሩ

ጋኒባል በእስር ላይ በቆዩበት ጊዜ ግን እንደ አንድ ወታደራዊ ኦፊሰር ደመወዛቸው ይከፈላቸው ነበር፡፡ ሆኖም ከሳይቤሪያ እንዳይወጡ ጥብቅ ቁጥጥር ተደረገባቸው፡፡ ከዚያም በቶምስክ የጦር ሠፈር ከደረጃ ዝቅ ተደርገው በሻለቃነት ማዕረግ እንዲያገለግሉ ተወሰነባቸው፡፡ ግን ብዙ ሳይቆይ አንድ ትዕይንት ተፈጠረ፡፡

መፈንቅለ መንግሥት፡- የተፈጠረው አዲስ ክስተትም በቅዱስ ፒተርሰቡርግ በሜጀር ጀነራል ቫሲሊ ሉኪች ዶልጎሩኮቭ የሚመራ በ1929 ዓ.ም የተካሄደው የመፈንቅለ-መንግሥት ትዕይንት ነው፡፡ የተካሄደውን መፈንቅለ-መንግሥት ተከትሎም የታላቁ ጴጥሮስ የእህት ልጅ እና የሩሲያ ንግሥት ሆና በመንገሥ በትረ-መንግሥቱን እንድትጨብጥ ተደረገ፡፡ የዶልጎሩኮቭ ቡድን አባላት በፖለቲካው መድረክ እጅግ በጣም አይለው ብቅ አሉ፡፡ በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም፡፡ ሜንሽኮቭ ከሥልጣን ወረደ፡፡ ማዕረጉ ተገፈፈ፡፡ የዘረፈው ሀብት ንብረት ሁሉ ተወረሰ፡፡ ከዚያም በሳይቤሪያ ውስጥ ወደሚገኝ ቤሪዞን ወደሚባል ቦታ ከልጁ ከሜሪ ጋር በተግዞት ታሰረ፡፡ በእርሷ አማካይነት ሩሲያን እስከ ዕለተ-ሞቱ ድረስ ‹እገዛለሁ› ብሎ የተመካባት ልጁ ሜሪ በፈንጣጣ በሽታ ሞተች፡፡ 

ይገርማል! “እግረ ቀጭን ይሞታል ሲባል እግረ-ወፍራም ቀድሞ ይሞታል” እንዲሉ በሳይቤሪያ ቅዝቃዜ ‹ቀድሞ ይሞታል› ለተባሉት አብርሃም ጋኒባል አዲስ ተስፋ ሲፈነጠቀላቸው፡፡ ሜንሽኮቭ ግን በሳይቤሪያ ውስጥ በእስር ላይ እንደነበረ አብርሃምን ቀድሞ፣ የልጁን እግር ተከትሎ፣ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡

ፈረንሳይ ውስጥ በትምህርት ላይ ሳሉ አንስቶ ቫሲሊ ሉኪች ዶልጎሩኮቭ የጋኒባል የልብ ጓደኛ፣ ደጋፊና ተቆርቋሪ ነበር፡፡ ስለዚህ ጋኒባል የመፈንቅለ-መንግሥቱን ዜና እንደሰሙ የማንንም ፈቃድ ሳይጠይቁ ከታሰሩበት ከሳይቤሪያ፣ ከቶምስክ ጦር ሰፈር፣ እግረ-ሙቃቸውን በገዛ እጃቸው አውልቀው ጥለው ወደ ፒተርስቡርግ ገስግሰው መጡ፡፡ ከመጡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን የጓደኛቸው የዶልጎሩስኮቭ መፈንቅለ መንግሥት በፍጥነት እንደተሳካ ሁሉ ሳይቆይ በፍጥነት ወደቀ፡፡ ዶልጎሩኮቭና አበሮቹ ለእስር ተዳረጉ፡፡ ሀብት ንብረታቸው ተወረሰ፡፡ ከዚያም ወደ ሳይቤሪያ ተግዘው ታሰሩ፡፡ ጋኒባል ይህን እንዳወቁ ተስፋቸው ደብዝዞ ግራ ተጋቡ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ያላሰቡት ሌላ አደጋ ከፊታቸው ተደቀነ፡፡ አደጋውም የጓደኛቸው የሜጀር ጀነራል ጎልጎሩኮቭ “‹መፈንቅለ-መንግሥት ተባባሪና ደጋፊ ነህ›” ተብለው ወደ እስር ቤት የመወሳዳቸው ክስተት ነበር፡፡

ላይክስ አይበድልም! ለጥቂት ወራት ታስረው እንደቆዩ ፊልድ ማርሻል ጀነራል ሚኒች የሚባል የሩሲያ መከላከያ ጦር ኤታማጆር ሹምና የጋኒባል ተማሪና አድናቂ የነበረ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከእስር በማስወጣትና ሕይወታቸውን በማትረፍ የጦር ሰፈር ምሽጎች መርማሪ በማድረግ በሥራ ላይ አቆያቸው፡፡ በእርግጥ ይህ ለውለታ ሲባል የተደረገላቸው አይደልም – የነበራቸው ከፍተኛ ወታደራዊ የሙያ ችሎታና ክህሎት አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት እንጂ! ይህም ሆኖ ጋኒባል ከዓይነ ቁራኛ ክትትል ነፃ አልሆኑም፡፡ ብዙ ሰላዮች ተሰማርተውባቸው በየአቅጫው ይከታተሏቸው ስለነበር ከፍርሀትና ከስጋት ነፃ ሆነው መኖር አልቻሉም ነበር፡፡

Description: F:\Gannibal\141px-Elizabeth_of_Russia_-_engraving_07.jpg

ሌላው መፈንቅለ መንግሥት፡- ጀነራል ቫሲሊ ሉኪች ዶልጎሩኮቭ እና የአበሮቹ የለውጥ እንቅስቃሴ ተኮላሽቶ ወደ ሳይቤሪያ ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ሌላ ጥንቃቀቄ የተሞላበት መፈንቅለ-መንግሥት በከፍተኛ የጦር አለቆችና ቁልፍ ሚና የተጫወቱትን አብርሃም ፔትሮቪች ጋንባልን ጨምሮ በታላቁ ጴጥሮስ የተሀድሶ ፈለግ ተቆርቋሪዎችና ደጋፊዎች ዘንድ ውስጥ ውስጡን ሲብላላና ሲያንሰራራ ከቆየ በኋላ ታህሳስ 6 ቀን፣ 1741 ዓ.ም በቅዱስ ፒተርስበርግ ተካሄደ፡፡ በውጤቱም የታላቁ ጴጥሮስ ልጅ ኤልዛቤጥ ፔትሮቭና የሩሲያ ንግሥት (ዛር) ሆና ነገሠች፡፡ ኤሊዛቤጥ እንደነገሠች እንደ ጀነራል ሚኒሽኮቭ እና እንደ ፊልድ ማርሻል ጀነራል ሚኒች  ያሉ ተጀምሮ ለነበረው የሩሲያ ተሀድሶ እርምጃ እንቅፋ የሆኑ ከፍተኛ የጦር መኮንችና መሣፍንት ሳይቤሪያ ውስጥ ወደሚገኘው ፔሊም ወደተባለ ቦታ ተግዘው እስር ቤት ተወረወሩ፡፡

ስዕል፡- የታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ ልጅ ንግሥት ኤልዛቤጥ ፔትሮብና

በአንፃሩ ደግሞ እንደ አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል በሳይቤሪያ ውስጥ በግዞት ይማቅቁ የነበሩትን ሁሉም የአባቷ የለውጥ ደጋፊዎች ተለቀው ወደ ሞስኮ እንዲመጡ አደረገች፡፡ ጀነራል ቫሲሊ ሉኪች ዶልጎሩኮቭም እንደዚሁ ነፃ ተደርጎ ከሳይቤሪያ ግዞት ወደ ሞስኮ መጣ፡፡ በተለይም ንግሥት ኤልሳቤጥ ታላቁ ጴጥሮስ ከሞተ በኋላ አብርሃም ጋኒባልን ከደረሰባቸው ስቃይ በማላቀቅ በተለያዩ የክብር ሹመቶች አሸበረቀቻችው፡፡ በመጀመሪያ ከሌፍትናንት ኮሎኔልነት ማዕረግ ወደ ሻለቃነት ማዕረግ እንዲወርዱ የተደረጉትን አብርሃምን ከፍ አድርጋ በሜጀር ጀነራልነት ማዕረግ በማሳደግ በሙያቸው እንዲሠሩና የቅርብ አማካሪዋ አድርጋ ሾመቻቸው፡፡ ቀጥሎ ከ1742 እስከ 1752 ድረስ የሬቫል (የዛሬዋ ቲላን፣ ኢስቶኒያ) አገረ ገዥ ሆነው አስተዳደሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ጥር 12 ቀን፣ 1742 ዓ. ም. የሩሲያ የመሥፍንነት (nobility) ደረጃ እና ለቤተሰቦቻቸው በተምሳሌትነት የሚያውርሱት ባለ አርማ ወታደራዊ የደንብ ልብስ (“ኮት ኦፍ አርምስ”) እንዲሰጣቸው ለንግሥት ኤልሳቤጥ የሚከተለውን ደብዳቤ ፃፉ፡-

… ንግሥት ሆይ! ከጥቁርነቴ በስተቀር ሁለንተናየ ሩሲያዊ ነው፡፡ አፍሪካዊ ነኝ፡፡ የተወለድኩ ሎጎን ነው፡፡ የልዑላን ቤተሰብ፤ የመሳፍንት ወገን ነኝ፤ በጥቁርነቴ እጅግ በጣም እኮራለሁ! ሀገሬን በሀቀኝነት፣ በታማኝነትና በቅንነት ከሙስና ንፁህ ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ እንደዚህ እንደ እኔ ሀገራቸውን ያገለገሉትን ሁሉ እጅግ የላቀ አክብሮት እሰጣቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ ላበረከትኩት አገልግሎት የሩሲያ የመሣፍንትነት (ኖቢሊቲ) ደረጃ እና ለቤተሰቤ አርማ የማስተላልፈው ወታደራዊ የማዕረግ ልብስ (ኮት ኦፍ አርምስ) እንዲሰጠኝ በታላቅ አክብሮት አመለክታለሁ፡፡

Description: File:A Hanibal signature.jpg

ንግሥቲቱም ማመልከቻውን ተቀብላ ፈቀደችላቸው፡፡ በመሆኑም በ1744 ዓ. ም. በፕስኮቭ ብላስት ውስጥ በሚገኜው በሚካይሎቭስካይ ወረዳ 10 ቀበሌዎችን የሚያጠቃልል በሽህ ከሚቆጠሩ ነጭ ጭሰኞች ጋር በርስትነት ተሰጣቸው፡፡

Description: https://upload.wikimedia.org/wikipedia/commons/thumb/4/4e/%D0%93%D0%B5%D1%80%D0%B1_%D0%93%D0%B0%D0%BD%D0%BD%D0%B8%D0%B1%D0%B0%D0%BB%D0%B0.PNG/220px-%D0%93%D0%B5%D1%80%D0%B1_%D0%93%D0%B0%D0%BD%D0%BD%D0%B8%D0%B1%D0%B0%D0%BB%D0%B0.PNG

ጋኒባል ጥር 12 ቀን፣ 1742 ዓ.ም በፊርማቸው

የፃፉት ደብዳቤ- በቲላን ከተማ ወመዘክር ተሰንዶ የሚገኝ፡፡

ጋኒባል እንዲሰጣቸው የጠየቁት ወይም የመረጡት የቤተሰብ ተምሳሌያዊ ምልክት ዝሆን እንዲሆን እና ከዝኾኑ ላይ ንሥር፣ ከሥሩ ደግሞ “FVMMO” የሚል ማህፀረ-ቃል ተበይዶ የተቀረጽበትና የሚንጠለጠል አርማ ነው፡፡ ምልክቱና አርማውም የሚከተለውን ቅርፅ ያካተተ ነው፡፡ ከዚህ ላይ የዝሆኑን ትእምርተ-ተምሳሌነትና “FVMMO” የሚለውን ማህፀረ-ቃል ትርጉም መግለጽ ያስፈልግ ይሆናል፡፡ የዝሆኑ ሁለንተናዊ ተምሳሌነት ኩራት፣ ታላቅነት፣ ታጋሽነት፣ ፅኑነት፣ ወዘተ. የሚያመለክት ሲሆን “FVMMO” የሚለው ደግሞ “Fortuna Vitam Meam Mutavit Omnino” የላቲን ቃላት የሚወክል ማህፀረ-ቃል ነው፡፡ ይህ በእንግሊዝኛው፡- “Fortune has changed my life entirely” የሚል ትርጉም ያሰጣል፡፡ ወደ አማርኛ ሲተረጎም ደግሞ፡- “ዕድል ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ቀየረችው” ማለት ይሆናል፡፡ ከአርማው ላይ እንደምናየው ንግሥት ኤልሳቤጥ ጋኒባልን የተለያዩ ብሔራዊ የክብር መዳሊያዎች ሸልማቸዋለች፡፡ 

አብርሃም ጋኒባል በ1752 ዓ. ም የሩሲያንና የሰዊድንን የድንበር ወሰን በኃላፊነት እንዲያካልሉ ተሾሙ፡፡ በመሆኑም ለአራት ዓመታት ኮሚሽኑን በመምራት እስከ ዛሬ ድረስ በሁለቱ ሀገሮች መካከል በቋሚነት የሚያገለግለውን የድንበር ወሰን አካለሉ፡፡ በ1756 የላዶጋ ካናል ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የሩሲያ የጦር ምሽጎች መርማሪ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ሠሩ፡፡ ከዚያም በኋላ አብርሃም እድሜያቸው እየገፋ በመምጣቱ በ1762 ዓ.ም. ከመንግሥት ሥራ ጡረታ ለመውጣት አመለከቱ፡፡ እንዳመለከቱም የሙሉ ጀነራልነት ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡ የጡረታ መብታቸውም ተከበረ፡፡ ነገር ግን እጅግ የሚያሳዝን አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ይኸውም አብርሃም ጡረታ እንደወጡ እንባቸውን ያበሰችላቸው፣ እንደ እህት የሚያምኗት፣ ንግሥት ኤልሳቤጥ ፔትሮቭና በዚያው ዓመት (በ1762 ዓ. ም.) (በ52 ዓመቷ) ሞት መገጣጠሙ ነበር፡፡ እርሷ እንደሞተች ካቴሪን ሁለተኛ ነገሠች፡፡ ምንም እንኳን ጀነራል አብርሃም ጋኒባል በጡረታ ቢገለሉም ንግሥት ካቴሪን ሁለተኛ ከቅዱስ ፒተርስበርግ እስከ ሞስኮ የሚዘልቀውን ካናል ፕላን እንዲቀይሱ ስለጠየቀቻቸው በተሳካ ሁኔታ ፕላኑን ሠርተው አስረከቡ፡፡ ከዚህ በኋላ እስከ በመሥፍንነት የተሰጣቸውን ሰፊ የእርስት መሬት በማሳረስ ሲጠቀሙ ቆይተው ሞቱ፡፡

ይቀጥላል

ኮሮናን እንዋጋ፣

ለአፍታ ሳንዘነጋ!


 41 total views , 1 views todayRELATED ITEMS:ታሪክ-ባሕል

CLICK TO COMMENT

ታዛ

ደብረ ያሬድ አሳታሚ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በንግድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 ዓ.ም መሰረት ተመዝግቦ በየወሩ የሚታተም በስነ-ጥበብ፣ ባህልና ትውፊት፣ ታሪክና ቅርስ እንዲሁም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር መፅሔት በ2009 ዓ.ም ተቋቋመ።

Copyright © 2018 ደብረ ያሬድ አሳታሚ

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories