ግድቦችን በሚሳይል ማፍረስ ይችላልን?

ከሶስት አመታት በፊት ታይዋን የቻይናውን ስሪ ጎርጂስ ግድብ መምታት የሚችል ሚሳይል ስለመታጠቋ በድረ-ገፅ ሚዲያዎቿ አስወራች። የቻይና መከላከያ ባለስልጣናትም የበዛ የሹፈት ‘ሙድ’ እንዲይዙባት ሆነ። ቻይኖቹ ሙድ መያዛቸው በባዶው አልነበረም…፤

ታይዋን 2017 ላይ ያንን ፕሮፓጋንዳዊ ዜና ያስለቀቀችው በ 2020 ቻይና ታይዋንን በቁጥጥሯ ልታውል ዕቅድ እንዳላት በመገመታቸው ነበር። ታዲያ የዛተችበት መሳሪያ Hsiung Feng IIE የተባለ ከአሜሪካ ከገዛችው F-16 ጦር ጄት መተኮስ እንዲችል የታሰበ ነበር።
ቻይኖችም አሉ “ግድባችን ሚጢጢ ኑክሌር ሚሳይል ቢያርፍበት ግፋ ቢል ጭረት እንጅ ፍንክች አይልም። ያም ቢሆን የማያፈናፍን የራዳር ሲስተማችን እንዴት ተደርጎ ተጥሶ? ከዛስ በኋላ የቻይናን ገሀነማዊ የአፃፋ በትር ማነው የሚቋቋመው?” ሲሉ ከአግራሞታዊ መደነቅ ጋር መለሱ።
ባለስልጣናቱ አስከትለውም ግድቡን ሊያፈነዳ የሚችለው bouncing bunker buster ቦምብ ብቻ ነው። እሱ ቦምብ ደግሞ በታይዋን የለም፤ አይኖርምም” ነበር ያሉት።

(ዜጋ ጓደኞቼ ሆይ! በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ለሚፈጠሩባችሁ ተጨማሪ ጥያቄዎች የኔ ፅሁፍ ብቻውን መልስ ሊኖረው አይችልምና በጉዳዩ ዙሪያ የናንተ ንባብ፣ እውቂያና የመረጃ ተጋልጦ ምን እንደሆነ ብታጋሩ የበለጠ ይሆናል። መረጃውን በበርካታ ምንጮች ዋቢነት ያጠናቀርኩት ነውና ሁሉንም መዘርዘሩ አያመችም። የምትፈልጉ ግን ጠይቁኝ አደርሳችኋለሁ)
….. …….. …….. ……… …….. …….
ሰው ልጅ ለአጥፊ ነገሮች ብዙ ተመራምሯል። ግድቦችንና የመሬት ውስጥ መዋቅሮችን እንዴት ማውደም አለብኝ የሚለው ጉጉቱም ሁለት መልክ ያላቸው የመሳሪያ ቴክኖሎጂ ፅንሰ-ሀሳቦች ስራ ላይ እንዲውሉ አድርጓል። ባውንሲንግ ቦምብ እና በስተር ቦምብ (bouncing bomb and buster bombs),

ስለ ባውንሲንግ ቦምብ

ይህ ቦምብ በተለካና በተሰላ የውሃ አካል ላይ ወደ ዒላማው guide እየተደረገ በጥንቃቄ የሚጓዝ፤ የቦንቡ ፍንዳታ timing እና ከዒላማው ሲደርስም ሆነ የሚፈነዳበት ጊዜ አስቀድሞ እንዲታወቅ ታስቦ የተሰረ ነው። የቦምቡ ፈጠራ የእንግሊዛዊው መሃንዲስ ባርኔስ ዋሊስ ሲሆን በ 1943 በ RAF Royal Air force ኦፕሬሽን ውስጥ በጀርመን ግድቦችን ለማፈንዳት ጥቅም ላይ ውሏል ።ቦምቡ ዒላማውን እስኪመታ ድረስ በውሃ ላይ የሚንሳፈፍ፣ የሚያጋጥሙትን እንደ “torpdenet” ያሉ የመከላከያ ሲስተሞችን ማለፍእንዲችልና በቀጥታ ወደ ዒላማው እንዲያመራ ይሆናል። ከኢላማው ነጥብ ላይ ሲደርስም እንዲፈነዳ ይደረጋል። ዓላማውም እንደ ሃይድሮ-ኤሌክትሪክ ግድቦች፣ ሰርጓመርከቦችን፣ መርከቦችንና የውሃውመስጥ ሜጋ መሠረተ ልማቶችን ለማውደም ነው። ይህ የቦምብ አይነት በሌሎች አገራትም የተወሰኑ ፕሮጀክቶች ተይዞለት ነበር። ጀርመን ከእንግሊዝ ጥቃት በኋላ ምርምሩን ከጀመሩት ጥቂት አገራት ውስጥ ናት።

buster bomb

ይህ አይነቱ ቦምብ ከከፍተኛ የአየር ከፍታ ተተኩሶ ኮንክሪትና መሰል አካላትን ሳይፈነዳ በስቶ በመግባት እስከ የምድር ውስጥ ኢላማና መሠረተ ልማት ለመምታት የታሰበ ነው። የተለያዩ ስያሜዎችን ይዞ በእንግሊዝ earthquake ተብሎ ተጀምሮ በነ አሜሪካና ሩሲያም የተለያዩ ስሪቶችን የያዘ ነው።

Earthquake ቦምብ

ይህ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ ላይ በእንግሊዛዊው መሐንዲስ የተፈለሰፈና በመቀጠልም በአውሮፓ ውስጥ ስትራቴጂካዊ ዒላማዎች ላይ በነበሩ ውጊያዎች ወቅት ጥቅም ላይ የዋለ ፅንሰ ሀሳብ ነው፡፡ ቦምቡ 40,000 ጫማ ወይም 12 KM በሚደርስ ከፍታ ላይ ወደ ምድር እንዲተኮስና ኢላማው ላይ ሲገናኝ ሳይፈነዳ ወደ ስር ዘልቆ እንዲገባ ዲዛይን የተደረገ ነው። ለዚህም በከፍተኛ ከባድ ቦምብና በጠንካራ ውጫዊ የብረት ጋሻ ጫፍ ሰርስሮ ወደ መሬት እንዲዘልቅ የሚሰራለት ነው።

በቀጥታ ወደ ታች ሲተኮስ የሚፈጠረውም ከአስር ቶን ጥይት ጋር የሚመጣጠን ነው። የኢላማውን የላይኛውን ጠንካራ አካል ሰርስሮ ከመሬት በታች እንዲፈነዳ ሲደረግ የተፈጠረው ማዕበል አነስተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አይነት ጥፋት ይከስታል። በዚህም earthquake ቦምብ ተብሏል።
በአቅራቢያ የሚገኙ እንደ ግድብ፣ የባቡር ሀዲዶች ወዘተ ያሉ ማናቸውንም መዋቅሮች ያወድማል።

ታዲያ ይህን ቦምብ እንግሊዛዊው ዎሊስ ያቀደው በ 40 ሜትር ከፍታ ያለው መሬት ውስጥ ለሚፈነዳ ባለ አስር ቶን ቦምብ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ቦምቡ ከ 40,000 ጫማ (12 ኪ.ሜ) መወርወር ነበረበት ፡፡ እንግሊዝ ግን በወቅቱ አሥር ቶን የቦንብ ጭነት ወደ ላይ ከፍ ለማድረግ ይቅርና እስከዚህ ከፍታ ድረስ ከፍ ብሎ መብረር የሚችል አውሮፕላን አልነበራትም። ለዚህም ባለ ስድስት engine አውሮፕላን ነደፈች፤ ይሁንና ከ 7 ኪ.ሜ በላይ መሄድ አልቻሉም ነበር።

Bunker buster bomb
ይህ አሜሪካ ሰራሽ ቦምብ ከ earthquake ቦምብ ጋር ተመሳሳይ ሚናና feature ያለው ነው። እዚጋ እንግሊዞች ያላሳኩትን የመተግበር አቅም በቦምቡና ጦር ጄቶች አቅም ላይ ልዩ አቅም መጨመርን ነው አሜሪካ ታሳቢ የምታደርገው። ምንም እንኳን mother of all bombs የዚሁ ቦምብ ዘመድ ቢሆንም ለአቅመ ዘመቻ የደረሰ ውጤት ላይ ግን አልደረሰችም። በዚህ ቦምብ የሰ.ኮሪያንና ኢራንን የምድር ውስጥ ኑክሌር ተቋም ለማውደም መሪዎቿ ከባለስልጣናት ጋር በተቃራኒ ጎራ ተሟግተዋል። በዕቅድ ደረጃም B-2 በተባለው ጄት እንዲተኮስና ከኮንክሪት ወለሎች በታች እስከ 80 ሜትር ሰርስሮ ገብቶ እንዲፈነዳ ተተልሞለት ነበር።
ከአመታት በፊት የኢራን ኑክሌር ማብላላት ስጋት የሆነባት እስራኤል ይህን ቦምብ አሜሪካ ዲዛይን አድርጋ እንድታቀርብላት ጠይቃም ነበር።
Boeing ኩባንያ 2019 ላይ ባለ 30,000 ፓውንድ GBU-57 bunker buster ቦምብ እንዲሰራ ኮንትራት ከአሜሪካ ጦር መውሰዱ ይታወሳል። ስራው ግን ከ 4 ዓመት በኋላ ሊፈፀም የሚችል ነው።

ማነው የነዚህ ቦምቦች ባለቤት?

ዋናው ነጥብ ይህ ነው። እስካሁን ድረስ ቦምቦቹ በቴክኖሎጂና በሙከራ ደረጃ እንጂ ጣጣውን ጨርሶ ለዘመቻ ዝግጁ አይደሉም። አሜሪካ ለራሷ ገና ከወራት በፊት ነው ፕሮጀክት የነደፈችው። ይህ ማለት ለራሷም አመታት ይወስድባታል። ለሌሎች አገራት ለመስጠት ደግሞ ለራሷ ከያዘች በኋላ ፈጠነ ከተባለ ለቅርብ የኔቶ አባላት 10 አመት፣ ለተቀሩት ደግሞ ከዚያ በኋላ ነው ሊሆን የሚችለው።
[ አዲስ በከፈትኩት YouTube ቻናሌ ቦምቡ በአሜሪካው B-2 ጄት ሲሞከር የሚያሳይ የ 2 ደቂቃ ቪዲዮ አስቀምጫለሁ። ከተመቻቸንም SUBSCRIBE በሉኝ ?? https://youtu.be/pTxZwvT8TEY ]
( )
ሌላው ቦምቡ ቢኖር እንኳን እሱን የሚሸከም ባለ ብዙ ጉልበትና ከፍ ብሎ በራሪ ጄት ይጠይቃል። ለምሳሌ፦ bunker buster ቦምቡን እጅግ የዘመኑት የአሜሪካ F-16 አሊያም F-35 ሊሸከሙት አይችሉም። በሙከራ ጀረጃ እንኳን የአሜሪካው B-2 ጄት ነው ከጠላት መከላከል ነፃ በሆነ ፍተሻ ላይ መሞከር የቻለው። እሱም ቢሆን ለእውነተኛ ዘመቻ ብቁ አይደለም። ( )

ከኛ ጋር በተያያዘ ግብፅን ብንወስድ አይደለም ገና ያልተሰራው Buster ቦምብ፣ አይደለም B-2 ጄት ….አሜሪካ F-35 እንኳ አልሰጠቻትም። F-35 ስለመቀበል ወሬውም የለም። ግብፅም አታስበውም። የተሰጣት F-16 (እኛም የተሰጠንን) ብቻ ነው።

ሌላኛው ቁልፍ ነጥብ፣ bouncing ቦምብም ሆነ buster ቦምቦች የተባሉትን መሠረተ ልማቶች ለማፍረስ የኢላማቸውን ትክተታዊ ነጥብ መቶ በመቶ መድረስ ያለባቸው መሆኑ ነው። ይህ ሁኔታ የሚፈለገው ፍጥነት እንዳይኖር አድርጓቸዋል። እንደ ሌሎች ጄቶች በፍጥነት ሄደው random እንዲተኩሱ ከፅንሰ ሐሳቡም ላይ የለም። መሰል random ተኩስ ቻይኖች እንዳሉት ከጭረት ውጪ ተኳሹን ማክሰር እንጂ መሠረተ ልማቱን መጉዳት አይችሉም።

አሜሪካ በዚህ ደረጃ ወጪ የሚጠይቀውን መሳሪያ አሜሪካ ዝግጁ የማድረግ ዕቅድ እንጂ በተጨባጭ የራሷንም ጉዳይ አልፈታችበትም። የአሜሪካ እያንዳንዱ ዘመቻ ሁለገብ አሳማኝ መግፍኤ ይጠይቃሉ። በዛቻ ደረጃ “fire and furious” ሲሉ በኑክሌር እነ ኪም ኡንን ሲያስጠነቅቁ የሚታወቁት ትራምፕ ከሰ.ኮሪያና ኢራን በላይ ፈተና አልገጠመውም። ያውም “ከነካኸኝ አልፈራህም” እያሉት። በነሱ ላይ እንኳን ቦምቡን የመጠቀም ምኞቱን Impossible ያደረጉበትን ነባራዊ ነገሮች መለወጥ አልተቻለውም።

እነዚህን ቦምቦች የሚሸከሙ ጄቶች ቀሰስተኝነት በራዳር መከላከያዎች አነፍንፈው በቀላሉ እንዲመቷቸው አመቺ መናቸው ሌላው ከል ነው። መሰል ቦምቦች የታለመላቸውን የኢላማ ትክተታዊ ነጥብ ጠብቀው ለመምታት የአየር ቀጠናውን ረዘም ላለ ጊዜ መቆጣጠር ይኖርባቸዋል ነው የሚሉት ሳይንቲስቶቹ። ይሄ ደግሞ በዚህ ዘመን አይታሰብም። በዚህ ዘመን ፈጣንና ቀላል የሆኑት እነ f-16 እና f-35 እንኳን ከራሺያው S-400 እና S-500 መቋዎሚያ ማምለጥ አይችሉም። የራሺያው ይህ ቴክኖሎጂ ደግሞ የድሮውን ዘመን ህግ በመሻር በደሀ አገራት ጦር መዳፍ ስር መዋል ማደር ከጀመረ ሰነባብቷል።

እንደ ሐይል ማመንጫ ያሉ ግድቦችን ማፍረስ የሚችሉ መሳሪያዎች ምናልባት ወደፊት በሚኖሩ ቴክኖሎጂዎች ቢሆን እንጂ የሉም መባሉም ለዚህ ነው። የትላንትናው የትራምፕ ንግግር ከሐቁ የተጣላ ነበር የሚባለውም ለዚህ ነው።

የዓባይ ልጅ | እስሌማን ዓባይ

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories