ግፍ እንዲህም ይፈፀማል?!…

የወልቃይቱ “የሞት ፍርደኛ” የ25 ዓመታት ሰቆቃ !!

የ25 ዓመታት ሰቆቃ! አቶ አበራ ዓለማየሁ የ68 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ናቸው። ከዚህ ውስጥ 25 ዓመቱን ያሳለፉት በሶስት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ እስር ቤቶች ነው። በአማራ ክልል ባዶ ስድስት፣ በአዲረመጥ፣ በጋሸና፣ በሁመራና በገሃነም፣ በአፋር ክልል በዱብቲ አካባቢ መሬት ውስጥ በሚገኝ ልዩ እስር ቤት እንዲሁም በትግራይ በሽ እና በመቀሌ እስር ቤቶች ውስጥ አሳልፈዋል።

አቶ አበራን ለእስር ያበቃቸው ወልቃይት የአማራ እንጂ የትግራይ አካል ሆኖ አያውቅም የሚለው አቋማቸው ነው። በደጀና ባዶ ስድስት እስር ቤት ውስጥ በነበሩበት ወቅት ከአባታቸው ጋር በአንድ ቦታ ላይ ታስረው ከፍተኛ ስቃይ ደርሶባቸዋል። በጥቂት የወያኔ ካድሬዎችም የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ከዛሬ ነገ ልገደል ነው ሲሉ ዓመታትን አሳልፈዋል። 25ቱ የእስር ቤት ቆይታቸው ሞት ተመኝተው ግን ያላገኙበት ጊዜ እንደነበር ይናገራሉ። አቶ አበራ በታሰሩበት ባዶ ስድስት እስር ቤት ውስጥ በመገኘት ትውስታቸውን አካፍለውናል፤ ከመሰረቱ እነሆ።

የደጀናው የሃይማኖት አባት

ቄስ አለማየሁ ይግዛው በደጀና የሚገኘው ጨርቆስ ቤተክርስቲያን የሚያገለግሉ የሃይማኖት አባት ናቸው። ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነመንግሥት ጀምሮ በዚሁ ቤተክርስቲያን አገልግሎት ሲሰጡ ነው የኖሩት። በአካባቢው የሚኖሩ የክርስትና እምነት ተከታዮችንም በእምነቱ ስነምግባር እያነፁና እያስተማሩ ቆይተዋል።

በ1974 ዓ.ም የህወሓት ታጋዮች ወደአካባቢው ሲመጡ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን ሰብስበው ወልቃይት የትግራይ መሆኗን እንዲቀበሉና ለሌሎችም እንዲያስተምሩ ለማግባባት ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

ቄስ አለማየሁም የእምነት አባት እንደመሆናቸው ስለእምነቱ በሚያስተምሩበት ወቅት የወልቃይትን ጉዳይ አንስተው ለህዝብ እንዲሰብኩ አግባቧቸው። ቄስ አለማየሁ ግን ይህ ፈጽሞ የሚቀበሉት እንዳልሆነ አጥብቀው ነገሯቸው። ወልቃይት የአማራ እንጂ የትግራይ አካል ሆኖ እንደማያውቅ በይፋ ነገሯቸው፤ ህዝቡም ይህንን የተሳሳተ ሃሳብ እንዳይቀበል በይፋ በአውደ ምህረት ተናገሩ።

የህወሓት ዓላማ ወልቃይትን መውረስ መሆኑ የገባቸው ቄስ አለማየሁ፣ እነዚህ ኃይሎች ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ምክራቸውን ለመለገስም ሞክረዋል። ነገር ግን ህወሓት አንዴ ይዞት የመጣው ዓላማ ነውና በቄስ አለማየሁ ሃሳብ የሚስማማ አይደለም። ይልቁንም ቀሳውስቱን ማስጠንቀቅ፣ ቤተክርስቲያኒቷንም የሚያዋርዱ ተግባራትን መፈጸም ጀመሩ።

የህወሓት ታጋዮች በቤተክርስቲያን ውስጥ ሴቶችን ይደፍሩ፤ መሳሪያም ያከማቹ ስለነበር ቤተክርስቲያን የክፉ መንፈስ ቤት መሆን የለባትም በሚል ቄስ ዓለማየሁ አጥብቀው ይቃወሙ ነበር። በዚህ ጊዜ ቂም የቋጠሩት የህወሓት ካድሬዎች ቄስ ዓለማየሁን ባዶ ስድስት ወደሚባል የማሰቃያ እስር ቤት አስገቧቸው። በዚያም ከፍተኛ እንግልት ደረሰባቸው። እሳቸውን ማሰር ብቻ አይደለም። ቤተሰባቸውንም ማሰቃየት፣ ሃብትና ንብረታቸውን መውረስ ዋነኛ ተግባራቸው አደረጉት።

የስቃይ ውርስ

ቄስ ዓለማየሁ ወደ ባዶ ስድስት ሲገቡ አቶ አበራ የ28 ዓመት ወጣት ነበር። ህወሓት በወቅቱ አባትን ሲያስር ልጅንም ማስከተሉ የተለመደ ስለነበር አቶ አበራ የህወሓት ተሳዳጅ ሆነ።

ጠዋትና ማታ ቤታቸው በህወሓት ካድሬዎችና ታጣቂዎች ይበረበራል፤ ቤተሰቡ የስነልቦና ቀውስ እንዲደርስበት ሲባል ቤታቸው ሙሉ ለሙሉ ተዘረፈ። አልጋ እንኳን ሳይቀር ተወስዶ የቤተሰቡ አባላት ለከፋ ስቃይ እንዲዳረጉ ተደረገ።
አቶ አበራ ግን ይህንን ግፍ መቀበል እንደሌለበት በማመን ከፋኝ በማለት በወቅቱ ከህወሓት ጋር ሊፋለሙ ወደጫካ ከገቡ ሌሎች የወልቃይት ጓዶች ጋር ወደበረሃ ወረደ። ከዚያም በዱር በገደል ሆኖ ወልቃይት ነጻ እስክትወጣ ድረስ መፋለምን ምርጫው አደረገ። በወቅቱም እስከ ቋራና መተማ ድረስ በመሄድ ከህወሓት ጋር ተፋልሟል።

በዚህ አይነት ሁኔታ አቶ አበራ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች ከህወሓት ጋር ሲፋለም ቆይቶ በ1983 ዓ.ም ህወሓት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በዱር በገደሉ ያላችሁ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ገብታችሁ ሰላማዊ ሕይወት መምራት ትችላላችሁ በሚል በተላለፈው ጥሪ መሰረት ወደተወለደበት ቀዬ ተመልሶ ወደእርሻ ሥራው ገባ።

ይሁን እንጂ ቂም ቋጥሮውን የማይረሳው ህወሓት ቃሉን አጥፎ አቶ አበራን ጨምሮ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችንና የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በሰላም ወደቀዬአቸው የተመለሱ የከፋኝ አባላትን ሰብስቦ ባዶ ስድስት በሚባለው እስር ቤት አስገባቸው። ግፉም እንደ አዲስ “ሀ” ብሎ ጀመረ።

የእስር ቤቶቹ ቆይታ

አቶ አበራ እንደሚሉት በመጀመሪያ የታሰሩት በባዶ ስድስት ነው። በባዶ ስድስት ውስጥ በሰው ልጅ ላይ ይፈፀማሉ ተብለው የማይታሰቡ ስቃዮችን አይተዋል። ባዶ ስድስት ዙሪያውን በድንጋይ ካብ የተሰራ እና መሬት ውስጥ የሚገኝ የምድር ገሃነም ነው። ስፍራው ሞቃታማ በመሆኑ እና ዙሪያውን በድንጋይ የታጠረ በመሆኑ እዚያ ውስጥ መዋልና ማደር በራሱ ትልቅ ቅጣት ነው። በአንድ ማጎሪያ ውስጥም እስከ ስድስት መቶ ሰዎች ይታሰሩ ነበር።

እስር ቤቱ በተራራ ስር ማንም የማይደርስበት ሰዋራ ስፍራ ነው የሚገኘው። እስረኞችም ቀን ቀን በዚህ ስፍራ ተዘግቶባቸው ከዋሉ በኋላ ማታ ማታ ለምርመራ ተራ በተራ እንዲወጡ ይደረጋል። ከዚህ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ሌላ የምርመራ ዋሻ ተወስደው የስቃይ አይነት ሁሉ ይፈፀምባቸዋል። በዚያ ስፍራ ሰዎች የሚደበደቡት በዱላ ብቻ አይደለም። መዶሻ ጭምር ሥራ ላይ ይውላል። ትንሽ የሚያስቸግር ከሆነ በመጀመሪያ ማጅራቱን በመዶሻ ተመቶ እራሱን እንዲስት ይደረጋል። ከዚያ ከሞተም በቃ፣ የሱ ታሪክ እዚህ ላይ ይፈጸማል፤ ከሰመመን ከተመለሰም ሌላ የማሰቃያ ቅጣት ይጠብቀዋል። ለምርመራ ከሚወጡት ተመርማሪዎችም ውስጥ አብዛኞቹ ሳይመለሱ በዚያው ይቀሩ ነበር።

እንደአቶ አበራ ገለፃ እሳቸውም ብዙ ጊዜ ወደዚህ ስፍራ ተወስደው ተገርፈዋል፤ በምርመራ ወቅት ከሚቀርቡላቸው ጥያቄዎችም ውስጥ አንተ ወልቃይት የአማራ እንጂ የትግራይ አይደለም ብለህ ነፍጥ አንግበህ ተዋግተሃል፤ የታጋዮችን ነፍስ አጥፍተሃል፤ ህዝቡን በኛ ላይ አነሳስተሃል፤ የሚሉ ሃሳቦች እንደሚገኙበት ይገልጻሉ።

አቶ አበራ ከባዶ ስድስት እስር ቤት ወደ አዲረመጥ፤ ከዚያ ሁመራ ቀጥሎም ወደሽሬ እና መቀሌ ተወስደው ታስረዋል። ቀጥሎም ከአላማጣ እስከ አፋር ድረስ በየእስር ቤቱ ተንከራተዋል። በመጨረሻም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እንዲሁ የህወሓት ሰዎች ተሰብስበው የሞት ፍርድ እንደፈረዱባቸው ይናገራሉ።

አቶ አበራ እንደሚሉት በወቅቱ ለመግደል ፈልገው ቢሆን ኖሮ ፍርድ መስጠቱ አስፈላጊ አልነበረም። ምክንያቱም ብዙዎቹ ተወስደው ቀርተዋልና። ነገር ግን በሞት ፍርድ ስም አስቀምጦ በየጊዜው ከዛሬ ነገ እሞታለሁ እያሉ በቁማቸው እንዲሞቱ ታስቦ እንደሆነ ይገልጻሉ።

አቶ አበራ ሞት ከተፈረደባቸው በኋላ ከዛሬ ነገ ወስደው ይገድሉኛል በሚል በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደኖሩ ይገልጻሉ። አብረው ከታሰሩት ጓደኞቻቸው ውስጥ በየጊዜው እየተወሰዱ በዚያው የሚቀሩ በመኖራቸው እሳቸውም አንድ ቀን የነሱ እጣ ፈንታ ይደርሰኛል በሚል ሁሌ ከሞት ጋር መኖራቸውን ይናገራሉ።

በዚህ መልኩ የሞት ፍርደኛ ሆኖ በሰቀቀን ማኖር አንዱ የህወሓት የማሰቃያ መንገድ ነው የሚሉት አቶ አበራ፤ አንደኛውኑ ሞቶ ማረፍን እስኪመኙ ድረስ ከፍተኛ የሞራልና የስነልቦና ጭንቀት ውስጥ መኖራቸውንም ያስታውሳሉ።

ከዚህም ውጭ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉም “አንተ እኮ ሞት ተፈርዶብሃል፤ አሁን የቀረው ወስዶ መረሸን ብቻ ነው” በሚል በቁም እንድትሞት ያደርጉሃል ይላሉ። በዚህ መልኩ ሞት ተፈርዶባቸው በሰቀቀን እና በስጋት ብቻ ለከፍተኛ የአእምሮ ህመም የተዳረጉና ራሳቸውን የሳቱ በርካታ እስረኞች እንደነበሩም አቶ አበራ ይናገራሉ።

በእስር ቤት ውስጥ ያልተፈፀመ ግፍ የለም የሚሉት አቶ አበራ ከድብደባና ማሰቃየት እንዲሁም ከመግደል በተጨማሪ ሞራላቸውን ለማላሸቅ በርካታ ተግባራት ይፈጸሙ እንደነበር ገልጸዋል። ከነዚህ መካከል ለምሳሌ ጀሪካን ለሁለት ቦታ በመሰንጠቅ ማታ ማታ ሰገራና ሽንታችንን እንድንሸናበት በማድረግ ቀን ቀን ደግሞ ምግባችንን እንድንመገብበት ያደርጉ ነበር ይላሉ።

በእስር ቤቱ ውስጥ ከእጅና እግራችን ላይ ሰንሰለት አይወርድም ነበር የሚሉት አቶ አበራ ከዚህም በተጨማሪ በዚያው ውስጥ የሚሞት ሰው ካለ አስከሬኑ እስከ ሶስት ቀን ድረስ ከዚያ እንዳይወጣ በማድረግ እንዲሸት ይደረግ ነበር ብለዋል።

ያም ሆኖ ግን በዚህ መልኩ የሞት ፍርደኛ ሆነው ከአንዱ እስር ቤት ወደሌላ እየተወሰዱና በየጊዜውም በምርመራ ስም እንደወጡ የሚቀሩ በርካታ ናቸው። እሳቸውንም ለ25 ዓመታት ቤተሰባቸውና ዘመዶቻቸው ይኑሩ ይሙቱ የሚያውቁት ነገር አልነበረም።

አቶ አበራ አንድ ቀን ተጠርተው የሞት ፍርዱ ወደእድሜ ልክ እንደተቀየረ ተገለፀላቸው። ከዚያ አፋር ውስጥ በሚገኝ ከምድር በታች በሆነ እስር ቤት አስገቡአቸው። ከዚያ ከ25 ዓመታት እስር በኋላ በ1988 ዓ.ም ምህረት በሚል ከእስር ቤት ተፈትተው ወደተወለደበት ቀዬ ተመለሱ።

የሞት ፍርድ የሚያስከትለው የስነልቦና ቀውስ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ትዕግስት ውሂብ እንደሚሉት ማረሚያ ቤት ለሰው ልጅ ከፍተኛ የስነልቦና ጫና የሚያሳድር ስፍራ ነው። አንድ ሰው ማረሚያ ቤት ሲገባ ከተለያዩ መብቶቹ የሚገደብበት በመሆኑ ነጻነት የሚገባውንና ለሰው ልጅ የአእምሮ ነፃነት የሚሰጠውን እረፍት ያጣል። በዚህ የተነሳ በየትኛውም ደረጃ ቢሆን ማረሚያ ቤት የአእምሮ ቀውስ የሚያሳድር ስፍራ ነው።

ማረሚያ ቤት አንድ ሰው በሰዎች ቁጥጥር ስር የሚሆንበት እና እንደፈለገ ለመንቀሳቀስ የማይችልበት፤ የተገደበ እንቅስቃሴ ብቻ የሚያደርግበት ስፍራ በመሆኑ አእምሮ ጥቂት ጉዳዮችን ብቻ እንዲያሰላስል ያደርጋል።

በወልቃይት ተፈፀመ የተባለው የእስር ሁኔታ ደግሞ አካላዊ ብቻ ሳይሆን የስነልቦና ጉዳት ጭምር የሚፈፀምበት ነው። አንድ ሰው መታሰሩ በራሱ የሚያስከትለው ገደብ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ላይ ስቃይ የሚፈፀምበት ሲሆን የሰዎችን ስነልቦና በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል። በዚህ አይነት ሁኔታ በዚህ ስፍራ የሚያሳልፉ ሰዎች ለከፍተኛ የአእምሮ ስቃይ እና ከፍ ሲልም ለሞት የሚዳጉበት እድል ሰፊ ነው።

በተለይ ያለፍርድ ቤት እውቅና ሞትን የሚያህል ትልቅ ፍርድ ሰጥቶ በእስር ቤት ውስጥ ሰዎችን ማጎር ከመግደልም በላይ ሰዎች በቁማቸው እንዲሞቱ መፍረድ ነው የሚሉት ዶክተር ትዕግስት እንዲህ አይነት ቅጣት ሰዎችን ከማስተማር ይልቅ ለማሰቃየት እና የስነልቦና ቀውስ ለመፍጠር የሚደረግ መሆኑን ይናገራሉ።

በዚህ አይነት ሁኔታ ሞት ተፈርዶበት በእስር ቤት የሚቆይ ሰው ከዛሬ ነገ እሞታለሁ ስለሚል እየኖረ ነው ማለት አይቻልም።

በመሆኑም ሁል ጊዜ ስለሞት እያሰቡ ከዛሬ ነገ እሞታለሁ ስለሚሉ ለከፍተኛ የስነልቦና ቀውስ ይዳረጋሉ። በዚህም ሰዎች እየተሰቃዩ ወደሞት ይሄዳሉ። በዚህ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት የሚችሉበት ሁኔታም ሰፊ ነው። በመሆኑም እንዲህ አይነት የማሰቃያ መንገዶች እጅግ አሰቃቂና አስከፊ የሰው ልጅ ላይም ሊፈፀሙ የማይገባቸው ኢሰብዓዊ ድርጊቶች መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ።

ህወሓት የእድሜዬን ግማሽ ቀምቶኛል የሚሉት አቶ አበራ፤ ይህ የሆነው ደግሞ ያለምንም ጥፋት በመሆኑ ከፍተኛ የህሊና ቁስል እንደፈጠረባቸው ይገልጻሉ።

“ሰው እንዴት ምንም ጥፋት ሳይፈጽም በዚህ መልኩ ሲሰቃይ ይኖራል፤ በማንነቴ ብቻ ከሞቱት በላይ፤ ከኖሩት በታች ሆኜ መኖሬ አሳዛኝ ነው። እኔ በዚህ ሁሉ ዓመት ብዙ ነገር መስራት እና ለራሴም ሆነ ለቤተሰቤ እንዲሁም ለሃገሬ ብዙ ቁምነገር ማበርከት ስችል ያለሃጢያቴ ሕይወቴን ቀምተውኛል፤ እናም ፈጣሪ ዋጋቸውን ይክፈላቸው” ሲሉም በምሬት ይገልጻሉ።

አቶ አበራ እነ ነጋ አስረስ፣ ቻላቸው ታደሰ የተባሉ ጓደኞቻቸውም የት እንደገቡ ሳይታወቅ ደብዛቸው መጥፋቱን ይናገራሉ። “በወቅቱ ለእስር ከተዳረጉ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ሞተዋል፤ እድለኛ የሆኑት ተሰደው ከሃገር ወጥተዋል፤ በሕይወት የወጣ ግን የለም” ይላሉ። እሳቸው ግን ከዚያ ሁሉ ስቃይ በኋላ ታሪክ ለመናገር በመቻላቸው እድለኛ ነኝ ይላሉ።

(አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም)

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories