
እስሌማን ዓባይ
ለግብፃዊያኑ ልዩ ታሪካዊ ቀን ናት። የህልውናም የሁለንተናቸውም መሰረት የሆነውን በረከት ዓባይ ይለግሳቸው ዘንድ በግንቦት 20(may 28) ጀምሮ የክረምቱን ውሃ/ጎርፍ አሀዱ ብለው መቀበል ይጀምራሉ። ዕለቱ በተለይም ከአስዋን ግድባቸው መቆም ወዲህ በውል የሚታወቅ አማካይ ነው። ከዚህች ግንቦት 20 ጀምረው ነው ግብፆቹ እኩይ ነገርን ከሚያስቡባት መጥፋትን ከሚመኙላት ኢትዮጵያዊ ምድር በሚደርስላቸው በረከት የጠወለገ ህይወታቸው መለምለም የሚጀምረው።
በዲጂታሉ አውድ ከእኛ ሲናከሱ ከምናውቃቸው ግብፃዊያን መካከል ዶክተር ሀኒ ኢብራሂም[በዛሬው ዕለት] ድባቴ የያዛቸው ይመስላሉ። የዘንድሮ ግንቦት 20 ከትካዜ ጥላቸዋለች። [ግን ምን አሳሰባቸው? ለምንስ ይጨነቃሉ?
ሰርክ የበረከት ጅማሮ የሆነችው ግንቦት 20 አሁን ላይ ግን ስጋት እየሆነ ነው ብለዋል። ግብፃዊው ዶክተር የቀጣዩ ሙሊት ከሁለት ወራት አይቀሬ መሆኑን በትካዜ አሻግረው እየመለከቱ ናቸው። “ግንቦታ 20 የህያው ናይል አመታዊ የፀጋ ምእራፍ ነው። ከዚህ በኋላ የሚመጣው አይታወቅም። በተረፈ ምን ብዬ እንደምቀጥል አላውቅም..።” ሲሉ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
ግንቦት ያመጣላቸውን የዓባይ ፀጋ ተከትሎም Wafaa el-Nil የተሰኘ በአላቸው ይከተላል። በዓሉ August 15 ይከበራል። ይሄኔ ለጣኦቶቻቸው የምስጋና መስዋእት ያበረክቱለታል። ከምግብና መጠጥ እስከ ሰው መስዋእት ማቅረብ ጥንታዊ ትውፊታቸው ነው።
ግብጻዊያኑ ከኢትዮጵያ የሚበረከትላቸውን የዓባይ ውሃ ISIS የተሰኘችው ጣኦታቸው እንባ ነው ይላሉ። ከአልሲሲ እንዲሁም ከአይሲስ ጋር ተመሳስሎ ያለው ስም ያላት iSIS የኦሲሪስ ሚስት ናት ይላሉ። ባሏ ኦሲሪስ መሞቱን ተከትሎ የምታፈሰው እምባ ነው በዬክረምቱ የዓባይ በረከት ሆኖ የሚመጣልን በማለት ነው ምስጋና ሲያቀርቡ እልፍ ዘመናትን የፈጁት።
በሌላ በኩል ደግሞ ኦሲሪስ የሚባለው የግብፆች ተመላኪ ከኢትዮጵያዊ ግንድ የሚመዘዝ ማንነት ያላቸው ንጉሥ እንደነበሩ ዲዮዶረስ የተባሉ የጥንታዊት ግሪክ የታሪክ ፀሐፊ ከትበውት እናገኛለን።
ሀፒ ሲሉ የሚጠሩት ከዚህ ባሻገርም የሚያመልኩት ጣኦት(Hapi) የደስታ፣ የናይል ጌታ፣ ሀይለኛ፣ ሲፈልግ በጎርፍ እና በድርቅ የሚቀጣ ይሉታል። ርህሩት ነውም ይሉታል። ከግምቦት 20 የጎርፍ ጅማሮ አንስቶ ክረምቱን የዓባይ ውሃን ያበረክትልናል በማለት።
ይሁንና፣ የዓባይ ፀጋ ከኦሲሪስ አሊያም ሀፒ ሳይሆን አላህ ከኢትዮጵያ ይፈልቅ ዘንድ የለገሰን ውድ ሀብት ነው። ከሀበሻ ምድር ተነስቶ እልቆ ቢስ ውጣ ውረድን በፅናት ተሻግሮ ከፈርኦናዊያን ምድረ በዳ መሬት ከተፍ ይላል – የህላዌ መሰረትም ይሆናል። ይህ የዓባይ ባህርይ የኢትዮጵያዊያን ቸርነት፤ የፅናታቸው መገለጫም ነው።
ግብፃዊው ዶክተር ሀኒ ቀጣዮቹን ግንቦት 20ዎች በስጋትና ጥርጣሬ አስግገው ይጠብቃሉ። እኛ ግን ሀሳብ አይግባችሁ እንላቸዋለን። መስሚያ ካላቸው ውሃ የኦሲሪስ ወይም ሀፒ ሳይሆን ከጀነት ፈልቆ ኢትዮጵያ ላይ እትብቱን ያደረገ ነው። የግብፃዊያን ምስጋና ከጣኦታት ይልቅ ለፈጣሪ እና ለኢትዮጵያ ይሁን። እንደ ኦሲሪስ እና ሀፒ የሰው መስዋእትን የእኛ ምድር ሰዎች ከግብፃዊያን አይሹም። ቢያንስ ከእኩይ ሀሳባቸው መታቀብ በቂያችን ነው። ፈርኦናዊ ማዳመጫቸውን በተአብዮ ባይደፍኑትና ከፍተው ቢያደምጡን በብዙው ባመሰገኑን። በልባቸው መልካም ነገርን በተመኙልን [እነሱ] ከስጋት ባልወደቁም ነበር።ያን ቢያደርጉ ኢትዮጵያ በድርቅ እና ጎርፍ የምትቀጣ ጉልበተኛ ትሆንብናለች በማለት እነ ዶክተር ሀኒ ፍርሃት ውስጥ ባልገቡ ነበር። እኛ ዓባይ ነን – የናይል 90 በመቶ የምንለግስ ፅኑ ሕዝቦች እኛ ነን። በመልካም ለተጎራበቱን ሁሉ መልካምን የማንነፍግ ልዩ ህዝቦች – ኢትዮጵያዊያን
እስሌማን ዓባይ ?? የዓባይ፡ልጅ