ጁዶ ስትራቴጂ ኢትዮቴሌኮም ቻይና እና አሜሪካ

us china


    Esleman abay  የዓባይ ፡ ልጅ                

አሜሪካ የቻይናን የኢኮኖሚ ግብግብ መመከት የሚያስችል ድል ተቀዳጀች” ዎልስትሪት ጆርናል ይዞት የወጣው ዘገባ ነው። ዎልስትሪት ይህን ያለው በአሜሪካ የሚደገፈው የቮዳፎን ጥምረት በቻይና የሚደገፈውን የ MTN ቡድን በኢትዮ-ቴሌኮም ጨረታ ላይ ማሸነፉን ተከትሎ ነው።

የዘገባው አንድምታ ከጩኸትም የዘለለ መሆኑን የሚያስረግጥልን ደግሞ የ Safaricom ጥምረትን ፈንድ እያደረገ የሚደግፈው አሜሪካዊ ተቋም፡  IFDC ከድሉ ዋዜማ ማለትም አርብ ላይ የተናገረውን ስንሰማ ነው።  “በትግራይ የተከሰተውን ቀውስ ከአሜሪካ መንግስት ኤጄንሲዎች ጋር በትኩረት እየተከታተልነው ነው” ነበር ያለው።  IFDC ያክልና “ነገሮች በ Vodafone ጨረታ እና የምናቀርበውን ፈንድ ተከትሎ የሚፈጠሩ ነገሮችንም በአንክሮ እየተከታተልን ነው” ብሏል። ይህን በተናገረ ማግስት የተመኘው የ vodafone ቡድን አሸነፈለት።

ስለ IFDC
“ቻይና ድፍን አለምን ልትቆጣጠር ነው” የሚለው የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎችን እንቅልፍ አሳጥቶ የሚገኝ አደጋ ነው። ስጋቱን ለመመከት ስትራቴጂ ከነደፉ ሰነባብተዋል። ስትራቴጂው አሜሪካ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ማብቃት በኋላ የሶቬት ተፅዕኖን ከምስራቅ አውሮፓ ለመንቀል ቀርፃው ከነበረው መጠነ ሰፊ የድጋፍ ዘመቻ ጋር የሚመሳሰል ማርሻል ፕላን ነውም የተባለለት ነው። እሱም IFDC ሲሉ ባቋቋሙት የፋይናንስ ተራድኦ ተቋም እንዲተገበር እየሆነ ይገኛል። ይህ International Development Finance Corp (IFDC), 2019 ላይ ነበር ወደ ስራ የገባው።

ይሁንና IFDC ያዘጋጀው 60 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነበር። ከሚጠብቀው ፈተና አንፃር ራሱም ደሃ ነው ነበር የተባለው በአሜሪካዊ ኢኮኖሚስቶች። ቻይና ለ’ሮድ ኤንድ ቤልት ኢኒሼቲቭ’ 1 ትሪሊዮን ዶላር ነው በጥሬው የመደበችው። IFDC ይህን የቻይና ግዙፍ መዋዕ ነዋይ በቀጥታ ማሸነፍ አይደለም መገዳደርም እንደማይችል ተገንዝበዋል። ቻይና በፓኪስታን ብቻ ያፈሰሰችው ገንዘብ ብቻውን ከ IFDC 60 ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ነበር። አሜሪካዊ ፖሊሲ አውጪዎች ታዲያ ሌላ መላ ዘየዱ። እሱም “ጁዶ-ስትራቴጂ” የሚባለው ነበር። ፎሬይን ፖሊሲ መፅሔት ላይ ከመፃፍ ባለፈ የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ አቅጣጫ በማመላከት ተደማጭ የሆኑ ጎምቱዎች Ethan B. Kapstein እና Jacob N. Shapir በግልፅ ያስቀመጡት መላ ነው፣ ጁዶ-ስትራቴጂ!

የኢኮኖሚክሱ ጠበብት ጁዶ-ስትራቴጂ የሚሉት አነስተኛ ኩባንያዎች ግዙፎቹን ጠልፈው የሚጥሉበትን መላ ነው። ለዚህም ሶስት ዘዴዎች ግብ መምቻ ናቸው አሉ። አንደኛ የቻይና የብድር አሰጣጥ ከአለማቀፉ የፋይናንስ አተገባበር አንፃር ግድፈቱን እየነቀሱ ማሳጣት። ይኸውም ቻይና ለታዳጊ አገራት የምታቀርበው ብድር የአገራቱን የመመለስ አቅምና ገንዘቡን በወጉ ስለመጠቀማቸው ተገቢውን ቅድመ ስራ ሳታከናውን ነው የሚል ነው። በዚህም አገራቱ እንደ ወደብ ያሉ ግዙፍ ሐብትና የማዕድን ሐብታቸውን ለመውረስና ቅኝ ለመግዛት ስለመሆኑ የአንዳንድ አገረት ገጠመኞችን ማሳያ እያደረጉ ማጥላላት ይገኝበታል።


ሁለተኛው በቻይና ብድር የታዳጊ አገራቱ ጥቂት ሰዎች ብቻ በሙስና የሚበለፅጉበት እንጂ ብዙሐኑን ድህነት ላይ ያቆያልና ይህንኑ ማጋለጥ የሚል ነው። ቻይና የራሷን ዜጎች በታዳጊ አገራት ጠቃሚ ስራዎች ላይ በስፋት ስለምታሰማራ ሰፊው ህዝብ የበይ ተመልካች ሆኗል የሚለውን በተደጋጋሚ ማስተጋባት። በቻይና ብድር የተጠቀሙ ሙሰኛ ግለሰቦችን ጉዳይ ይፋ ማድረግ። ይህንንም በታዳጊ አገራቱ በሚገኙ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ሚዲያና ተቋማት በተጨባጭ ማስጮህ። ተጠያቂም ማድረግ።
ሶስተኛው ዘዴ በቻይና ብድር ሊወረሱ የተቃረቡ የታዳጊ አገራት ሐብት ንብረቶችን የአሜሪካ ኩባንያዎች የ IFDC ተቋም በሚያቀርበው ፈንድ እየታገዙ እዳውን ከፍለው ከመወረስ ማስጣል። እንዳስፈላጊነቱም የማስለቀቂያ ገንዘቡን ጥቂት ጊዜ አብሮ በመስራት እያካካሱ ነፃ ማስቀጠል። በዚህም ቻይናን ከአፍሪካና ከተቀሩት ታዳጊ አገራት ማፋታት ይቻላል ይላል የጁዶ ስትራቴጂው።

MTN ፡ Vodafone ፡ Safaricom
የደቡብ አፍሪካው mtn ግሩፕ የቻይናውን ሁዋዌ እና ዜድቲኢ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ረጂም ጊዜ አጋር ነው። በቅርቡም ከቻይናው road and belt ጋር ትብብር በመፍጠር ከአገሪቱ ሁለት ባንኮች የሚቀርብ ፈንድን መጠቀም የጀመረ ነው።

የአሜሪካው IFDC ለቮዳፎን እና ሳፋሪኮም ከየትኛውም ንግድ ባንክ ባነሰ ወለድ ብድር እያቀረበላቸው ነው። በዚህም ኩባንያዎቹ የቻይና ቴክኖሎጂን አይጠቀሙም። በከንፃሩ እንደ ኤሪክሰን ኤቢ ሳምሳንግ ኖኪያ ካሉት እንዲጠቀሙ የተስማሙበት ነው።

° የአሜሪካ ቻይና የንግድ ጦርነትና ኢትዮ ቴሌኮም
አሜሪካና ቻይና ለበላይነት የሚያደርጉት ፍልሚያ በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ነው” የሚለውን የአቶ ዘመዴነህ ንጋቱ አስተያየት ዛሬ ከ ኤኒውስ ዘገባ ውስጥ ተመልክቻለሁ። በተጨማሪም ኢትዮ-ቴሌኮም የውጭ ኩባንያዎችን እንዲወዳደሩ ሲጋብዝ ዘርፉ ካለው አለማቀፍ ተመራጭነት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታና በትግራይ ጦርነት የተከሰተበት ወቅት ላይ መሆኑ አለማቀፍ ፉክክርና ትንቅንቁን ከቢዝነስም በላይ አክርሮታል ይላል ዘገባው።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች የመረጃ ልውውጥ ስምምነት ካላቸው ሀገሮች አንዷ ናት። በተመሳሳይ ከቻይና ጋርም ቅርብ ወዳጅነት አላት። ኢትዮ-ቴሌኮም ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የቻይና ኩባንያ መሳሪያዎችን ነው የሚጠቀመው።
አሜሪካ የቻይናው ሁዋዌን መሳሪያዎች ከሚጠቀሙ ሀገራት ጋር የፀጥታና ደህንነት መረጃዎችን መለዋወጥ አቆማለሁ ማለት በጀመረችበት ወቅትም ጉዳዩ ከኢትዮቴሌኮም ጋር መድረስ የጀመረው ያኔ ከአመታት በፊት ነው። በወቅቱ ቻይና ሰራሽ የኔትወርክ መሰረተ ልማት የሚጠቀመው ኢትዮ-ቴሌኮም በአሜሪካና ቻይና የንግድ ውዝግብ ሳቢያ የገጠመኝን ፈተና ከቻይና መንግስት ጋር በመነጋገር ለመፍታት እየሞከርኩ ነው ያለው የዛሬ 3 አመት ገደማ ነበር።

የሁዋዌይ ኩባንያ ኢትዮጵያ ከ 2010 እ.ኤ.አ ጀምሮ በተገበረችው የሁለተኛው ዙር የቴሌኮም ኔትወርክ ማስፋፊያ ውስጥ ትልቁን ስራ የያዘ ነው። የአዲስ አበባን ኔትወርክ ማስፋፊያም ሰርቷል። ከሌላኛው የቻይና ኩባንያ ዜድቲኢ ጋርም ትልቁን ድርሻ ይዞ እስከ ሶስት ቢሊየን ዶላር የኔትወርክ ማስፋፊያ አከናውኗል። ለኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና የነበረውም ሁዋዌ የጀመረው በቢሊየን ዶላር የሚተመን ፕሮጀክት በሁለቱ ፀብ መስተጓጎሉ ነበር። ሁዋዌይ ለሚያቀርባቸው ቁሳቁሶች የአሜሪካ ምርቶችን ጭምር መጠቀሙ ማዕቀብ ከተጣለበት በኋላ ስራውን ማከናወን የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶም ነበር። በማዕቀቡ የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ጭምር የኪሳራ አደጋ በማንዣበቡ በጊዜያዊነትም ቢሆን ዋሽንግተን ማዕቀቡን በከፊል እንድታላላ አስገድዷት እንደነበርም የሚታወስ ነው።

ከለውጡ ፡ ወዲህ
ጠሚ አብይ ወደ ስልጣን እንደመጡ አየር መንገድ ቴሌ እና ኤሌክትሪክን ወደ ግል አዛውራለሁ ሲሉ ምዕራባዊያን ወደ ኢትዮጵያ ትኩረታቸውን አዞሩ።
የኢትዮጵያን ሪፎርም በመደገፍ ግዙፍ ፈንድ በ IMF WORLD BANK እና በሌሎችም ተቋማት ሰፊ ገንዘብ አቀረቡ። ገንዘብ ብቻ አይደለም ያቀረቡት። የአሜሪካ መንግስት  የኢትዮጵያን ለውጥ በደህንነት በመረጃና በወታደራዊ መስኮች ለመደገፍ ስራ መጀመሩን የገለፀው በይፋ ነበር። በኢትዮጵያ የባንክ አቪዬሽን የቴሌኮም ዘርፎች ለመሰማራትም የምዕራባዊያኑ በተለይም የአሜሪካ ኩባንያዎች ውትወታ ትንፋሽ የሚቅርጥ ነበር።

በአንፃሩ ጠሚ አብይ የኩባንያዎቹን ጨረታ ያዝ ለቀቅ እያደረጉ የሪፎርም ተግባራትን ቀጠሉ። አየር መንገድና ኤሌክትሪክን አቆይተው በቴሌኮሙ ጨረታ ላይ ቀጠሉ። በሂደትም አገራዊ ለውጡ በትግራይ ጦርነት ሳቢያ ሌላ አክል ተጋረጠበት። ጦርነቱ በተጀመረ ማግስት ወቅቱ ዶናልድ ትራምፕ በተቀመጡበት ነጩ ቤተ መንግስት መግለጫ ተሰጠ። ይኸው በማይክ ፖምፒዮ የተሰጠ መግለጫ “ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን የማስከበር ነውና በአጭር ጊዜ ህግ የማስከበር ዘመቻውን ቋጭታ ፀጥታዋን መመለስ አለባት የሚል ነበር። ሰራዊቱ መቀሌን በሳምንታት ውስጥ ሲቆጣር ግን የአሜሪካ መግለጫ ይለወጥ ጀመረ። ርዳታ ሚዲያ ምፈገለልተኛ ምርመራ ወዘተ..መግለጫው ዛቻ መልክ ያዘ። በዚህ ዚቻ መሃል ጠሚ አብይ የቴሌኮም ጨረታው የውጭ ኩባንያዎችን ለመቀበል ዝግጅቱን በማገባደድ ላይ ነው ማለታቸው ይታወሳል።  በዛን ወቅት ይህን መግለጫ ለመስጠት መንስኤው ግልፅ ነው።
ጎን ለጎንም እነ IMF WORLD BANK የቴሌኮም ጨረታው ፍትሃዊና ግልፅ ስለመሆኑ እየወተወቱ ነበር። በአንድ በኩል ስለ ትግራዩ ጦርነት በሌላ በኩል ጨረታው አካሄድ ላይ ጫናው ቀጠለ። ነገሩ ለብርቱ የውጪ መዳፎች በለስ ነበርና አለማቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ማብዛታቸው አይቀሬ መሆኑንም እነ ኳርትዝና ሌሎችም አስነብበውት ነበር።

በመጨረሻም አሜሪካ ሀፍረቷን ጥላ በሰብአዊ መብት ሰበብ ማዕቀብ ልጥል የመጨረሻ አይነት ዛቻዋን ገለፀች።  የ belt and road ተቀናቃኙም ስለ ትግራይ ጉዳይና ስለ voadfone ፈንድ የአሜሪካን አቋም ተከትሎ እውነታውን ተናገረ ።
በማግስቱ ይፋ የተደረገው የአሜሪካ መራሽ ኩባንያው ማሸነፍ የኢትዮጵያ መንግስት ያዝ ለቀቅ ያደረገውን ካርታ ባግባቡ ተጫውቶት ይመስለኛል።

አሸናፊዎችስ?

በኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭ አሸነፉ ከተባለው የቮዳፎን ጥምረት ባለፈ አሜሪካም ከቻይና ጋር በገባችበት የኢኮኖሚ ጦርነት ውስጥ ወሳኝ ድል ስለመቀዳጀቷ ተዘግቧል። ፍጥጥ ብሎ በመጣው የአሜሪካ ዙሪያ ገብ የማዕቀብ ናዳ ፊት ለፊት ጠሚ አብይም ውጤታማ አጨዋወት ስለመከተላቸው እየተገለፀ ነው። በተለይም ጨረታውን ከአገራዊ የሪፎርም ተግዳሮቶች ጋር እያናበቡ ውሳኔውን በማቆየት መላቸው።
ፕሮፌሰር አልማርያም ደጋግመው ሲያስጠነቅቁ እንደነበረው የባይደን መንግስት ቻይናን በአፍሪካ ለመግጠም ኢትዮጵያንም እጅ መፍቻ ሊያደርጉ ነው ብለዋል። ለባይደን ዘመቻ ፊታውራሪ የሆነውና እነ ቮዳፎንን አይዟችሁ ሲል የቆየው IFDC ስለ ትግራዩ ቀውስ እጁን አስገብቶ ነበርና የጨረታውን ውጤት ተከትሎ ለውጥ እንደሚያመጣ አያጠራጥርም። ግን እስከ ምን ድረስ የሚለውን አብረን እናያለን።
በቻይና የሚደገፈው የ MTN ቡድን በጨረታው መሸነፍ ቤይጂንግ ከአዲስ አበባ ከምትጠቀማቸው ሌሎች አማራጮች አንፃር ቅሬታ ይፈጥርባቱ ይሆን?
ኢትዮ ቴሌኮም የሁለቱ ፀብ የደቀነበትን ፈተና ከቻይና ጋር መምከር የጀመረው ከአመታት በፊት መሆኑንም እዚጋ ልብ ይሏል።
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የበረታባት ተፅዕኖ road and belt ን በኢትዮ ቴሌኮም ድል ለማዳከም ከማሰብ የመነጨ ነው በሚለውን ሐሳብ ለሚስማማ ሰው በርግጥም “አንድ ታዳጊ አገር በዚህ ወቅት በቢዝነስ ከሚካሄድ ጨዋታ የተሻለ ምን ካርታ ሊኖራት ይችላል?”

     esleman abay የዓባይ ልጅ

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories