ግብጽ ረቂቅ ህገ-መንግስት እና የአባይ ውሃ ጉዳይ

የ2011ዱ የአረብ ፀደይ አብዮት ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን ሲወገድ የተተካው የሞሐመድ ሞርሲ መንግስት ስለ ናይል “የደም ጠብታችን ወይም የናይል ውሃ” የሚል መርህ ነበር የተከለው። ይሁንና ብዙም ሳይቆዩ በሀይል ስልጣን ለቀቁ።
የሞሐመድ ሞርሲን መንግስት የተካው የሽግግር መንግስት አድሊ መንሱር በሚባሉ የህግ ባለሙያ ፕሬዝዳንትነት የሚመራ ነበር፡፡መንግስት ህገ-መንግስት የማሻሻል ስልጣን የተሰጠው ይህ መንግስት ሃምሳ አባላት ያለው ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራውን አጠናቅቆ ለፕሬዝዳቱ የህገ መንግስቱን ረቂቅ አስረከበ፡፡
ረቂቅ ህገ-መንግስቱም ለህዝበ-ውሰኔ በ14 እና 15 ጥር 2013 እኤአ ቀርቦ በ97 በመቶ ድጋፍ ተቀባይነት አገኘ ተባለ፡፡ በዚህ ህገ መንግስት በተለይም አንቀጽ 44 ላይ ስለ ዓባይ ውሃ ያስቀመጠው ድንጋጌ የግብፅን ጥንታዊ ግትርነት ያስረጠ ነበር።

ናይል/ዓባይ በግብፅ ህገ-መንግስት

የአንድ ሀገር ህገ መንግስት ተፈፃሚነት በግዛቷ ውስጥ ቢሆንም የውጭ ግንኙነት ዋና መስመራወቸው ላይም ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው። Foreign policy is a reflection of domestic policy እንደሚባለው።

በግብጽ አዲስ ረቂቅ ህገ-መንግስት ውስጥ ማውጫውን ጨምሮ ናይል የሚለው ስም 7 ጊዜ ተጥቅሷል፡፡ በመግቢያው ላይ ያረፈው ዓረፍተ ነገር “ግብፅ የናይል ስጦታ ነች እንዲሁም የግብፃውያን ስጦታ ለሰብዓዊነት” ይላል፡፡ ማንም የሚክደው ሐቅ አይደለም ግብፅ የአባይ ስጦታ ለመሆኗ፡፡ አባይ ባይኖር ኖሮ ጥንት ግብፅ ደረቅ በረሐ በሆነ ነበር (አሁን ግን በተገኘ ሳይንሳዊ መረጃ ግብፅ አባይ እንኳን ቢደርቅ ለ500 ዓመታት የሚበቃ የከርሰ ምድር ውሃ ባለቤት ናት)፡፡ የሆነ ሆኖ ግብፅ የአባይ ስጦታ ናት ማለት አባይ የግብፅ ስጦታ ነው ማለት አይደለም፡፡ አባይ/ናይል የሚጋሩት ሀገራት ሁሉ፤ የህዝባቸው ስጦታ ነው፡፡ አባይ/ናይል የሚጋሩት የአስራ አንዱ ሀገራት ገጸ-በረከት ነው፡፡ ይሁን እንጅ ይህን ሐቅ የሚያፈርስ ነገር በግብፅ ረቂቅ ህገ-መንግስት አንቀጽ 44 ሰፍሮ ይገኛል፡፡

አንቀጽ 44 “መንግስት የናይልን ወንዝ ለመከላከል፣ እንዲሁም የግብፅን ታሪካዊ መብት ለማስጠበቅ፣ ጥቅሞቹንም ለማሳደግ እና  ለማረጋገጥ፣ ውሃውንም ከብከነት እና ከብክለት ለመጠበቅ ቁርጠኛ ነው፡፡…. (The state commits to protecting the Nile River, maintaining Egypt’s historic rights thereto, rationalizing and maximizing its benefits, not wasting its water or polluting it…) (በከፊል የተተረጎመ) ይላል፡፡ አሁን እዚህ ላይ ዋና ጉዳዩ ግብፅ በህገ-መንግስቱ ስለ ናይልን ከብከነት እና ከብክለት ለመጠበቅ እንዲሁም ደግሞ ጥቅሙን ከፍ ከማድረጓ አይደለም ችግራችን፡፡ እሱን ቢያደርጉ ምንኛ ባመሰገንናቸው፡፡ ዋናው ጉዳይ ያለው “…የግብፅን ታሪካዊ መብት ለማስጠበቅ…” የሚለው ሀረግ ላይ ነው፡፡ ግብፅ ይህን ስትል ምን ለማለት ፈልጋ ነው? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡

ግብፅ አለኝ የምትለው “ታሪካዊ መብት” የሚባል ነገር እንደ ግብፃውያን ትንታኔ በቅኝ ግዛት ዘመን በእንግሊዝ የተፈረመውን የ1929 “ስምምነት” እና እንዲሁም በ1959 በግብፅ እና በሱዳን መካከል የተደረገን ስምምነት የተመረኮዘ ነው፡፡ በነዚህም “ስምምነቶች” መሰረት ግብፅ የተፋሰሱ አምባገነን እንድትሆን ያደረገ ሲሆን ውሃ ከመከፋፈል ባለፈ የላይኛው ተፋሰስ የውሃ ስራዎችን የመቆጣጠር እንዲሁም ስራዎችን የመፍቀድ እና የመከልከል መብት የሚሰጡ ናቸው፡፡ የ1929 “ስምምነት” እንግሊዝ ቅኝ የምትገዛቸውን ሀገራት በመወከል ለራሷ ስትል ከራሷ ጋር የፈረመችውደብዳቤ ልውውጥ ነበር፡፡  ይሁን እንጅ የ1929 የቅኝ ግዛት ውል በመሆኑ እና ነፃ የወጡ ሀገራት አይመለከተንም ሲሉ የሻሩት መሆኑ እንዲሁም ሱዳን ነፃ እንደወጣች እንዲቀየርላት የጠየቀች በመሆኑ ወድቅ የሆነ ያረጃ እና ያፈጀ ጉዳይ ነው፡፡ የ1959 ስምምነትም በግብፅ እና በሱዳን መካከል የተደረገ የሁለትዮሽ ስምምነት ሲሆን የናይልን ዓመታዊ ፍሰት ሙሉበሙሉ በመከፋፈል ለግብፅ 55.5 ቢሊዮን፣ ለሱዳን 18.5 ቢሊዮን እንዲሁም ሰሐራ በረሐ ላይ በተሰራው አስዋ ግድብ እና በተፈጠረው አባካኝ የናስር ሐይቅ አማካኝነት ለሚፈጠር ትነት ከ10 ቢሊዮን በላይ ኪዩቢክ ሜትር ውሃን ይሰጣል፡፡ ለላይኛው የናይል ተፋሰስ ሀገራትም አንዳችም ዓይነት ውሃም ያስቀረ ስምምነት አልነበረም፡፡ ሀገራቱም እንደነበሩ አልጠቆጠሩም፡፡ እንግዲህ ግብፅ ይህን አምባገነናዊ ስርዓት ነው “ታሪካዊ መብቴ” የምትለው፡፡ ኢትዮጵያ በወቅቱ ነፃ መንግስት ስለነበረች ይህ ስምምነት ሲፈረም በይፋ በዓለም መድረክ ተቃውሞዋን ያሰማች ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ያላማከለ ማናቸውም የናይል ስምምነት ዋጋ የሌለው እንደሆነ በግርማዊ ቀደማዊ ኃይለሥላ የዙፋን ንግግር እና ካይሮ በሚገኙ ዲፕሎማቶቿ በኩል በ1957 እኤአ አወጀች፡፡ ከዚህ ባሻገረም ማናቸውም ዓይነት ያልተሳተፈችበት ውል የአባይን ውሃ ከመጠቀም እንደማያግዳት ብሎም የዜጎቿን ፍላጎት ለማሟላት ንብረቷ የሆነውን ውሃውን እንደምትጠቀም በግልፅ አሳወቀች፡፡ በወቅቱ በቅኝ ቅዛት የነበሩ ሀገራትም ነፃ በወጡ ማግስት በቅኝ ገዥዎች የተፈረሙ ስምምነቶች እንደማይመለከቷቸው አሳወቁ፡፡ የኔሬሬ ዶክትሪን ለዚህ አንዱ አብነት ሊሆን ይችላል።

“ታሪካዊ መብት” ከዓለምአቀፍ የውሃ ህግ አንፃር

ዓለም አቀፍ የውሃ ህግጋት ሁሉንም የዓለም ሀገራት በአንድ ያስተሳሰረ ወጥ ዓለማቀፋዊ ኮንቬንሽን የለም፡፡ ሆኖም ግን በተለያዩ ጊዚያት ዓለምአቀፍ ፍርድ ቤቶች የወሰኗቸው ውሳኔዎች እንዲሁም ደግሞ ወሰን ተሸጋሪ ወንዞችን በሚጋሩ ሀገራት መካከል በተደረጉ ስምምነቶች መሰረት ወደ ልማዳዊ ህግነት ያደጉ መርሆዎች አሉ፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በተለያየ ጊዜ የመጡ የዓለምአቀፍ ህግ ምሁራን በምክኒያታዊነት ያስቀመጧቸው ሐተታዎች እና ትንታኔዎች አንድ የህግ ምንጮች ናቸው፡፡

በጥቅሉ ሲታይ አሁን ባለው የዓለም ስርዓት መሰረት የልማዳዊ ህግ መርህነት ማማ ላይ የወጣው ሚዛናዊ እና ምክንያታዊ የውሃ ግልጋሎት/Equitable and reasonable utilization የተሰኘው መርህ  ነው፡፡ ይህ መርህ በሀገራትም፣ በምሁራንም ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያስቻለው ዋናው ምክንያት በግርጌም ሆነ በራስጌ ሀገራት ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል አቅም እንዳለው በመታመኑ ነው፡፡ ለምሳሌ በዳኒዩብ ወንዝ ጋብችኮቮ-ናጊማሮስ ፕሮጀክት ጉዳይ ላይ በሀንጋሪ እና በስሎቫኪያ መካከል በነበረው አለመግባበት የዓለምአቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት/International Court of Justice ለጉዳዩ ውሳኔ የሰጠው በሚዛናዊ እና ምክንያታዊ የውሃ ግልጋሎት መርህ በመንተራስ ነው፡፡ በአንፃሩ ታሪካዊ መብት የሚባል ዓለምአቀፍ ህግ የሚያውቀው መርህም የህግም ድንጋጌ የለም፡፡ በርግጥ “ታሪካዊ መብት” የሚባለው ሃሳብ “ቀድሞ የመጠቀም መብት፣ የቆየ መብት” ወዘተ በሚሉ ቅጥያ ስሞቹ አንደ አንድ ህልዮት ወይም መሰረተ-እምነት በተለያየ መልኩ ይነሳ ነበር፡፡ ይህም ከወረቀት ያለፈ ነገር የለውም፡፡ በዓለምአቀፍ ህግ መርሆነትም የሚታወቅ ነገር አይደለም፡፡ ለትብብር ስምምነት ማዕቀፉ በተደረጉ ድርድሮችም ሆነ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በሚደረጉ ውይይቶች ግብፆቹ ይህን “ታሪካዊ መብት” አለን የሚል ፈሊጥ የሚያስገቡት እና የሚያነሱት ከተራ የትምክህተኝነት እና የማንአለብኝነት እብሪት የመነጨ እንጅ እውነታውን ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡

የናይል ተፋሰስ ዲፕሎማሲ

በዓለምአቀፍ ህግ መሰረት ሀገራት ዓለምአቀፍ ጉዳዮችን የሚዳስስ ሀገራዊ ህግን ቢያወጡም ወይንም በህገ-መንግስታቸው ቢጠቅሱም  ሌሎች ሀገራት ይህን የመከታተልም ሆነ የማወቅ ግዴታ የለባቸውም፤ የተፈፃሚነት ወሰኑ ህገ-መንግስቱን/ህጉን ባወጣችው ሀገር ግዛት የተገደበ በውስጥመሆኑ። በዚህም ግብፅ ዓለምአቀፋዊ የህግ መሰረት የሌለውን “ታሪካዊ መብት” የሚል ድምጋጌ በህግ-መንግስቷ ማካተቷ የሚያስገኝላት ህጋዊ ውጤት የለም፡፡ ይልቁንም የናይልን ውሃን በተመለከተ ለሚደረጉ ውይይቶች ፍቃደኛ አላይለመሆኗን ድጋሚ ያስረግጣል።

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories