ጌታቸው ወልዩ
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ቀመር ኦክቶበር 7 ቀን 1944 ቁጥራቸው አናሳ የሆነ ዐረብ አገሮች ተሰባስበው፤ በተለምዶ “ፕሮቶኮል ኦፍ አሌክሳንድሪያ” (Protocol of Alexandria) የተሰኘውንና በአማርኛ “የእስክንድርያ ፕሮቶኮል” እየተባለ በሚጠራው የዐረብ ሊግ እርሾ ወይም ጥንስስ ሀሳብ ላይ ከተወያዩ በኋላ፤ ከመግባባት ላይ ደረሱ።
ከዚያም በሚመሠርቱት ድርጅት፣ ኅብረት፣ ጥምረት፣ ትብብርና ሊግ ዙሪያ እሰጥ አገባ ውስጥ በመግባት፤ በስም አጠራሩ ላይ ውዝግብ ጀመሩ። በተለይ ምንም ነገርን ከራሷና ራሷ ጋር ብቻ አዛምዳ መጠቀም የምትፈልገው ግብጽ፤ ገና ከማለዳው “እኔ ያልኩት ካልሆነ በጭራሽ ሌላ ስም መሆን የለበትም!’ ብላ ክርክርና ውዝግብ መፍጠር ጀመረች።
ለምሳሌ:- ኢራቅ “የዐረብ ኅብረት (Arab Union) የሚል መጠሪያ ስም ለሁላችን ይበጀናል!” በማለት ሀሳብ አቀረበች። ሶሪያ በበኩሏ “የዐረብ ኅብረት፣ ጥምረት ወይም ትብብር (Arab Alliance) የሚለው መጠሪያ ስም የተሻለ ነው!” ስትል ሀሳቧን ሰነዘረች።
የመሥራቾቹ ዋነኛ ዘዋሪ የሆነችው፤ ራሷን የዐረብ አገሮች ወኪል፤ የሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ጠበቃ፤ የመካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ የበላይ አድርጋ የምትቆጥረው፤ ስሟን “የግብጽ ዐረብ ሪፑብሊክ” ብላ በመጥራት የምትታወቀውና ከአፍሪካዊነቷ ይልቅ ለዐረባዊነት ቅድሚያ የምትሰጠው ግብጽ፤ የሁለት እጆች ጣቶችን ያህል ቁጥር ባልነበራቸው “የእስክንድሪያ ፕሮቶኮል” ላይ ከመግባባት በደረሱ ዐረብ አገሮች ላይ ጫናዋን ማሳደር ጀመረች።
ይኸውም ግብጽ፦ “የዐረብ አገሮችን ያስተባብራል!” በሚል እንዲመሠረት የታቀደው የዐረብ አገሮች ጥምረት ስምና ግብርን በተመለከተ ኢራቅና ሶሪያ በጥቆማ ያቀረቡትን ሀሳብ፤ ጥንብ እርኩሱን በማውጣትና አፈር ድሜ በማስጋጥ፤ “ሞቼ እገኛለሁ!” በማለት፤ ከቀድሞ የቅኝ ግዛት አሳዳሪዋ እንግሊዝና ሊግ ኦፍ ኔሽን ቃላት ተበድራ “የዐረብ ሊግ” (Arab League) የሚል ስያሜ ሊሰጠው ይገባል ስትል ተሟገተች።
መታወቅ ያለበት የግብጽ ቅኝ ገዢ የነበረችው እንግሊዝ የዐረብ ሊግ ከመመሥረቱ ቀድማ ገና እንደ አውሮፓውያን ቀመር በ1942 የዐረብ ሊግ ምሥረታ ሂደትን ስታበረታታ የነበረች ነች። (1942-The United Kingdom promotes the idea of the Arab League.)
ይሁንና ኢራቅና ሶሪያ ግን “ዋናው ነገር የዐረብ አገሮች የትብብር መድረክ መፈጠሩና መኖሩ ነው እንጂ ስሙ ብዙ አያጨቃጭቀንም!” በማለታቸውና ኋላ ላይ የዐረብ አገሮች ቁጥር በርከት እያለ በመምጣቱ ውይይቱ ተጋግሎ፤ የዐረብ አገሮችን እንዲያስተባብርና እንዲያስተሳስር በማሰብ፤ “የዐረብ አገሮች ሊግ” (The League of Arab States جامعة الدول العربية Jāmiʿa ad-Duwal al-ʿArabiyya) የሚለው ስም ሊጸድቅ ቻለ። የግብጽ ጫናም በሊጉ አገሮች ላይ “ሀ” ብሎ ተጀመረ።
በዚህም መሠረት:- ኢትዮጵያ እርሾ ካኖረችበትና ስምና ግብሯ ከገዘፈበት ከፓን-አፍሪካዊነት መጠሪያ ስም በመኮረጅና ፓን-ዐረባዊነትን በማቀንቀን፤ “የእስክንድርያ ፕሮቶኮል” ከተፈረመ ከሁለት ወራት በኋላ በጎርጎሮሳውያኑ ቀመር ማርች 1945 (መጋቢት 1937 ዓመተ-ምህረት) የዐረብ አገሮች ሊግ በካይሮ ተመሠረተ።
በቀዳማይ መሥራች አባልነትም:-ግብፅ ፣ ኢራቅ ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሊባኖስ፣ ሶሪያና የዚያን ጊዜ “ትራንስጆርዳን ኢምሬት” ትሰኝ የነበረውና በጎርጎሮሳውያኑ ቀመር 1949 “ዮርዳኖስ” የሚል መጠሪያውን የመረጠችው ዮርዳኖስ (ጆርዳን) መንግሥታት ስማቸው ሊጠቀስ በቃ። ወዲያውም የመን (ኋላ ላይ ሰሜን የመን) በመግባቷ፤ የመሥራቾቹ አባል አገሮች ቁጥር ስድስት ደረሰ። እናም ግብጽ የዐረብ ሊግ ከተመሠረተ በኋላ፤ የተለመደ የጫናና የብልጣ ብልጥ ዘዴዎቿን ተጠቅማ የሊጉን መቀመጫ ካይሮ ላይ እንዲሆን አስደረገችው።
ግብጽ በተመሳሳይ ሁኔታ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (Confederation of African Football) በኢትዮጵያ፣ በራሷ፣ ሱዳንና በዚያን ዘመን አፓርታይድ ሥር በነበረችው ደቡብ አፍሪካ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ቀመር በ1957 ከተመሠረተ በኋላ፤ በየትኛውም ዘርፍ ያላትን ተሰሚነት ለመጨመር በምታራመድው የእኩይ ስትራቴጂ መንገዶቿ ተጠቅማ የኮንፌዴሬሽኑን ዋና ጽሕፈት ቤት መናገሻ ከተማዋ ካይሮ ውስጥ ማስቀረቷ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የበርሊን ኮንፈረንስ እሳቦትንና ድርጊትን ቀድማ በአድዋ ጦርነት አሸናፊነቷና ድል አድራጊነቷ በመበጣጠሷ እና አያሌ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት እንዲወጡ በፓን አፍሪካኒዝም ትግል ወርቃማ ተግባር መከወኗ ወይም መፈጸሟ በቀሪ አፍሪካ አገሮች በጉልህ መታወቁ በጀ እንጂ፤ ግብጽ እኮ?! “አፍሪካ ኅብረት ያለበት የአዲስ አበባ አካባቢ ጭምር አመቺ ካለመሆኑ ባሻግር፤ ኢትዮጵያ ሰላሟ ያልተረጋገጠና ዘወትር ፀጥታዋ የሚናጋ በመሆኑ፤ የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት) ዋና ጽሕፈት ቤት ከኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ አዲስ አበባ ይውጣና ወደ ካይሮ ይሂድ! ወይም ይዛወር!” ብላ የምትናገር፤ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋሟ የገነገነ ለይምሰል “አፍሪካዊ ነኝ!” የምትል በዐረባዊነት ሽፋን በከንቱ የምትኮፈስ እኩይ አገር ነች።
ይሁንና “የዐረብ አገሮች ሊግ” ከተመሠረተ አንስቶ ነጻ አገር ሆነው ለመቀላቀል የሚፈልጉ ዐረቢኛ ተናጋሪ አገሮች ወደ ሊጉ መግባትን አጀንዳቸው አደረጉት። በመቀጠልም አፍሪካዊቷ ሊቢያ ነጻነቷን ካረጋገጠች ሁለት ዓመታት በኋላ እንደ አውሮፓውያን ቀመር በ1951 የዐረብ ሊግ አባል አገር ሆነች።
ከዚያ ደግሞ ሱዳን፣ ሞሮኮና ቱኒዚያ ከቅኝ ግዛት ከወጡ በኋላ እየተፋጠኑ ወደ ዐረብ ሊግ ተቀላቀሉ። እንደ አውሮፓውያን ቀመር በ1961 ኩዌትና በ1962 አልጀሪያ ወደ ዐረብ ሊግ ሲገቡ፤ ደቡብ የመን ነጻነቷን ተከትላ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1967 የሊጉ አባል አገር ሆነች።
የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች፣ ኦማን፣ ኳታርና ባህሬን በበኩላቸው፤ በተመሳሳይ ዓመት በአውሮፓውያን ቀመር 1971 ላይ የዐረብ ሊግ አባልነት ቦታን አገኙ። ሞሪታኒያ ደግሞ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች ከ13 ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያን አመት በ1973 ወደ ዐረብ ሊግ አመራች።
ቀጣዩ አስገራሚው ነገር ደግሞ፤ ግብጽ መንገዱን የመራቻትና ዐረብ ያልሆነችው የሶማሌያ ሪፑብሊክ፤ በኢትዮጵያ የየካቲት 1966ቱን አብዮት ተከትሎ የነበረውን የመንግሥት ለውጥና ያለመረጋጋት ገምግማ፤ ያቀደችውን አቅዳ፤ የኀይል ሚዛንና ድጋፍ ለማግኘት፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1974 (የካቲት 1967 ዓመተ-ምህረት) የዐረብ ሊግ አባል አገር ሆና ተመዘገበች።
ፍልስጤም በበኩሏ፤ ገና የአገር ቁመና ሳይኖራት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1976 “የፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት” (Palestine Liberation Organization) በሚለው የድርጅት ስሟ የዐረብ ሊግ አባል ሆነችና አንገቷን ቀና አድርጋ እስራኤልን የጎሪጥ መመልከት ጀመረች።
ከወራት በኋላ ደግሞ፤ ኢትዮጵያ በአምባገነኑ (ፋሺስቱ) ዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሌያ ሪፑብሊክ ወራሪ ሠራዊት የተከፈተባትን ጦርነት ለመቀልበስ ፍልሚያ በምታደርግበት ወቅት ሁኔታውንና አጋጣሚውን ተጠቅማ የሶማሌያ ሪፑብሊክን መንገድ የተከተለችው ጅቡቲ፤ በግብጽ እቅፍ ውስት ገብታ እሹሩሩ እየተባለች፤ የግብጽ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነች እስኪመስል የዐረብ ሊግ ደጃፍን አንኳኩታ የአባልነት መዝገብ ላይ ስሟን አስጻፈች።
በየደረጃውም የዐረብ ሊግ አባልነት እየተጠናከረ ሲመጣ፤ ሰሜን የመንና ደቡብ የመን ተዋኻዱና “የመን” የሚል መጠሪያ ስም በመያዝ፤ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በሜይ 1990 (ግንቦት 1982 ዓመተ-ምህረት) የዐረብ ሊግ አባል ሆኑ። ሚጢጢየዋ አፍሪካዊት አገር ኮሞሮስ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1993 አባል ስትሆን፤ ኤርትራ ደግሞ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን ስሌት በ2003 የዐረብ ሊግ ተለዋጭ አባል ሆና ተመዝግባ የዐረብ አገሮች ሊግን አባላት ቁጥርና አናሩት።
አባል አገሮቹም:- አልጀሪያ፣ ባህሬን፣ ኮሞሮስ፣ ጅቡቲ፣ ግብጽ፣ ኣርትራ (ተለዋጭ አባል)፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ኩዌት፣ ሌባኖስ፣ ሊቢያ፣ ሞሪታኒያ፣ ሞሮኮ፣ ኦማን፣ ፍልስጤም፣ ኳታር፣ ሳዑዲ ዐረቢያ፣ ሶማሌያ፣ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ ቱኒዚያ፣ የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶችና የመን ሆኑ። በተመልካችነት ደግሞ:-ብራዚል፣ ቬንዝዌላ፣ቻድ፣ ሕንድና አርሜኒያ ይገኙበታል።
እንደሚታወቀው የዐረብ አገሮች ሊግ ዐላማው:- እንደ ሰሜን አትላንቲክ ቃል-ኪዳን አገሮች የጋራ ጥምረት ወይም ስምምነት እንደሆነው (ኔቶ) እና በመደበኛ መጠሪያው የምሥራቅ ሶሻሊስት አገሮች ኀብረት እንደ ነበረውና “የወዳጅነት፣ ትብብር ወይም የጋራ መደጋገፍ ድርጅት” በአጭር አገላለጽ “የዋርሶው ስምምነት” (Warsaw Pact (WP) ተብሎ የሚጠራው የዋርሶው ስምምነት ድርጅት (The Warsaw Treaty Organization -WTO) አይነት ሆኖ፤ ቀዳማይ ተልዕኮውና ተግባሩም “በዐረቡ ዓለም ወይም በቀጣናው ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ማጠናከር!” የሚል ሆነ።
በተለይም ምጣኔ ሀብታዊ ትስስርን ማጠናከር፣ ግጭቶችንና ውዝግቦችን ለመፍታት በወታደራዊ ጉዳዮች መተባበር እና ፖለቲካዊ ዓላማዎችን ለማሳካት ትብብር ማድረግ የሚሉ ጉዳዮችንም አካተተ። [“የዋርሶው ስምምነት” /Warsaw Pact- WP/፦ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረትና በሰባት የምሥራቅ አውሮፓ ብሎክ /ሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም/ አገሮች በፖላንድ መዲና ዋርሶው በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የተፈረመ የጋራ ወታደራዊ መከላከል ስምምነት ነበር።]
ምንም እንኳን ከጊዜ በኋላ የዐረብ አገሮች ያልሆኑ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮችን ጭምር ለዓላማው ማስፈፀሚያ በአባልነት ያስገባው ይኸው “የዐረብ አገሮች ሊግ” በሥሩም:- በምኅጻረ-ቃል “የዐረብ ገንዘብ ፈንድ” (the Arab Monetary Fund -AMF)፣ “የዐረብ ፈንድ ለምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ልማት” (Arab Fund for Economic and Social Development -AFESD)፣ “የዐረብ ምጣኔ ሀብታዊ ልማት ባንክ” (Arab Economic Development Bank -BADEA) እና የዐረብ አየር አገልግሎት ድርጅትን (Arab Air Carriers Organization) አቅፏል። ሁሉም አባል አገራቱ ደግሞ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት (Organisation for Islamic Cooperation) አባላት ናቸው።
የዐረብ ሊግ በየአምስት ዓመቱ የሚመረጥ ዋና ፀሓፊ ያለው ሲሆን ሊጉን ከሳዑዲ ዐረቢያ ጋር በመፎካከር በማጦዝ የምትታውቀው ግብጽ ነች። ለአብነት ያህል:- ቀደም ሲል በተባበሩት መንግሥታት የግብጽ ዐረብ ሩፑብሊክ ቋሚ መልእክተኛ የነበሩት፤ እንደ አውሮፓውያኑ ቀመር ከ2004-2011 በግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት፤ በግብጽ የታወቁት ፖለቲከኛና ዲፕሎማት አህመድ አቡል ጌይት፤ ከግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ከለቀቁ በኋላ በተደጋጋሚ የዐረብ ሊግ ዋና ፀሓፊ ሆነው በመመረጥ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
አህመድ አቡል ጌይት ደግሞ፤ በግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ዘመን (በኢትዮጵያ 2002 ዓመተ-ምህረት) ለኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ ሊሰጡ ይችላሉ ለተባሉ አገሮች ሁሉ “ለኢትዮጵያ ማናቸውንም የገንዘብ ድጋፍ አትስጡ!” ብለው የትእዛዝ ያህል ደብዳቤ የጻፉ፤ በኢትዮጵያ ጥላቻ የተለከፉ የግብጽ ዲፕሎማትና ፖለቲከኛ ናቸው።
ውድ ወገኖቼ:- ግብጽ የዐረብ ሊግን ተጠቅማ የምታደርገውን የክፋት ከፍታ፤ ፀረ-ኢትዮጵያ ልማትና ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ተመልከቱ? ግብጽ ደግሞ እንኳን የዐረብ ሊግ አንድ የምታውቀው አነስ ያለ ዐረባዊ ተቋም በኢትዮጵያ ከውሃ ጋር በተለይም ከዐባይ ተፋሰስ ጋር ተያያዞ ለሚካሄድ ልማት ድጋፍ ሊያደርግ ቢነሳ እግር በእግር ተከታትላ እገዛውን የምታስተጓጉል ምቀኛ አገር ነች።
ግብጽ የዐረብ አገሮች ሊግን እንደ ኪስ ገንዘቧ የመመንዘሯን ያህል ዓለም ባንክም ባለሙያዎቿን አሰርጋ አሰገብታ፤ በሌላ በኩል የዐረብ አገሮችን እያጦዘች የፈረደባት ኢትዮጵያ ላይ ታሳድማለች። ወቅታዊ ሁኔታ ብንመለከት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2016 አንስቶ ተቀራራቢነት አላቸው የሚባሉት ባሕሬን፣ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ (ጆርዳን)፣ ኢራቅ፣ ኩዌት፣ ሊባኖስ፣ ሊቢያ፣ ማልዲቭስ፣ ኦማን፣ ኳታር፣ የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶችና የመንን በመወከል በዓለም ባንክ ኦልተርኔት ኤክሱኩዊቲቭ ዳይሬክተር የሆኑት፤ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ግብጻዊው ራጉዊ ኤል ኢትሬባይ ናቸው።
በተለይ ግብጻዊው ራጉዊ ኤል ኢትሬባይ የቅርብ ክትትል የሚደረግላቸው አገሮች ማለትም ከማልዲቭስ በስተቀር ራስዋን ግብጽን ጨምሮ ባሕሬን፣ ዮርዳኖስ (ጆርዳን)፣ ኢራቅ፣ ኩዌት፣ ሊባኖስ፣ ሊቢያ፣ ኦማን፣ ኳታር፣ የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶችና የመንን አገሮች በሙሉ የዐረብ ሊግ አባል አገሮች እንደሆኑ ሲታሰብና በአሁኑ ጊዜ የዐረብ ሊግ ዋና ፀሓፊ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ደግሞ ግብጻዊው አህመድ አቡል ጌይት ከመሆናቸው አኳያ፤ ግብጽ የዐረብ አገሮችን እያሳደመች ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ድጋፍ እንዳታገኝ ምን ያህል የተደራጀ መንገድ እየተከተለች እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል።
እነሆ የዐረብ ሊግ :-በሰሜን አፍሪካ፣ በዐረቢያ ልሳነ-ምድርና በአፍሪካ ቀንድ (ምሥራቅ አፍሪካ) የሚገኙ 22 አገሮች ጥምረት ነው። ሁሉም የዐረብ ሊግ አገሮች በጋራ 13 ነጥብ 15 ሚሊየን ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቆዳ ስፋት አላቸው። ይህም የዓለማችንን ሰዎች የሚኖሩባቸው 8 ነጥብ 7 በመቶ ቆዳ ስፋት አካባቢዎች ያካልላል።
የዐረብ ሊግ አባል አገሮች ወሳኙ ክፍላቸው በሰሃራ በረሃና በሩብ ዐል-ቻሊ የአሸዋ በረሃ የተሸፈነ ሲሆን፤ ካላቸው ከ440 ሚሊየን የሚበልጥ ሕዝብ የዓለምን 5 ነጥብ 6 በመቶ ሕዝብ ቁጥር ይሸፍናሉ።