ጓዶች፣ HR6600 አይጣልም አይነሳም ግን እያንዣበበ ይቀጥላል

የአሜሪካ ወዳጃዊ መርዝ – ከቻይና እስከ ኢትዮጵያ

   ▪️የዓባይ፡ልጅ ✍️ እስሌማን፡ዓባይ
አሜሪካ የተቀረው አለም በራሷ ርእዮት ይሾርላት ዘንድ አለማቀፉን የበላይነቷን የማስጠበቅ የውጪ ፖሊሲዋ ግድ ይላታል። ህወሃት የጀመረውን ጦርነት ተከትሎ የተያያዘችው የጫና ፖሊሲ ኢትዮጵያ በሰላም ወቅት ከተሳሰረቻቸው ሀገራት በዚህኛው አስቸጋሪ የቀውስ ጊዜዋ ተበጣጥሶ ጥቅሟ እንዲጠበቅላት ያለመችው ነው። ይህን ጉዳይ ከቀናት በፊት የአሜሪካ ጦር አዛዥ በግልፅ ደግመውታል። በአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በአጠቃላይ በአፍሪካ ለአሜሪካ ስጋት በማለት ከዘረዘሯቸው ውስጥ የሩሲያና ቻይና መስፋፋት እና አሃዳዊነት የሚሉት ይገኙበታል። ዋነኛ አላማዋ ኢትዮጵያን ወደ ቻይና፣ ሩሲያ እንዲሁም ቱርክ አይነት ሀያላን ጋር ያላት ትብብብር ሆኗል።

ለአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች እንቅልፍ እንደነሳ የቀጠለውን የቻይና ግስጋሴ መመከቻ ስትራቴጂ መንደፋቸውን አላቆሙም። ብሊንኬን በጥር 2019 በብሩኪንግስ ፖሊሲ ተቋም ላይ በተፃፈ ትንተና ላይ የቀረበ ሀሳባቸው ነበር። ከተሾሙ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሌንከን ቁልፍ ያላቸዉን ጉዳይ ምሰሶዎች አስቀምጦ ነበር።
ሶስቱን ብንጠቅሳቸው፣ የመከላከያ ዲፕሎማሲን እና ጡንቻን ተጠቅሞ ብርቱ ጫና የማሳደር deterrence አንዱ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ ዘዴ “ፋታ በማይሰጥ የዲፕሎማሲ አካሄድ እና ወታደራዊ ዲፕሎማሲን እያቀላቀለ ይተገበራል። የሚፈጠሩ የቀውስ ክፍተቶች ሳያመልጧቸው ለራስ ጥቅም ለማዋል የሚጠቀሙበት አይነት ፖሊሲ ነው።
ንግድና ቴክኖሎጂ ሁለተኛው ምሰሶ ሲሆን “ጠብ ጫሪው ካፒታሊስት ዓለማቀፍ ተገዳዳሪዎችን ለመመከት ስራ ላይ ያውለዋል።
3ኛው ከአጋር ሀገራትና ተቋማት ተባብሮ ዓለም አቀፍ የንግድ መረብ መፍጠር ነው። ይኸውም አሜሪካ የአውሮፓና እስያ አጋሮቿ ጋር ” የቻይናን Belt and  Road ስትራቴጂ ለማክቸፍ እየተከተሉት የሚገኘው አይነት ነው፡፡ IFDC ለዚሁ አላማ በአሜሪካ መሪነት በቅርቡ የተቋቋመ ነው።
“ዲተርረንስ” የአሜሪካ የመከላከያ እና ወታደራዊ ፖሊሲ ዋና አካል ሲሆን ዋሽንግተን በታሪክ ውስጥ ሁለት ዓይነት ድተርንሰ ተግባራዊ አድርጋለች።
“እምቢታ” አሜሪካ አንድን በማትፈልገው አቋም ላይ የሚገኝ አካልን ጉዞ ለማደናቀፍ የምትወስደው ርምጃ።
“ክለከላውን ማስፈፀሚያ የቅጣት ጫና” የጉዳቱን አድማስ የቅጣት  በማስፈራሪያን ለጫና መጠቀም።

የዋሽንግተን ስጋት ኢትዮጵያን ከአሜሪካ ባላንጣ ሀገራት መነጠል ከሆነ የ HR6600 ረቂቅ ፀድቆ ቢተገበር ውጤቱ ለአሜሪካ በተቃራኒው ሆነ ማለት ነው። ሁለት ነገሮችን እገምታለሁ። አንደኛ ኢትዮጵያ ወደ የአሜሪካ ተቀናቃኝ ሀገራት ጋር ልትጠቃለል ትገደዳለች። ለዚህ ደግሞ ቤይጂንግ ለአፍሪካ ቀንድ ያቀረበችውን አዲስ ፓኬጅ ማስታወስ ይቻላል። ይህን ዋሽንግተን የማትፈልገው ነው። ምናልባትም ማዕቀቡን ተከትሎ በሚፈጠሩ ሁኔታዎች ህዝባዊ አመፅ እንዲቀሰቀስ መጠበቅ ብሎም መስራት፤ ሁለተኛው ደግሞ በማእቀቡ ማስፈራሪያ መንግስትን በማንበርከክ የምትሻውን በራሷ ጥቅም ዙሪያ የሚጓዝ ማድረግ።
ማዕቀብ ለዋሽንግተን ዲፕሎማሲያዊ የመፍትሄ እርምጃ አካል ተደርጎ ይገለፃል፣ ይሰበካልም። በዚህም ታላሚውን አካል አቋም ለማስለወጥ deterrence መፍጠሪያ ነው። ይሁንና መሰል የማእቀብ ጫና ሰላምም ሆነ ዲሞክራሲ ሲያመጣ አልታየም። ይልቁንም ረሃብ ሞትና የማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ የከተታቸው ሀገራት በርካታ ናቸው። ለኢትዮጵያ በምን ታዕምር ጠቃሚ እንደሚሆን የረቂቁ ደጋፊዎች ካላስተማሩን በስተቀር ሊገባኝ አይችልም።

ጦርነት የሚወገዘው ከሚፈጥረው ውድመት ባለፈ ወንጀሎችና የሕግ ጥሰቶች የሚያስከትል በመሆኑ ጭምር ነው። ድህረ ጦርነት ላይ ፍትህ እንዲሰፍን እውነተኛ ምርመራ ማድረግና ወንጀለኞች በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ጉዳይ ሁሉንም የሚያግባባ ነው።
ይሁንና የጦርነትን ጣጣ በማዕቀብ ጫና ለማስቆም አሜሪካ የምትወስደው ርምጃ ምን ትርፍ እንዳስገኘ እስከ ዛሬ ድረስ ከምታደርጋቸው ተግባራት አንፃር በአጥፊነቱ የሚመዘገብ ነው። ማዕቀቡ በመንግስት ላይ ጫና አድርጎ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመጥቀም ነው ሲል የባይደን አስተዳደር ቢገልፅም እውነታው ግን ከፖለቲካዊ ፍላጎት ማስፈጸሚያነት፣ ነገሮችን ከማባባስና ከማወሳሰብ ያለፈ ፋይዳ አለው ወይ? የሚለውን መመለስ የሚጠይቅ ነው።

የባይደን አስተዳደር ከኢትዮጵያ የነበረውን ረጂምና ከፍተኛ ቦታ የነበረውን የዲፕሎማሲ ታሪክ ማፍረሱን ቀጥሎት በጫና (Detterence) ፖሊሲ ኢትዮጵያ ላይ እንደዘመቱ ይገኛሉ። በኢኮኖሚ የጫና ዘዴያቸው ከብድር ስረዛ ዛቻ እስከ ከአጎዋ ማስጠንቀቂያ ብሎም እገዳ ተጉዘዋል፤ የሰብአዊ መብት ካርታዎችንም በተመሳሳይ የጫና ካርድ አርገውት ቀጥለዋል። ከወታደራዊ ዲፕሎማሲ እስከ ወታደራዊ ጫናዎች የተለያዩ ሙከራዎችም ነበሩ። ሲቀጥልም Gunboat ዲፕሎማሲ በሚሉት ስልት ጂቡቲ ያለው ጦር ሰፈሯንና የጦር መርከቦቿን ለስነልቦናዊ ጫና መፍጠሪያነት ለመጠቀም ከቢቢሲ የዜና ቪዲዮ ጋር የተባበረ ማስፈራራትን ሞክራም ነበር።
ፕሮፌሰር አልማርያም “እንደ እኔ እይታ የብሊንኬን “የመከላከያ ዲፕሎማሲ እና ድተርንሰ” ሲሉ የተናገሩት አንደኛ ዲፕሎማሲን በመጠቀም ከበስተጀርባ ደግሞ ወታደራዊ አማራጭ እንዳለ በማስቀመጥ ድርድር ማድረግ ነው። በቅቱ ይህን በተመለከተ የፃፉት ፕሮፌሰር አልማርያም ወታደራዊ አማራጩን ከንቱ ምኞት ነው።” ፕሮፌሰሩ እንዳሉትም አሜሪካ ህወሃትን የደገፈችበት አካሄድ ተገታ። ነገር ግን የአሜሪካ ማለቂያ የሌለው ጦሰኛ ፖሊሲ ቀጥሏል።
የአሜሪካ አላማ የቻይና ሩሲያ ቱርክና መሰሎች ወደ አፍሪካ የሚደረግ ጉዞን መግታት በመሆኑ ጥረታቸውን አላቋረጡም። አንድም በብድር ሌላ ጊዜም በዛቻና በማዳቀቅ ካርዶች። ያመጡትን አዲስ አካሄድ እንመልከት። ከወር በፊት Global Gateway Initiative የተባለ ፓኬጅ በአውሮፓ ህብረት በኩል ይፋ ተደርጓል። ወዲያውም europe-africa የተባለው ስብሰባ በዚሁ ላይ ተመስርቶ ተደረገ። 130 ቢሊዮን ዩሮ የመደቡለት ይኸው አዲስ ፕሮጀክት ይፋ ሲደረግ ህብረቱ በመግለጫው “ኢኒሼቲቩ አፍሪካና ኢትዮጵያን ማልማት ከፍተኛው ትኩረቱ ነው።” ነበር ያለው። ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አህጉር ጋር በተለዬ እና በእኩል ትኩረት መጥቀሱን እዚህ ላይ ልብ ይሏል። ይህ ድፍን አፍሪካን ካስነሳችው ኢትዮጵያ ነገር አርግበው ወደ ወዳጅነት ሲመለሱ ከጀመሩት አዲስ መላ ውስጥ አንዱ ካርታ መሆኑ ነው።
ታዲያ HR6600 የኢትዮጵያን ህዝብ ከመንግስት ነጥሎ ይጠቅም ይሆን? የሚጠቅም በሆነ እኔም ልቀበለው ባልከበደኝ። እዚጋ በተለያዩ ሀገራት ምን ሚና እንደነበራት ደግመን እናውሳ።

አሜሪካ መራሹ የሶሪያ ጦርነትና ቀውስ ውስጥ 350,000 ዜጎች ሞተዋል። 6.8 ሚሊዮን ዜጎች መጠለያ አልባ ሆነው በሀገር ዉስጥ  6.7 ሚሊዮኖች ደግሞ ወደ ውጭ ተሰደዋል። (የተፈናቀለው 13.5 ሚሊዮን ህዝብ)።
በአፍጋኒስታን 219,439 ዜጐች በጦርነቱ ሞተዋል::  2.2 ሚሊዮን ዜጎች ወውጪ ሀገራት 3.5 ሚሊዮኖች አፍጋናዊያን በሀገር ውስጥ ተሰደዋል።  በኢራቅ IRAQ 461,00 ዜጐች በጦርነቱ ሞተዋል። 3.5 ሚሊዮን ኢራቃዊያን ከአገር ውጪ ተሰደዋል። በየመን  233,000 በጦርነቱ ሞተዋል። 4 ሚሊዮን የመናዊያን (79% የሚሆኑት ሴቶችና ሕፃናት) ተፈናቅለዋል። 20 ሚሊዮን የመናዊያን ሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊ ናቸው። የጦርነቱ ጦስ 2/3ኛ በላይ የየመን ዜጎችን በአሉታዊ ጎን ነክቷል።

ከሊቢያ 6. 9 ሚሊዮን ህዝብ 35,000 በጦርነቱ ሞቶዋል። 19,700 ቁስለኞችና 435,000 ተፈናቃይ ሆነዋል።
በአጠቃላይም ከመስከረም 11 2001 እኤአ ጀምሮ አሜሪካ በመራቻቸው ጦርነቶች በአፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ፓኪስታን፣ የመን፣ ሶማሊያ፣ ፊሊፒንስ፣ ሊቢያ እና ሶሪያ ቢያንስ 37 ሚሊዮን ሰዎች  በግዳጅ በማፈናቀልና በስደት ሀገር አልባ ሆነዋል። ለተጠቀሱት ሀገራት ያንን መከራ ያወረደው የአሜሪካ ወታደራዊና የማእቀብ ጫና ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት ይጠቅማል? ይህ ማእቀብ ቢፀድቅ ሁሉን አቀፍ ሆኖ ተግባራዊ ለማድረግ ከአሜሪካ በተጨማሪ የፀጥታው ምክርቤት አባል ሀገራት፣ አውሮፓ ህብረት፣ የNATO አባል ሀገራትና ሌሎች የአሜሪካ ወዳጅ ሀገራት ተሳታፊ የሚሆኑበት ነው።
የ HR6600 ደጋፊ ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም እና ደህንነት” በሚል የማዕረግ ስም የተደገሰውን ረቂቅ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ብቻ ያነጣጠረ ነው የሚሉት የእነዛን ባለነዳጅ ሀገራት ዜጋ ጓዳና ጉሮሮ ያደረቀው፣  መፃኢ ተስፋቸውን ጭምር ያራቆተው ማእቀብ እዚህ በኢትዮጵያ ጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ቢያስረዱን እላለሁ። በነገራችን ላይ ህወሃት የከፈተውን ጦርነት በዛ ደረጃ በሰልፍና በዲጂታል ዘመቻ የተቃወምነው የውጭ ፍላጎትን ይዞ በመመምጣቱ ነውንጂ በፖለቲካ ፉክክር ብቻ ሉአላዊነትን ሳይዘነጋ ቢሆን ኖሮ ዘመቻችን ሌላ መልክ በኖረው ነበር። በነገራችን ላይ ቻይና እንደዛሬው ሀያል ሳትሆን ተመሳሳይ የጣልቃ ገብነት ታክቲክ ከአሜሪካ ደርሶባታል። የማኦ ዚዶንግ ሶሻሊስታዊ አብዮት ድል ካደረገ ማግስት በቻይና ሰላማዊ ሽግግር እንዲኖር በሚል አሜሪካ ምን ነበር ያደረገችው? እሱን በማውሳት ላብቃ።

የአሜሪካ የያኔው ታክቲክ ከህዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ ያላትን ግንኙነትን በተመለከተ የሲአይኤ “How to do manual” በሚል የዛሬይቱ ቻይናውያን መሳለቂያ ሆኖ ይገኛል። መጀመሪያ የተጻፈው በ 1951 እኤአ ነው። በወቅቱ የሲኖ-አሜሪካ ግንኙነት በጣም የሻከረበት ነበር። የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን መለዋወጥ እየተከተለም በየጊዜው ሲከለሰ ነበር።  እስካሁንም ድረስ። “አስርቱ ትእዛዛት” በመባልም ይታወቃል። ይፋ ያደረጉት በቅርቡ ሲሆን “ተገርመናል” ይላሉ ይህን የታዘቡ አንድ ቻይናዊ። ከአስሩ ውስጥ የተወሰኑትን ልጥቀሳቸው።
የመጀመሪያው ወጣቱን በቁሳዊ ነገሮች የማባበልና አይምሮውን የማበላሸት corrupt የማድረግ ስራ የሚል ነወሰ። በዚህ ዘዴ የቻይና የሆነውን ርዕዮተ ዓለምና አስተምህሮ በተለይም ኮሚኒዝምን  እንዲንቁ እና የበለጠ እንዲቃወሙት ማበረታታት።
ሁለተኛ፡- ፊልሞችን፣ መጻሕፍትን፣ ቴሌቪዥንን፣ ሬዲዮችን…ለማስፋፋት የተቻለንን ሁሉ ማድረግ። በዚህ ዘዴ የምንለብሰውን፣ የምንመግበውን፣ የምንኖርበትን ቤት፣ የምንጓዝበትን፣ የምንዝናናበትና የምናስተምርበትን መንገድ እንዲመርጡት ካደረግናቸው ይህ የጦርነት ግማሽ ነው ይላል።
በሶስተኛው ወጣቶች ከሀገራቸው መንግስት ጋር ስለሀገራቸው የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ እንዳይኖር መስራት የሚለው ነው።  አእምሯቸውን በስፖርታዊ ትእይንቶች፣ የብልግና ቪዲዮዎች፣ በተድላዎች፣ ጨዋታዎች፣ በወንጀል ፊልሞችና በአጓጉል ሃይማኖታዊ አመለካከቶች ላይ ያተኩራል።
አራተኛ፣ ህዝቡ በይፋ የማይነጋገርባቸው ጉዳዮችን እንዲወያዩባቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት። ይህ በተለይም በsubconcious አእምሯቸው ውስጥ መከፋፈልን ሳያስቡት መትከል ላይ ያነጣጥራል። አናሳ የሚሏቸው ብሔረሰቦች መካከል በክልል፣ በብሔረሰብ፣ እንዲሁም በስሜታቸው ሁሉ መከፋፈልን ቀመፍጠር በመካከላቸው የቆዩና አዳዲስ ጥላቻዎችን ለመፍጠር መልካም አጋጣሚዎችን ያማትራሉ።
አምስተኛው፣ ተከታታይ ዜናዎችን በመስራት መሪዎቻቸውን ማጥላላት።  ጋዜጠኞቻቸው እነሱን ቃለ መጠይቅ በማድረግ በእነርሱው ላይ ዘገባውን ማድረስ።
በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የአሜሪካን የዴሞክራሲ ፍልስፍና ማነብነብ። ባገኘነው በዬአጋጣሚው ሁሉ፣ ትልቅም ይሁን ትንሽ፣ የሚታይም ሆነ የማይታይ፣ ዕድሉን ተጠቅመን ዴሞክራሲያዊ የሚባል ስም የተሰጣቸው ንቅናቄዎችን ማበረታታት። ይህን ሲደጋግሙት ህዝባቸው እኛ የምንናገረውን እውነት ነው ብሎ በእርግጠኝነት ያምናል። እኛ የምንይዘው ሰዎችን ነው።
የቀድሞው የአሜሪ ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን በ Sun Tzu የጦርነት ጥበብ Art of War ፅንሰ-ሀሳብ ላይ በመመስረት “ያለ ጦርነት ድል ማድረግ” በሚል ርእስ መጽሐፍ አሳትመው ነበር። በመጽሃፉቸው “ወጣት ቻይናውያን በአባቶቻቸው ትምህርትና በባህላቸው ላይ መተማመን ሲያቆሙ ያኔ እኛ አሜሪካውያን ያለ ጦርነት እናሸንፋቸዋለን…” ነበር ያለው።
ማኦ ዜዶንግ ይህንን የአሜሪካ ሴራና አላማ ከረጅም ጊዜ በፊት ገምቶ እንደነበር የሚገልፁም አሉ። ከማኦ ጥቅሶች ውስጥ “ድሉን አሳክተናል። ግን መኩራራት የለብንም ። የጠላት ሀይል በመደበኛ ውጊያ ሊያሸንፈን አይችልም። ጓዶቻችን በጠመንጃ ጠላትን አሸንፈዋል። በዚህም የጀግና ማዕረግ ይገባቸዋል። ነገር ግን እነዚህ የጦር ሜዳ ጀግኖች በስኳር የተሸፈነ ጥቃት ድል ማድረግ አይቻላቸውም። በስኳር የተሸፈነው ቦምብ ያንበረክካቸዋል።” ብለዋል ማኦ ዚዶንግ።
በመጨረሻም፣ የHR ደጋፊዎች ፍላጎታቸው ስልጣን፣ የህዝባቸው ሰላም ወይም ሁለቱም ነው እንበል። ይህ አላማቸውን ከህወሃታዊው በምእራባዊያን ላይ ተስፋውን ካደረገው ዘዴ በተለየ ጉዳት አልባ የማሳኪያ መንገድ ለምን አይቀይሱም? ለመንግስትም የምጠይቀው አለኝ፤ የኢትዮጵያ መንግስታዊ ተስፋ  አሜሪካ እና አውሮፓ ብቻ ናቸውን? አውን የአለም ሚዛን ወደ ምዕራብ እንዳጋደለ እነሱ ብቸኛ ሰጪ እና ለጋሽ የሚሆኑበት ዘመን እያበቃ አይደለምን?

Esleman Abay የዓባይ ልጅ
[ፌስቡክ ለተወነ ጊዜ ስላገደኝ ቴሌግራም ላይ ታገኙኛላችሁ ⬇️

Esleman Abay #የዓባይልጅ

Share:

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

On Key

Related Posts

VK Russian online social media and social networking service

© 2022 Esleman Abay. All rights reserved.

Follow Us

Categories