ግብፅ የዓባይ/ናይል የጀልባ ቤቶች እንዲፈርሱ ስትወስን

ለበርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች በናይል ወንዝ ዳር በደማቀ ቀለም የተቀቡ፣ የእንጨት የቤት ጀልባዎች የግብፅ መዲና ካይሮ የበለፀገ የባህል እና የሥነ-ሕንፃ ቅርስ መገለጫ ናቸው።

ነገር ግን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአጠቃላይ 30 ያህሉ የቀሩ ጀልባዎች ላይ የተሰሩ ቤቶች በግብፅ ባለሥልጣናት እንዲወገዱ ዕቅድ ተይዟል። ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት የጀልባ ቤቶቹ መፍረስ የወንዙን ዳርቻ ለማስዋብ የሚደረገው ጥረት አካል ነው ።

የተወሰኑት ተንሳፋፊ የጀልባ ቤቶች በቋሚነት በወንዝ ዳር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ዝቅተኛ አቅም ያላቸው ነዋሪዎች የሚኖሩባቸው ናቸው። ሌሎች የጀልባ ቤቶች ደግሞ በከፍተኛ ገንዘብ እንዲታደሱ ተደርገዋል። ጥቂት የጀልባ ቤቶች ደግሞ ወደ ሬስቶራንቶች፣ ቢሮዎች እና ጂም ተለውጠዋል።

ግብፃዊ ደራሲ አህዳፍ ሱኢፍ ከልጇ ጋር

“በእነዚህ የጀልባ ላይ ቤቶች ያለው የተለየ የአኗኗር ዘይቤ ነው። ሙሉ በሙሉ በተፈጥሮ ውስጥ ናችሁ። ወንዙ ከእናንተ በአንድ ሜትር ርቀት ላይ ብቻ ነው ያለው” በማለት የቤተሰቦቿ ጀልባ ቤት የሆነው መኖሪያዋ ሊፈርስ መሆኑ የተነገራት ታዋቂው ግብፃዊት ደራሲ አህዳፍ ሱኢፍ ታስረዳለች።

“በጀልባ ላይ የተገነቡት ቤቶች ሀሳብ ከተለመደው ወጣ ያለ ነው” የምትለው አህዳፍ “ለግብፃውያንና አረቦች በርካታ ትውልዶች የፍቅር ስሜት የሚሰማቸው ስፍራ ነው” ትላለች።

ከእርሷ በረንዳ ሆኖ ክሬኖችና መኪናዎች በመዲናዋ መሃል ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። ባለሁለት ፎቅ የሆኑ ሦስት የጀልባ ቤቶች ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ እንዲነሱ ተደርገዋል። በሳምንቱ መጀመሪያ ሌሎች እንዲወሰዱ ሲደረግ አንደኛው በሂደቱ ፈራርሷል።

የካይሮ ከተማ

በማኅበራዊ ትስስር ገፆች በአረብኛ አዋማት (ተንሳፋፊ) በመባል በሚታወቁት የጀልባ ላይ ቤቶች ላይ የተወሰደው እርምጃ ከበርካታ ግብፃውያን ዘንድ ውግዘት ደርሶበታል።

“እነዚህ ጀልባዎች ለብዙ አሥርት ዓመታት የሰዎች መኖሪያ ብቻ ሳይሆኑ አንዳንዶቹ ታሪካዊ ሐውልቶች ናቸው። እነሱ የማይጠፉ የቅርሶቻችን አካል ናቸው” ስትል ኖራ ዘይድ በትዊተር ላይ አስፍራለች።

“እነዚህ የካይሮ ውብ ታሪክ አካል አይደሉም ያለው ማነው?” በማለት ዳኬል ሀፊን በትዊተር ገጹ ጠይቋል።

“ናይል ላይ ሆነን አዋማትን ስንመለከታቸው ስለእነሱ የተነገሩ ተረቶችን፣ ልብወለዶችንና እና አፈ ታሪኮችን ልንናገራቸው” ይገባል ይላል።

ጥቂቶች ብቻ ስለ ውበት ዕሴታቸው በአሉታዊ መንገድ ይከራከራሉ። ሙስጣፋ ኤል-ጋፊ የተባለ ግለሰብ በትዊተር ገጹ “አስቀያሚ” ናቸው ብሏል።

የጀልባ ቤቶች

የግብፅ መንግሥት የጀልባዎቹ ቤቶች የተገነቡት ያለፈቃድ ከብዙ አሥርት ዓመታት በፊት መሆኑን እና ባለቤቶቻቸው ትክክለኛውን ፈቃድ ሳያገኙ መቆየታቸውን ምክንያት በማድረግ እንዲፈርሱ የሰጠውን ትዕዛዝ በመደገፍ ተሟግቷል።

የመስኖ ሚኒስትሩ በበኩላቸው “ሕግ በግልፅ በመጣስ” በወንዙ ዳር የተገነቡ ቤቶችን የማስወገድ ዘመቻውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ መሐመድ አብደል አቲ “በናይል ወንዝ ላይ ተላልፈው ለሚሰሩ ሰዎች ግልጽ መልዕክት ነው” ብለዋል።

በርካታ የጀልባ ቤቶች ነዋሪዎች በበኩላቸው የቤቶቹ ባለቤት እንደሆኑ የሚናገሩ ሲሆን፣ በቅርቡ የመኪና ማቆሚያ እና ወደ ወንዙ ዳር ለመድረስ ክፍያዎች በከፍተኛ ሁኔታ ከመጨመራቸው ጋር ተያይዞ ሁኔታውን በሕግ ለመፍታት መሞከራቸውን ይናገራሉ።

የጀልባ ቤቶቻቸውን ለሚያጡ ሰዎች ምንም አይነት ካሳ እየተሰጠ አይደለም።

የ87 አመቷ የእድሜ ባለጸጋ ኤክላስ ሄልሚ

“በአምላክ ስም እምላለሁ ወዴት እንደምሄድ አላውቅም” በማለት የ87 ዓመቷ የእድሜ ባለጸጋ ኤክላስ ሄልሚ ንብረታቸውን እየሰበሰቡ ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ ያስረዳሉ።

“እህቴ ጋር የተወሰነ ዕቃዬን፣ እንዲሁም ወንድሜም ጋር የተወሰነውን አስቀምጫለሁ። ሁለቱም በሁኔታው ደስተኛ አይደሉም። ዕቃዎቼን እንድጥል ነግረውኛል።”

በጎረቤቶቻቸውና በቤተሰቦቻቸው ዘንድ ማዳም ሄልሚ በመባል የሚታወቁት ኤክላስ የተወለዱትና ያደጉት በጀልባ ቤት ላይ ሲሆን ምግባቸው ዓሳ ነው።

በኋላም ባለቤታቸው ገና በወጣትነታቸው መሞታቸውን ተከትሎ በውሃ ላይ የራሳቸውን ቤት ገነቡ። በአሁኑ ወቅት ባለው ቤታቸው ከውሾቻቸው፣ ከድመታቸው እና ዝይዎቻቸው ጋር ለሦስት አስርት ዓመታት ኖረዋል።

በናይል ወንዝ ላይ ያሉ የጀልባ ቤቶች

በናይል ወንዝ ላይ ያሉ የቤት ጀልባዎች ታሪክ ረጅምና በቀለማት ያሸበረቀ ነው። አንጋፋዎቹ የጀልባ ቤቶች በፈርዖኖች ጊዜ የተሰሩ ሲሆን ረዘም ላለ የወንዝ ጉዞዎች ታቅደው የተገነቡ ናቸው።

በጊዜ ሂደትም በእንጨት ወይም በብረት ምሰሶዎች የተሰሩ ተንሳፋፊ የብረት ኮንቴይነሮች የመገንባት ዘዴ መጣ።

በኦቶማን ቱርክ አገዛዝ ዘመንም ቱጃር የሆኑ የግብፃውያን ፓሻዎች የቤት ጀልባዎችን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው በመውሰድ እንግዶቻቸውን በሙዚቃ እና በዳንስ ለማስደሰት ይጠቀሙባቸው ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የብሪታንያ ኃይሎች በነዚህ የጀልባ ቤቶች ውስጣቸው ይኖሩ ነበር።

የአዋማት ቤቶች አብዛኛውን ጊዜ ከምስጢራዊ ግንኙነት እና ኢ-ሞራላዊ ተግባራት ጋር ይያዛሉ ።

በበርካታ የግብፅ ጥንታዊ ፊልሞች እንዲሁም የኖቤል ተሸላሚ በሆነው ደራሲ ናጊብ ማህፉዝ ሥራዎች ላይ የጀልባ ቤቶቹ ማዕከል ሆነዋል።

ናጊብ ማህፉዝ በአውሮፓውያኑ በ1966 ያሳተመው “ኤ ድሪፍት ኦን ዘ ናይል” የተሰኘው ልቦለድ ድርሰቱ፣ ሌሊት ላይ በጀልባ ተሳፍረው አደንዛዥ ዕፅ ለማጨስ የሚሰበሰቡትን ወጣት ምሁራን ሕይወትን ይቃኛል።

የካይሮ ከተማ በአውሮፓውያኑ 1932

በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በካይሮ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቤት ጀልባዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ በርካቶቹ ቀስ በቀስ በባለሥልጣናት ተጠርገው ወይም እንዲነሱ ተደርገዋል።

አሁን በስጋት ላይ ያሉት የቤት ጀልባዎች ኪት ካት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተሰብስበው ይገኛሉ።

በአንድ በኩል ከናይል ወንዝ ማዶ በዛማሌክ ደሴት ላይ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች እና ውድ ሆቴሎች፣ በሌላኛው በኩል ደግሞ ጎስቆል ባለው የኢምባባ ሰፈር ተከበዋል።

በካይሮ የሚገኘው የዛማሌክ ደሴት

ከዚህ ቀደም ይህንን የውሃ ዳርቻ ክፍል ለንግድ ተቋማት እንዲሰጡ የማድረግ ግፊት ነበር።

አመሻሽ ላይ በናይል ወንዝ ዳርቻ የሚገኙ ሬስቶራንቶች፣ ካፌዎች እና የግል የስፖርት ክለቦች ይጨናነቃሉ።

የግብፅ መንግሥት በቅርቡ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የእግረኛ መንገድ የመጀመሪያውን ክፍል ገንብቶ በርካታ ትናንሽ ንግዶችን እንዲሁም የጀልባ ኪራዮች እንዲነሱ አድርጓል።

በወንዙ ዳርቻ እየተካሄደ ያለው ልማት የዋና ከተማዋን ልዩ ውበትና የሕዝብ መለዮ የሆነው ስፍራ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን? የሚለው ላይ ክርክሮች እንዲነሱ አድርጓል።

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories